Skip to main content
x
ከስብሰባው ይልቅ የስብሰባው ቦታ የሚያጓጓው የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆንግ ኡን ውይይት
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልዶ ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ሙከራዋን ማቆሟን ያመሠገኑበት የቴሌቪዥን ሥርጭት

ከስብሰባው ይልቅ የስብሰባው ቦታ የሚያጓጓው የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆንግ ኡን ውይይት

እ.ኤ.አ. ከ1980ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በሰሜን ኮሪያ የመንግሥት የፕሮፓጋንዳ ሥራዎች ማዘጋጃ በሆነው በመንግሥታዊው ቾሱን አርት ፊልም ስቱዲዮ የተሠራውና በአምስት ተከታታይ ክፍሎች የተሠራጨው ‹‹ያየኋት አገር›› (The Country I Saw) የሰሜን ኮሪያ ፊልም፣ የሰሜን ኮሪያና የአሜሪካ ቀረቤታን በሚመለከት ትንቢታዊ መልዕክት አስተላልፏል ይባልለታል፡፡

ፊልሙ በተደጋጋሚ በምታደርጋቸው የኑክሌር ሙከራዎችና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣውን የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር አቅም በመገንዘብ ሥጋት ያደረባቸው አሜሪካና አጋሮቿ በመተባበር ማዕቀቦችንና የተለያዩ ተፅዕኖ ማሳደሪያ መንገዶችን ቢጠቀሙም፣ የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር አቅም ከማደግ ሊያስቆሙት አልቻሉም፡፡ ከተለያዩ ሙከራዎች በኋላ ከሰላማዊ መንገድ ውጪ አማራጭ እንደሌለ የተገነዘቡት አሜሪካና አጋሮቿ፣ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ድርድር ለማድረግ ወደ ጠረጴዛው ይመጣሉ፡፡

በፊልሙ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ በቀድሞው የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኢል ድፍረትና ጥንካሬ በሥጋትና በጭንቀት ሲነጋገሩ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

ከስብሰባው ይልቅ የስብሰባው ቦታ የሚያጓጓው የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆንግ ኡን ውይይት
የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን የኑክሌር ሙከራ ማስቆማቸው ውጥረት አርግቧል

 

በመጨረሻም ፊልሙ ሌላው አማራጭ ሁሉ አላዋጣ ያላት አሜሪካ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን፣ ‹‹እኩያቸው የሆኑትን›› የሰሜን ኮሪያ መሪ ለመጎብኘት ይመጣሉ፡፡ በዚህም ለሰሜን ኮሪያ ኃያልነትና የኑክሌር አቅም ዕውቅና ይሰጣሉ፡፡

ይህ ፊልም ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር ውይይት ለማድረግ የሚደረገውን ሒደት የምትመለከትበት አንዱ መነጽር ይሆናል ሲል ዋሽንግተን ፖስት አስነብቧል፡፡ ፊልሙ ከሌላ ከፍተኛ የአሜሪካ የሥራ ኃላፊ ይልቅ በፕሬዚዳንት ጉብኝት መደምደሙ፣ ሰሜን ኮሪያ ምን ያህል የኑክሌር ዲፕሎማሲውን እንደምታመልከው ለማየት ያስችላልም የሚል ማጠቃለያ ይሰጣል የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ፡፡

ምንም እንኳን ባለፈው ወር አጋማሽ ላይ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ሊነጋገሩ እንደሆነ ሲገልጹና ሰሜን ኮሪያም የኑክሌር ጦር መሣሪያና የሚሳይል ሙከራዋን ለማቆም መስማማቷ ሲሰማ፣ ይኼ ውይይት ለውጤት ከበቃ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትልቁ ስኬት ሆኖ ይመዘገብላቸዋል ሲባል ተደምጧል፡፡

የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በወጡ መረጃዎች፣ ኪም የሰሜን ኮሪያ ደኅንነት አደጋ ላይ እንደማይወድቅ ዋስትና ከተሰጣቸው የኑክሌር ጦር መሣሪያ ለአገራቸው ያለው አስፈላጊነት እምብዛም እንደሆነ እንደሚያምኑ ተሰምቷል፡፡

ደቡብ ኮሪያ በድንበር ላይ የሰሜኑን ወታደሮች ለመስበክ የምትጠቀምባቸውን በርካታ የድምፅ ማጉያዎች ከተሰቀሉበት ማውረዷ፣ በአካባቢው ያለው ውጥረት እውነትም ሊረግብ ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ከስብሰባው ይልቅ የስብሰባው ቦታ የሚያጓጓው የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆንግ ኡን ውይይት
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር ለመገናኘት ተስማምተዋል

 

ምንም እንኳን ሁለቱ አገሮች ሊገናኙ ነው ቢባልም፣ ሁለቱ መሪዎች በምን ጉዳይ ላይ ሊነጋገሩ እንደሚችሉ ግልጽ የሆነ ነገር የለም ሲል ታይም መጽሔት ጽፏል፡፡

ይሁንና አሁን ሁለቱ አገሮች ከሚነጋገሩበት አጀንዳ ይልቅ የት ተገናኝተው ሊነጋገሩ ይችላሉ የሚለው ሐሳብ ብዙዎችን እያወያየ ነው፡፡ ለዚህም አምስት አማራጮች እንዳሉ ዶናልድ ትራምፕ ገልጸዋል፡፡

ለድርድር አዲስ ያልሆኑትና የሪል ስቴት አልሚ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከማንም በላይ የድርድር ሥፍራን ወሳኝነት በቅጡ ይረዱታልና በቦታው ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡

ዶናልድ ትራምፕና ኪም ጆንግ ኡን ሊገናኙባቸው ይችላሉ የተባሉት የመጀመርያዎቹ ሥፍራዎች የሰሜን ኮሪያዋ ዋና ከተማ ፕዮንግያንግ፣ አልያም ዋሽንግተን ዲሲ ናቸው፡፡ ዋሽንግተን መሆን ካልቻለች እንኳን በዶናልድ ትራምፕ የጎልፍ መጫወቻ ሥፍራ ማር አ ላጎ፣ አለበለዚያም ኒውዮርክ በሚገኘው የትራምፕ ሕንፃ ሊሆን ይችላል፡፡

ይሁንና እነዚህ ሥፍራዎች የሁለቱ መሪዎች መገናኛ ላይሆኑ የሚችሉባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን የአስተናጋጅነትን ሚና ለዶናልድ ትራምፕ መስጠት፣ ገዥ መሬትን አሳልፎ እንደ መስጠት ይቆጥሩታል ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሶቪዬት ሠራሽ የሆኑት የሰሜን ኮሪያ አውሮፕላኖች ይኼንን ያህል ርቀት የመጓዝ አቅም እንደ ሌላቸው በመጥቀስ፣ ኪም ጉዞውን ለማድረግ አዳጋች ስለሚሆንባቸው ግንኙነቱ ዋሽንግተን እንዲሆን እንደማይፈልጉ የሚገልጹ አሉ፡፡ በሌላ አገር አውሮፕላን ቢጠቀሙ ደግሞ፣ የአገራቸውን ገጽታ እንደ ማጥፋት ይቆጥሩታል፡፡

የዶናልድ ትራምፕ በፕዮንግያንግ መገኘት ደግሞ ሰሜን ኮሪያውያን በፊልማቸው ያለሙት እንዲፈጸም መፍቀድ ነው፡፡

ስለዚህ ሌላ አማራጮችን ማየት የግድ ይላል፡፡ ለውይይቱ ምቹ ሥፍራን እኛ ማቅረብ እንችላለን በማለት ትራምፕና ኪም ወደ አገራቸው እንዲመጡ ስዊዘርላንድና ሞንጎሊያ ግብዣቸውን አቅርበዋል፡፡

ሰሜን ኮሪያ ከስዊዘርላንድ ጋር ያላት ግንኙነት እምብዛም ጠንካራ ያለመሆኑና ለአሜሪካ ልታደላ ትችላለች በሚል ምክንያት፣ ሞንጎልያ ሁለቱ መሪዎች ሊገናኙባት ይችላሉ የሚል ተስፋ የተጣለባት አገር ነች፡፡

ምንም እንኳን እንደ አባታቸው በአውሮፕላን የመጓዝ ፍርኃት ባይኖርባቸውም፣ በባቡር ለመጓዝ ለሚመርጡት ኪም ሞንጎሊያ ምቹ አማራጭ ነች፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ሰሜን ኮሪያን በቤጂንግ አድርጎ ከሞንጎሊያ ጋር የሚገናኝ የባቡር መስመር መኖሩ ነው፡፡ ካስፈለገም በሩሲያ በኩል ሊያሳልፍ የሚችል የባቡር መስመር ተዘርግቷል፡፡

ኪም ጆንግ ኡን ከወራት በፊት በቻይና እንዳደረጉት ጉብኝት ባቡር አማራጫቸው ሊሆን ይችላልም ተብሏል፡፡

ሞንጎሊያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላት ግንኙነት ከኮሪያ ጦርነት አስቀድሞ የነበረ ሲሆን፣ ከጦርነቱ በኋላም ከዓለም ሁለተኛ አገር በመሆን ለሰሜን ኮሪያ ዕውቅና የሰጠችው አገር ሞንጎሊያ በመሆኗ፣ የሁለቱን መሪዎች ግንኙነት ለማስተናገድ ሰሜን ኮሪያን የሚቆረቁራት አይሆንም፡፡

ሞንጎሊያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ ስለምትፈልግም፣ በዚህ አጋጣሚ ትኩረት ውስጥ መግባትም ትፈልጋለች፡፡

ሆኖም በአጭር ጊዜ ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቅ የውይይት ቀጠሮ ከ25 እስከ 30 ሰዓታት የሚፈጅ የባቡር ጉዞ አድርጎ፣ የሞንጎሊያ ዋና ከተማ ኡላንባታር መግባት ከፍተኛ ድካም ስለሚኖረው ተመራጭ አይሆንም፡፡

ስለዚህ ቅድሚያ የሚሰጠው አማራጭ በሰሜንና በደቡብ ባሉ ሞክሼ አገሮች መካከል ያለው ከጦርነት ነፃ የተደረገ ቀጣና ነው፡፡ ይኼ ሥፍራ ባራክ ኦባማን ጨምሮ የተለያዩ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የጎበኙት ቢሆንም፣ የዚህ ዓይነት ውይይት ተደርጎበት ግን አያውቅም፡፡

ከስብሰባው ይልቅ የስብሰባው ቦታ የሚያጓጓው የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆንግ ኡን ውይይት
የሰሜን ኮሪያ ኑክሌር ማስወንጨንፊያ ባለስቲክ ሚሳይሎች ሥጋት ሆነው ቆይተዋል