Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሕፃናት የሚበዘበዙባቸው የጎዳና ሥራዎች

ሕፃናት የሚበዘበዙባቸው የጎዳና ሥራዎች

ቀን:

በአዲስ አበባ ጎዳና በሕፃናት ላይ የሚተገበሩ በርካታ ሕገወጥ ተግባሮች ይታያሉ፡፡ ከእነዚህ ሕገወጥ ሥራዎች መካከል ሕፃናትን ከቀያቸውና ከትምህርት ገበታ ላይ በማፈናቀል በተለያዩ ሥራዎች ማሰማራት ይገኝበታል፡፡

 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በብዛት በሚዛን፣ ሶፍት፣ ሚስክና ሌሎች ጥቃቅን ቁሳቁሶች በማዞር ሥራ ላይ የተሰማሩ በርካታ ሕፃናትን ማየቱም የተለመደ ሆኗል፡፡

ከሕፃናቱ መካከል ዕድሜያቸው ከአሥር ዓመት በታች የሚገመቱ ሲሆኑ አብዛኞቹ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ብቻ አቀላጥፈው መናገር የሚችሉ ናቸው፡፡

ሕፃናቱ ከተሰማሩባቸው ሥራዎች አንዱ ሚዛን ሲሆን፣ በየአሥር ሜትሩ ‹‹የተመዘኑ›› ጥሪ መስማት ነው፡፡ የተለመደ ለምን እንደዚህ እንደሆኑ የሚጠይቅላቸው አካል ግን አይታይም፡፡ ለዚህም የአዲስ አበባ መንገድ ዳር ሚዛን መሬት አድርገው ቀን ሙሉ የተመዘኑልን ልምና የሚያስተጋቡ ሕፃናት ምስክር ናቸው፡፡

ከወላይታ፣ አካባቢ እንደመጣ የሚናገረው የስምንት ዓመቱ ጳውሎስ ተካልኝ ሚዛን ሥራ ላይ ከተሰማራ አንድ ዓመት እንደሆነው በተኮላተፈ አማርኛው ይናገራል፡፡ ታዳጊ ጳውሎስ ከወላይታ አካባባቢ የመጣው እሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጓደኞች ጭምር መሆናቸውን ገልጿል፡፡ በተወለደበት ቀዬ የአንደኛ ክፍል ተማሪ እንደነበር የተናገረው ጳውሎስ፣ እኛ ስናናግረው በሁሉም አቅጣጫ በመጠራጠር ይመለከት ነበር፡፡ ምን ሆኖ እንደሆነ ስንጠይቀው፣ አሠሪዎቹ በዚያው አካባቢ ያሉ በሊስትሮ ሥራ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ነግሮናል፡፡

ታዳጊው እንደተናገረው፣ በቀን እስከ አንድ መቶ ብር ገቢ ማስገባት የግዴታው ነው፡፡ ይህን መቶ ብር በቀን ካልሠራ ምግብ እንኳን አይመገብም፡፡ እርቦ አፉ ላይ ለሚቀምሰው ካጎደለ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡

ለዚህም ያለው አማራጭ ሰዎች እስኪሰለቹ እየለመነ የሚጠበቅበትን ገቢ ማግኘት ነው፡፡  

ስሙን መግለጽ ያልፈለገው በሊስትሮ ሥራ ላይ የተሰማራ አንድ ወጣት ለሪፖርተር እንደተናገረው፣ አብዛኛው ሕፃናት በቅርብ ዘመዶቻቸው አማካይነት ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡

ከቤታቸው ሲያመጧቸው እንደሚያስተምሯቸውና እንዲማማሩና መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው እንደሚሟላላቸው ቤተሰብን በማሳመን ነው፡፡ እዚህ ከመጡ በኋላ ግን የትምህርትን አላስፈላጊነት ሰብከው በሚዛንና በሌሎች ሥራዎች ላይ ያሰማሯቸዋል፡፡

 ወጣቱ ለአራት ዓመታት በሊስትሮ ሥራ ላይ ተሰማርቶ እየሠራ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ እሱም በዚህ ችግር ውስጥ ማለፉን ጠቁሟል፡፡

