በመከላከያ ሚኒስቴር በተለያዩ ክፍለ ጦር ውስጥ ያሉና የለቀቁ የሠራዊት አባላት፣ ባለሀብቶችን ዒላማ በማድረግ አጥንተውና ለይተው በማሳደድ፣ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሠረተ፡፡
የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ)፣ 33 እና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(2) ድንጋጌዎችን በመተላለፍ፣ ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው፣ መቶ አለቃ ሀጂ ቱሉ፣ ኦፊሰር መንግሥቱ በቀለ፣ ሻምበል ሻምበል ከሀሊ፣ አሸናፊ ወልደ ሰማያት፣ ሹምበዛ ፍቃዱ፣ አዲስ ዓለሙ፣ ተስፋዬ ለሚ (በሌሉበት) እና ሻለቃ ዱጉማ (ከመከላከያ የለቀቁና በሌሉበት የተከሰሱ) ናቸው፡፡
ተከሳሾቹ በቡድን በመደራጀት የማይገባ ብልፅግና ለማግኘትና ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ፣ ሰሌዳ ቁጥር ያለጠፈ የመከላከያ መኪና ይዘው (ኦፊሰር መንግሥቱ፣ አሸናፊና ሹምበዛ) ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ቦታው ስልጤ ሠፈር በሚገኙ ተበዳይ አቶ አብዱል በርናምስ መኖሪያ ቤት መሄዳቸው በክሱ ተጠቅሷል፡፡ ግለሰቡ ከቤታቸው እንዲወጡ አድርገው በያዙት የመከላከያ መኪና ውስጥ ካስገቧቸው በኋላ፣ በሕገወጥ መንገድ ‹‹ስኳር፣ ዘይትና መሣሪያ ትሸጣለህ፡፡ እንድንለቅህ አምስት ሚሊዮን ብር ክፈል፤›› በማለት መደራደራቸውን፣ ነገር ግን ተበዳዩ የተጠየቁትን ያህል ገንዘብ መክፈል እንደማይችሉ ገልጸው፣ 700,000 ብር ለመክፈል ተስማምተው በተለያዩ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ዳሸን ባንክ በተከፈቱ የቁጠባ ሒሳብ ቁጥሮች (ተጠቅሰዋል) ክፍያ መፈጸማቸውን ክሱን የመሠረተው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
ተከሳሾቹ በድርጊታቸው በመቀጠል ሃና ማርያም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑትን አቶ ሙሉጌታ ታደሰን መከታተል ይጀምራሉ፡፡ አቶ ሙሉጌታ የሚከታተሏቸው ሰዎች እንዳሉ በማወቃቸውና በመሥጋታቸው ለላፍቶ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ሁኔታውን እያስታወቁ እያሉ፣ ተከሳሾቹ ተከትለዋቸው ወደ ፖሊስ ጣቢያው በመግባት ‹‹ከደኅንነት ነው የመጣነው›› በማለት ተበዳዩን በወንጀል እንደሚፈልጓቸው ገልጸውና አለቃቸው (ሻለቃ ዱጉማ) እየመጣ መሆኑን በመግለጽ፣ እዚያው ፖሊስ ጣቢያ ይቆያሉ፡፡ አለቃቸው የተባለው ተከሳሽ እንደደረሰም ተበዳዩ በወንጀል እንደሚፈለጉና ወደ ፌዴራል ፖሊስ ተወስዶ እንደሚታሰሩ በመንገር፣ ከፖሊስ ጣቢያ ይዘዋቸው እንደሄዱ ክሱ ያብራራል፡፡
ተበዳዩ ይዘውት የነበረን መኪና እንዲወስዱላቸው እህታቸውን ጠርተዋቸው ሲመጡ ‹‹እሷም ወንጀለኛ ነች ትታሰራለች›› በማለት ሻለቃ ድጉማ በሚያሽከረክሩት የመከላከያ መኪና ውስጥ አሳፍረው ወደ ፌዴራል ፖሊስ ይሄዳሉ፡፡ ገነት ሆቴል አካባቢ ሲደርሱ መኪናውን በማቆም ተበዳይ አቶ አብዱልበርን ‹‹ይኽ የሕይወት ጉዳይ ነው፡፡ እህትህን እንድንለቃት ከፈለክ ሦስት ሚሊዮን ብር ክፈል፤›› እንዳሏቸው የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡
ተበዳዩ የተጠየቁትን ያህል ገንዘብ እንደሌላቸው ሲናገሩ፣ 300,000 ብር እንዲከፍሉ ተስማምተው ክፍያውን መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ተንትኗል፡፡ ተከሳሾቹ ድርጊታቸውን በመቀጠል ተበዳይ ወ/ሮ አዜብ በርሔ የተባሉ ግለሰብ በመደወል፣ ‹‹ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሀብት ማስመለስ ቢሮ ነው የደወልነው፡፡ ልናነጋግርሽ እንፈልጋለን፤›› በማለት ለቡ አካባቢ ካገኟቸው በኋላ፣ ‹‹ባለቤትሽ ጄኔራል ነው፡፡ ትግራይ በመሄድ እያዋጋ ነው፡፡ ቤትሽን በተመለከተ እያጣራን ስለሆነ ካርታና አስፈላጊ ሰነዶች ይዘሽ ነይ፤›› በማለት ይዘው እንዲመጡ ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡
የማስረጃ ሰነዶቹን ከተቀበሏቸው በኋላ ‹‹እንድንረዳሽ 500,000 ብር ክፈይ ይሏቸዋል፡፡ የተጠየቁትን ያህል ገንዘብ መክፈል እንደማይችሉ ገልጸውላቸው 200,000 ብር ለመክፈል ተስማምተው ለጊዜው ይዘውት የነበረውን 15,000 ብር ሰጥተዋቸው ይሄዳሉ፡፡ ቀሪውን እንዲከፍሉ እየደወሉ ሲጠይቋቸው ‹‹ሕጋዊ መሆናችሁን እንዴት አውቃለሁ?›› ይሏቸዋል፡፡ ከዚያም ሻለቃ ዱጉማ ልደታ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ቀጥሯቸው፣ የመከላከያ ታርጋ ያልለጠፈ ተሽከርካሪ ይዞ በመምጣት የመከላከያ ሠራዊት አባል መሆኑን ገልጾ፣ በሀብት ማስመለስ ሥራ ላይ እንደተመደበ በመግለጽ ሴትዮዋን የጠየቋቸው ተከሰሳሾች ሕጋዊ መሆናቸውን ሲገልጽላቸው፣ ሹምበዛና ተስፋዬ ለተባሉት ተከሳሾች 90,000 ብር እንደሰጧቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በአጠቃይ ተከሳቹ በመመሳጠር በፈጸሙ ሥልጣንን አላግባብ መገልገል ከባድ የወንጀል ክስ ተከሰው፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሙስና ወንጀሎች ችሎት ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀርበዋል፡፡