Skip to main content
x
የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ወዲያው ባላቸው ጋ ደወሉ

የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ወዲያው ባላቸው ጋ ደወሉ

[ክቡር ሚኒስትሩ ለደላላ ወዳጃቸው ስልክ ይደውላሉ]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንኳን አደረሰህ ወዳጄ፡፡
 • የምን በዓል አለ ደግሞ?
 • ምን ዓይነት ጥያቄ ነው የምትጠይቀኝ?
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ የሠራተኞች ቀንን ሲያከብሩ ዓይቼ አላውቅም ብዬ ነዋ፡፡
 • በአሽሙር ሠራተኛ አይደለህም እያልከኝ ነው?
 • እውነቱን ካወራንማ እኔና እርስዎ ዘራፊዎች እንጂ ሠራተኞች አይደለንም፡፡
 • ታዲያ ሌሎቹ የሠራተኛ ቀንን ሲያከብሩ እኛም ደግሞ ማክበር አይገባንም?
 • ምንድነው የምናከብረው ክቡር ሚኒስትር?
 • የዘራፊዎችን ቀን ነዋ፡፡
 • መቼም ቀልደኛ ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ቀልዱን ተወውና ቀኑን እንዴት አታስታውሰውም?
 • ልደትዎ ደረሰ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ይላል ይኼ?
 • ታዲያ የምን ቀን ክቡር ሚኒስትር?
 • ሜይ 3 ምን እንደሆነ አታውቅም?
 • የእኔም ልደት አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የፕሬስ ነፃነት የሚከበርበት ቀን ነው፡፡
 • ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን የሚከበርበት ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትሩ አይደለም እንዴ የሚያወሩኝ?
 • ምን ሆነሃል ሰውዬ?
 • ክቡር ሚኒስትር የፕሬስ ነፃነት ነው ያሉኝ?
 • አዎን፣ ምነው?
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ እኮ የሚዲያ ጠላት ነበሩ?
 • አሁን ጊዜው የፍቅር ነው፡፡
 • ይኼን ከእርስዎ መስማት ይገርማል፡፡
 • ስማ የለውጡ ንፋስ አግኝቶኝ ነዋ፡፡
 • ሚዲያ ለአገር አይጠቅም፣ መጥፋት አለበት ብለው እኮ ሲሟገቱ የነበሩ ሰው ነዎት?
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ስለሚዲያው ያወሩትን አልሰማህም እንዴ?
 • ምን አሉ?
 • የአገሪቷ ሚዲያ ሊጠናከር ይገባዋል እያሉ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ነበር፡፡
 • ይህ እኮ ታዲያ ለእኛ መጥፎ ዜና ነው፡፡
 • ለምን ተብሎ?
 • ሚዲያው ነፃና ጠንካራ በሆነ ቁጥር ለእኛ የእግር እሳት መሆኑ አይቀርማ፡፡
 • ሁልጊዜ እንደ ነጋዴ ነው ማሰብ ያለብህ፡፡
 • ምን እያሉኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ሚዲያ ነፃ ሆኖ ይጠናከር ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?
 • ምን ማለት ነው?
 • ለሚዲያው የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ይደረጋል ማለት ነው፡፡
 • አይ እርስዎ!
 • ስለዚህ የሚዲያ ተቋማት በማበረታቻነት በነፃ የሚያስገቧቸው ዕቃዎች ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡
 • ስለዚህ ምን እናድርግ?
 • በአስቸኳይ ማማረጥ አለብን፡፡
 • ምኑን ነው የምናማርጠው?
 • ከጋዜጣ፣ ከቲቪና ከሬዲዮ ነዋ፡፡
 • ምን ለማድረግ?
 • ለማቋቋም ነዋ፡፡
 • ምንድነው የምናቋቁመው?
 • የራሳችንን ሚዲያ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሙያ ይደውልላቸዋል]

 • ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ዛሬ እንዴት ደወልክልኝ?
 • አንድ ጥናት እየሠራሁ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የምን ጥናት ነው?
 • በአገሪቷ ስላለው ችግር ጥናት እያደረግኩ ነበር፡፡
 • እኔ ጋ የደወልከው የአገሪቷን ችግር መንስዔ ሆኜ ነው?
 • ኧረ አልወጣኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ምን ፈልገህ ነው የደወልከው?
 • ያው ስለጥናቱ ለመነጋገር ብዬ ነው፡፡
 • ምንድነው የምንነጋገረው?
 • የአገሪቷ ችግር እጅግ ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ነው፡፡
 • እሱማ የአገሪቷን ችግር የሚፈታ ከጠፋ ሰነባበተ፡፡
 • አሁን ግን አገሪቷ ተስፋ ያላት ይመስለኛል፡፡
 • እንደዚህ ለምን አልክ?
 • ያው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሕዝቡ ላይ ተስፋ ዘርተውበታል፡፡
 • ተስፋው ተዘርቶ ካልታጨደ ምን ይጠቅማል?
 • ክቡር ሚኒስትር የአገሪቷን ችግር እኮ አንድ ሰው ሊፈታው አይችልም፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • አዲሱ ተስፋ ሊታጨድ የሚችለው ከላይ ወደ ታች ከወረደ ነው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ከላይ ካሉት ባለሥልጣናት ይልቅ ሕዝቡን ማግኘት የሚችሉት ከታች የተቀመጡት ስለሆነ ነዋ፡፡
 • ከላይ ያላችሁት ምንም አትጠቅሙም እያልከኝ ነው?
 • ኧረ አልወጣኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ምንድነው የምትለው?
 • ከእናንተ ይልቅ ቀን በቀን ሕዝቡን የሚያገኙት ከታች ያሉት አመራሮች ናቸው፡፡
 • እነሱ አይደል እንዴ ሕዝቡን እያማረሩት ያሉት?
 • ለዚያ ነው እነሱ ላይ በሚገባ መሠራት ያለበት፡፡
 • ምንድነው የምንሠራው?
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያወሩትን ከታች ያለው ሰው ካልተገበረው፣ ውኃ ቢወቅጡት እምቦጭ ነው የሚሆነው፡፡
 • እሱስ ልክ ነህ፡፡
 • አንድ ገበሬ ዳመና ስለመጣ ብቻ ፍሬ ሊያገኝ አይችልም፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ገበሬው ፍሬ የሚያገኘው ከላይ የታየው ዳመና ወደ ምድር ዝናብ ሆኖ ከመጣ ብቻ ነው፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው ታዲያ?
 • የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር እንደ ዳመና ብናየው፣ ታች ያለው መዋቅር ውስጥ ካልወረደ ፍሬ አልባ ነው እያልኩዎት ነው፡፡
 • ተፈላሳፊ ነህ ልበል?
 • እየተፈላሰፍኩ ሳይሆን፣ የታየኝን እየነገርኩዎት ነው፡፡
 • አሁን ዳመና ብቻ ነው የታየው እያልከኝ ነው?
 • ወደታች ካልዘነበ ከንቱ ልፋት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን እያልክ ነው ታዲያ?
 • ከታች ካለው አመራር ጋር በአስቸኳይ ማወራረድ አለባችሁ፡፡
 • ምኑን ነው የምናወራርደው?
 • ሐሳቡን!

[አንድ ባለጉዳይ ወደ ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ለመግባት ከጸሐፊያቸው ጋር እያወራ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትሩን ፈልጌ ነበር፡፡
 • ቀጠሮ አለህ?
 • የምን ቀጠሮ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትሩ ጋር ለመግባት ነዋ፡፡
 • ያለቀጠሮ መግባት አልችልም?
 • እዚህ ቢሮ ለሁለት ዓመት ተመላልሰህ እንዴት ይኼን አታውቅም?
 • ለሁለት ዓመት እኮ አግኝቻቸው አላውቅም፡፡
 • ታዲያ ዛሬ እንደምታገኛቸው ምን እርግጠኛ አደረገህ?
 • አሠራራችሁ ተቀይሯል ስለተባለ ነዋ፡፡
 • የምን አሠራር ነው የተቀየረው?
 • በፊት ክቡር ሚኒስትር የሚሰጡት ምክንያት ጥቅም አልባ ተደርጓል ብዬ ነዋ፡፡
 • ምን እያልክ ነው ሰውዬ?
 • ሁሌ ስመጣ ወይ ከአገር ውጭ ናቸው ወይም ስብሰባ ላይ ናቸው፡፡
 • አሁን ስብሰባ ላይ አለመሆናቸውን በምን አወቅክ?
 • ስብሰባ ከሥራ ሰዓት በኋላ ይካሄድ ተብሏል እኮ?
 • ቀጠሮ ከሌለህ ግን ክቡር ሚኒስትሩ ጋ ዝም ብሎ አይገባም፡፡
 • ያማ በድሮ ሥርዓት ቀረ፡፡
 • ወይ ጉድ?
 • መቼም አንቺ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ አይደለሽም?
 • ምን እያልከኝ ነው ታዲያ?
 • ገብተሽ ንገሪያቸው፡፡
 • እሺ፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]

