Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቼክ ለሚፈጸሙ ማጭበርበሮች የኢትዮ ቴሌኮም አሠራርና ሠራተኞች ተወቀሱ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም አሠራሩ ዘመናዊ መሆኑን በመግለጽ ወቀሳውን አስተባብሏል

የፍትሕ ሚኒስቴር ምርመራ ባደረገባቸው 155 በባንኮቸ ላይ የሚፈጸሙ የምዝበራ ወንጀል መዛግብትን መሠረት አድርጎ ባካሄደው ጥናት፣ ከመዛግብት ዓይነቶች ውስጥ በቼኮች ላይ ለሚፈጸሙ ማጭበርበሮች የኢትዮ ቴሌኮም የአሠራር ክፍተቶች፣ እንዲሁም የአንዳንድ ሠራተኞች ተሳትፎ ዋነኛው መሆኑ ተገለጸ።

ሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል በፍትሕ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የተለያዩ ባንኮች ፕሬዚዳንቶች የተገኙ ሲሆን፣ በዓይነቱ ልዩና የመጀመርያ የሆነ ትኩረቱን በባንኮችና አሠራሮቻቸው ላይ ያደረገ ጥናት ይፋ ሆኗል፡፡ በጥናቱ ግኝት መሠረት ባንኮችም ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉ በዝርዝር አብራርቷል፡፡

ጥናቱ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የወንጀል ምርመራዎችና ክርክር ሒደቶች ላይ ያሉና ውሳኔ ያገኙ 16 ባንኮችን ያካተተ ነው በባንክ ምዝበራ ወንጀሎች በተካተቱት መዝገቦች ባንኮች 1.9 ቢሊዮን ብር ያህል መመዝበራቸውን፣  370.6 ሚሊዮን ብር ብቻ ማዳን መቻሉ ተገልጿል።

በፍትሕ ሚኒስቴር ጥናት መሠረት ባንኮቹ የተመዘበሩት በዘጠኝ የማጭበርበር  የወንጀል ዓይነቶች ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ የተሰረቁ ቼኮች ስምንት በመቶ፣ ሐሰተኛ ቼኮች ደግሞ 30 በመቶ የሚሆነውንና ድርሻ ይዘዋል።

ማጭበርበር ተፈጽሞባቸዋል ከተባሉት ዘዴዎች ውስጥ በቁጠባ ደብተር 21 በመቶ፣ ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም 18 በመቶ በመሆን ከፍተኛውን ድርሻ ሲይዙ፣ እንደ ሐሰተኛ ሲፒዮ፣ ሞባይል ባንኪንግ፣ ኤቲኤም፣ ሃዋላ፣ የይለፍ ቃል ስርቆትና ሌሎች ምክንያቶች ተጠቅሰዋል።

ከፍተኛውን ድርሻ በያዙት ቼኮችን መሠረት ያደረጉ የማጭበርበር ወንጀሎች፣ የኢትዮ ቴሌኮም አሠራር ክፍተትና የአንዳንድ ሠራተኞች ተሳትፎ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው በጥናቱ ተገልጿል።

ከኢትዮ ቴሌኮም አስተዋጽኦዎች ውስጥ የባለቼኮቹን ስልክ ለአጭር ጊዜ ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የስልኩን ጥሪ ወደ ሌላ ስልክ ማዛወርና ትክክለኛ ሲም ካርድ አዘግቶ ምትክ ሲም ካርድ ማውጣት እንደሚገኙበት፣ በፍትሕ ሚኒስቴር የጥናት ቡድን ሰብሳቢ አቶ ገብረ እግዚአብሔር ወልደ ገብርኤል በምክክር መድረኩ ላይ ገልጸዋል።

እንደ ቡድኑ ሰብሳቢ ገለጻ የተለያዩ ክፍተቶች የታዩባቸው አሠራሮች ሲኖሩ፣ እነሱም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ አለማድረግ፣ የምትክ ሲም ካርድ አሰጣጥ ሥርዓት ክፍተት፣ የሠራተኞች ሥነ ምግባር ክፍተት፣ የሕግ ጥሰት በፈጸሙ ሠራተኞች ላይ ማስረጃ አለመስጠትና ትብብር አለማድረግ ይጠቀሳሉ። ለዚህም ጥናቱ የመረመራቸውን መዛግብት በመጥቀስ እንደ ምሳሌ አካቷል።

‹‹ወንጀሉን ፈጻሚዎች ኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ በሚሠራ ሰው አማካይነት የተበዳይን ሲም ካርድ ፒዩኬ ቁጥር (PUK Code) በማግኘት ደውለው ስልኩን ያዘጋሉ፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ገብረ እግዚአብሔር፣ እንዴት የተሰረቀ ቼክ ጽፈውና ፈርመው ወደ ባንክ በመሄድ ብር እንደሚያወጡ አስረድተዋል።

በኢትዮ ቴሌኮም በኩልም ተቋሙ አሠራሩን በመቀየር ዘመናዊ ያደረገ መሆኑን በመግለጽ፣ ማንም ግለሰብ ሲም ካርድ ከባለቤቱ በስተቀር ፒዩኬ ቁጥር (PUK Code) ማግኘት አይችልም ተብሏል።

ከአሠራሮች አንደኛው ደንበኞች ወደ 994 በሚደውሉ ጊዜ የሚደረገው የድምፅ ቅጂ፣ ‹‹በአሁን ጊዜ የደንበኞች አገልግሎት ሠራተኞች ማግኘት ስለሚችሉ፣ ማን እንደ ደወለና ጥፋት እንደፈጸመ ማወቅ ይቻላል፤›› ያሉት፣ በኢትዮ ቴሌኮም የመረጃ ደኅንነትና የምዝበራ ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ጀማል መሐመድ ናቸው።

‹‹ሳይደወልለትና ሳይጠየቅ ማንኛውም ባለሙያ የሰው ፒዩኬ ቁጥር (PUK Code) እና ሌሎች መረጃዎችን ገብቶ ቢያይም፣ በቼክና ባላንስ ማወቅ ይቻላል፤›› ሲሉ አቶ ጀማል የተቋማቸውን የቁጥጥር አሠራር ለሪፖርተር ገልጸዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በዘረጋው አሠራር ማንኛውም ሠራተኛ የማንኛውንም ደንበኛ መረጃ ቢያይ ተቋሙ ሙሉ ለሙሉ ማወቅ እንደሚችል፣ የሕግ ክፍሉም አስፈላጊ መረጃዎችን በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የማይሰጥበት ምክንያት እንደሌለ አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የድርጅቱ ሠራተኞች በሐሰተኛ መታወቂያ ሊጭበረበሩ እንደሚችሉ፣ እንዲሁም በተጨማሪ እነሱም በትብብር ሊሳተፉ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ ድርጊቱን ፈጽሞ በሚገኝ ሠራተኛ ላይ ድርጅቱ የማያዳግም ዕርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል። ‹‹ባለፈው ዓመት ብቻ በርካታ ሠራተኞችን በዚህ የሕግ ጥሰት ከሥራ ተሰናብተዋል፤›› ሲሉ አቶ ጀማል ገልጸዋል።

የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ የተለያዩ መደረግ አለበት ያሏቸውን ምክረ ሐሳቦች ጠቅሰዋል። የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኞች የሚፈጽሙዋቸውን ጥሰቶች የሚከላከል መመርያ ማውጣት፣ ሲም ካርድ በጥንቃቄ እንዲወጣና እንዲዘጋ ማድረግና የባዮሜትሪክ ዳታን በሲስተሙ ውስጥ ማስገባት ለጥንቃቄ እንደሚጠቅም አስረድተዋል። ‹‹ድርጅቱ ጥፋተኞችን አሳልፎ በመስጠትና ክትትል በማድረግ ረገድ የድርሻውን መወጣት አለበት፤›› በማለትም አክለዋል። 

በውይይቱ ላይ የተገኙት የባንክ ኃላፊዎች በቼክ አማካይነት የሚፈጸም ማጭበርበር ከገንዘብ ለውጡ ጋር ተያይዞ በመጡ አሠራሮች ምክንያት፣ ባለቼኮች በርካታ ገንዘብ ወጪ ማድረግ ስለማይችሉ እንደቀነሰ ገልጸዋል።

ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪም በሌሎች በርካታ ተቋማት ላይ ያለውን የአሠራር ክፍተት ጥናቱ ያካተተ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ በራሳቸው በባንኮች የሚስተዋሉ ከፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት ለመሸሽ መሞከር፣ ገለልተኛ ኦዲተር አለመኖር፣ እንደ ባዮሜትሪክ ዳታ ዓይነት ዘመናዊ አሠራር አለመከተልና የደንበኛን ሚስጥራዊ መረጃዎች  ሠራተኞች እንደፈለጉ እንዳይመለከቱ አለመገደብ ተጠቅሰዋል።

ሌላው ተቋም ደግሞ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ሲሆን፣ በኤጀንሲው ሐሰተኛ ውክልናዎች መስጠት መበራከት፣ በሐሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ ውክልና እንዲሰጥ ማድረግና የኤጀንሲው ሠራተኞች ከወንጀለኞች ጋር ትብብር ማድረጋቸውን ይጨምራል። በወሳኝ ኩነት ምዝገባ በኩልም የመታወቂያ አሰጣጥ እንደ ክፍተትና ምክንያት ታይቷል።

በአጠቃላይ ተመዘበረ ከተባለው ገንዘብ ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈጸመ መሆኑን፣ አቢሲንያ ባንክ በ17 በመቶ በሁለተኝነት እንደሚከተል፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክና ወጋገን ባንክ እያንዳንዳቸው ከስምንት በመቶ በላይ የተመዘበረ ገንዘብ በማስመዝገብ ሦስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸው በጥናቱ ተመልክቷል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች