Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኑሮ ውድነትን ይቀርፋል የተባለው ኤግዚቢሽንና ባዛር

የኑሮ ውድነትን ይቀርፋል የተባለው ኤግዚቢሽንና ባዛር

ቀን:

በኢትዮጵያ ከመጠን በላይ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት መንግሥት መሠረታዊ ፍጆታዎች በዱቤ ከውጭ አገር እንዲገቡ መፍቀዱ ይታወሳል፡፡ በተለይም በማኅበረሰቡ ዘንድ ጥያቄ እየፈጠሩ የሚገኙ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የተለያዩ ባዛርና ኤግዚቢሽኖችን እንዲሁም በቅርቡ የተጀመረው የእሑድ ገበያን መንግሥት እንደ አማራጭ አቅርቧል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ዘርፉ ላይ እየታየ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ‹‹የኅብረት ሥራ ማኅበራት ግብይት ለሰላምና ለተረጋጋ የገበያ ሥርዓት›› በሚል መሪ ቃል ከግንቦት 18  እስከ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ከተማ አቀፍ ኤግዚቢሽን እያካሄደ ይገኛል፡፡

የኅብረት ሥራ ኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ዓሊ እንደገለጹት በመካከለኛና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ምርትና ምርታማ የሆኑ ነገሮችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ አስተዳደሩ እየሠራ ነው፡፡

በዚህ መሠረት በከተማዋ የሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየሠሩ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ይህንንም አጠናክሮ ለመቀጠል የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ያላቸውን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ አንድ ሚሊዮን ብር ዘዋሪ (ሪቮልቪንግ) ፈንድ መስጠቱን አክለው ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩም ያቀረበው ፈንድ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን የምርት አቅርቦታቸውን እንዲያሳድጉ የሚረዳ መሆኑን፣ በተለይም ደግሞ በከተማዋ እየተስተዋለ ያለው ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ለማረጋጋት ትልቅ አማራጭ ይሆናል ብለዋል፡፡

የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከገጠር አምራች ኅብረት ሥራ ማኅበራትና ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ እንዲሁም ደግሞ የልምድ ልውውጥ እንዲያካብቱ ኤግዚቢሽኑ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አቶ ግዛቸው አብራርተዋል፡፡

የገንዘብ ቁጠባና ብድር አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በከተማዋ የተደራጁ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ወጣቶች፣ ሴቶችና የመንግሥት ሠራተኞች የቁጠባ ባህል እንዲያዳብሩ ለማድረግ በተለያዩ የሥራ ፈጠራ ውስጥ ገብተው የራሳቸውን ሕይወት እንዲመሩ የቤት ባለቤት እንዲሆኑና የኑሮ ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ዕገዛ እያደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በተደረገላቸው ፈንድ እስካሁን ጤፍ፣ ስንዴና ፍርኖ ዱቄት ጨምሮ 287 ሺሕ ኩንታል ማስገባታቸውን ይኼም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገበያዩ ይረዳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በቅርቡም የተጀመረው የእሑድ ገበያ ከ50 በላይ መድረሱን የገለጹት አቶ ግዛቸው፣ እነዚህም የገበያ ማዕከሎች ምርቶችን በማስገባት ከመደበኛ የገበያ ዋጋ በመቀነስ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እያደረጉ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በእርግጥ አንዳንድ የኢንዱስትሪ ምርቶች ማለትም መኮሮኒ፣ ፓስታ፣ ዘይትና ሌሎች መሰል ምርቶች ላይ ከመደበኛ ገበያ ጋር ምንም ዓይነት የዋጋ ልዩነት እንደሌለው ገልጸው፣ የግብርና ምርቶች ላይ ግን ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ልዩነት አለው ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይም የዋጋ ልዩነት እንዲኖርም መንግሥት የፍራንኮ ቫሉታ የፈቀደላቸው አቅራቢዎች ጋር በቀጥታ በማገናኘት ምርቶች በብዛት ለማቅረብ በቀጣይ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት እየተስፋፋ የመጣው የእሑድ ገበያ ላይ የአብዛኛውን የሸማቾች ችግር መቅረፍ እንደተቻለ፣ በተለይም ደግሞ የግብርና ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸው የሸማቾችን የመግዛት ፍላጎታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር አድርጎታል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባም በከተማ ግብርና ላይ የተሰማሩ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ገና በጅምር ላይ ያሉ ቢሆንም፣ ለከተማችን የምግብ ዋስትና አጋዥነት በተለይ አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት እንዲሁም በአረንጓዴ ልማት በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡

የእሑድ ገበያ እንድ አንድ የገበያ መዳረሻ ሆኖ የማኅበረሰቡን አንገብጋቢ ችግር ለመፍታት የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እያደረጉ ላሉ የከተማ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትና የኦሮሚያ አጎራባች አምራች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ላደረጉት ጉልህ ሚና ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት ምክንያት በዓለም ላይ የነዳጅ፣ የዘይት፣ የስንዴና ሌሎች መሰል የምግብ ሸቀጦች መናሩ የኑሮ ውድነትን አባብሶታል ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ናቸው፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት በኢኮኖሚው ዓውድ ሸማቹን ከሰው ሠራሽ የኑሮ ውድነትና በዓለም አቀፋዊ ገፊ ምክንያቶች የተፈጠረውን የምግብ ምርቶች ዋጋ ንረት ከመታደግ አንፃር፣ ያልተገባ የግብይት ሰንሰለቶችን በማስወገድ አምራቹን ከሸማቹ ጋር ቀጥታ የገበያ ትስስር በመፍጠር በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

ሕገወጥ የሆኑ ደላሎችን ከቀጣናው በማውጣትና ማኅበረሰቡ ከነጋዴው ጋር በቀጥታ በማገናኘት የኑሮ ውድነትን የማረጋጋት ሥራ እየተሠራ እንደሆነ የተናገሩት ኃላፊው ይኼንንም ሥረ አጠናክሮ ለመቀጠል ተቋሙ የበከሉን ድርሻ ይወጣል ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን የኢንዱትሪ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን አንስተው በተለይም የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ያላግባብ አከማችተው የተገኙ ነጋዴዎች ላይ አስፈላጊ ዕርምጃ መወሰዱንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...