Sunday, July 14, 2024

ጋዜጠኞችና የሰሞኑ የእስር ዘመቻ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ የጋዜጠኛ መብት ተቆርቋሪዎች፣ የጋዜጠኛ ማኅበራት፣ የማኅበረሰብ አንቂ ግለሰቦች፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ አገር አቀፍና ዓለም ዓቀፍ የሚዲያ ተቋማት፣ ኤምባሲዎችና የበርካታ የሙያ ተቆርቋሪ ድርጅቶች መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተውና የቀጠለው የጋዜጠኞች ድንገተኛ ዕገታና እስር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንዱስትሪ ታይቶ የነበረውን የተስፋ ጭላንጭል ያደበዘዘ፣ ለሙያ ተዋናዮቹም አስፈሪ ገጽታ መፍጠሩ ብዙዎችን ያሳምማል፡፡

በ2010 ዓ.ም. ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ሥልጣን ተቆናጠው መንግሥታዊ ለውጥና ሪፎርም ባካሄዱ ማግሥት በውል እመርታ ካሳዩ ዘርፎች መካከል የሚዲያ ኢንዱስትሪው በጉልህ ተጠቃሽ ከመሆኑም በላይ፣ እ.ኤ.አ. በ2019 የዓለም ፕሬስ ነፃነት ቀን ለመጀመርያ ጊዜ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

አገሪቱ ይህንን ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ እንድታዘጋጅ ካደረጓት ምክንያቶች መካከል ትልቁ እምብዛም ለጋዜጠኞች ምቹ ካልሆኑና ጋዜጠኛ አሳሪ ከሚባሉ አገሮች በቀዳሚነት ተርታ ስትጠራ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ አንድም ጋዜጠኛ ያላሰረች በመሆኗና የመገናኛ ብዙኃን ሙያ ነፃነት ጉልህ ተስፋ ማሳየቱ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወቅቱ የታዩትን ተስፋዎች፣ በተለይም በየዓመቱ ይፋ በሚደረገው የአገሮች የሚዲያ ዘርፍን ለማሳደግና ነፃ ለማድረግ የሚያደርጓቸውን ጥረት ለማመላከት የሚወጣው ዓለም አቀፍ ደረጃ ጠቋሚ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከ180 አገሮች መካከል እ.ኤ.አ. 2018 ከነበረችበት 150 ደረጃ በ2019 ወደ 110  ደረጃ ከፍ ብላ የነበረ ቢሆንም፣  ዘንድሮ ከተመሳሳይ 180 አገሮች ሦስት ደረጃዎችን ዝቅ በማለት ወደ 114 ወርዳለች፡፡

ለዚህ ደረጃ መውረድና የአገሪቱ የሚዲያ ተሳትፎ ደረጃ ከነበረበት የተሻለ ቁመና ዝቅ ማለት ሰፋ ያሉ ማሳያዎችን መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም፣ ጠቅለል ያለው ማሳያው ግን ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ከተከሰተው የፖለቲካ ግርግርና ጡዘት ጋር እንደሚገናኝ፣ በዚህ ሁሉ የፖለቲካ ግለት አንዳንድ የሚዲያ ባለሙያዎችና ተቋማት ለፖለቲካው መዘበራረቅ ምክንያት ሌሎች ደግሞ የችግሩ ገፈት ቀማሽም ሆነዋል፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት እንዳለው የሚገልጽ ሲሆን፣ ይህ ነፃነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት ነፃነቶችን እንደሚያካትት ይደነግጋል፡፡

በዚሁ አንቀጽ ውስጥ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሐሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ እንደሚደረግለት ተቀምጧል፡፡

በ2010 ዓ.ም. የተካሄደውን የመንግሥት ሥርዓት ለውጥ ተከትሎ የሚዲያ ኢንዱስትሪውን በተሻለ መንገድ ያግዛል የተባለው የመገኛ ብዙኃን አዋጅ ተሻሽሎ መውጣቱ ይታወሳል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 48 ድንጋጌዎች መሠረት ማንኛውም የመገናኛ ብዙኃን ዜና ወይም መረጃ የመሰብበስ የመቀበልና የማሠራጨት፣ በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ወይም ትችት የማቅረብ ዘመናዊ የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎችንና መሣሪያዎችን የመጠቀም መብት ይሰጣል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 84 መሠረት የስም ማጥፋት ተግባር በመገናኛ ብዙኃን ሲፈጸም፣  ከፍትሕ ብሔር ኃላፊነት በስተቀር በወንጀል ተጠያቂ እንደማያስደርግ ተደንግጓል፡፡

በተመሳሳይ በአዋጁ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር የተያያዙ ክሶች ስለሚቀርቡበትና ስለሚሰሙበት ሁኔታ በሚያትተው አንቀጽ 86 መሠረት፣ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዓቃቤ ሕግ አማካይነት ለፍርድ ቤት መቅረብ እንደለበት ተደንግጓል፡፡

በመሆኑም አዋጁ ከዚህ በፊት የስም ማጥፋት በሚል በመገናኛ ብዙኃንና በጋዜጠኞች ላይ ይቀርብ የነበረው የወንጀል ተጠያቂነት በማስቀረት፣ በፍትሐ ብሔር ብቻ እንዲታይ አድርጎ አስቀምጧል፡፡

ይሁን እንጂ በዘርፉ ተዋናኞች ዘንድ ተስፋ የተጣለበት የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ወደ ሥራ ቢገባም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጋዜጠኖች ሰፋ ያለ እንግልትና ከሕግ ዕውቅና ውጭ የሚደረግ እስርና አፈና መባባሱን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

በተለየም ባላፉት ሁለት ዓመታት በፌዴራል መንግሥቱና በሕወሓት ኃይሎች መካከል በተፈጠረው አለመግባባትና ጦርነት፣ እንዲሁም በመላው አገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ የፖለቲካ ትኩሳቶች የሚፈጠሩ ድንገቴ ክስተቶችን አስመልክቶ ዘገባ የሠሩ ጋዜጠኞች ተገድለዋል፣ ለእስርና ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ጥይት ተተኩሶባቸው ከተገደሉ ጋዜጠኞች መካካል የቀድሞው የትግራይ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ፣ እንዲሁም የኦሮሚያ ቴሌቪዝን ጋዜጠኛ ሲሳይ ፊዳ ተጠቃሽ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል በዚሁ ሁለት ዓመት ውስጥ በተለያየ ጊዜ በፀጥታ ኃይሎች በደንገት ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ የተለቀቁት ጋዜጠኞች ቁጥር ከፍተኛ ነበር፡፡

በግንቦት ወር ሦስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ብቻ ከመኖሪያ ቤታቸውና ከመሥሪያ ቦታቸው በፀጥታ ኃይሎች የተወሰዱ ጋዜጠኞች ቁጥር ከ18 አልፏል፡፡ አንዳንዶቹ  የተጠረጠሩበት ያልተገለጸና በቁጥጥር ሥር ከዋሉም በኋላ የት እንደሚገኙ በግልጽ የማይታወቅ ሲሆን፣ በቁጥጥር ሥር ለዋሉት አብዛኞቹ ጋዜጠኞች በፖሊስ እንደ ምክንያት ሆኖ እየቀረበ ያለው ሁከት፣ አመፅና ብጥብጥ በማስነሳት የሚል ነው፡፡

የፀጥታ ኃይሎች በርካታ ቁጥር ያላቸውን ጋዜጠኖች በሁለት ሳምንታት ውስጥ በቁጥጥር ያዋሉት የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ፣  ከፍተኛ ተፅዕኖ የፈጠሩና በተለይ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭታቸው በአገር ሰላምና ደኅንነት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር ሆኖ የተገኘባቸውን በመለየት የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ መረጃቸው ተደራጅቶ ለሚመለከተው የሕግ አስፈጻሚ አካል መላኩን በተናገሩ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

የሕዝብ  ተወካዮች  ምክር ቤት  የሕግ፣  ፍትሕና  ዴሞክራሲ  ጉዳዮች  ቋሚ  ኮሚቴ፣ ሚያዝያ  21  ቀን  2014  ዓ.ም.  የባለሥልጣኑን የዘጠኝ  ወራት  ዕቅድ  አፈጻጸም  ሪፖርትን  በገመገመበት  ወቅት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር፣ ከሕግ ተጠያቂነት ጋር ተያይዞ የሕግ አስፈጻሚ አካላት በሚያደርጓቸው ምርመራዎች ላይ የተቋሙን ሙያዊ ድጋፍ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉንም የቀረበ ጥያቄ በሕጉና በሕጉ ብቻ መሠረት አድርገን ሙያዊ ድጋፍ ሰጥተናል በማለት ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተናግረው ነበር፡፡

በዚህም ባለሥልጣኑ ሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር አሠራጭተዋል ባላቸው ስድስት መገናኛ ብዙኃን ላይ ምርመራ እንዲካሄድባቸው ሰነዶች አደራጅቶ ለፌዴራል ፖሊስ መላኩን፣ እንዲሁም ባለሥልጣኑ ምዘገባ ሳያከናውኑ በበይነ መረብ አማካይነት በሕገወጥ መንገድ የሚዲያ ሥርጭት ላይ የተሰማሩ 25 ድርጅቶችን በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ሒደት መጀመሩንም አክለው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ባለሥልጣኑ ምዘገባ ሳያከናውኑ በበይነ መረብ አማካይነት በሕገወጥ መልክ የሚዲያ ሥርጭት ላይ የተሰማሩ 25 ድርጅቶችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ ቢነገርም፣ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ አንቀጽ 28 ላይ እንደተደነገገው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ምዝገባ አስመልክቶ  ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ሰው በግል ወይም በድርጅት ማቋቋም እንደሚችል እንጂ የመመዝግብ ግዴታ የለበትም፡፡

የጋዜጠኞች በቁጥጥር ሥር መዋልን ተከትሎ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪቆች ስሞታ እያቀረቡ ቢሆንም፣ የመገናኛ ብዙኃንን በበላይነት የሚቆጣጠረው የመገናኛ ብዙኃን ቦርድ ስለጉዳዩ እስካሁን ምንም ያለው ጉዳይ የለም፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋዜጠኞች እስር ላይ በተከታታይ ባወጣቸው መግለጫዎች በተለያዩ አካባቢዎች ጋዜጠኞች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችና ሌሎች ሰዎች በእስር ላይ መሆናቸውን በመግለጽ  በርካታ ታሳሪዎች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ መታሰራቸውን፣ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንና በቤተሰብ አለመጎብኘታቸውን አስታውቋል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ሊወስድ የሚችላቸውን ዕርምጃዎች ኢሰመኮ የሚረዳ ቢሆንም፣ ‹‹የዚህ ዓይነት የሰብዓዊ መብቶች መርሆዎችን ያልተከተለና የተስፋፋ እስር ተገቢ አለመሆኑን፤›› በመግለጽ የፌደራልም ሆነ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን ከወንጀል ምርመራ በፊት ከማሰር፣ ጋዜጠኞችን በሥራቸው ምክንያት ከማሰርና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ ሰዎችን ከማሰር ሊታቀቡ እንደሚገባ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

በተጨማሪም በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ተፈጽሟል ተብሎ የሚጠቀስ የትኛውም ጥፋት ባለፈው ዓመት የፀደቀውን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እንደሚጥስ የገለጹት ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር)፣ አዋጁ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የሚከሰሱ ሰዎች ላይ የሚደረግን ከችሎት በፊት የሆነ እስርን እንደሚከለክል ተናግረዋል፡፡ ኮሚሽኑ መንግሥት ሁሉንም ጋዜጠኞችና የመገናኝ ብዙኃን ሠራተኞች በአስቸኳይ እንዲለቅ አሳስቧል፡፡

በተመሳሳይ የመብቶች ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣ የኢትዮጵያ አርታዒያን ማኅበር፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበርና ሌሎች ማኅበራት ግንቦት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በጋራ ባወጡት መግለጫ የዘፈቀደ የጋዜጠኞች እስር እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

