Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከአቅም በታች ለማምረት ሲገደዱ በ24 ሰዓት ውስጥ እንዲያሳውቁ ሊገደዱ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማዕድን ሚኒስቴር የሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱና በአቅማቸው ልክ ማምረት የማይችሉበት ሁኔታ ሲከሰት፣ በ24 ሰዓት ውስጥ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዲያሳውቁ የሚያዝ ረቂቅ መመርያ አዘጋጀ፡፡

ረቂቁ፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ዓመታዊና ወርኃዊ የምርት መጠን ዕቅዳቸውን እንዲያሳውቁ የሚደነግግ ሲሆን፣ በየሳምንቱ ያመረቱትን ምርት ዓይነትና መጠን እንዲያሳውቁም ያስገድዳል፡፡ የረቂቅ መመርያውን ድንጋጌዎች በማናቸውም መልኩ በሚተላለፉ ፋብሪካዎች ላይ እንደ ጥፋቱ ክብደት ማስጠንቀቂያ ሊሰጣቸው፣ ለጊዜው ሥራውን እንዲያቆሙ ሊደረግ ወይም ፈቃዳቸው ሊሰረዝ እንደሚችል በረቂቁ ላይ ተቀምጧል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር ለሪፖርተር እንዳስታወቀው የሲሚንቶ ምርት ሒደትን የሚመለከተው ይኼ ማዕድንና ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴሮች በጋራ እያዘጋጇቸው ካሏቸው ሁለት መመርያዎች አንዱ ነው፡፡ ከምርት በኋላ የሚኖረውን የገበያ ሰንሰለት የሚመራ መመርያ ደግሞ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እየተዘጋጀ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

‹‹የሲሚንቶ ግብዓትና የሲሚንቶ ምርት ጥራትን ለመቆጣጠር›› በሚል በተዘጋጀው ረቂቅ መመርያ ላይ እንደተቀመጠው መመርያው ለሲሚንቶ አምራቾች ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች በመፍታት በሙሉ አቅማቸው የሚያመርቱበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡ የሲሚንቶ ምርት ምርታማነትና ጥራት ከፍ ማድረግ እንዲሁም የሲሚንቶ ምርት ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናት በሚመረቱባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን የልማት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥም መመርያውን አስፈላጊ ያደረጉት ምክንያቶች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በዚህ ረቂቅ መመርያ ላይ ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች ከተጣሉባቸው ግዴታዎች ውስጥ አንዱ የፋብሪካቸውን ከፍተኛና ዝቅተኛ የማምረት አቅም በየሩብ ዓመቱ ማሳወቅ የሚል ይገኝበታል፡፡ ፋብሪካዎቹ በየሳምንቱ ያመረቱትን የሲሚንቶ መጠን ከማሳወቅ ባሻገርም ረቂቅ መመርያው፣ ፋብሪካዎቹ የተጠቀሙትን የግብዓት መጠንና ሌሎች ማስረጃዎችን የሚያሳዩ ሰነዶችን እንዲያቀርቡ ያዛል፡፡

ዓመታዊና ወርኃዊ የምርት መጠን ዕቅዳቸውን በማሳወቅም ከአቅም በታች ለማምረት የሚገደዱበት ሁኔታ ሲፈጠር በ24 ሰዓት ውስጥ የማምረት ፈቃድ ለሰጣቸው ማዕድን ሚኒስቴር የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ የግብዓትና የሲሚንቶ አቅርቦት ሥርዓቱን በማናቸውም መልኩ የሚያዛቡ ወይም የሚያስተጓጉሉ ማናቸውንም ተግባራትን አለመፈጸምም ረቂቁ ፋብረካዎች ላይ ከጣለው ግዴታዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

ረቂቁ ከአምራች ፋብሪካዎች ባሻገር የግብአት አቅራቢዎችንም የሚመለከት ሲሆን፣ የግብዓት አምራች ባለፈቃድ ወጣቶች የሲሚንቶ ግብዓት ማቅረብ የሚችሉት ለሁለት ዓመት ብቻ ለመሥራት ውል ከገቡ እንደሚሆን አስቀምጧል፡፡ መመርያው ሲጸድቅ ግብዓት አቅራቢዎች እንደ አምራች ፋብሪካዎች ሁሉ ዓመታዊና ወርኃዊ የምርት ዕቅዳቸውን ፍቃድ ለሰጣቸው አካል አስቀድመው የማቅረብ ግዴታ ይጣልባቸዋል፡፡

ማዕድን ሚኒስቴር ባዘጋጀው ረቂቅ መመርያ ላይ የሲሚንቶ ግብዓት ማዕድናትን ዋጋ የመተመንና በተመኑ መሠረት ግብይት እንዲፈጸም የማድረግ ኃላፊነት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይሆናል፡፡ በረቂቁ መሠረት ማዕድን ሚኒስቴር፣ ፋብሪካዎች በገቡት የውል ግዴታና የሥራ ፕሮግራም መሠረት መሥራታቸውን እንደሚከታተል ተቀምጧል፡፡ ረቂቁ፣ ያለበቂ ምክንያት ከአቅም በታች የሚያመርቱ ወይም ማምረት ያቆሙ የሲሚንቶና የግብዓት አምራቾች በመለየት ድጋፍ የማድረግ እንደ አስፈሊጊነቱም የዕርምት ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነትም ለሚኒስቴሩ ሰጥቷል፡፡

በክልሎች የማዕድን ሥራዎችን ለማስተዳደር ሥልጣን የተሰጠው አካል የሲሚንቶ ግብዓት በተተመነበት ዋጋ እንዲሸጥ ክትትል ማድረግን ጨምሮ ከግብዓት አቅራቢዎች ጋር የተያያዘ ኃላፊነቶችን እንደሚወስድ በረቂቁ ላይ ተቀምጧል፡፡

የማዕድንና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ባለሥልጣናት ረቂቁ ላይ በተደጋጋሚ እንደመከሩበት የገለጸው ሚኒስቴሩ ረቂቁ ለመጽደቅ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ሚኒስቴር፣ አሁን የሲሚንቶ ሽያጭ የሚከናወንበት የነጻ ገበያ ሥርዓት ለቁጥጥር አመቺ ባለመሆኑ የትርፍ ህዳግን በመወሰን የመሸጫ ዋጋ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ማሰቡን ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ሀሰን መሐመድ ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡ ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመርያ የሲሚንቶ ምርት ሥርጭትንም ለመቆጣጠር እንደሚያገለግልና ሲሚንቶ ከምርት እስከ ሽያጭ ሒደቱ ክትትል እንደሚደረግበት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች