Wednesday, December 6, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስፈልገው በነፃነት የሚኖርበት ሥርዓት ነው!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው ትልቁ በሽታ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ አለመሆን ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ መሆን እንዳለበትና ተጠያቂነትም እንዳለበት በሕግ ቢደነግግም፣ ፌዴራል መንግሥቱንም ሆነ ክልላዊ መንግሥታትን የሚመሩ ኃላፊዎች ተግባራዊ ሲያደርጉት አልታየም፡፡ ይልቁንም የመንግሥት አሠራር ድብቅ፣ ለሐሜት የተጋለጠና በሴራ የተጀቦነ ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ እየሆኑ ከፍተኛ ጉዳቶች አጋጥመዋል፡፡ ኢሕአዴግ ለሦስት አሠርት ያህል በመራት ኢትዮጵያ ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት በመጥፋቱ ከፍተኛ ሕዝባዊ ቁጣ ተቀስቅሶ፣ የሕይወት መስዋዕትነት ባስከተለ አመፅ የአስተዳደር ለውጥ ተደርጓል፡፡ ሥርዓተ መንግሥቱ ተናግቶ የሥርዓት ለውጥ ለማከናወን ግፊቱ ቢቀጥል ኖሮ፣ ኢትዮጵያን አሁን ባለችበት ሁኔታ ለማግኘት ያዳግት ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ሰላማዊ ሽግግር ተደርጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመሩት አስተዳደር፣ ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት በላይ ኢትዮጵያ የተለያዩ ክስተቶች አጋጥመዋታል፡፡ ለማመን የሚከብዱ በርካታ አዎንታዊ ተግባራት የተከናወኑትን ያህል፣ አገርንና ሕዝብን ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ የጣሉ አሳዛኝ ድርጊቶችም ተፈጽመዋል፡፡

በተደጋጋሚ እንደምንለው ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ናት፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ በፍጥነት መውጣት ካልተቻለ ቀውስ ይፈጠራል፡፡ ከ115 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥነት ያስጨንቃታል፡፡ የኑሮ ውድነቱ እየባሰበት የሕዝቡን ሕይወት እያመሰቃቀለ ነው፡፡ በድርቅና በመፈናቀል ምክንያት ሚሊዮኖች አስቸኳይ ዕርዳታ ይለመንላቸዋል፡፡ ሰፊ ለም መሬትና ከፍተኛ የውኃ ሀብት ቢኖርም አሁንም ግብርናው ኋላቀር ነው፡፡ ደካማ የሆነው የአምራች ዘርፍ ከውጭ የሚመጡ የካፒታል ዕቃዎችንና የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን መተካት አልቻለም፡፡ የአገሪቱ የወጪና የገቢ ንግድ ሚዛን አሁንም ከፍተኛ ጉድለት አለበት፡፡ ሌሎች በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ግን መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ለጋራ ራዕይና ዓላማ አንድ ላይ መሠለፍ አለባቸው፡፡ ሠልፉን ለማስተካከል ደግሞ የሕግ የበላይነት ትልቁ መሣሪያ ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ ላይ መተማመን እንዲቻል መንግሥት ግልጽነትን፣ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን ከታች እስከ ላይ የማስፈን ግዴታ አለበት፡፡ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ አርሶ አደሮች፣ ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ ፖለቲከኞች፣ ወዘተ ለሕግ የበላይነት መገዛት አለባቸው፡፡ 

‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ መፍትሔ ሳያገኙ የቆዩ ችግሮች ላይ በየዕለቱ አዳዲስ ችግሮች እየተጨመሩ፣ የኢትዮጵያ በሽታ ከማገገም ይልቅ እየፀና መሄድ ጀምሯል፡፡ ኢትዮጵያ የዛሬ አራት ዓመት በአዲስ የለውጥ ጎዳና መጓዝ ስትጀምር፣ ለዘመናት የተከማቹ የቤት ሥራዎቿ መቃለል ይጀምራሉ ተብሎ በብዙዎች ተስፋ ተደርጎ ነበር፡፡ ለዓመታት የተንሰራፋው ጭቆና ተወግዶ ዜጎች ለአገራቸው የሚጠበቅባቸውን የሚያበረክቱበት ዕድል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡ ያለመታደል ሆኖ ለውጡ ለጥቂት ጊዜያት በተስፋ ጎዳና ከተጓዘ በኋላ፣ ጫፍና ጫፍ የረገጡ ሐሳቦች እየተሳሳቡ ጭራሽ የባሰ ሥጋት ውስጥ ተገብቷል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ታፍኖና ተዘግቶ የነበረ ቤት ሲከፈት መጥፎ ጠረን ሊኖር ስለሚችል፣ ነገሮችም ቀስ በቀስ ሊስተካክላሉ ይችላሉ በሚል ዕሳቤ እስካሁን ተቆይቷል፡፡ ሆኖም እንደታሰበው ነገሮች ከመስተካከል ይልቅ ጭራሽ እየባሰባቸው ነው፡፡ በመሀላቸው ቅራኔ መፍጠር የማይገባቸው አካላት ሳይቀሩ እርስ በርስ እየተገፋፉ፣ ልዩነትን ይዞ አገርን በጋራ ለማሳደግ ፍላጎት እየጠፋ ነው፡፡ 

በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ አገር መሠረታዊ ለውጥ ውስጥ ስትገባ፣ ከየአቅጣጫው የተለያዩ ፍላጎቶችና ስሜቶች መንፀባረቃቸው አይቀሬ ነው፡፡ እነዚህ ፍላጎቶችና ስሜቶች እርስ በርስ ከመደጋገፍ በተጨማሪ፣ የእርስ በርስ ጉሽሚያና ፍትጊያም ስለሚያስከትሉ ለውጡ በወጀብ ሊናጥ ይችላል፡፡ የተለያዩ ክስተቶችም የሚያስከትሉት ወጀብ መደናገጥን፣ ሥጋትን፣ ግራ መጋባትንና ተስፋ መቁረጥን ጭምር ሊያመጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን ወጀቡን በፅናት በመቋቋም የተስፋ ጭላንጭል የመፍጠር ኃላፊነት፣ ለአገራቸው የሚያስቡ ዜጎች ግዴታ መሆን ነበረበት፡፡ ኢትዮጵያም ከአራት ዓመታት በላይ የተጓዘችበት ለውጥ በርካታ ተስፋ ሰጪ ጅማሬዎች ቢኖሩትም፣ በየአቅጣጫው የሚሰሙ አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ ክስተቶች እየበረከቱ ነው፡፡ ነገር ግን የአገር ጉዳይ ተስፋ ስለማይቆረጥበት፣ ለማንም አደራ ስለማይባልበትና ስለማይዘናጉበት ሆደ ሰፊ መሆን የግድ ይላል፡፡ ለሥልጣን፣ ለግል ጥቅም፣ ዝና፣ ክብርና ስም ሲባል የሚፈጸሙ አላስፈላጊ ድርጊቶችን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር ሆና ለዜጎች ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና ፍትሕ በእኩልነት ተደራሽ እንዲሆኑ ተባብሮ መሥራት ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመንግሥታዊ ሥልጣንም ሆነ የአገር ሀብት ሉዓላዊ ባለቤት መሆኑን በተግባር ማረጋገጥ የግድ ነው፡፡

ከአገር ህልውና በላይ የሚቀድም ስለማይኖር የግለሰቦችና የቡድኖች ጩኸት አገር ማደንቆር የለበትም፡፡ ጥቂቶች መድረኩን ተቆጣጥረው አጀንዳ እየፈበረኩ ብዙኃኑን ማስጨነቅ አይኖርባቸውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጥቂቶች ይጮሃሉ፣ ብዙኃን ግን በዝምታ ተውጠዋል፡፡ አጋጣሚው የተመቻቸላቸው እንዳሻቸው አገርን ሲያምሱ፣ የብዙኃን በአርምሞ ውስጥ መሆን ያሳስባል፡፡ ያለችው አንድ አገር ስለሆነች ለህልውናዋ በፅናት መቆም የግድ መሆን እንዳለበት መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ አክቲቪስቶች፣ ምሁራንም ሆኑ የሃይማኖት መሪዎች፣ እንዲሁም የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል መጨነቅና መጠበብ አለባቸው፡፡ ጥግ ይዞ ማጉረምረም ወይም በሐሳብ መብሰልሰል ፋይዳ የለውም፡፡ ተወደደም ተጠላም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ አንድ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ በዘመናት አብሮነቱ የሚጋራቸው በርካታ የጋራ ጉዳዮች አሉት፡፡ ሥነ ልቦናው በጣም የተቀራረበ በመሆኑም አንዱ ያለ ሌላው ሕይወት ይከብደዋል፡፡ ይህንን የቤተሰብ ያህል የተዛመደ ሕዝብ ለማበጣበጥና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመግፋት መሞከር አይገባም፡፡

ለኢትዮጵያ ሰላም ያስፈልጋል፡፡ በማንኛውም መንገድ ጦርነት አቁሞ ሰላም ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ ሰላምን እያናጉ ዓላማን ማሳካት የሚፈልጉ ወገኖች ካሉም፣ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት ትርምስ ውስጥ ነው የሚገቡት፡፡ ይህ ደግሞ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ግጭት በመቀስቀስ ሰላማዊ ዜጎችን መግደል፣ ማፈናቀል፣ መዝረፍና የሁሉም ነገር የበላይ ለመሆን መሞከር ውጤቱ ቀውስ ነው፡፡ ለሕግ የበላይነት ባለመገዛት ሥርዓተ አልበኝነት መፍጠርም የማይወጡት አረንቋ ውስጥ ይከታል፡፡ ከትናንት ጉልበተኞች አወዳደቅ ያልተማሩ አዳዲስ ጉልበተኞችም መረዳት ያለባቸው፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ የፈለጉትን መፈጸም እንደማይቻል ነው፡፡ የጉልበት መንገድ የሚወስደው ወደ አምባገነንነት ነው፡፡ አምባገነንነት ደግሞ ለዚህ ዘመን የማይመጥን ኋላቀርነት ነው፡፡ ኋላቀርነት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጥሎት ያለፈው ጠባሳ ዛሬም ከእነ ክፋቱና ውርደቱ በጉልህ ይታያል፡፡ አገራቸውንና ሕዝባቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያዊያን መገንዘብ ያለባቸው፣ ተመራጩና የሚያዋጣው መንገድ ወደ እኩልነት የሚደረገው ጉዞ ብቻ እንደሆነ ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል የሚሆኑበት ሥርዓት የግንባታው መሠረት ጥብቅና አስተማማኝ እንዲሆን፣ አስፈላጊዎቹን ነገሮች ሁሉ ለሟሟላት መረባረብ የግድ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስፈልገው በነፃነት የሚኖርበት ሥርዓት ነው

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...