የመገናኛ  ብዙኃን አዋጁን በመጥቀስ የወጣው መግለጫ የሕግ የባለይነትን ያልተከተለ አሠራር ለሕግ የበላይነት፣ ለሚዲያ ነፃነት፣ ለጋዜጠኞች ደኅንነትና ለኢትዮጵያ ሰላም መረጋጋት አደጋ እንደሚፈጥር አጥብቀው እንደሚቃወሙ አስታውቀዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ፈቃዱ ፀጋ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃል ምልልስ፣ በፍትሕ ተቋማት የሚታዩ ግድፈቶች ስለመኖራቸውና ምንም እንኳ የተዘረጋው የመንግሥት መዋቅርና ሕጎች ያንን የሕግ ግድፈት እንዲፈጸም የማይፈቅዱ ቢሆንም፣ በቸልተኝነት ወይም በተለያዩ ምክንያቶች አንዳንድ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አካላት የፈጸሟቸው ስለመሆናቸው አጠያያቂ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ከሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ሙላት ዓለማየሁ (ዶ/ር)፣ ከሰሞኑ በጋዜጠኞች ላይ የተደረገው ድንገተኛ እስር በኢትዮጵያ ሚዲያ ኢንዱስትሪ ታይቶ የነበረውን ጭላንጭል ተስፋ መቶ በመቶ ሊያጠፋው እንደሚችል በቀጣይም ዘርፉ እንዲቀጭጭ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ለሪፖርተር  ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ በተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ሳቢያ እየታየ ያለው ጋዜጠኞችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ተግባር፣ በቀደሙት ዘመናት በፖለቲካው ችግር ሰበሰብ ጋዜጠኞች ላይ ይደርስ የነበረው ዓይነት ሁኔታ በድጋሚ እየታየ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከሰሞኑ ወደ ሃያ የሚደርሱ ጋዜጠኞች እስር የሚያመለክተው 120 ሚሊዮን የሚደርሰውን ሕዝብ ድምፅ እንደማፈን በመሆኑ፣ አካሄዱ ዘርፉን አስፈሪና ከፍተኛ በሆነ ሁኔታ አደጋ ላይ ይጥለዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ጌታቸው ድንቁ  (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደነገሩት፣ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ሲሻሻል ዋነኛ ዕሳቤ ከነበሩት ጉዳዮች መካካል አንዱ ጋዜጠኝነት ወንጀል ተደርጎ እንዳይወሰድና የሚከሰቱ ችግሮች በፍትሐ ብሔር እንዲታይ በሚል መሻሻሉን ነው፡፡

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ጋዜጠኞች ምንም እንኳ እያንዳንዳቸው የቀረበባቸውን ክስ በግልጽ ለማወቅ ቢቸግርም፣ ሕዝቡ የሚያውቃቸውጋዜጠኝነት ሲሠሩ ወይም የማኅበረስብ አንቂዎች መሆናቸውን ነው ብለዋል፡፡

ስለሆነም የወንጀል ነው ወይም ሽብር የማነሳሳት የሚለው ጉዳይ ትልቅ የሆነ መረጃ የሚያስፈልገው እንደሆነ በመግለጽ፣ የተከሰሱት ሰዎች መከሰስ ያለባቸው በወንጀል ሳይሆን በሐሳባቸው ምክንያት በፍትሐ ብሔር መሆን እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ከባዱ ነገርና የሚታየን ጉዳይ ጋዜጠኞች ኃላፊነት ባለው መንገድ  በነፃነት እንዳይሠሩ ለማድረግ ትልቅ ጫና እንደሚያሳድር፣ እንዲሁም በተለይ አንዳንዶቹ የተያዙበት መንግድ ‹‹እጅግ ተቀባይነት የሌለው›› እና ዜጎች በመሆናቸው አፈና የሚባለው ነገር ሊመጣ እንደማይጋባ፣ ሕጋዊ የሆነ አሠራር በመኖሩ ጋዜጠኞች ሥራቸውን እየሠሩና ሰላማዊ ኑሯቸውን እየመሩ ክሳቸውን መከታተል እንደሚችሉ ጌታቸው  (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ የጋዜጠኞቹ እስር መዘዙ ከባድ እንደሆነ ገልጸው፣ ሥራ ላይ ባሉ ጋዜጠኞች ላይ የሚያሰድረው ፍርኃትና ኅብረተሰቡ ሊያገኝ የሚገባውን ያህል መረጃ ሊያገኝ አንዳይችል እንደሚያደርገው አክለው፣ ‹‹በዚህ ፍጥነትም እንዲህ ዓይነት ክስተቶች ይፈጠራሉ ብዬ አስቤ አላውቅም፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -