Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው

ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ በጠዋት ከሚስታቸው ጋር ቁርስ እየበሉ ነው]

 • አልበዛም?
 • ምኑ?
 • አሁንስ ሰለቸኝ፡፡
 • ምኑ ነው የሰለቸህ?
 • አንገሸገሸኝ አልኩሽ፡፡
 • እኮ ምኑ ነው ያንገሸገሸህ?
 • ያልገባኝ እኮ አንድ ነገር ነው፡፡
 • ምኑ ነው ያልገባህ?
 • ለምን በግልጽ አትነግሪኝም?
 • ምኑን ነው የምንግርህ?
 • አስጠልተኸኛል ብለሽ በግልጽ ብትነግሪኝ ይሻላል እኮ?
 • ምንድነው የምታወራው?
 • እኔ እንድሞት ነው እንዴ የምትፈልጉት?
 • ማን ነን እኛ?
 • መንግሥት፣ አንቺም፣ ሁላችሁም፡፡
 • ሰውዬ ጤና የለህም እንዴ?
 • እናንተ እያላችሁ እኔ እንዴት ጤና ይኖረኛል?
 • ምንም አልገባኝም፡፡
 • መንግሥት በግምገማ ስኳርና ደሜን ሰቅሎታል፡፡
 • ለእሱማ መድኃኒት እየወሰድክ አይደል እንዴ?
 • መድኃኒቱ ራሱ አልሠራ ካለኝ ስንት ዘመኑ?
 • ታዲያ እኔ ምን ላድርግህ?
 • የመንግሥትን እሺ ተይው፣ አንቺ ደግሞ ሌላ አቃጣይ ሆነሻል፡፡
 • በጠዋቱ የምን ምሬት ነው?
 • ይኸው በጠዋቱ ያቀረብሽልኝ ቁርስ እኮ ለእኔ ጠላት ለመሆንሽ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ይኸው ይኼ ሁሉ በርበሬ ጨጓራዬን መለጠው እኮ?
 • ስማ ይኼንንም ያጣ ብዙ ሰው እንዳለ አትርሳ፡፡
 • አንቺማ ምኞትሽ እኔ በችግር እንድሞት ነው፡፡
 • አሁን ይኼ ፍርፍር ምን ይወጣለታል?
 • አንድ ድፍን ሳምንት ሙሉ ፍርፍር ልብላ?
 • ትናንትና ጨጨብሳ አይደል እንዴ የበላኸው?
 • ያው ነው፣ ቂጣ ተፈረፈረ እንጀራ ተፈረፈረ፣ ፍርፍር ፍርፍር ነው፡፡
 • ከመቼ ጀምሮ ያመጣኸው ባህሪ ነው? አንተ ለምግብ ግድ ኖሮህ አያውቅ?
 • ከአሁን በኋላ ግድ ይሰጠኛል፣ ሐኪም አስጠንቅቆኛል፡፡
 • ምን ላድርግ ታዲያ እኔ?
 • በርበሬና ጨው የበዛበት ምግብ ተከልክያለሁ አይደል?
 • ምን ይሠራልህ ታዲያ?
 • ምናለበት እንቁላልና ወተት ብትሰጪኝ?
 • ችግሩ አልገባህም?
 • አሁን ቢያንስ ቢያንስ ዳቦ ይጠፋል?
 • ዳቦ ከጠፋ ስንት ጊዜው እንደሆነ አታውቅም፡፡
 • ዳቦ ቢጠፋ እንቁላል ፍርፍር ወይ እንቁላል ቁጭ ቁጭ ማድረግ አቅቶሽ ነው?
 • እንቁላል ለመግዛት ያልዞርኩበት ሱፐርማርኬት የለም፡፡
 • አሁን ጨጓራዬ ስለተቃጠለ ወተት አምጪልኝ፡፡
 • እኔ ገበሬ መሰልኩህ እንዴ?
 • ወተት እኮ ነው የጠየቅኩሽ?
 • ወተትም ቢሆን በከተማው የለም፡፡
 • ለምን ተብሎ?
 • እንግዲህ ዶሮዎቹንና ላሞቹን ምን እንደነካቸው አላውቅም፡፡
 • ዶሮዎቹ እንቁላል ካልሰጡ፣ ላሞቹም ወተት ካልሰጡ የሚበሉትን ምግብ ቀይረዋል ማለት ነው፡፡
 • ምግባቸው ምን ሆነ ልትል ነው ደግሞ?
 • ዶላር!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ሰው ደወለላቸው]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ልበል?
 • በእውነት በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡
 • ለምን?
 • የእርስዎን ቁጥር ለማግኘት ያልገባሁበት ቦታ የለም፡፡
 • ማን ነህ አንተ?
 • እኔን እንኳን አያውቁኝም፡፡
 • ምን ፈልገህ ነው?
 • ከፍተኛ በደል ነው የደረሰብኝ፡፡
 • የምን በደል?
 • ክቡር ሚኒስትር በደረሰብኝ በደል በጣም አዝኛለሁ፡፡
 • እኮ ምን ሆንክ?
 • ይኸው እርስዎ ጋ የደወልኩት የደረሰብኝን ለማሰማት ነው፡፡
 • ምንድነው የደረሰብህ ነገር?
 • ከዛቻ ዛቻ፣ ዱላም ቢሆን ቦክስ የቀመስኩ ሰው ነኝ፡፡
 • የምን ዛቻና ቦክስ ነው?
 • ይኸው በየሳምንቱ ኑሮዬ ዛቻና ቦክስ ሆኗል፡፡
 • ምንድነው የምታወራው?
 • በቃ እኔ ሥራዬን ተረጋግቼ መሥራት አልቻልኩም፡፡
 • የምን ሥራ ነው?
 • ከአሁን አሁን ሞቼ ልጆቼ ሊበተኑ ነው እያልኩ እየሠጋሁ ነው፡፡
 • በአገሪቷ ሕግ አለ አይደል እንዴ?
 • እኔማ በአገሪቷ ሕግ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡
 • እንዴት ነው ሕግ የሌለው?
 • ይኸው በተደጋጋሚ የደረሰብኝን ዛቻና ድብደባ ባመለክትም የሚሰማኝ አጣሁ፡፡
 • ለመሆኑ ይኼ ሁላ ዛቻና ድብደባ ለምንድነው የሚደርስብህ?
 • እኔማ በሙያዬ ሕዝቡን አገልግላለሁ ብልም፣ በየቅዳሜውና በየእሑዱ መፈንከት ሆኗል ዕጣዬ፡፡
 • ታዲያ እኔ ምን ልርዳህ?
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎን የምጠይቅዎት አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • እኔ በሙያዬ እንዴት ነው መቀጠል የምችለው?
 • ማንም ሰው በሚወደው ሙያ አገሩን ማገልገል ይችላል፡፡
 • እኔ ግን ሕዝብን ባገለገልኩ መፈንከትና ዛቻ ሆኗል ደመወዜ፡፡
 • ለመሆኑ በየጊዜው የሚያስፈነክትህ ሙያ ምን ይሆን?
 • እኔማ ዳኛ ነኝ፡፡
 • የዳኞችን ችግርማ ስለተረዳነው በአፋጣኝ መፍትሔ ይሰጠዋል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሁሌም እንደዚህ እኮ ነው የምንባለው፡፡
 • የአሁኑማ ለየት እንዳለ እኔ ራሴ በቲቪ ተመልክቸዋለሁ፡፡
 • ድብድቡ በቲቪ ተላልፏል እንዴ?
 • ሚዲያዎች ሁሉ የዳኛውን መደብደብ ሲያስተላልፉ አልነበር እንዴ?
 • ስለምንድነው የሚያወሩት ክቡር ሚኒስትር?
 • ስለእግር ኳስ ዳኛው ነዋ፡፡
 • እኔ እኮ የእግር ኳስ ዳኛ አይደለሁም፡፡
 • ምን?
 • በሙያ መመሳሰል ነው በየሳምንቱ የምቀጠቀጠው፡፡
 • አንተ የምን ዳኛ ነህ?
 • የዕቁብ ዳኛ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር እኔ በጣም እየተጨናነቅኩ ነው፡፡
 • ምን ሆነህ?
 • በቃ ሥራ መሥራት አልቻልኩም፡፡
 • እኮ ምን ሆነህ?
 • እንደምታዩት ከተማ ውስጥ ምንም እንቅስቃሴ የለም፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ምንም ዕቃ ኢምፖርት ማድረግ አልቻልንም፣ በዚያ ላይ ሁሉ ነገር ተቀዛቅዟል፡፡
 • ሁሉ ነገር ስትል?
 • በቃ የመሬቱም ገበያ ቀዝቅዟል፣ ቤትም የሚገዛ ጠፍቷል፣ ብቻ ሁሉ ነገር ደስ አይልም፡፡
 • አንተ ደግሞ ቶሎ ነው ተስፋ የምትቆርጠው፡፡
 • አገሪቷ እኮ አውቶ ፓይለት ላይ ነው ያለችው፡፡
 • ምን ማለት ነው እሱ?
 • ዝም ብላ ያለ መሪ ነዋ እየሄደች ያለችው፡፡
 • አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በቅርቡ አይደል እንዴ የተሾመላት?
