ኮካ ኮላ ቤቭሬጂ አፍሪካ በዓመት ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚሆን የታሸጉ የኮካ ኮላ የለስላሳ መጠጥ ምርቶችን ለማምረት አቅም ያለውን ፋብሪካ ግንባታ አጠናቆ ሥራ አስጀመረ፡፡
ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የወጣበትና በሰበታ ከተማ የተገነባው ይህ ፋብሪካ ትናንት በተመረቀበት ወቅት እንደተገለጸው የፋብሪካ ሥራ መጀመር የወጪ ንግድ ዕድሎችን የሚከፍት ጭምር ነው ተብሏል፡፡
በዋናነት ከሚያመርተው የለስላሳ መጠጦች ባሻገር ለፋብሪካው ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችሉት የምርት መስመሮች ያሉት ሲሆን የፕላስቲክ ጠርሙዝች፣ የፕላስቲክ ጠርሙዝ ክዳኖችና ሌሎች ግብዓቶችን ማምረት ይችላል፡፡
የእነዚህ ምርቶች በፋብሪካው መመረት ከውጪ የሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶችን እንዲቀንሱና ለእነዚህ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ የሚያስቀር ጭምር ነው ተብሏል፡፡
ኩባንያው አሁን በሰበታ ከተማ ካስገነባው ፋብሪካው በተጨማሪ በሐዋሳ ከተማ ስድስተኛውን ፋብሪካ ለመገንባት በዝግጅት ላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኩባንያው የፋብሪካውን ምረቃ በማስመልከት ባወጣው መግለጫው በሰበታ የተመረቀውም ሆነ በሐዋሳ የሚገነባው ስድስተኛ ፋብሪካው ኩባንያው ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የያዘው ዕቅድ አካል ነው፡፡ ኩባንየው ይህንን ኢንቨስትመንት በአምስት ዓመት ለመተግበር አልሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በዕለቱ ተገልጿል፡፡ የአዲሱ ፋብሪካ ሥራ መጀመር ተጨማሪ ለ500 ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ዳሬል ዊልሰን ተናግረዋል፡፡
ኮካ ኮላ በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ባደረገው ኢንቨስትመንቱ እ.ኤ.አ. እስከ 2004 ድረስ አንድ ሺሕ የሚደርሱ ሠራተኞቹን በ2022 ወደ 3,500 ያደረሰ ሲሆን ከ70 ሺሕ በላይ ዜጎች ለሚሆኑ ደግሞ በንግድ ትስስር ተጠቃሚ እንደሆኑ ማስቻሉ ተገልጿል፡፡
በሰበታ ከተማ ሥራ የጀመረውን ፋብሪካ በቦታው ተገኝተው የመቁት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ ማስተደድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ናቸው፡፡
ኮካ ኮላ ማኅበራዊ ኃላፊቱን ከመወጣት አንፃር በኢትዮጵያ ውስጥ በሰበታ ከተማ 236,000 ዶላር የሚያወጣ ትምህርት ቤት ገንብቷል፡፡ በተመሳሳይም በአምቦና በባህር ዳር 3,360 ለተማሪዎች የሚሆን የመማሪያ ክፍሎችን በ700 ሺሕ ዶላር መገንባቱን ገልጿል፡፡