ሕፃናቱ በብዛት የሚመጡት ከወላይታ፣ አርባ ምንጭና በዙሪያዋ ከሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች መሆኑን፣ ቤተሰቦቻቸውም ስለትምህርትና መሠረታዊ የሰው ልጆች ፍላጎቶች ዙሪያ ግንዛቤ ስለሌላቸው ብዙዎቹ ስለልጆቻቸው እንደማይጠይቁ ይናገራል፡፡

በምሳሌነት ያነሳውም የእሱን ቤተሰቦች ነው፡፡ ከአምስትና ከስድስት እኩዮቹ ጋር ወደ አዲስ አበባ መምጣቱን፣ በብዙ ችግሮች ውስጥ ማሳለፉንም ያስታውሳል፡፡ ይህ የብዙዎች የጎዳና ላይ ሚዛን ሠሪዎች፣ ሶፍት አዟሪዎች ታሪክ ነውም ይላል፡፡

አብዛኞቹ ሕፃናት ጫማና ልብስ እንደሌላቸውና ምግብ በሰዓቱ እንደማያገኙ ገልጾ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ፖሊስና ሌሎችም የመንግሥት አካላት አይተው እንዳላዩ የሕፃናቱን መሠረታዊ ችግር ተረድተው መፍትሔ እንዲያበጅ ጠይቋል፡፡

መማር ያለባቸው ሕፃናት ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ፣ ምግብና መሠረታዊ ፍላጎታቸውን አለማሟላትና ድብደባ መፈጸም እናስተምራለን ብለው ከቤተሰብ ባስመጡ ወጣት ሊስትሮዎች የሚተገበር ነው ብሏል፡፡

በተለይ ሚዛን ላይ የተሰማሩ ሕፃናት ዘጠኝና አሥር ዓመት በላይ ሲሆናቸው በተለያዩ ቦታዎች እየዞሩ ጫማ እንዲጠርጉ እንደሚታዘዙ አክሏል፡፡

በራሳቸው ብቻ የሚሠሩ ወጣቶች እንዳሉ፣ ነገር ግን በተለይ በአብዛኛው ‹‹ሚዛን›› ላይ የተሰማሩ ሕፃናት አብዛኞቹ በሕገወጥ መንገድ ቀድመው የመጡ ዘመዶቻቸው ያመጧቸው መሆናቸውን አስረድቷል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕፃናት ጥበቃ ግንዛቤ ማካተት ዳይሬክተር አቶ በለጠ ዳኜ እንደተናገሩት፣ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ይመለከተዋል፡፡

ከመብት ጥሰትና ሌሎች ችግሮች ላይ የሚሠሩ ሥራዎችን በተመለከተ በቀድሞ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ በአሁኑ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አማካይነት የሚታዩ ናቸው፡፡ የሕፃናት የጉልበት ብዝበዛን በተመለከተ በሁለት ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በተለይም በየጎዳና የሚገኙ ሚዛንና መሰል ሥራዎች ላይ ስለተሰማሩ ሕፃናት ጥናቶች እንደሌሉ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ በሚኒስቴር ደረጃ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የግንዛቤ ሥራዎች እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ይህ የሕፃናት ድጋፍና መብት በሚሉ ሁለት ክፍሎች የሚታይና በፌዴራል ደረጃ የሚሠራው የሚወጡ ሕጎችን በክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እንዲተገበሩ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግና የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት በፌዴራል ደረጃ የሚሠሩ መሆናቸውን፣ ወደ ታች ወርደው የሚሠሩት ደግሞ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዋናነት ጎዳና የሚሠሩና የሚኖሩ ሕፃናትን በተመለከተ ችግሩ የት እንዳለ ለማወቅ፣ ከምንጩ ለማድረቅ ደግሞ ክልሎች ከወረዳ ጋር ታች ወርደው እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በደቡብ አርባ ምንጭና ወላይታ፣ ኦሮሚያ ዝዋይና አካባቢው፣ ደሴ ደቡብ ወሎ ሲዳማና ሌሎች አካባቢዎች የሕፃናት ፍልሰትና ሕገወጥ ሕፃናት ዝውወር ይበዛባቸዋል በሚባሉ ቦታዎች ላይ መድረክ በማዘጋጀትና ቡድን በመላክ ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ከሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ጋር በተያያዘ አርባ ምንጭ፣ ጨንቻና ሌሎችም አካባቢዎች ድረስ በመሄድ ባለፉት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ሠራታቸውን አቶ በለጠ አክለዋል፡፡

