Skip to main content
x
ሴት ከዘር ምንጭነት እስከ እውነት አረጋጋጭነት በድራሼ
ድራሼዋ በቡና ለቀማ

ሴት ከዘር ምንጭነት እስከ እውነት አረጋጋጭነት በድራሼ

በዕለተ ሰንበቱ በዓለም ዙሪያ የእናቶች ቀን እየተከበረ ይገኛል፡፡ በዓሉ እናቶችን፣ እናትነትን፣ ወላጅነትና እናቶች ለማኅበረሰቡ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የሚዘከርበት ነው፡፡ በየዓመቱ የሜይ ወር ሁለተኛ እሑድ የሚከበረው የእናቶች ቀን፣ ዘንድሮ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ግንቦት 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ላይ ውሏል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓሉ በኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱ ይታወቃል፣ ምንም እንኳን ብሂል ከባህል አዛምዶ ከአገሬው ጓዳ ጨልፎ በማቅረብ ረገድ ክፍተት ቢኖርም፡፡

ሴቶች ከእናትነት ባለፈ ለማኅበረሰቡ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በየደርዙ፣ በየዘርፉ ይኖራል፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኘው የድራሼ ብሔረሰብ ለዕለት ጉርስ፣ ለዓመት ልብስ ለሚያስፈልገው ሁሉ ነገር የዘር ምንጭ ሴት ናት ተብሎ ይታመናል፡፡

የሕግ ባለሙያና የተለያዩ ብሔረሰቦች ባህላዊ ሕጎችን ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን ያጠኑት አቶ አብዱልፈታህ አብደላህ በድርሳናቸው እንደገለጹት፣ በድራሼ ባህል ሴት ልጅ የማንኛውም ዘር ምንጭ ናት፡፡ ለዘር የሚሆነውን እህል የምታስቀምጠው፣ በሚዘራበት ወቅት ካለበት አውጥታ፣ አዘጋጅታ መስጠት ያለባት ሴት ናት፡፡ አለበለዚያ ዘሩ የተባረከ አይሆንም፡፡ በዚህም ምክንያት ድንገት ባልና ሚስት ተጣልተው ሚስት ወደ ቤተሰቦችዋ በተመለሰችበት ወቅት የዘር መዝራት ጊዜ ቢደርስ ባል የገባበት ገብቶ፣ የሚከፍለውን መስዋዕትነት ከፍሎ ታርቆ እንድትመለስ የማድረግ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ ይህንን ሳያደርግ ቢቀር የተረገመ፣ የተወገዘ፣ ዘሩም ያልተባረከ ይሆናል፡፡ እንደዚሁም ጋብቻው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደፈረሰ ይቆጠራል:: ከዚህ በኋላ እርቅ ብሎ ነገር አይኖርም፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ቢሆንም ዘሩን እሱ ወስዶ መዝራት አይገባውም፡፡ ሌሎች የቅርብ ሴቶች እንዲያወጡለትና እንዲያዘጋጁለት አድርጎ ነው የሚዘራው፡፡

 እንደ አቶ አብዱል ፈታህ አገላለጽ፣ የድራሼዎች ትውፊት የሚያመለክተው ሴት ልጅ ምን ያህል የተከበረችና የተወደደች መሆንዋን ነው፡፡ የዘር ምንጭ መሆንዋ ታምኖ፣ ተረጋግጦ፣ የማንኛውም ዘር በረከት በእሷ እጅ መሆኑን ተቀብሎ ለእርሷ ዕውቅናና ክብር መስጠት መቻል ትልቅ ዋጋ ያለው እሴት ነው፡፡ በቅርቡ ባሳተሙት ‹‹የድራሼ ወረዳ ሕዝቦች የባህል ሕግ ሥርዓት›› መጽሐፍ እንዳመለከቱት ሴት ልጅ የእውነት ማረጋገጫ ናት፡፡

እንደእሳቸው ማብራሪያ፣ ሰዎች እያወሩ ወይም እየተከራከሩ ካልተማመኑ አንዳቸው በመጀመርያ እህታቸው ስም ከማለ ሰውዬው እውነት እንደተናገረ ይቆጠራል፡፡ ማንም ሰው በእህቱ በተለይም በመጀመርያ እህቱ ስም በውሸት አይምልም ተብሎ ይታመናል፡፡ ምክንያቱም የመጀመርያ እህት የምትከበር፣ የቅድስናና የንፅህና ምልክት ናት፡፡ በእርሷ ስም በውሸት መማል ከፍተኛ ዳውራ (ነውርና ኃጢያት የሚያስከትል) ጉዳይ ነው፡፡ ኃጢያቱም ዘር ማንዘርን ሊያመነምንና ሊያጠፋ የሚችል ይሆናል ተብሎ ይፈራል፡፡

በሌላ ባህላዊ ገጽታ በማናቸውም ባህላዊ በዓላት ወቅት ሴት ከሌለች በዓሉ በዓል አይሆንም፡፡ ባልና ሚስት ድንገት ተጣልተው በተለያዩበት አጋጣሚ በዓል ቢደርስ አሁንም ባል ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አድርጎ፣ እግሯን ስሞ፣ ድንጋይ ተሸክሞ የማስመለስ ሸክሙ በእርሱ ላይ ተጥሏል፡፡ ሸክሙን የመወጣት ግዴታ ከፍተኛ ነው፡፡ ያንን ካላደረገ ጋብቻው ለዘለዓለሙ እንደተቋረጠ ይቆጠራል፡፡ ጋብቻን መፍታት ማለት ደግሞ በባህሉ የመጨረሻ ክፉ ተግባርና ሥራ ነው፡፡

በድራሼ ባህል የባልና ሚስት ፀብና ጭቅጭቅ የማይፈለግና የተጣላ ተግባር መሆኑን የሚያወሱት አቶ አብዱልፈታህ፣ በተለይም ደግሞ ሕፃናት እየሰሙና እያዩ ከሆነ ደግሞ ፍጹም ክልክል የሆነ ተግባር ነው ይላሉ፡፡ ‹‹የባልና ሚስት ፀብና ጥላቻ እርግማንን ወደ ቤት ስቦ ወይም ጠርቶ ያስገባል፡፡ ልጅ እንዲሞት፣ ሀብት ንብረት፣ በረከት ከቤታችን እንዲጠፋ የመሳሰሉት ችግሮች እንዲፈጠሩ ያደርጋል፤›› ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለሆነም ባልና ሚስት ላለመጣላት፣ ላለመጣላላት እጅጉን ጥንቃቄ ሲያደርጉ ይኖራሉ፡፡ አላስችል ያላቸው ነገር እንኳ ቢገጥማቸው በልጆቹ ፊት እንዳይጨቃጨቁና ንትርክ ውስጥ እንዳይገቡ ባህሉ ያስገድዳቸዋል፡፡

 ‹‹ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት›› እንዲሉ በድራሼዎች ኅልፈት ካጋጠመ አክስት ሳታጥብ አስክሬን አይቀበርም፡፡ እንደ መጽሐፉ አገላለጽ አንድ ሰው ሲሞት አክስት መጥታ አስከሬኑን ማጠብ አለባት፡፡ ከሩቅ አካባቢ ብትሆንም እስክትደርስ ይጠበቃል፡፡ አክስት ከሌለችም እንደ አክስት የምትቀርብ ሌላ ሴት አስከሬኑን ታጥባለች፡፡ ቁም ነገሩ የአክስት (የሴት) እጅ ቅዱስ መሆኑን ያመለክታል፡፡

እንደ አዘጋጁ አተረጓጐም ‹‹አጎት አልተባለም፡፡ ሌሎች ወንዶች አልተጠቀሱም፡፡ አክስት እንድታጥብ የተመረጠበት ምክንያት ብዙ ነው፡፡ ሴት ልጅ አዛኝ፣ ሩኅሩኅ፣ ቅን፣ የቤተሰቦችዋን ገበና የምትሸፍን፣ አስተማሪ፣ ቅዱስና የመሳሰሉት ባህሪያት ባለቤት ናት ተብሎ ስለሚታመን እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡››