 • ባለጉዳይ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ዛሬ እኮ ቀጠሮ የለኝም፡፡
 • ባለጉዳዩ ካልገባሁ እያለ ነው፡፡
 • እኔን ያለቀጠሮ ማናገር እንደማይቻል ንገሪው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ላለፉት ሁለት ዓመታት የተመላለሰ ሰው ነው፡፡
 • ገና ሌላ ተጨማሪ ዓመታት ይመላለሳል፡፡
 • እንደዚያ እንኳን ማድረግ የምንችል አልመሰለኝም፡፡
 • አንድ ምክንያት ስጪው፡፡
 • ምክንያቶች መስጠት እንደማንችል የሚያውቅ ሰው ስለሆነ ቢያናግሩት ይሻላል፡፡
 • እሺ አስገቢው፡፡

[ባለጉዳዩ ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገባ]

 • ያለቀጠሮ እኔን ማናገር አትችልም እኮ?
 • ክቡር ሚኒስትር የመጣሁት እኮ ጉዳይ ኖሮኝ ነው፡፡
 • ቢሆንም ቀጠሮ ያስፈልግሃል፡፡
 • እዚህ የተቀመጡት ሕዝብ ሊያገለግሉ መስሎኝ?
 • እሱን አንተ አትነግረኝም፡፡
 • ስለዚህ ጉዳዬን ያዳምጡ፡፡
 • የአንተን ጉዳይ አሁን ላዳምጥ አልችልም፡፡
 • ለምንድነው የማያዳምጡት?
 • ስብሰባ አለኝ፡፡
 • የምን ስብሰባ?
 • ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስብሰባ አለኝ፡፡
 • ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋርማ በሥራ ሰዓት እንደማይሰበሰቡ አውቃለሁ፡፡
 • ሰውዬ አንተ እኔን ልትቆጣጠረኝ አትችልም፡፡
 • ወዴት ሊሄዱ ነው አሁን?
 • ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋ አልኩህ?
 • እንግዲያው እኔም ሪፖርት ላደርግ እሄዳለሁ፡፡
 • ወዴት?
 • ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ!

[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ወደ ውጭ ሊወጡ ሲሉ ኤርፖርት ላይ ተከለከሉ]

 • መውጣት አይችሉም እመቤቴ፡፡
 • ምን?
 • ከአገር መውጣት አይችሉም፡፡
 • ቪዛ እኮ አለኝ፡፡
 • ቪዛ ቢኖርዎትም ከአገር መውጣት አይችሉም፡፡
 • ለምን ተብሎ?
 • ከበላይ ነው የተላለፈልኝ፡፡
 • ማን እንደሆንኩ አውቀሃል?
 • አላወኩም እመቤት፡፡
 • የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ነኝ፡፡
 • ቢሆኑም አይወጡም!

[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ወዲያው ባላቸው ጋ ደወሉ]

 • ስማ በተከበርኩበት አገር ልዋረድ?
 • ምን ሆንሽ?
 • ከአገር አትወጪም ተባልኩ እኮ?
 • ማን ነው ያለሽ?
 • የቁም እስረኛ ተደርጌያለሁ፡፡
 • ማን ነው ያሰረሽ?
 • አንተ እያለህ እንዴት ይህ ይፈጸምብኛል?
 • ምንድነው የሆንሽው?
 • ከአገር አትወጪም ተባልኩ፡፡
 • ለምንድነው የማትወጪው?
 • ሊስት ውስጥ አለሽ ተብዬ ነዋ፡፡
 • ምን ላድርግልሽ ታዲያ?
 • በአስቸኳይ ከአገር እንድወጣ አስደርገኝ፡፡
 • እሱንማ ማድረግ አልችልም፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • መመርያ ከተላለፈ ምንም ማድረግ አልችልም፡፡
 • እና እኔ ከአገር አልውጣ?
 • የአንቺ ከአገር አትውጪ መባል ይገርምሻል እንዴ?
 • ለምን አይገርመኝም?
 • እኔ ከየት እንዳልወጣ እንደተከለከልኩ ታውቂያለሽ?
 • ከየት አትውጣ ተባልክ?
 • ከቢሮ!