የሕፃናት ማኅበራዊ ችግር ያለበት መጠነ ሰፊ በመሆኑ፣ በአንድ ጊዜ ለውጥ የሚታይበት አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ችግሩን ከምንጩ ለመቅረፍ ሕፃናቱ ከሚወጡባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ማኅበረሰቦች የግንዛቤ ማስበጫና ቤተሰቦቻቸው ስለችግሩ እንዲረዱ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡

የሕፃናት ጉዳይ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሥር ተያዘ እንጂ የፍትሕ አካላት፣ የትምህርትና ዘርፍ፣ የጤና ዘርፎችና ሌሎችም ተካተው የሚሠሩት እንደሆነ ዳይሬክተሩ አክለው፣ በፌደራል ደረጃ ቻይልድ ፕሮቴክሽን ኬዝ ማኔጅመንት ፍሬም ወርክ የሚባል ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን የሚዳስስ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለእያንዳንዱ ሕፃናት አገልግሎት እንደማይሰጡ፣ ዕቅድና መመርያ በማውጣት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን መከታተል በየዓመቱ በሚደረገው የዕቅድ ግምገማ ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች እንዲወርድ እንደሚደረግ አቶ በለጠ ተናግረዋል፡፡

በፌዴራል ደረጃ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ፣ ታች ወርደው የሚሠሩ ደግሞ ክልሎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕፃናት ድጋፍ እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ አንዱዓለም ታፈሰ በበኩላቸው፣ በአብዛኛው እየተሠራ ያለው የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግና ሥልጠና መስጠት ላይ እንደሆነና በሕፃናት ላይ የሚሠሩ ወንጀሎችን ለመከላከል ትኩረት እንደተሰጠ ጠቁመዋል፡፡

በዋናነት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ የሚሠራ ቢሆንም፣ ጥቃቶች ተፈጽመው ሲገኙ፣ ሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ሲደረግባቸው፣ በሕገወጥ መንገድ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ ከፖሊስ ጋር በመሆን ወደ ሕግ እንዲቅርቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ሕፃናት በሚያሠሯቸው ግለሰቦች ዙሪያ ቢሮው መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ችግሩ ላይ በስፋት ለመሥራት በ2015 ዓ.ም. ራሱን የቻለ አሠራርና መመርያዎች ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ አንዱዓለም ተናግረዋል፡፡

የሕፃናት ልመናና፣ ጉልበት ብዝበዛንና የጎዳና ተጋላጭነትን አስመልክቶ በራሱ የውስጥ አሠራር መመርያዎችን ለመተግበር ሒደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ ጎዳና ላይ ያሉ ችግሮችን ከማየት ባሻገር ወደ ቤተሰቦቻቸው የተቀላቀሉ ብዙ ሕፃናት ተመልሰው የሚወጡበት አጋጣሚዎች የጎላ በመሆኑ፣ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ በፌደራል ደረጃ እየተሠራ አስረድተዋል፡፡

ሕፃናት በጦርነት፣ በድርቅ፣ በድህነትና ሌሎችም ችግሮችም የሚፈልሱ መሆናቸውን፡፡

ለጉልበት ብዝበዛ የተጋለጡ ሕፃናት ዙሪያ ጥቆማዎች እንደሚመጡ የገለጹት አቶ አንዷለም፣ በወረዳ መዋቅሮች አማካይነት ከፖሊስ አባላት ጋር እየሠሩ እንደሚገኙ፣ ዘንድሮ ሁለት ጊዜ ጥቆማ እንደደረሳቸው 19 ሕፃናትን መታደጋቸውን አስረድተዋል፡፡

ሕፃናቱን ሲያሠራ የነበረው አንድ ግለሰብ መሆኑን፣ ልጆቹም ንፋስ ስልክ (ሃና ማርያም) አካባቢ እንደተገኙም አክለዋል፡፡

ሕፃናቱ በማገገሚያ ከቆዩ በኋላ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ መደረጋቸውን፣ ግለሰቡ ለሕግ ቀርበው ቅጣት እንዲቀበሉ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ የሕፃናት የጉልበት ብዝበዛና መሰል ወንጀሎችን መከላከል በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋሞች ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ፣ የማኅበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...