ሌላው የድራሼዎች ትውፊት ከሦስት ጉልቻ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሙሽሪት ወደ ሙሽራው ቤት የምትመጣው እህት ስትፈቅድለት መሆኑ ይገለጻል፡፡ በመጽሐፉ እንደተጠቆመው፣ በጋብቻ ጊዜ ሙሽራው ቤት ከመግባቷ በፊት በሙሽራው በተመረጠ ዘመድ ቤት ተቀምጣ እንድትቀለብ፣ እንድታርፍና እንክብካቤ እንዲደረግላት ይደረጋል፡፡ ይህም ሥርዓት ‹‹ቆሮማት›› ተብሎ ይታወቃል፡፡ ‹‹ማን - ቆሮማት›› የምትዝናናበት ቤትን ያመለክታል፡፡ የመዝናናቱ ሒደት ከሦስት እስከ ስድስት ወር ሊወስድ ይችላል፡፡ ዓላማው ሙሽሪት በቂ ሥነ ምግባር፣ አካላዊ የትዳር ዝግጅት እንዲኖራት ማድረግ ነው፡፡ አንድ ሙሽሪት የቆርማት ሒደቷን ጨርሳ ወደ ሙሽራው ቤት እንድትገባ ለማድረግ አንድ ክንውን መደረግ ይኖርበታል፡፡ እሱም የወንዱ ወይም የቤተሰቡ የመጀመርያ ሴት ልጅ (እህቱ) ወደ ሙሽሪት ወደ ምትቀለብበት ቤት ሄዳ ቅቤ መቀባት ይኖርባታል፡፡ ይህ ሥነ ሥርዓት ሳይፈጸም ሙሽሪት ወደ ሙሽራው ቤት ልትመጣ አትችልም፡፡ ያለ እህት ቡራኬ ሙሽሪት ብትመጣ መካን ልትሆን ትችላለች፤ ብትወልድም ጤነኛ ልጅ ላይሆን ይችላል፡፡ ሳያድግና ለወግ ማዕረግ ሳይበቃ ባይሞትም  የረባ ሰው አይሆንም ተብሎ ይፈራልና፡፡ 

ስለሆነም ወንድም እህቱን በእንክብካቤ መያዝ አለበት፡፡ ድንገት በተጣሉ ጊዜ ጋብቻው ቢፈጸም አንድም ለምኖና ታርቆ ሥርዓቱን ያስፈጽማል እንጂ፣ ጋብቻው አይፈጸምም፡፡ ጋብቻው በእህት (በሴት) እንዲባረክ ለምን ተደረገ? የእህት (የሴት) ቅዱስነት፣ የዘር ምንጭነትና ክቡርነት መልሶ መላልሶ ይታወስበታል ሲሉም ይገልጹታል፡፡

በድራሼ ሴት ልጅ የዘር ምንጭ፣ የእውነት ምልክት፣ ቅዱስና ክቡር መሆንዋን የባህል ሕግ ሥርዓት ያስታውቃል፡፡ እነዚህን ታላላቅ የባህል ሕግ ሥርዓቱ እሴቶች ይዞ፣ አልምቶና አሳድጎ መጠቀም የአገር፣ የሕዝብና፣ የመንግሥት ኃላፊነት ተግባር መሆኑን የአቶ አብዱል ፈታህ መጽሐፍ ያሳስባል፡፡

የድራሼ ሴቶች በተለያዩ የሥራ ወቅቶች በጋራ የሚሠሩበት አንዱ ማኅበራዊ ተቋማቸው ካላ ይባላል፡፡ የካላ ስብሰብ አባላት ብዛት ከ10 እስከ 30 ሴት ወጣቶች የሚሳተፉበት ሲሆን፣ የቡድን መሪዋ የማዕረግ ስም ‹‹ካዳይት›› ነው፡፡ 

እንደ ድርሳኑ ማብራሪያ፣ ቡድኑ እስከ ጋብቻ ዘመን ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ የቡድኑ አባላት የራሳቸውን ሥራዎች፣ እንደዚሁም በተመጣጣኝ ክፍያ የሌሎችንም ሥራዎች ይሠሩበታል፡፡ በተለይም በአረም ወቅት ተራ በተራ ማሳቸውን ያርሙታል፡፡ ‹‹ማሳቸውን ለማረም ጉልበታቸውን እንደሚያስተባብሩ ሁሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስንክ ሳሮቻቸውንም ለማረም ካላን እንዲጠቀሙ ብናስችል፣ ብናግዝ፣ ብንመራ፣ ብናስተባብር፣ ብዙ ለውጥ ማስመዝገብ ይቻለናል፤›› ሲሉ አዘጋጁ ያሳስባሉ፡፡