 • እሱ አይደል እንዴ ችግሩ?
 • የምን ችግር አመጣህ ደግሞ?
 • በቃ ሁሉ ነገር ተቆላልፎ እንዴት እንንቀሳቀስ?
 • ማን ነው የቆላለፈው?
 • እውነት እናውራ ከተባለ ክቡር ሚኒስትር፣ እኔና እርስዎ ያለ ሌብነት ምን እንችላለን?
 • እ…
 • በየቀኑ እየተሳቀቅኩ መኖርም አልቻልኩም፡፡
 • አንዳንዴ ሞኝ ነህ ልበል?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ካፊያ ነው ብለህ ከቤት ላትወጣ ነው እንዴ?
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አሁን ያለው ካፊያ ነው፣ ዣንጥላ ይዘህ መውጣት ነው ዋናው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ግን የመጣብን ጠራርጎ የሚወስድ ነው ባይ ነኝ፡፡
 • ዝም ብለህ አትሞቦቅቦቅ፡፡
 • እኔ ግን ድርሻዬን ሰጥተውኝ ብንለያይ ባይ ነኝ፡፡
 • ምን አልክ?
 • እኔ ሁኔታው ስላላማረኝ ከአገር ብወጣ ይሻላል፡፡
 • ለምንድነው የምትወጣው?
 • እዚህ ለእኛ ምንም ተስፋ እየታየኝ አይደለም፡፡
 • ለምን ተስፋ የለንም?
 • ሁሉም ሥራችን እኮ መስመሩን ያልፋል፡፡
 • የምን መስመር?
 • የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቀይ መስመር ነዋ፡፡
 • ታዲያ ምን ችግር አለው?
 • እንዴት የለውም ክቡር ሚኒስትር?
 • በሌሎች መስመሮች መጫወት እንችላለን፡፡
 • አልገባኝም?
 • ለምሳሌ አረንጓዴ መስመር አልተከለከለም፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • የጫት ንግድ ውስጥ መግባት እንችላለን፡፡
 • አይ ክቡር ሚኒስትር?
 • ከእሱ ይልቅ ግን ለእኛ የሚያዋጣን ሌላ መስመር ነው፡፡
 • የትኛው መስመር?
 • ጥቁሩ መስመር፡፡
 • እሱ ደግሞ ምንድነው?
 • በአፋጣኝ እሱን መጀመር አለብን፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ጥቁር ገበያ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር የእርስዎ ነገር ግራ እያጋባኝ ነው፡፡
 • ምኑ ነው ግራ የሚያጋባው?
 • አገር በአንድነት እየዘመረ እርስዎ ለምን እእንደሚያፈነግጡ አይገባኝም?
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • ሰው አገሬ አገሬ ሲል፣ እርስዎ እኔ እኔ እያሉ ነው፡፡
 • ተረቱን አታውቀውም እንዴ?
 • የትኛውን ተረት?
 • ከራስ በላይ ንፋስ የሚለውን ነዋ፡፡
 • እኔ እንኳን ያስታወስኩት ያችን አህያ ነው፡፡
 • የትኛዋን አህያ?
 • እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ያለችውን አህያ ነዋ፡፡
 • ሰውዬ እየተሳደብክ እኮ ነው? ብንከባበር አይሻልም?
 • ስንተዋወቅ አንተናነቅ አሉ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • እርስዎ አሁን እየፈጠሩት ያለው ችግር አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳይሠሩ ለማድረግ ነው፡፡
 • ታዲያ የማን ሥራ ቆሞ የማን ይቀራል?
 • እሱማ የእርስዎ ዋነኛ ሥራ ሌብነት መሆኑ ይታወቃል፡፡
 • እኔ ብሰርቅ እኮ መልሼ አገሬን ነው የማለማው፡፡
 • ትንሽ እንኳን አያፍሩም ክቡር ሚኒስትር?
 • አገሬን ማልማት ምን ያሳፍራል?
 • አገር በስርቆት አይለማም፡፡
 • ለመሆኑ ምን አጠፋህ ነው የምትለኝ?
 • በየካቢኔ ስብሰባው የሚፈጥሩት ችግር ለምን እንደሆነ ተደርሶበታል፡፡
 • አሁንም እቀጥልበታለሁ፡፡
 • እኔ ግን ከዚህ አፍራሽ ተግባርዎ እንዲቆጠቡ እመክርዎታለሁ፡፡
 • እያስፈራራኸኝ መሆኑ ነው?
 • ይህን አፍራሽ ተግባርዎን ከቀጠሉበት እኛም የዘጋነውን እስር ቤት መክፈታችን አይቀርም፡፡
 • የትኛውን እስር ቤት?
 • ማዕከላዊን!