Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሰው እንሁን!

ሰላም! ሰላም! ‹‹ሰላምን ከጠረጴዛ ዙሪያ የማይፈልጋት ከጦር ሜዳ እንዲያገኛት ይገደዳል›› የሚለው የዘመነ አብዮት አባባል ትዝ ቢለኝም፣ እኔ ግን እላለሁ ሰላምን ለማስፈን ዋናው መንገድ ሆደ ሰፊነት ነው፡፡ ሆደ ሰፊ እንሁን ሲባል ከጠዋት እስከ ማታ ልኳንዳ ቤት ከዳቢት እስከ ሻኛ እያማረጥን፣ በላዩ ላይ ቢራና ውስኪ ስንቸልስ እንዋል የሚል የሚመስላቸው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የአገር ሀብት ዘርፎ መክበርን ሙያ አድርገው የሚያዩና እሴት ሳይጨምሩ መሬት እየቸበቸቡ የሚቀናጡ ከንቱዎችን ማለቴ ነው፡፡ እነዚህ ከንባቡም ሆነ ጠለቅ ካለው የዕውቀት ዓለም ጋር የተለያዩ ስለሆነ፣ መልዕክቱ ለእነሱ ሳይሆን የአገር ጉዳይ እንቅልፍ ለሚነሳቸው ወገኖቼ ነው፡፡ የሠራ ሲኖትራክ አሻሽጬ ኮሚሽኔን ልቀበል የሆነ ካፌ በረንዳ ላይ ተጎልቼ የባጡን የቆጡን አስባለሁ። ለካ አንዱ ከጎኔ መለስ ቀለስ እያለ ይነድፈኝ ይዟል። ዘመኑን ሳስበው የሰው ዕባብ ወይ ጊንጥ የነደፈኝ ነው የመሰለኝ። ይኼ አስመስሎ መሳል ነገር አለ አይደል? እንደ ፎቶግራፍና የንድፍ ምሥል ማለቴ ነው። ለነገሩ ዘንድሮ ሳይቀነስ ሳይጨመር የማይገለበጥ ነገር የለም። ‘ኮፒ ፔስት’ ይለዋል እንግሊዝኛው። በጥበብ ስም ‘ኮፒ’ መብዛቱ ገርሞን ሳናበቃ ልብ ‘ኮፒ’ ለማድረግ የሚጥርም እያየን ነው። ልብ አውልቁ እኮ በዛ እናንተ!

እናላችሁ ቆፍጠን ብዬ ‹‹እንዴት አንተ? እግዜር እኮ ሲፈጥረኝ እንድሳሳት ጭምር ነው። እንድሳሳት ብቻ ሳይሆን ተሳስቼ እንድታረም አድርጎ ነው። እንዴት አንተ ላታርምና ላታርቅ በእርሳስ ትቸከችከኛለህ?›› እለዋለሁ፣ ‹‹ሥልጣን ስለሌለኝ ቀለም ከየት አመጣለሁ?›› አይለኝ መሰላችሁ? እንዲያ ሲለኝ ላጲስ መዋጥ አማረኝ በቃ። የት አባቴ ልግባ? ነዶኝ ብቻ ‹‹እሺ እንዴት ሳታስፈቅድ ትስለኛለህ?›› ብዬ ስደነፋ (ውሸት ምን ያደርጋል ሸጋ አድርጎ ስሎኛል፣ ቀን አልወጣልኝ እያለ በዚያ ስይዘው በዚህ እየተበተብኝ ለምን እንደሆን እንጃ ፎቶና ሥዕል ይወጣልኛል) ‹‹ለመጻፍና ለመናገር እንጂ ለማየትና ለመስማት ሜዳው ነፃ ነው…››  ሲለኝ ‘አሃ ይኼ ሰው ከጀርባው ሌላ ተልኮ ይኖረዋል’ ብዬ ብድግ አልኩ። በኋላ ምሁሩን የባሻዬን ልጅ አግኝቼው የገጠመኝን ስነግረው፣ ‹‹አንተ ለምን ታካብዳለህ፣ አደባባይ የወጣ ሁሉ ከካሜራና ከብዕር ዕይታ ማን ነው ነፃ ያደረገው…›› ብሎኝ ሳቀብኝ፡፡ ዝም ብዬ ሳስበው ለካ የተናገረው እውነቱን ነው፡፡ ሥልጣን ያሉ ተመልካቻቸው ብዙ ነው፣ ጥሪት በስፋት የሚቋጥሩ ከማንም ዕይታ አያመልጡም፡፡ ለምን አያችሁኝ፣ ተናገራችሁኝ፣ ተቻችሁኝ፣ ወቀሳችሁኝ፣ ወዘተ ማለት አይቻልም፡፡ አደባባዩ ውስጥ ቀድሞ የገባ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ሁሉ፣ እንቅስቃሴ ውስጥ ጎልቶ የሚታየውም እንዲሁ ነው፡፡ ይኸው ነው!

እናላችሁ በርካታ ሚሊዮኖች የፈሰሱበት አንድ አዲስ አስፋልት መንገድ ተመረቀና ሥራ ጀመረ አሉ። ኋላ ሰው ቢታይ ቢታይ በዜብራው አልሻገር ይላል። ‹‹ለምንድነው በዜብራ የማትሻገሩት?›› ሲባል መልሱ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? ‹‹እንዳያልቅ ብለን ነው›› አሉ ተባለ፣ ጉድ እኮ ነው። ታዲያ የማያልቅ ነገር አለ? ሲጨንቀውማ ትራፊክ ፖሊሱ በዜብራ የማይሻገር 100 ብር፣ ግራውን ይዞ የማይጓዘውን 80 ብር ቅጣት ይከፍላል ብሎ ሲወስን ተስተካከሉ አሉ። አንድ የማውቀው ነገር ቢኖር ግን ሰዎቹን እንዲህ ያለ ስህተት ውስጥ የጣላቸው፣ በፌስቡክ ማንነቱ በማይታወቅ ሰው የተላለፈ የቀልድ መልዕክት ነው አሉ፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ መንገድ የተሠራው የሰው ልጅ እንዲገለገልበት ነው፡፡ ሰው በሠራው ነገር መገልገል ካልቻለ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ፈጣሪ የሰጠንን አዕምሮ በቅጡ ብንጠቀምበት እኮ እንኳንስ ከመናኛ ኮሌጅ የወጣ ጥራዝ ነጠቅ፣ ከሃርቫርድ የመጣ ፕሮፌሰር ሊቀልድበት አይችልም፡፡ በዚህ ዘመን ግን ሰዎች አዕምሮአቸውን መጠቀም አቅቷቸው የሸረኞች መጫወቻ ሆነዋል፡፡ እኔ እንኳ በደላላ ዕውቀቴ ስንቱን ሀብትና ሥልጣን የተሸከመ ፈዛዛ አየሁ መሰላችሁ፡፡ አንዳንዴ ብልጭ ሲልብኝ እነዚህ ናቸው እንዴ እኔን በልጠው ሀብት ያካበቱ ወይም ግዙፍ ሥልጣን የያዙ እያልኩ እበሳጫለሁ፡፡ ወይ ነዶ!

ስለትርፍና ኪሳራ እንጫወት እስኪ። ያው ሁሌ እንደማወጋችሁ ገቢዬንና ወጪዬን በተመለከተ ማንም አያምነኝም። እኔ በእኔ ገቢና ወጪ እመኑ ትድናላችሁ አላልኩ። እስኪ ይታያችሁ ጥሎብን ግን አለመተማመን ይቀናናል። አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹ሰው ዝም ብሎ የአምላኩን ማዳን ቢያምን ለእርሱ መልካም ነው…›› እያሉ ቃል የሚጠቅሱት አንድም ይኼን ይኼን ሲታዘቡ ነው። ታዲያ ሰው በሰው ጉዳይ ምን አገባው? ይኼ ነው ትርክቱ። አንድም ‘የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል’ ይሏት ብሂል፣ አንድም ቅናት በዚህች በእኛዋ ምስኪን አገር ያሉ፣ የነበሩ፣ ወደፊት ግን እንዳይኖሩ የምመኛቸው ነገሮች እንቅልፍ ስለሚነሱን ነው። ‘ደላላው አንበርብር ምንተስኖት በተለይ የአባልነት መታወቂያ ካርድ ካወጣ በኋላ ገቢው ከኢኮኖሚ ዕድገቱ በሁለት አኃዝ ጨምሮ አድጓል’ ነው አሉ የሚሉኝ። የሚሉኝ እንኳን ራሳቸውን ስለማያውቁ የት ይሁኑ እነ ማን እንጃላቸው። አንድ ነገር ግን እንዳትረሱ፡፡ እነሱ ፈጥረው ያወሩትን የሚያስተጋቡ ብዙ የዋሆች ወይም ጅሎች አሉ፡፡ ስንቱ የተጎዳው ከተናገረው ይልቅ እየዞረ ባሠራጨው ነው፡፡ አይደል እንዴ!

ታዲያ ግርም የሚለኝ የዚህ የአባልነቱ ነገር ነው። በተለይ መቼ ዕለት አንድ ስካቫተር እያሻሻጥኩ ሳለሁ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ባልደረባዬ የነበረ ሰው ዓይቶኝ፣ ‹‹እኛማ ቸርኬ የሌለው ጎማ እናሻሽጥ እንጂ። ይኼው ባለጊዜ በላያችን ላይ ሚሊዮን ይቆጥራል…›› ብሎኝ አለፈ። ዓይን ያወጣ ፀብ ስለተጣላን ከእሱ የምጠብቀው ነበር። ይልቅ ያልጠበቅኩት ጊዜ በምን ተዓምር ለእኔ ወግኖ መታየቱን ነው። ሳስብ ያቺ የአባልነት ሐሜት ትዝ አለችኝ። ብግን አልኩ። ‘ለምን አባል ሆኜ አንደኛውን የአበጠው አይፈነዳም?’ ብዬ ቱግ ስል ስካቫተሩን ለመግዛት በማስፈተሽ ላይ የነበረ ደንበኛዬ አስተውሎኝ፣ ‹‹ተረጋጋ እንጂ፣ እርግብ የዶሮ አባል ብትሆን ጭሮ መብላት ይቀርላታል? ተቧደንክ አልተቧደንክ ሠርተህ መብላትህን አትተው። ይልቅ ለአሉባልታ ጆሮ አትስጥ…›› አለኝ። ‘እሱስ ተሰርቆም እየተበላ ነው’ ብዬ በውስጤ ቅዝቅዝ አልኩ። ሌላው በጎረሰው እኔን ለምን ይነቀኝ? እንጃ!

በዚህ እየተገረምኩ ጧት ማታ ቤቴን ቤቴን እንዳልኩ አንገት ደፍቼ መኖሬን ያዩት ደግሞ፣ ሌላ ትርፍና ኪሳራ ሊያሰሉ ባልጠበቅኩት መንገድ መጡብኝ። የዕድራችን አባል በድንገት አረፈ ተብሎ ቀብረን መጥተናል። ንፍሮ ሊያዘግነኝ መስሎ አንድ የአሉባልታ መሐንዲስ (ቀዬው ያወጣለት ስም ስለሆነ ነው የተጠቀምኩት) መጣና አጠገቤ ተቀመጠ። ‹‹ማንጠግቦሽ እንዴት ናት ለመሆኑ? ደህና ናት?›› አለኝ በጥርጣሬ በዓይኑ እያነሳ እየጣለኝ። ‹‹ደህና ናት…›› አልኩት። ደግሞ ምን ሊወራ ነው እላለሁ። ይታወቀን የለ ነገር በሰው አንጎል ሲጋገር? ዝም ብለን ነው እንጂ በጀት የምናባክነው ‘ጆሮ ጠቢ’ አያስፈልገንም እኮ ለዚህ ለዚህ። ‹‹አንበርብር እውነቴን ነው የምልህ እንዲያው አንተ ወልደህ ቢሆን ኖሮ እኔ ሌላ ሥራ አይኖረኝም ነበር። እንዲያው ነጋ ጠባ ልጅህን ስስም ብውል ደስ እንደሚለኝ ታውቃለህ? እንዲያው ለመሆኑ ማንጠግቦሽስ ዝም ትላለች?›› ብሎኝ ትክ ብሎ ዓየኝ። ዘንድሮ እኮ ማን በየት በኩል መጥቶ ምን እንደሚያመጣባችሁ አታውቁምና ጠንቀቅ በሉ፡፡ እንዲያ ነው!

እኔ በአገሬ የወንድ ሞግዚት አይቼ አላውቅ። የሽንት ጨርቅ መቀየር ቀርቶታል እኮ ሰውዬው። ‹‹አልገባኝም?›› ስለው ኮስተር ብዬ፣ ‹‹ይኼውልህ አንበርብር ትዳር እኮ በተለያዩ የጊዜ ክፍልፋዮች የተከፋፈለ ነው። ለአፍላ ፍቅር፣ ለጫጉላ፣ ጎጆን ለማደርጀት ጊዜ አለው። አንተ እኮ ይኼው አገሬው ሁሉ በቅርቡ በስሙ ሕንፃ ገንብቶ ሳያከራይ አይቀርም የሚልህ የዶላር ችግር የሌለብህ ሰው ነህ። መታደል እኮ ይኼ ነው! ኧረረረረ! አይምሰልህ! መታደል ነው። ታዲያ ዘር ከሌለበት ፍቅርም እኮ ይቀዘቅዛል። መላመድ አለ…›› ቅብጥርሶ እያለ ሲቀጥል ልቤ በንዴት ነፈረ። ቀዝቀዝ ካልኩ በኋላ ከአጠገቡ ተነስቼ ሄድኩ፡፡ ነገሩ እንዲያው ግርም ብሎኝ በኋላ ለማንጠግቦሽ ስነግራት፣ ‹‹መውለድ አቅቶኝ ቢሆን፣ እሱም የሚያከራየው ማህፀን ኖሮት ቢሆን አንድ ነገር ነው። ያልፀነሰውን ከሚያምጥ ያረረ ድስቱን አያማስልም?›› ብላ አራስ ነብር ሆና ሰነበተች። ትዳር መኪና ቢሆን ብላችሁ አስቡ ለቅፅበት። ‘አልቻልክበትም እኔ ስነዳ እይ’ ሊባል ነው እንዴ? በሰው እግዚኦ!

እንግዲህ ጨዋታም አይደል የያዝነው? ከደላላ አንዱና ዋነኛ ተግባር ስለላ ነው። ዘወር ዘወር ማለት አለ። ማሰስ ደግሞ ከመሀል አይጀመርም። ለነገሩ የኮንዶሚኒየሙ ትውልድ እንጀራ መጋገር ስለተወ የምጣድ ምሳሌ ይለፈው። ስካቫተሩን አሻሽጬ ያገኘሁትን ጠቀም ያለ ረብጣ ባንክ ቤት ከትቼ ሻይ ቡና እያልኩ ደግሞ ሌላ ሥራ ልፈልግ ስወጣ ሠፈራችን በአንድ እግሩ ቆሟል። ‹‹ምንድነው?›› ስል ሳያሰልሱ ከባሻዬ ጋር በአጥር የሚጣሉ አባወራ መሀል መንገድ ላይ ቁጭ ብለው ሲፀዳዱ ደረስኩ። መንደርተኛው እግዚኦ ይላል። ‹‹በቃ ሰውዬው ለቀዋል አማኑኤል እንውሰዳቸው…›› ትላለች ከኋላዬ አንደኛዋ በመብረቅ ድምፅ። ገና ለገና ባሻዬ የዕድሩ ሰብሳቢና ገንዘብ ያዥ ናቸው በሚል አጉል ተስፋ ደግሞ ጆሮ በሚበሳ ድምፅ፣ ‹‹እሰይ ባሻዬ ተገላገሉ፣ አረፉ ከእኝህ ነገረኛ ሰውዬ…›› ይባልልኛል። ዘወር ስል የባሻዬን ልጅ አየሁት። ተጠቃቀስንና ወደ አዛውንቱ ጠጋ ብለን፣ ‹‹ምነው? ምነው? አሁን ይኼ ከእርስዎ ይጠበቃል? በተከበሩበት አገር?›› ብዬ ጀመርኩ። አገጫቸውን እንደተደገፉ ምንም የመደንገጥ ምልክት ሳያሳዩ፣ ‹‹አይ ልጄ እኔስ ሆን ብዬ ነው ይህን የማደርገው፣ ይብላኝ ለአፋሹ…›› እያሉ ሳቁ። የባሻዬ ልጅ ተናዶ፣ ‹‹እኮ ምን አስበው?›› አላቸው። ‹‹አይገርምህም? ይኼ የአካባቢያችን ሰው እኔ እዚህ የተፈጥሮ ግዳጄን ስወጣ ዓይቶ እንደደነገጠው፣ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ቦምብ ሙከራ አደረገች፣ አሜሪካ ሊሰነዘርባት ከሚችል ማንኛው አደጋ ራሷን ለመጠበቅ የጦር ኃይሏን በተጠንቀቅ አሠለፈች፣ ሩሲያ ምዕራባውያንን አዲዮስ ብላ ዩክሬንን ወረረች፣ ዓለም መጥፊያዋ ደረሰ… ሲባል ደንግጧል? አልደነገጠም፡፡ የፍትሕ ዕጦቱን፣ የእጅ አዙር ጣልቃ ገብነቱን፣ የመልካም አስተዳደር ብልሽቱን፣ ዝርፊያውንና ሌላውን ውንብድና ለምደነው ምን እልሃለሁ? በቃ ለምደነው ጭራሽ ስንኮተኩተው እንውላለን። አሁን እስኪ ከእኔ ድርጊትና ከነገርኩህ የቱ ጨርቅ ያስጥላል?›› ብለው ሁለታችንም ላይ ሲያፈጡ ማን የአዕምሮ ሐኪም ዕገዛ እንደሚያስፈልገው ገባኝ። አልገባችሁም? ልድገመው እንዴ!

