Monday, March 20, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቢሊዮኖችን የተመዘበሩት የአገር ውሰጥ ባንኮችን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ለመቀነስ የቀረቡ መፍትሔዎች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ2014 የግማሽ የሒሳብ ዓመት የባንኮች አፈጻጸምን የተመለከተው ሪፖርት የአገሪቱ ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ይህ የተቀማጭ የገንዘብ መጠን በሒሳብ ዓመቱ የዘጠኝ ወር መጨረሻ ላይ ደግሞ ወደ 1.65 ትሪሊዮን ብር መድረሱ ይገመታል፡፡ ይህንን የሕዝብና የአገር ሀብት በአደራ ተቀብለው ያስቀመጡት ባንኮች ናቸው፡፡ 

እነዚህ ባንኮች ይህንን ሀብት በአግባቡ ከመጠበቅ አንፃር የየራሳቸው የመቆጣጠርያ ስልት ቢኖራቸውም በአጭበርባሪዎች መመዝበራቸው ግን አልቀረም፡፡ በተለያዩ ስልቶች የሚጭበረበረው የገንዘብ መጠንም በየዓመቱ እየጨመረ መሆኑ የሚነገር ሲሆን በተለይ የውስጥ (የባንክ ሠራተኞች) በዚህ የማጭበርበር ተግባር በመሳተፍ ቀዳሚ መሆናቸው የነገራል፡፡ ሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በፍትህ ሚኒስቴር በቀረበ አንድ የምርመራ ውጤት ላይ የአገሪቱ ባንኮች ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ መንገዶች ከ1.52 ቢሊዮን ብር በላይ መመዝበራቸውን አስታውቋል፡፡ በፍትሕ ሚንስቴር ባቀረበው የምርምራ ሪፖርቱ መሠረት በተጠቀሱት ዓመታ 1.9 ቢሊዮን ብር የምዝበራ ሙከራ በ16 የኢትዮጵያ ባንኮች ላይ ተፈጽሞ 1.52 ቢሊየን ብሩ መመዝበሩን እና የተቀረው ግን የምዝበራ ሙከራ ተፈጽሞበት የቀረ ነው።

ከተመዘበረውና የምዝበራ ሙከራ ከተደረገበት አጠቃላይ 1.9 ቢሊየን ብር ውስጥ ከሃምሳ በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል።

ቀሪው ገንዘብ ደግሞ በ15ቱ ባንኮች ላይ የተፈጸመ እና የተሞከረ ምዝበራ መሆኑን ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡ በዚህ ሪፖርት ውስጥ አሁን በሥራ ላይ ካሉ 18 ነባር ባንኮች ውስጥ 16ቱ ምዝበራው ጎብኝቷቸዋል። በስራ ላይ ከሚገኘት የአገሪቱ ባንኮች ውስጥ በዚህ የምዝበራ ሪፖርት ያልተጠቀሱ ሁለት ባንኮች ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም ዘመንና እናት ባንኮች ናቸው፡፡ ሌሎቹ ባንኮች መጠናቸው ይለያይ እንጂ ምዝበራ የገጠማቸው ናቸው ተብለዋል፡፡ ከመንግሥት ባንኮች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 590 ሚሊዮን ብር ስለመጭበርበሩ ሲገለጽ 370 ሚሊዮን ብር ደግሞ ሙከራ ተደርጎበት ነበር ተብሏል፡፡

ከግል ባንኮች ከፍተኛ መጭበርበር የደረሰባቸው ተብለው የተጠቀሱት ቀዳሚ ባንኮች ውስጥ አቢሲኒያ ባንክ፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክና ወጋገን ባንኮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሦስት ባንኮች በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከ550 ሚሊዮን ብር በላይ በተለያዩ መንገዶች ተጭበርብረዋል፡፡ 

ዶክመንቶችን በመቀያየር፣ የሚስጥር ቁጥሮችን በመስበር፣ በባንክ ውስጥ ባሉ ሠራተኞች በሚሰጥ መረጃ፣ በተጭበረበሩ ቼኮችና የመሳሰሉት ሕገወጥ ተግባራት ጥቅም ላይ የዋሉ የምዝበራ ስልቶች መሆናቸውም ተጠቁሟል። በሪፖርቱ የተጠቀሱት 16ቱ ባንኮች በድምሩ 155 የምዝበራ ሙከራዎችን እንዲስተናገዱና ጉዳዩ በሕግ መያዙ የተመለከተ ቢሆንም ባንኮቹ ተመዘበረ ከተባለው ገንዘብ አብዛኛውን አለማግኘታቸው ተግልጿል።

ይህ ሪፖርት ግን ለአንዳንድ ባንኮች የሥራ ኃላፊዎች ምቾትን የሰጠ አልሆነም፡፡ የፍትህ ሚኒስቴር እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን በመከታተል ማቅረቡና ተነሳሽነቱ መልከም ቢሆንም ችግሩን የባንኮቹ ብቻ አድርጎ ማቅረቡ ግን ተገቢ እንዳልሆነ ያነጋገርናቸው የባንክ ኃላፊዎች ይገልጻሉ። ሪፖርቱ እንዲህ ባለ መንገድ ከመቅረቡ በፊት ምክክር ሊደረግበት ይገባ ነበር ሲሉም ቅሬታቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል።

