Skip to main content
x
በባለሥልጣናት የውጭ ጉዞ ላይ ተጨማሪ ገደብ የሚጥል ሰርኩላር ተሠራጨ

በባለሥልጣናት የውጭ ጉዞ ላይ ተጨማሪ ገደብ የሚጥል ሰርኩላር ተሠራጨ

ከሳምንታት በፊት በተሠራጨ ሰርኩላር መሠረት በመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎችና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባለሥልጣናት፣ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የውጭ ጉዞ ላይ ገደብ የሚጥል ተጨማሪ ቁጥጥር ወጣ፡፡

በቀድሞ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ተፈርሞ በወጣው ሰርኩላር መሠረት፣ ወደ ውጭ የሚደረጉ ጉዞዎች በጥብቅ ዲሲፕሊን መከናወን ይኖርባቸዋል፡፡

በዚህም መሠረት በመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችና በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ባለሥልጣናት፣ የሥራ ኃላፊዎች፣ ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ዋና ዳይሬክተሮችና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች፣ መካከለኛ አመራሮችና ባለሙያዎች የሚያደርጓቸው የውጭ ጉዞዎች ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ታዟል፡፡

በተጨማሪም የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎችና ምክትሎቻቸው፣ ዋና ሥራ አስኪያጆችና ምክትሎቻቸው፣ ዋና ዳይሬክተሮችና ምክትሎቻቸው፣ መካከለኛ አመራሮችና ባለሙያዎች በዚህ ውስጥ ተካተዋል፡፡

የውጭ አገር ጉዞ ማድረግ ሲያስፈልግ የፕሮግራሙ ዓላማ፣ የተሳታፊ ብዛት፣ የቆይታ ጊዜ፣ ለጉዞ የሚያስፈልገው የወጪ መጠንና የገንዘብ ምንጭ፣ በጉዞው የሚገኘው ጥቅም ሳይቀር በዝርዝር ተገልጾ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቀርቦ ሲፈቀድ ብቻ ጉዞው ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጋር በተያያዘም የጉዞው ጥያቄ መጀመርያ በተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶቻቸው፣ በመቀጠልም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አማካይነት መፅደቅ አለበት፡፡

ከዚህ ቀደም ከወጪ ቅነሳ ጋር በተያያዘ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መመርያ ወጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ መመርያው የውጭ ጉዞ ወጪዎችን የሚመለከቱ ቁጥጥሮችን አካትቶ ነበር፡፡

ነገር ግን ይህ መመርያ ቢወጣም በአግባቡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተግባራዊ እንዳልነበረ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የመንግሥት ኃላፊ አስረድተዋል፡፡

ይኼ ክፍተት ለአሁኑ ሰርኩላር መውጣት ምክንያት ሊሆን ይቻላል ሲሉም አክለዋል፡፡

የውጭ ጉዞን በተመለከተ ከወጣው አዲሱ ሰርኩላር በተጨማሪ ራሱን ችሎ መመርያ ሊወጣ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