Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊተስፋ የተሰነቀባቸው የዳግማዊ ምኒልክ 30 የኩላሊት እጥበት ማሽኖች

ተስፋ የተሰነቀባቸው የዳግማዊ ምኒልክ 30 የኩላሊት እጥበት ማሽኖች

ቀን:

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኩላሊት በሽታ የሚሰቃዩ በርካታ ወገኖች መኖራቸው በየመንገዱ እጃቸውን ለምፅዋት የዘረጉት ምስክር ናቸው፡፡

ምንም እንኳ የሕመሙ መንሥዔ የተለያየ ቢሆንም፣ ሕክምናውን ለማግኘት ጥቂት የማይባል ገንዘብ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ብዙዎች እጃቸውን ለመዘርጋት ይገደዳሉ፡፡ የኩላሊት ሕመም መንስዔው ብዙ መሆኑን፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ቅድመ መከላከሉ ላይ ጠንከር ማለት እንደሚገባም ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

ይህም ተደርጎ ለኩላሊት ሕመምተኞች ጊዜያዊ እፎይታ የሚሰጠው የኩላሊት እጥበት ማሽን በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑንም ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለኩላሊት እጥበት የሚሆናቸውን ገንዘብ የሚያጡ ወይም ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ሕመምተኞች ጥቂት አለመሆናቸውም የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

እነዚህም ሕመምተኞች የሚጠበቅባቸውን የኩላሊት እጥበት ባለማድረጋቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሰውነት ማበጥና ሌሎች ችግር እንደሚያስከትልባቸው ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ የኩላሊት ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ቁጥራቸው በርካታ ሲሆኑ፣ የኩላሊት እጥበት የሚያስፈልጋቸው ደግሞ ከ400 ሺሕ በላይ መሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ለዚህም መንግሥት በተለያዩ ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት ማሽን ቢያስተክልም፣ ብልሽት አጋጥሟቸው ሥራቸውን ያቆሙ ጥቂት እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ያለውን ችግር ለማቃለል የተለዩ መንግሥታዊም ሆነ ያልሆኑ አካላት ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ የኩላሊት መድከም ላለባቸውና በየጊዜው እጥበት (ዳያለሲስ) ለሚያደርጉ ወገኖች አገልግሎት የሚሰጥ አዲስ ማዕከል በዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል ተቋቁሟል፡፡

ሠላሳ የኩላሊት እጥበት ማሽኖች ያሉበት ማዕከሉ ከዚህ ቀደም ከኩላሊት እጥበቶች ጋር በተያያዘ አጋጥመው የነበሩት የግብዓት እጥረቶችን የሚቀርፍለት እንደሆነ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ታደሰ ሀብተዮሐንስ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የኩላሊት እጥበት ማሽኖቹ ወደ ማዕከሉ የገቡት ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ አውስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ በሁሉም ማሽኖች እንደማይሰጥ የገለጹት ታደሰ (ዶ/ር)፣ አዲስ ማሽኖቹ ቀስ በቀስ ለአገልግሎት ክፍት ይደረጋሉ ብለዋል፡፡

የኩላሊት እጥበት ከሚያስፈልጋቸው 80 በመቶዎቹ ከክፍያ ነፃ የሚደረግ መሆኑን፣ የተቀረው በክፍያ እንደሆነ፣ የክፍያ መጠኑም ከግል ሕክምና ተቋማት ጋር ሲነፃፀር በጣም ዝቅተኛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በዘውዲቱ ሆስፒታል በርካታ ታካሚዎች ለእጥበት ወረፋ እየጠበቁ መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊው፣ አሁን ላይ በዚሁ ሆስፒታል አገልግሎቱን ያገኛሉ ብለዋል፡፡

በሒደት  የኩላሊት ንቅለ ተከላ አገልግሎት የመጀመር ዕቅድ መያዙንም ሥራ አስኪያጁ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከማዕከሉ መሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ ውኃ፣ መብራትና ሌሎችም ወጪዎች በከተማ አስተዳደሩ የተሸፈነ ሲሆን፣ የማሽን ግዥው በተመለከተ ግን መረጃው እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

ለምርቃት የበቃው የኩላሊት እጥበት ማዕከሉ ቀድሞ በመንግሥት ሆስፒታሎች ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በአምስት እጥፍ እንደሚያሳድገው የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በጣም በርካታ ዜጎች የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ለማግኘት ተመዝግበው ወረፋ እየጠበቁ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ማዕከሉ በሙሉ አቅሙ ሲሠራ በቀን እስከ 240 ለሚሆኑ ታካሚዎች አገልግሎት መስጠት ይችላል ብለዋል፡፡

አንድ ታካሚ የኩላሊት እጥበት ለማግኘት አራት ሰዓትን እንደሚወስድ የገለጹት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ በሦስት ፈረቃ አገልግሎት መስጠት ከተቻለ ለበርካታ ታካሚዎች እፎይታ እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡

የኩላሊት እጥበት ማዕከሉ ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲመረቅ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ እንደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል 30 የኩላሊት እጥበት ማሽኖች ዓይነት ሥራዎችን ማየት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...