የሕንፃዎች የቀለም ኮድ ከከተማ ንድፍ ቀድሞ መዘጋጀቱ ተተችቷል
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሪል ስቴት ኩባንያዎች ለሚገነቧቸው አፓርትመንቶችና ቪላ ቤቶች የከተማ አስተዳደሩ ከሚያወጣው የቀለም ኮድ ውጪ፣ የራሳቸውን ቀለም በመለየት ማፀደቅ እንደሚችሉ ተገለጸ፡፡ የሪል ስቴት ኩባንያዎች ከቤት ሕንፃዎች የውጭ ግድግዳ ቀለም በተጨማሪ፣ የጣሪያ ቀለም ወስነው ማፀደቅ እንደሚኖርባቸው ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሕንፃዎች የቀለም ረቂቅ ስታንዳርድ ለማዘጋጀት በስታዲየም፣ በፒያሳ፣ በለገሃር፣ በአራት ኪሎ፣ በመርካቶና በመገናኛ አካባቢዎች ዳሰሳ አድርጎ 65 በመቶ የሚሆኑት የከተማዋ ሕንፃዎች ቀለም “RAL 7000-7048” በሚባለው የግራጫ (gray) ቀለም ዝርያ ውስጥ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡ በዚህም መነሻነት የሕንፃ ቀለም ስታንዳርድ ሲዘጋጅ በዚህ ዝርያ ወስጥ ያሉ ቀለሞችና ተመሳሳይነት ያላቸውን “RAL 9001-9003፣ 9006፣ 9007፣ 9010” ቀለሞች ለመጠቀም ማሰቡን እሑድ ግንቦት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ለኪነ ሕንፃ ባለሙያዎችና ለዘርፉ ሙያ ማኅበራት ገለጻ አድርጓል፡፡ ከእነዚህ ቀለሞች መካከል ከግራጫ የወጣ ቀለም ያላቸው ክሬምና ነጣ ያለ ቀለማት የሚባሉት፣ “RAL 9001፣ RAL 9003፣ RAL 9010” ናቸው፡፡
ስለስታንዳርዱ ገለጻ ያደረጉት በግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የሕንፃ መጠቀሚያ ፈቃድ አሰጣጥ ዳይሬክተር አቶ ሔኖክ ረጋሳ እንዳስረዱት፣ የሕንፃ ቀለም ስታንደርዱ በከተማዋ የሚገኙ የመንግሥትና የግል ሕንፃዎች ላይ በሙሉ ተግባራዊ የሚሆን ቢሆንም ይህ ቀለም የማያካትታቸው የሕንፃ ዓይነቶች ተለይተዋል፡፡ በቅርስነት የተመዘገቡ ሕንፃዎች፣ ዓለም አቀፍ መለያ ያላቸው ተቋማት ሕንፃዎች፣ የባህል ማዕከላት፣ ፋብሪካዎች፣ ማከማቻዎች፣ እንዲሁም የጤና፣ የእምነትና የትምህርት ተቋማት ሕንፃዎች ይህ የቀለም ኮድ ተግባራዊ እንደማይደረግባቸው አብራርተዋል፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ፣ ‹‹ብዙውን ጊዜ ለሕንፃዎቻቸው ተመሳሳይ ቀለም ይጠቀማሉ›› የተባሉት የሪል ስቴትና የመንግሥት የጋራ መኖሪያ ቤት ሕንፃዎች በከተማ አስተዳደሩ የሚወሰነው ቀለም አስገዳጅ እንደማይሆንባቸው አቶ ሔኖክ ተናግረዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ የሪል ስቴት አልሚዎች ለሚገነቧቸው ለአፓርትመንት ሕንፃዎችና ለነጠላ ቤቶች በራሳቸው የተለያየ ቀለም በማምጣት በከተማ አስተዳደሩ አፀድቀው መጠቀም ይችላሉ፡፡ አቶ ሔኖክ አክለውም፣ ‹‹የከተማዋን የቀለም ቫራይቲ መጠበቅ ስለሚያስፈልግ እነዚህ ሪል ስቴቶች “RAL” ዝርያ ውስጥ አይገደቡም፤›› ብለዋል፡፡ በመንግሥት ለሚገነቡ የጋራ ቤቶች ማለትም 20/80 እና 40/60፣ እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶች የራሳቸውን ምርጫ እንደሚያፀድቁ አስታውቀዋል፡፡
በሚመረጠው የቀለም ስታንዳርድ የሚጠቀሙ የግልና የመንግሥት ሕንፃዎች ቀለሙ የሚወሰንላቸው ለሕንፃቸው የውጭ አካል ሲሆን፣ ሪል ስቴቶችና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግን የጣሪያቸው ቀለምም ተመሳሳይ እንዲሆን ይገደዳሉ፡፡ የሪል ስቴት አልሚዎችና የጋራ መኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶች እንደ የሕንፃ የውጭ ቀለም ሁሉ የጣሪያ ቀለም ምርጫቸውን ወስነው ማፀደቅ ይኖርባቸዋል፡፡
በተጨማሪም ስታንዳርዱ እስከ ስድስት ሜትር ያለ የሕንፃ ግንባታ ክፍል በቀለም ሳይገደብ፣ አርክቴክቱ የፈለገውን ቁስ ወይም ቀለም እንዲጠቀም እንደሚፈቅድ አቶ ሔኖክ አስረድተዋል፡፡
ይኼ ገለጻ የተደረገላቸው ባለሙያዎችና የሙያ ማኅበራት ተወካዮች የቀለም ስታንዳርድ መዘጋጀቱ ላይ ስምምነት እንዳላቸው ቢገልጹም፣ በከተማ አስተዳደሩ የሕንፃ ቀለም ምርጫና ረቂቅ ስታንዳርዱ በተዘጋጀበት ሒደት ላይ ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡ በተሳታፊዎቹ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ጎልቶ የወጣው፣ ከተማዋ እንዲኖራት የሚፈለገውን ገጽታና አካላዊ አቀማመጥ ከተለያዩ ዘርፎች አንፃር (multi-disciplinary) የሚያስቀምጠው የከተማ ንድፍ (urban design) ሳይዘጋጅ፣ ከዚህ ውስጥ ነጠላ የሆነ የቀለም ስታንዳርድ የመዘጋጀቱ ጉዳይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አማኑኤል ተሾመ፣ ‹‹አዲስ አበባ ይህ ዓይነት የቀለም ኮድ ሲወጣላት ዓላማው ምንድነው የሚለው ከስትራክቸር ፕላን የሚቀዳ መሆን አለበት፤›› ብለው፣ በዚህ መሠረት የወጡ የሌሎች ዘርፎችም ስታንዳርዶች በተቀናጀ መንገድ ለተመሳሳይ ዓላማ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ በተደረገው ገለጻ ላይም የቀለም ስታንዳርዱ ሲዘጋጅ ከሌሎች የከተማ ንድፍ ማስፈጸሚያ ስታንዳርዶች ጋር በመሆን ምን ዓላማን ለማሳካት እንደታሰበ እንዳልተገለጸ ተናግረዋል ፡፡
አቶ ተሾመ ኢጆ የተባሉ አርክቴክትና የአርባይ ዲዛይን ባለሙያም ሐሳቡን ተጋርተው፣ የከተማ ንድፍ ሳይኖር የቀለም ስታንዳርድን ማስፈጸም አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ይኼንን ሲያስረዱ፣ ‹‹ስለ አንድ [ቀለም] ሕንፃ ነው እያወራን ያለነው፣ ሕንፃዎቹ ተሰባስበው ይኼንን ምሥል ሊሰጡን ይገባል የሚለው አልተቀመጠም፣ ይኼ የሚመጣው ከከተማ ንድፍ ነው፣ የከተማ ንድፍ ሲዘጋጅ ፓተርን ቡክና ዲዛይን ብሪፍ ይኖራል፣ እነዚህ ውስጥ ቀለም ይገኛል፣ ይኼም ቢሆን ሁሉም ቦታ አንድ ዓይነት አይሆንም፣ አንዱ ቦታ ከአንዱ ቦታ ይለያያል፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የከተማ ፕላነሮች ማኅበርን ወክለው የተገኙት አቶ ሮቤል የሺዋስም በብዙ አገሮች የቀለም ኮድ የከተማ ንድፍ ላይ አባሪ ገጽ ሆኖ እንደሚወጣ በመጥቀስ፣ የቀለም ኮድ ከከተማ ንድፍ ሊለይ እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ ከተማዋ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ዘርፎች የየራሳቸውን ስታንዳርድ እያወጡ እንደሚንቀሳቀሱ የጠቆሙት አቶ ሮቤል፣ ይህም ከተማዋ ወጥ የሆነ ገጽታ እንዳትላበስ እንዳደረጋት አብራርተዋል፡፡ ይህ ወጥ ገጽታ በቀለም ብቻ ስለማይመጣ ሁሉም ዘርፎች እየቀዱ እንደሚጠቀሙበት የሚያስችል ገዥ ሥርዓት (Comprehensive urban planning system) መተግበር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ስለከተማዋ ሕንፃዎችና የቀለም ስታንዳርድ ጽሑፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኪነ ሕንፃና ከተማ የትምህርት ክፍል መምህር አቶ ዳዊት በንቲ በበኩላቸው፣ የከተማ ሕንፃዎች ቀለም የከተማ ንድፍ ምንነትና ውጤታማነት ላይ በንፅፅር አነስተኛ ተፅዕኖ ካላቸው ዝርዝሮች ውስጥ የሚመደብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ቀለም ምንጩ የሆነ የዕይታ ረብሻ አዲስ አበባ ውስጥ ማግኘት አልቻልኩም፤›› ብለው፣ ቀለምን ነጥሎ ከማየት ይልቅ ስለከተማ ንድፍ መነጋገር የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ፕላንና ልማት ኮሚሽን የመጡት አቶ ግፋው ሀሰን ለዚህ የባለሙያዎች አስተያየት ምላሽ ሲሰጡ፣ ‹‹ቀለም በራሱ ተነጥሎ አንድ ነገር ሆኖ የሚወጣበት አግባብ የለም፣ በተጻፉ ሕጎች የተቀመጠው የከተማ ንድፍ አካል ሆኖ ነው፤›› ብለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት አስተያየቶች እየተነሱ ያሉት የከተማ ንድፍ መመርያው ስላልፀደቀ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ግፋው፣ የከተማ ንድፍ ደንብ በቅርቡ ፀድቆ መመርያው እንደሚወጣ አስረድተዋል፡፡
የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ስጦታው አካሉ (ኢንጂነር)፣የቀለም ስታንዳር አፈጻጸም ከከተማ ንድፍ የተለየ እንደማይሆን በመግለጽ በቀጣይ የመሠረተ ልማት፣ የድምፅ ብክለት፣ የአረንጓዴ ሥፍራዎችና ሌሎችም ስታንዳርዶች እንደሚዘጋጁ ተናግረዋል፡፡