ይህንን ሐሳብ ከሚጋሩት መካከል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ አንዱ ናቸው፡፡ ጉዳዩ የቆየ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አቤ፣ ባንካቸው እያንዳንዱን ተፈጸመ የተባለ ድርጊት በወቅቱ ሪፖርት ማድረጉንና ነገሩ ሰሞኑን በቀረበው የፍትህ ሚኒስቴር ጥናት ልክ እንዳልሆነ ይከራከራሉ፡፡ 

‹‹ሁሉንም በአግባቡ በመመልከት ተነጋግረንበትና ተመካክረንበት ቢቀርብ ጥሩ ነበር። የሪፖርቱ አቀራረብ ሌላ ሥዕል የሚያሳይ ነው። ቢሆንም የቀረበውን ሪፖርት ተንተርሰን ትክክለኛውን መረጃ ይፋ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡ 

በዚህ ሪፖርት ላይ የተለያየ አመለካከት የሚሰነዘር ቢሆንም መፍትሔ ይሆናል የተባሉ ሐሳቦች ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት ተንፀባርቋል፡፡ ከዚህ ሪፖርትና በአጠቃላይ ከፋይናንስ ደኅንነት አንፃር ትልቁ ተግዳሮት ይህ አይደለም የሚለው አመለካከትም ጎልቶ ተሰምቷል፡፡ ያነጋገርናቸው የፋይናንስ ባለሙያዎች በአሁኑ ወቅት በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ትልቁ ተግዳሮት የዘመናዊ ባንክ አገልግሎት ጋር ተያይዞ እየተፈጸሙ ያሉ ማጭበርበሮች መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡ 

አቶ አቤም ‹‹የእኛ ትልቁ ፈተና ከባንክ ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ እየተፈጸሙ ያሉ ማጭበርበሮች በመሆናቸው እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን እንዴት እንደፍናለን በሚለው ላይ ነው›› ብለዋል፡፡ በተለይ ከቴሌ ጋር በተያያዘ እየገጠማቸው ያለ ችግር ከፍተኛ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ 

የኢንፎርሜሽን ደኅንነት አገልግሎት የዲቪዥን ኃላፊ አቶ ሃኒባል ለማ ለሪፖርተር እንደገለጹትም በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃትና ተያያዥ ድርጊቶች መጠን እየጨመረ መሆኑን ነው፡፡ የሳይበር ጥቃት ትኩረት የሚያሻና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በግልም ሆነ በጋራ ሊሠሩበት የሚገባ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ጥንቃቄ ካልተደረገበትም የወደፊት የጦርነት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።  በመሥሪያ ቤታቸው መረጃ መሠረት ለተከታታይ ዓመታት በዋናነት የሳይበር ጥቃት ሲደርስባቸው ከነበሩ ተቋማት ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የመንግሥት ቁልፍ ተቋማት፣ መሠረተ ልማትና የፋይናንስ ተቋማትም በይበልጥ ጥቃቱ የሚፈጸምባቸው ናቸው፡፡ በአብዛኛው እነዚህ ተቋማት ላይ ትኩረት አድርጎ ጥቃቶች ሲፈጸሙ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ 

የፋይናንስ ተቋማት ጨምሮ ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት ላይ ጥቃቱ በይበልጥ ያነጣጠረበት ዋና ምክንያት ገንዘብ ለማጭበርበር ቢሆንም ፖለቲካዊ ፍላጎት ያነገቡ ጉዳዮች መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡

ሰሞኑን በቀረበው የፍትህ ሚኒስቴር የምርመራ ሪፖርት ላይ በሳይበር ጥቃት የተፈጸሙ ማጭበርበሮች መጠን ምን ያህል እንደሆነ ባይገልጽም፣ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ተከትሎ የሚቃጣ የማጭበርበር ድርጊትን በቴክኖሎጂ የሚደገፉ የአሠራር ሥርዓቶችን ጥቅም ላይ በማዋል ደህንነትን ማረጋገጥና የፋይናንስ ተቋማት ለመሰል ጥቃቶች እንዳይጋለጡ ማድረግ እንደሚገባ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

ችግሩ እንዳይከሰት ከተጠቃሚ አንፃር የሚሰጡ መፍትሔዎች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ሃኒባል ከእነዚህም ውስጥ ቴክኖሎጂን በጥንቃቄ መጠቀም አንዱ መፍትሔ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም አስገዳጅ የጥንቃቄና የደህንነት ሥርዓትን ማቋቋም ሌላው መፍትሔ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ጠንካራ የቁጥጥርና ክትትል ስርዓትን እንዲሁም ተጠያቂነትን የሚያሰፍን አሠራር መዘርጋት ከገንዘብ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሔ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ የጥንቃቄ ሥርዓቱ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ከሳይበር ጥቃትም ሆነ ቴክኖሎጂን መሠረት ካደረጉ ማጭበርበሮች ለመጠበቅ፣ እንዲሁም ችግሩ ሊከሰት መሆኑን በቶሎ አውቆ ምላሽ መስጠት እንዲቻል ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ተጋላጭነታቸው ምን ያህል እንደሆነ ኦዲት ማስደረግ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡ 

‹‹ዋነኛና ትልቅ የቤት ሥራ የሚጠቀሙዋቸውን ቴክኖሎጂዎችና የአሠራር ሥርዓቶች ለጥቃት ያጋልጣቸዋል ወይስ አያጋልጣቸውም የሚለውን መፈተሽ ነው›› ያሉት አቶ ሃኒባል ደህንነትን ለማረጋገጥ ጋር ኢንሳና ባንኮቹ በጋራ የሚሠሩት ይሆናል ይላሉ፡፡ 

የፋይናንስ ተቋማት ከመጭበርበርና ከፋይናንስ ጥቃቶች እንዲጠበቁ ግን አስገዳጅ ሕግጋቶችና አሠራሮች መተግበር እንደሚኖርባቸውም አመልክተዋል፡፡ 

ከቴክኖሎጂ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ማጭበርበሮች ለመከላከል እንዲሁም ባንኮች ምን ያህል ዝግጁ እንደሆኑና ቁጥጥር ለማድረግ በቅርቡ የወጣው የብሔራዊ ባንክ መመርያ ጥሩ ጅማሮ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ 

መመርያው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሚከሰቱ የደኅንነት ሥጋቶችን የሚመለከት ሲሆን፣ የፋይናንስ ተቋማት በዚህ ረገድ ጥብቅ የደኅንነት ዝግጅት እንዲያደርጉና የሚገጥሟቸውን ሥጋቶች ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ነው፡፡ 

የፋይናንስ ተቋማቱ አሁን የወጣውን መመርያ በትክክል መፈጸም ከቻሉ ከአይቲ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የአደጋ ተጋላጭነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሳያድግ መቀልበስ የሚያስችላቸው በመሆኑ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን እንዲፈትሹ አቶ ሃኒባል ይመክራሉ፡፡ አጠቃቀማቸውን ከመፈተሽ ተሻግረው የሚፈለገውን የቁጥጥር ሥርዓት ካበጁ ከመጭበርበር ሥጋቶች እንደሚጠበቁም ገልጸዋል።

በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚከሰቱ የምዝበራ ተግባራትን በዋናነት የመከታተል ሥራ የሚሠራው የፋይናንሻል ኢንተለጀንስ አገልግሎት ሲሆን፣ ተቋማቱ የሚዘረጓቸውን የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች ደኅንነት የማረጋገጥና የመደገፍ አገልግሎት የሚሰጠው ደግሞ የመረጃ መረብ ደኅንነት አገልግሎት (ኢንሳ) እንደሆነ አቶ ሃኒባል ገልጸዋል።

ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ ጥቃት የዓለም ሥጋት እየሆኑ ስለመምጣታቸው በቅርቡ ከሳይበር ጥቃት ጋር በተያያዘ በተሰናዳ መድረክ ላይ የተገለጸ ሲሆን በዓለም ላይ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት በአሁኑ ወቅት ከገበያቸው ዘጠኝ  በመቶ የሚሆነው ወጪያቸው ከዚሁ የሳይበር ጥቃት ደኅንነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ 

በኢትዮጵያም በ2014 ግማሽ ዓመት የደረሰው የሳይበር ጥቃት በ2013 ሙሉ በጀት ዓመት ከደረሰው በእጥፍ በልጦ መገኘቱን ኢንሳ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ 

ከቴክኖሎጂ ተመርኩዞ የሚደረጉ ጥቃቶች እጅግ በብርቱ እንድናስብበት የሚያደርገን በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች የሚደረጉ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ በመጨመራቸው መሆኑን አቶ አቤ ገልጸዋል፡፡ 

ለዚህም ምሳሌ አድርገው የጠቀሱት ዘንድሮ በዘጠኝ ወር ብቻ በባንኩ ከተንቀሳቀሱ ገንዘብ ውስጥ 59 በመቶ የሚሆነው በዲጂታል ባንኪንግ የተንቀሳቀሰ እንደሆነና በዚያው ልክ ሥጋቱ ስላለ በዚህ ላይ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ 

ቴክኖሎጂ ቀመስ አገልግሎቱን ሥጋት ለመቀነስ ባንኮች እጅግ ከፍተኛ የሆነ ወጪ እያወጡ እየሠሩበት ነው የሚሉት የእናት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሚያስ አንድአርግ በበኩላቸው ለዚህ ጥበቃ ለሠራተኞች እየወጣ ያለው ወጪ ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡ ባንኮች የአይቲ ዲፓርትመንታቸውን በምክትል ፕሬዚዳንት ደረጃ እያዋቀሩ ያሉበት ምክንያትም ይህ እንደሆነ ገልጸዋል።

አቶ ሃኒባል ደግሞ በተለይ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ቅድሚያ ጥበቃ ለሚገባቸውና አስተማማኝ የደኅንነት ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል አዲስ አዋጅ እየተዘጋጀ በመሆኑ ይህ ሥጋቱን በመቀነስ አስተዋጽኦ አለው ይላሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች