- እሺ ውይይቱን ከየት እንጀምር?
- ዴሞክራሲን ለመትከል ተግዳሮት ከሆኑብን ጉዳዮች ብንጀምር መልካም ይመስለኛል ክቡር ሚኒስትር።
- ጥሩ።
- አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። እንደሚታወቀው ዴሞክራሲን ለማስረፅ ከጀመርናቸው እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ መሥራት መሆኑ ይታወቃል።
- ከታወቀ ለምን ትደግመዋለህ?
- ለመንደርደሪያ ያህል ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ከመንደርደር በቀጥታ ጉዳዩን ማንሳት አይሻልም?
- ጥሩ ክቡር ሚኒስትር። ተቀራርቦ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ባስቀመጠነው አቅጣጫ መሠረት አቅርበናቸዋል ብቻ ሳይሆን መቀራረባችንን የሚመጥን ስያሜ እንዲያገኙ አድርገናል።
- የምን ስያሜ?
- ተቃዋሚ የሚለውን ስያሜ በመቀየር ተፎካካሪ ብለናቸዋል።
- አሁንም መንደርደሪያ ላይ ነህ?
- አቤት ክቡር ሚኒስትር?
- ለምን ወደ ጉዳዩ አትገባም?
- ወደ እሱ እየመጣሁ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሺ ተፎካካሪ ብለን ሰየምናቸው። ምን አገኘን?
- ተፎካካሪ ብለን በመሰየም ብቻ አላቆምንም። የካቢኔ አባል ጭምር እንዲሆኑም አድርገናል።
- ጤና የለውም እንዴ ሰውዬው! ምን ልትነግረኝ ነው የፈለግከው?
- ክቡር ሚኒስትር መሠረቱን ያነሳሁት ቀጥዬ ለማቅርበው ዋና ጉዳይ ጠቀሜታ ስላለው ነው።
- እሺ ቀጥል።
- አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። በገለጽኩት መንገድ መሠረቱን በማስያዛችን አሁን ላይ ውጤቱን ማየት ጀምረናል።
- ምንድን ነው መታየት የጀመረው ውጤት?
- ክቡር ሚኒስትር የእኛን ካድሬዎች ጣልቃ እንዲገቡ ሳናደርግ መናቆር ጀምረዋል።
- ያስቀመጥነው ግብ መናቆር ነው ወይስ መቆም እንዳይችሉ ማድረግ? ይህንን ነው ውጤት የምትለው!
- ክቡር ሚኒስትር አሁን የታየው ጅማሮ ነው። ያስቀመጥነው ግብ ላይ በፍጥነት መድረሳቸው አይቀርም።
- ያስቀመጥነው ግብ ላይ በፍጥነት መድረስ ካልቻልን ዴሞክራሲን ማፅናት ፈጽሞ አንችልም።
- ትክክል ነው ክቡር ሚኒስትር።
- እሱን ንገረኝ አላልኩም።
- ግቡን በፍጥነት ማሳካት የምንችልበትን ስትራቴጂ ቀርፀን እየተንቀሳቀስን ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ምን ለማድረግ ነው ያሰባችሁት?
- የበለጠ ማቅረብ!
- ጥሩ። ከእኛ ጋር በቅርበት የማይሠሩት ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንቅስቃሴስ ምን ይመስላል?
- እርማት ክቡር ሚኒስትር?
- የምን እርማት?
- እነሱን ተፎካካሪ ፓርቲ ብለን አንጠራቸውም።
- እና?
- ተቃዋሚ ነው የምንላቸው። እነሱም እንደተቃዋሚ ነው የሚንቀሳቀሱት።
- ይሁን እሺ። የእነሱን ጉዳይ እንዴት እየተከታተላችሁ ነው? ለምሳሌ በቅርቡ ለሚዲያ ቃለመጠይቅ የሰጡ እንዳሉ ሰምቻለሁ።
- አሁን የተቸገርነው በሚዲያዎች ነው።
- ለምን … እንዴት?
- አብዛኞቹን አስገብተናቸዋል ስንል….ከሥር ይፈላሉ!
- በቅርቡ ቃለመጠይቅ የሰጡት ተቃዋሚ ላይ የሚደረገው ክትትል እንዴት ነው?
- ክትትሉን አጠናክረን ቀጥለናል ክቡር ሚኒስትር። ከሰሞኑ የሰጡት ቃለመጠይቅም በጎ የሚባል ነው።
- አገሪቱ ገደል አፋፍ ላይ የቆመ አቶብስ እንደምትመሰል መግለጻቸው ነው በጎ የሚባለው?
- ዋናው ነገር …
- እሺ። የፊት ጎማቸው ገደሉ ውስጥ ገብቶ በኋላ ጎማቸው ብቻ ነው የተንጠለጠሉት ማለታቸው ነው በጎ ነገር?
- አውቶብሱን ተጋግዘን ማውጣት አለብን ብለዋል እኮ ክቡር ሚኒስትር?
- እሱስ ቢሆን? በራሳቸው መውጣት አይችሉም ማለታቸው አይደለም?
- ዋናው ነገር …
- ምንድን ነው ዋናው ነገር … ዋናው ነገር የምትለው? ምን ዋና ነገር አለው!
- ሹፌሩ አውቶብሱ ውስጥ አለ ብለዋል።
- እርግጠኛ ነህ እንደዚያ ብለዋል?
- ሹፌሩ ከአውቶብስ ውስጥ እንዳለ አውቶውብሱን ተጋግዘን እናውጣ ነው ያሉት!
- እንደዚያ ከሆነ ጥሩ ነው።
- እንደዚያ ነው ያሉት። በዚህ ከቀጠሉ ትንሽ አይተን ስያሜያቸው ቢቀየር ጥሩ ነው።
- ስያሜያቸው ምን ሊባል?
- አጋር፡፡
- በአንድ ጊዜ አጋር?
- እና ምን ይሻላል?
- በተፎካካሪ ይቆዩ።
- Advertisment -
- Advertisment -