Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመንግሥት ሠራተኞች በኪራይ የተሰጣቸውን ቤት የራሳቸው ለማድረግ የሚያስችላቸውን ውል እየፈጸሙ ነው

የመንግሥት ሠራተኞች በኪራይ የተሰጣቸውን ቤት የራሳቸው ለማድረግ የሚያስችላቸውን ውል እየፈጸሙ ነው

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2010 ዓ.ም. በኪራይ የጋራ መኖሪያ ቤት የሰጣቸው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች፣ የቤቱ ባለቤት ለመሆን የሚያስችላቸውን ውል ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እየፈጸሙ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የመንግሥት ሠራተኞቹ በኪራይ የተሰጣቸውን ቤት በባለቤትነት የሚወስዱት የቤት ማስተላለፊያ ዋጋው ድጎማ ተደርጎበት ሲሆን ውል የሚፈጽሙበት ዋጋ የከተማ አስተዳደሩ አሁን ላይ አንድ ካሬ ሜትር ቤት ከሚያስተላልፍበት ዋጋ በ43.5 በመቶ የቀነሰ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በአማካይ ከፍተኛው የአንድ ቤት ሙሉ ክፍያ 180 ሺሕ ብር ሲሆን ትልቁ የቅድመ ክፍያ ዋጋ ደግሞ 20 ሺሕ ብር ነው፡፡

ይኼንን ቅድመ ክፍያ አሁን ላይ መክፈል የማይችሉ የመንግሥት ሠራተኞች አንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ እንደሚሰጣቸውና በሚገቡት ውል መሠረት ሙሉ ክፍያውን ለመፈጸም የ20 ዓመት ጊዜ እንደሚኖራቸው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጋሻው ተፈራ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንደገለጹት እነዚህ አምስት ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከአራት ዓመት በፊት በኪራይ የተላለፉት ደመወዛቸው ከአራት ሺሕ ብር ለማይበልጥና በተለያዩ የከተማ አስተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች ለሚሠሩ ሠራተኞች ነው፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በቦሌ አራብሳ፣ ኮዬ ፈጬ፣ የካ አባዶና ቂሊንጦ ፕሮጀክት ሳይቶች የሚገኙ መሆናቸው የገለጹት አቶ ጋሻው፣ ሠራተኞቹ ለከተማ አስተዳደሩ ሲከፍሉ የነበሩት የቤት ኪራይ አነስተኛ እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡

አሁን ግን የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኞቹን በዘላቂነት የቤቱ ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ መውሰዱ ተገልጿል፡፡ ቤቶቹ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተገኘ ብድር የተሠሩ መሆናቸውን እንደ አንድ ምክንያት የጠቀሱት አቶ ጋሻው በኪራይ የሚገኝ ገንዘብ ከመሰብሰብ ይልቅ ውል ሲገቡና ከገቡ በኋላ በሚከፍሉት ክፍያ ብድሩን መመለስ የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሠራተኞቹ ውል እንዲፈጽሙ የማድረግ ሥራው ከመጀመሩ በፊት ገለጻ እንደተሰጠ ያስረዱት አቶ ጋሻው፣ አሁን ቅድመ ክፍያውን መፈጸም ለማይችሉ ሠራተኞች አንድ ዓመት ጊዜ የሚሰጠው ዝግጅት እንዲያደርጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወቅታዊ የቤት ማስተላለፊያ ዋጋ በካሬ ሜትር 4997.17 ብር እንደሆነ፣ ሠራተኞቹ ውል እየገቡ ያሉት ግን በካሬ ሜትር በ4511.27 ብር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለውል ፈጻሚዎቹ የተደረገው ድጎማ ለከተማ አስተዳደሩ አዋጪ እንዳልሆነ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ በዚህ መንገድ ቤቶቹ ለሠራተኞች ካልተላለፉ የቤት ባለቤት የመሆን ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን አብራርተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ከተያዘው ግንቦት ወር አንስቶ ሠራተኞቹ የቤት ባለቤት ለመሆን የሚያስችላቸውን ውል እንዲፈጽሙ እየተደረገ መሆኑንና እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ 1056 ሠራተኞች ቅፅ ሲወስዱ 556 ደግሞ ውል መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ ሁሉንም ሠራተኞች በ60 የሥራ ቀናት ውስጥ ውል ለማስገባት ዕቅድ ተይዞ ፕሮግራም ወጥቷል፡፡ ሠራተኞቹም በወጣው ፕሮግራም መሠረት በስልክ ጥሪ እየመጡ ውል እንዲፈጽሙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሠራተኞቹ ውሉን ለመፈጸም ሲመጡ ከዚህ ቀደም ይኖሩበት ከነበረው ወረዳ ቤት የሌላቸው መሆኑን ማረጋገጫ፣ ቤት ከተሰጣቸው በኋላ ኪራይ ሲከፍሉ ማስረጃና ሌሎች ሰነዶችን ማቅረብ እንደሚኖርባቸው አስረድተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከዚህም ቀደም በኪራይ ቤት የተሰጣቸው መምህራን ተመሳሳይ ውል እንዲፈጽሙ ማድረጉን የገለጹት አቶ ጋሻው፣ በቀጣይም የመንግሥት ሠራተኞች በኪራይ ቤት የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...