በሉ እንሰነባበት። ያጫወትኳችሁ የሰውየው ድርጊት የአለቃ ገብረ ሃናን ነገር አስታወሰኝ። አንዳንዶች የዚህ ታሪክ ዋና ባለመብት ሌላ ሰው ናቸው ሲሉ ብሰማም፣ ‘ቱ ሌት’ በማለት በአለቃ ገብረ ሃና ስም አጫውታችኋለሁ። በነገራችን ላይ አሻሻልኩ ብሎ አንድን ጥሩ መሠረት ማናጋት በበኩሌ ማወቅ አልለውም። ከመፈላሰፌ በፊት ግን የአለቃን የምታውቋትን ጨዋታ ጫፍ ላስያዛችሁ። ግብዣ ተጠርተው ኖሮ የአዘቦት ልብሳቸውን ለብሰው ሲሄዱ አትገቡም ተባሉ አሉ። ተመልሰው የክት ልብሳቸውን ለብሰው ሲሄዱ ታሪኳ ትዝ ትላችኋለች። አስታወሳችኋት? ላለማሰልቸት አልጨርሳትም። በዚህ አጋጣሚ እንኳን ፕሮፓጋንዳ ተረትም ሲደጋገም እንደሚሰለች መልዕክት ለማስተላለፍ በማለት ያለ ስፖንሰር የሠራሁት ማስታወቂያ ነው። ምናልባት አንዳንዶቻችሁ ኤርፎን ሰክታችሁ ቴሌቪዥን እያያችሁ ከሆነ ምራ አልመራም ከሚባለው ጣጣ ስላመለጣችሁ ደስ ይበላችሁ። ግን በስም እንኳ ዴሞክራሲ ባይኖር አሁን ይኼን ሁሉ ብዬ የት እገባ ነበር? አይታወቅም!

ስቀጥል… (ከአጀማመራችሁ ይልቅ ለአጨራረሳችሁ ፀልዩ እያልኩ አጨራረሴን ላከሽፈው ነው መስል) እንኳን ከሕይወት ከሞት መማር ባንወድም ከአለቃ ‘ልብሴ እንጂ እኔ አልተጠራሁም’ ተረት የምንመዛት ነገር አለች። በያዝነውና ባፈራነው ልክ እንጂ የሰው ዘር አባል በመሆናችን ብቻ መከባበር ድሮ ቀርቷል። ለነገሩ ድሮም ባይኖር ነው አለቃ ልብሳቸውን ወጥ የለቀለቁት። ግን ወደፊት ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም? ለተሻለ ነገ፣ ለተሻለ ብሩህ ወደፊት በስሚንቶና በብሎኬት ብቻ መሠረት አይጣልም እላለለሁ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት። አዋጅ ከመሰለም ይምሰል፡፡ ማን አውጆ ማን ይቀራል? እንዴ? ሳንከባበር ፍቅር አለ ታዲያ? ፍቅር ሳይኖር እኛ የሚባል ተውላጠ ስም ባዶ ቃል አይሆንም? አገር ያለ ሰው ካልቆመች ሰው እንደ ሰውነቱ ሊታይ አይገባውም? እስኪ የሰው ዘር አባል እንሁን መጀመሪያ፡፡ ሰው ከመሆን በፊት የሚቀድምብን ካለ ዳርዊን የሚባለው ሰውዬ እንዳለው ዝምድናችን ከጦጣ ወይም ከዝንጀሮ እንዳይሆን እሠጋለሁ፡፡ እኛ ግን በአምላክ አምሳል የተፈጠርን ስለሆንን ሰው እንሁን፡፡ ሰው ከመሆን በፊት ምንም አይቅደምብን፡፡ ሰው መሆን ልዩ ነገር ነው፡፡ በዓለም ውስጥ ያሉ እንስሳት፣ አዕዋፍ፣ የባህር ፍጥረታትና ተክሎች በሙሉ ከሰው በታች ናቸው ይላል ቅዱስ መጽሐፉ፡፡ ሰው የተፈጠረውም የእነዚህ ሁሉ የበላይ ለመሆን ነው፡፡ እኔም እላለሁ መሬት ከሰው አትበልጥም፡፡ ማንም ከሰው አይበልጥም፡፡ ስለዚህ ሰው እንሁን! መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት