Monday, April 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊባለቆልማማ እግር ጨቅላ ሕፃናትን የሚታደገው ሕክምና

ባለቆልማማ እግር ጨቅላ ሕፃናትን የሚታደገው ሕክምና

ቀን:

ቆልማማ እግር በውጩ ቋንቋ አጠራር ‹ክለብ ፉት› የሕፃናት እግር ወደ ውስጥ ተጠማዞ የሚታይበት እክል ነው፡፡ ይህም ጨቅላው በማህፀን ውስጥ እያለ አጥንቶቹ ጅማቶቹና ጡንቻዎቹ ባልተለመደ ዕድገት ምክንያት የሚከሰት ውስብስብ የአካል ጉድለት መሆኑን ባለሙያዎቹ ይገልጹታል፡፡

ቆልማማ እግር በአንዱ ወይም በሁለቱም እግሮቹ ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህ የአፈጣጠር ችግር የሚከሰተው መንስዔው በማይታወቅበት ሁኔታ እናትየው ጨቅላውን ስትወልደው የሚታይ ችግር ነው፡፡

አቶ እንዳሻው አበራ ‹‹የሆፕ ዎክስ›› የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ አባባል ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ይወለዳሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ከአምስት ሺሕ በላይ ያህሉ ከዚህ አፈጣጠር ችግር ጋር ይወለዳሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደዚህ ዓይነት እክል ያለባቸው ጨቅላዎች በተወለዱ በአሥራ አምስተኛው ቀን ለዚሁ ተብሎ የተዘጋጀውን ሕክምና በቶሎ ማግኘት አለባቸው፡፡ ከአንድ/ ከሁለት ዓመት በኋላ ቆይቶ መምጣት ወይም ዘግይቶ መታከም ግን በሕክምናው ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር፣ እናቶችንም ለከፋ እንግልት እንደሚዳርግ ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

‹‹ክለብ ፉትን ማስተካከል ነገን ማስተካከል ነው›› በሚል መሪ ቃል ዓርብ ግንቦት 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ የሚውለውን የዓለም ክለብ ፉት ቀን አስመልክተው አቶ እንዳሻው በተለይ ለሪፖርተር እንዳመለከቱት ክለብ ፉት አራት ዓይነት መገለጫዎች አሉት፡፡

ከመገለጫዎቹም መካከል አንደኛው እግሩ ወደ ውስጥ ገብቶ ከተገቢው በላይ ነርቩ መሥራት፣ ሁለተኛው የእግሩ የመጀመሪያው አካላት ወደ ውስጥ መግባት ወይም መቆልመም፣ ሦስተኛው የእግሩ ተረከዝ ቀጥ ማለት ሲገባው ወደ ውስጥ መሸሽና አራተኛው ደግሞ የቁርጭምጭሚቱ አንጓ ወደ ታች ብቻ ታጥፎ መቅረት ናቸው፡፡

እነዚህንም መገለጫዎች በጄሶ፣ በጅማትና በጫማ ሕክምና ዘዴ ማዳን እንደሚቻል በተለይ የጅማት ሕክምናው ዘዴ አንጓው ቀና እንዳይል ወጥሮ የያዘውን በትንሽዬ የጅማት ቀዶ ሕክምና ማላቀቅ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ አጠቃላይ ሕክምናውም ከአምስት እስከ ስድስት ሳምንት ብቻ እንደሚወሰድ፣ ከዚያም በቀጣይ የጫማ ሕክምናን መከታተል ወይም ማድረግ ግድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጨቅላው የጫማ ሕክምናውን የሚያደርገው አምስት ዓመት እስከሚሞላው ድረስ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ሲባል ጫማውን ቀኑን ሙሉ ያደርጋል ማለት ሳይሆን የመጀመሪያውን የጀሶ ሕክምና ከጨረሰ በኋላ ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት ጠዋትና ማታ፣ ከሦስት ወራት በኋላ ደግሞ ማታ ብቻ ማድረግ ያለበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሲተኛም ጫማውን ማውለቅ እንደሌለበት፣ ይህ እንዲሆን ያስፈለገውም የተፈጥሮው ችግር ተመልሶ እንዳይመጣና እንዲመክንም ለማድረግ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡ ሕክምናው አዋጭነቱና ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውም ይህ ዓይነት ሕክምና ብቻ እንደሆነ ነው ያመላከቱት፡፡

በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች ይህ ዓይነቱን የሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚችሉ 48 የክለብ ፉት ክሊኒኮች እንደሚገኙ፣ በሚቀጥለው ዓመት የክሊኒኮችን ቁጥር ወደ 56 ከፍ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በዘንድሮ ሕክምናውን የሚከታተሉ ሕፃናት 2,200 ሲሆኑ፣ ለከርሞ ወደ 2,500 ከፍ ለማድረግና በአሥር ዓመታት ውስጥ ግን በአገሪቱ ውስጥ የመቆልመም ችግር ላለባቸው ጨቅላ ሕፃናት ሁሉ ሕክምናውን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ከማብራሪያቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ ይህ ዓይነቱ የሕክምና አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ አሥር ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ 19,000 ጨቅላ ሕፃናትም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ እንዳሻው እንደገለጹት፣ የክለብ ፉት ቀን ታስቦ በሚውልበት ዋዜማ (ሐሙስ ግንቦት 25) የእግር ጉዞ፣ በዕለቱ ደግሞ የፎቶ ዓውደ ርዕይ እና በክለብ ፉት ዙሪያ ዓውደ ጥናት ይካሄዳል፡፡ ከቆልማማ እግር ችግር ሙሉ ለሙሉ ተላቅቀው በሥነ ሥርዓት መራመድ የሚችሉ 50 ሕፃናትም የሚመረቁ ሲሆን ሕክምናውም በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲጀመርና እንዲስፋፋ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሕክምና ባለሙያ የዕውቅና ይቸራቸዋል፡፡

የዓለም ክለብ ፉት ቀን ግንቦት 26 ቀን በየዓመቱ የሚከበረው፣ በክለብ ፉት ችግር ዙሪያ ለ50 ዓመታት ያህል ምርምር አድርገው በስተመጨረሻ ችግሩ ያለቀዶ ሕክምና በጄሶና በጅማት ሕክምና ማዳን እንደሚችል የደረሱበትና ይህንንም ግኝታቸውን ለዓለም ያበረከቱት የአጥንት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ኢግናሽየስ ፖንሲቲ (ዶ/ር) የተወለዱበት ቀን በመሆኑ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...