Skip to main content
x
ተሰናባቹ የእናት ባንክ ቦርድና አዲሱ አመራር ርክክብ ፈጸሙ

ተሰናባቹ የእናት ባንክ ቦርድና አዲሱ አመራር ርክክብ ፈጸሙ

እናት ባንክን ለማቋቋም መንቀሳቀስ የጀመሩት መሥራቾች ውጥናቸው የተጀመረው ከአሥር ዓመታት በፊት ነበር፡፡ በአሥር እንስቶች ዋና አደራጅነትም ባንኩን የማቋቋም ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ለባንኩ ምሥረታ የሚያስፈልገው 75 ሚሊዮን ብር በአክሲዮን ሽያጭ አማካይነት ከተሟላ በኋላ፣ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቶ ባንኩ ሥራ ከጀመረ ስድስተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡

ሴቶችን ማዕከል ያደረገ የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ታስቦ የተመሠረተውን እናት ባንክን፣ በቦርድ ሊቀመንበርነት የመሩት የመጀመርያዋ እንስት  ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ናቸው፡፡ እርሳቸው ይመሩት በነበረው ቦርድ ውስጥ ሰባት ሴቶችና አምስት ወንዶች አባላት ነበሩ፡፡

የባንኩ መሥራች የቦርድ ሊቀመንበርና አባላቱ የሁለት ጊዜ የምርጫ ዘመን ቆይታቸውን አጠናቀው ለአዲሱ ቦርድ አስረክበዋል፡፡ የእናት ባንክ ባለውለታ እየተባሉ የተሞካሹት የመጀመርያዎቹ የቦርድ አባላት ስላከናወኗቸው ሥራዎች ዕውቅና ለመስጠት ግንቦት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ወቅት እንደተጠቀሰው፣ ባንኩ ለደረሰበት ደረጃ ተሰናባቹ ቦርድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

ፕሮግራሙን በማስመልከት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ከበደ፣ ‹‹ከባንኩ የቀድሞ ቦርድ አባላት መካከል አብዛኞቹ የባንኩ መሥራቾች ናቸው፡፡ ላለፉት ዓመታት ባንኩ የተቋቋመለትን ዓላማ መሠረት በማድረግ በታማኝነትና በጠንካራ አመራር ሰጪነት ሠርተዋል፤›› በማለት ስለተሰናባቾቹ አመራሮች ተናግረዋል፡፡ ባንኩን ከትርፋማነት ባሻገር ሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መደላደል በመፍጠር ከባንክ ኢንዱስትሪው የተለየ ሥራ ስለማከናወናቸውም አቶ ወንድወሰን ጠቅሰዋል፡፡

የባንኩን የቢዝነስ ሞዴል በመቅረጽ ጭምር አስተዋጽኦ ያበረከተው የቀድሞው ቦርድ፣ የተዋጣለት አመራር በመስጠትና በማስተግበር ባንኩ በተቃና ጎዳና እንዲጓዝ ማስቻላቸውን በመመስከር ዕውቅና መስጠቱ እንዳስፈለገ ገልጸዋል፡፡ የአዲሱን ቦርድ ሰብሳቢነት የተረከቡት ወ/ሮ ሃና ጥላሁንም ከቀድሞ ቦርድ ብዙ እንደሚማሩ ገልጸው፣ ከቀደሙት የቦርድ አባላት ለወደፊቱም እገዛቸውን አንሻለን ብለዋል፡፡  

ተሰናባችዋ የቦርድ ሊቀመንበር ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በበኩላቸው ባንኩን አሁን ለሚገኝበት ደረጃ ለማብቃት በርካታ ውጣ ውረዶች እንደታለፉ ጠቅሰዋል፡፡ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ደጅ መጥናታቸውን የገለጹት ወ/ሮ መዓዛ፣ በመጨረሻም ውጤታማ ባንክ ለመፍጠር ስለተቻለበት መንገድ አውስተዋል፡፡ ባንኩ የተከተለው ሞዴል ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ማገልገል ሲሆን፣ በሴቶች ላይ ትኩረት ማድረግ የሚለው ግን ለየት ያለ ሞዴል ሆኖ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡

እናት ባንክ ሥራ ከጀመረበት ዓመት ጀምሮ አትራፊ መሆን የቻለ ባንክ በመሆኑ ከሌሎች ባንኮች የተለየ ያደርገዋል ያሉት ወ/ሮ መዓዛ፣ ባንኩ የተቋቋመበትን ዓላማ ከማሳካት አንፃር እንደ ውጤት ሊጻፍ ይችላል በማለት ከተጠቀሱት ውስጥ ባለአክሲዮኖች ካመነጩት አንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል ውስጥ 65 በመቶ የሴቶች ሀብት መሆኑ ነው፡፡ ከባንኩ ሠራተኞች ውስጥ 60 በመቶው ሴቶች እንደሆኑ ወ/ሮ መዓዛ አስታውሰው፣ በከፍተኛ የባንኩ አመራር ውስጥ ካሉት ሠራተኞች ውስጥም 38 በመቶው ሴቶች ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡ የሴት አመራሮችን ቁጥር ወደ 50 በመቶ ለማድረስ ባንኩ ዕቅድ እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡

እናት ባንክ የተለየ ገጽታ እንዲይዝ የተደረገበት ሌላው አሠራር ቅርንጫፎችን ሲከፍት ስያሜያቸውን በሕዝቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስለማበርከታቸው በሚታመንባቸው ሴቶች ባለውለታዎች ማድረጉ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 41 ቅርንጫፎች ያሉት እናት ባንክ፣ ሁሉም በባለውለታ ሴቶች ስም እንዲጠሩ አድርጓል፡፡ ይህም የባንኩ ብራንድ እንደሆነ የጠቀሱት ወ/ሮ መዓዛ፣ እንዲህ ያለው አሠራር በሌሎች ባንኮችም እንዲለመድ ማነሳሳቱን በምሳሌ ጠቅሰዋል፡፡ የተለያዩ ባንኮች ለሴቶች ተበዳሪዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን የጀመሩት ከእናት ባንክ መመሥረትና ለሴቶች ከሚያደርገው እገዛ በመነሳት እንደሆነ ጠቅሰው፣ ባንኮች ሴቶች ላይ ያተኮረ አገልግሎት እንዲሰጡ እናት ባንክ ፈር ቀዳጅ መሆኑም ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡

ባንኩ ከተመሠረተ ጀምሮ ካሉት ጠቅላላ አስቀማጮች ውስጥ 50 በመቶው ሴቶች ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት 200 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች ሲሸጥም አብዛኛውን የገዙት ሴቶች ነበሩ፡፡ ሴት ተበዳሪዎች ያለምንም የብድር ዋስትና ማዝያዣ እንዲበደሩ ማድረጉም ለየት እንደሚያደርው ያምናሉ፡፡ ከባለአክሲዮኖች ትርፍ አምስት በመቶ በመቀነስና ከሌሎች በጎ ፈቃደኞች በዝግ ሒሳብ የተመቀጠን ገንዘብ እንደማስያዣ በመጠቀም 17 ሚሊዮን ብር ማስያዣ ለሌላቸው ሴቶች አበድሯል፡፡

ወ/ሮ መዓዛ በንግግራቸው መቋጫ ወቅት፣ ብሔራዊ ባንክ ማስተካከል ይገባዋል ስላሏቸው ሕጎች ጠቅሰው ነበር፡፡ የፋይናንስ ተቋማት ኢኮኖሚውን ወደፊት ለማራመድ ካላቸው ሚና አንፃር ብሔራዊ ባንክ አስተሳሰቡን በማስፋት ከጊዜው ጋር የሚራመዱ ፖሊሲዎችን ማውጣት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

 ገዥው ባንክ የግሉን ዘርፍ በአጋርነት ሊመለከተው እንደሚገባ የተናገሩት ወ/ሮ መዓዛ፣ ብሔራዊ ባንክ ለለውጥ የሚያግዙ ፖሊሲዎችና መመርያዎች እንዲኖሩትም ጠይቀዋል፡፡ በባንኮችም በኩል ተወዳዳሪነታቸው እንዳለ ሆኖ የማስተማር ሥራዎች መሥራት ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

ባንኮችን በቦርድ ሊቀመንበርነት ከሚመሩት ውስጥ ብቸኛዋ እንስት ወ/ሮ መዓዛ ነበሩ፡፡ ከ18ቱ ባንኮች የቦርድ ሊቀመንበሮች መካከል አሁንም ብቸኛዋ ሴት አዲሷ የእናት ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር ወ/ሮ ሃና ናቸው፡፡ ይህ መወለጥ እንዳለበትና ወደፊትም በባንክ አመራርነት ሚና ውስጥ የሴቶች ቁጥር ሊጨምር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በክብር እንግድነት የተገኙት የኢንሹራንስ ባለሙያው አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ ለተሰናባቾቹ የቦርድ አባላት የዕውቅና ሠርተፊኬት ከሰጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ እናት ባንክ እንዲቋቋም የእርሳቸው እገዛ እንደነበረበት አስታውሰዋል፡፡ በሕብረት ኢንሹራንስ ከሚተዳደሩ ሠራተኞች ውስጥ 50 በመቶው ሴቶች መሆናቸውን በመግለጽም፣ የእናት ባንክ ጉዞ በሴቶች ተሳትፎ እያደገ እንደሚሄድ ጠቁመው፣ የተሰናባቹን ቦርድ ጥንካሬና ተተኪውም ቦርድ በቀደመው ቦርድ አግባብ እንደሚጓዝ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

እናት ባንክ በአሁኑ ወቅት ከ13 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖችን ያቀፈ ሲሆን፣ ከብርሃን ባንክ በመከተል በርካታ ባለአክሲዮኖችን ማፍራት የቻለ የግል ባንክ ነው፡፡