በብሔራዊ ምክከሩ ለመሳተፍ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል
ከግንቦት 14 እስከ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባውን በሰመራ ከተማ እንዳደረገ ያስታወቀው የአፋር ሕዝብ ፓርቲ በክልሉ ግለሰቦች የሚፈነጩበት የሕዝብ ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል ጠየቀ፡፡
ፓርቲው ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባው ክልላዊና አገራዊ ጉዳዮችን በዝርዝር ተመልክቶ ውሳኔዎችንና አቅጣጫ ያላቸውን ጉዳዮች አቅርቧል፡፡
ሰመራን ጨምሮ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ከፍተኛ የውኃ እጥረት ከመኖሩ በላይ ባለሥልጣናት ቦቴ ተሽከርካሪዎችን ገዝተው 20 ሊትር ውኃን በ35 ብር በመሸጥ ዋናውን የውኃ መስመር ዘግተው ሕዝቡን ለከፍተኛ የውኃ ጥም አጋልጠውታል ብሏል ፓርቲው በመግለጫው፡፡ ደርጊቱ ይቅር የማይባል የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመሆኑ በፍጥነት ሊስተካከል እንደሚገባ ተገልጾ፣ በሌላ በኩል በክልሉ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ ከመኖሩ ባሻገር ከፍተኛ የትራንስፖርት እጥረት ማጋጠሙን አመላክቷል፡፡
የአፋር ሕዝብ ፓርቲ በመግለጫው ግለሰቦች የሚፈነጩበት የሕዝብ ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል የጠየቀ ሲሆን፣ መንግሥት አውቶቡሶችን በግዢም ሆነ በኪራይ በማቅረብ ለሕዝቡ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደሚገባው አስገንዝቧል፡፡
የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ‹‹ከሕዝብ የወጡና ነገ ወደ ሕዝብ የሚመለሱ የማይመስላቸውን አረመኔዎች›› እንደሚያወግዝ አስታውቆ፣ የክልሉ አስተዳደር አስቸኳይ የዕርምት ዕርምጃ እንዲወስድባቸው አሳስቧል፡፡
ፓርቲው ጨምሮም የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ደግሞ የአፋር ሕዝብ በብልፅግናና በሕወሓት የሥልጣን ጥማት ያልተገባ የሀብትና የሕይወት ዋጋ ለመክፈል ተገዷል፡፡ ከጦርነት በተጨማሪ በሕዝቡ ላይ ከሁሉም አቅጣጫ ጦርነት ተከፍቶበት በገዛ መሬቱ ላይ በየቀኑ እየተገደለ ይገኛል ብሏል፡፡ አያይዞም መንግሥት በየዕለቱ በከንቱ የሚሞቱትን ዜጎች ከለላ እንዲሰጥና ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ ፓርቲው በአፅንኦት አሳስቧል፡፡
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ፓርቲው እንዳስታወቀው፣ በክልሉ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተከስቷል፡፡ ሴቶች በመንጋ ተደፍረዋል፣ ሕፃናት ከወላጆቻቸው ተነጥለዋል፣ ከከፍተኛ የአካል ጉዳት ባሻገር ሕዝቡ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ ለስደት ተጋልጧል፡፡
ዜጎች በስደት በሚገኙባቸው ማጎሪያዎች ውስጥ የምግብ፣ ውኃና የመድኃኒት ቀውስ ከፍተኛ መሆኑን የዳሰሰው ፓርቲው፣ ከአገር ውስጥም ሆነ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚገኘው የስብዓዊ ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ ስለማይውልና የግለሰቦች መበልፀጊያ ስለሆነ ሕዝቡ ለከፍተኛ የርሃብና የጤና ችግር መጋለጡ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል፡፡ ስለሆነም መንግሥት እነዚህን አንገብጋቢ የሕዝብ ችግሮች በአስቸኳይ እንዲፈታና የዜጎችን ሕይወት እንዲታደግ አሳስቧል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው እንዳመላከተው በዚህ ወቅት ሐሳባቸውን ለመግለጽ የሞከሩ በርካታ ወጣቶች በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በእስር ቤት ውስጥ የሰብዓዊ መብት ገፈፋ እንደሚፈጸምባቸው ተጠቅሶ፣ እነዚህ ዜጎች በሕጉ መሠረት ፍርድ አግኝተው እንዲለቀቁ ተጠይቋል፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቱን ለዓለም ማኅበረሰብ ለማሰማት ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ፓርቲው አስታውቆ፣ በዚህም ሒደት የአገር ውስጥና የውጭ አገሮች ተቋማትን በአካልና በደብዳቤዎች ግንኙነት በመፍጠር እውነቱን ለማስረዳት መሞከሩ ተገልጿል፡፡
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የመብት ጥሰቶችን አስመልክቶ ለአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ለአውሮፓ ኅብረት የምሥራቅ አፍረካ ልዩ መልዕክተኛ፣ ለዩኬ የምሥራቅ አፍሪቃና የቀይ ባህር ልዩ መልዕክተኛ፣ ለአፍሪካ ኅብረት የስብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአካል ቀርበው ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በአፋር ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ዳተኝነት ማሳየታቸውን ፓርቲው ጨምሮ ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ከብሔራዊ ምክክሩ ጋር በተገናኘ ፓርቲው የአገሪቱ ወቅታዊና ዘላቂ ችግሮች በፍትሐዊ፣ ሀቀኛ፣ ታዓማኒ፣ ግልፅና ሁሉን አቃፍ ብሔራዊ ምክክር መፈታት አለበት ብሎ እንደሚያምን አስታውቋል፡፡
የተቋቋመው ኮሚሽን ከላይ የተገለጹትን ዝቅተኛ መሥፈርቶችን ያላሟላ፣ ትጥቅ ያነሱትን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ኃይሎችን አንድ ላይ አምጥቶ ዘላቂ ሰላም ማምጣት የማይችል በመሆኑ፣ የጊዜና ጉልበት ብክነት ብቻ ካልሆነ መፍትሔ ያመጣል ብሎ እንደማይጠብቅ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ገልጿል፡፡
በሒደት ውስጥ የባከነ ነገር ባላመኖሩና ከጉዳዩ አስፈላጊነት አንፃር የማይረፍድበት አጀንዳ በመሆኑ ችግሮቹ ተስተካክለው በቅንነት አገሪቱን እንታደግ የሚል ጥያቄ እንደሚጠይቅ ያመላከተው ፓርቲው፣ በመሆኑም ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎችን እስኪሟሉ በሒደቱ ለመሳተፍ እንደሚቸግር አስታውቋል፡፡
በተያያዘም ትናንት መኢአድ፣ እናትና ኢህአፓ ፓርቲዎች በሰጡት መግለጫ በአፋር ክልል በሕወሓት ተፈጸመ ያሉትን ጥቃትና ውድመት አንስተዋል።
ሕወሓት በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ዳግም ሥጋት ወደማይሆንበት ደረጃ እንዲወርድ ተደርጓል ቢባልም ሆኖም ከዚያ ወዲህ በአፋር ክልል ጥቃት ከፍቶ ውድመት ማድረሱን ፓርቲዎቹ በጋራ መግለጫቸው አመልክተዋል።
ሕውሓት በአፋር ክልል በአምስት ወረዳዎች ያደረሰውን ውድመት በአካል ጭምር ለመመልከት መቻሉን ያመለከቱት መግለጫ የሰጡት የፓርቲዎቹ አመራሮች ለዚህ ደግሞ መንግሥትንም ተጠያቂ አድርገዋል።
መንግሥት የሕግ ማስከበር ሚናውን በአግባቡ ቢወጣ ኖሮ የአፋር ክልል ዳግም በሕወሓት ጥቃት አይደርስበትም ነበርም ሲሉ ተናግረዋል።