Skip to main content
x
በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ግጭት ላይ የተጠናቀረውን ሪፖርት ለማቅረብ የፓርላማው ጥሪ እየተጠበቀ ነው
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ግጭት ላይ የተጠናቀረውን ሪፖርት ለማቅረብ የፓርላማው ጥሪ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በመስከረም ወር 2010 ዓ.ም. በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ባጋጠመው የዜጎች መፈናቀል ወቅት የተፈጠሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ ያጠናከረውን ሪፖርት ይፋ ለማድረግ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥሪን እየጠበቀ እንደሆነ ዋና ኮሚሽነሩ አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር)  አስታወቁ፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ ይህን ያስታወቁት ሰኞ ግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. የተለያዩ ጉዳዮችን አስመልክተው በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

በሁለቱ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ችግር የተፈናቀሉ ወገኖችን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ለመረዳት ለአራት ወራት ያህል ምርመራ መካሄዱን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ሪፖርቱም ተጠናክሮ ለምክር ቤቱ በጥር ወር መላኩን አስታውሰዋል፡፡

‹‹በምርመራው ወቅት ሰፊ የቆዳ ሽፋን ተካቷል፡፡ ከ1,500 ኪሎ ሜትር በላይ የሸፈነ ሲሆን፣ ከሞያሌ ጫፍ እስከ ምሥራቅ ሐረርጌ ድረስ ከሁለቱም ክልሎች 10 ዞኖች፣ 40 አካባቢ ወረዳዎች የሚገኙ በርካታ ባለጉዳዮች፣ ተጎጂ ቤተሰቦችንና ተፈናቃዮችን አነጋግረናል፤›› በማለት ምርመራው የሸፈነውን የቆዳ ስፋት አመላክተዋል፡፡

ምንም እንኳን ኮሚሽኑ በዚህ ጥናት መሠረት ያገኛቸውን ውጤቶችን አጠናቅሮ ለምክር ቤቱ ቢልክም፣ እስካሁን ግን አቅርቡ ባለመባላቸው አቅርቡ የሚባሉበትን ወቅት እየጠበቁ እንደሆነ በመግለጽ፣ ኮሚሽኑ ሪፖርቶች በወቅቱ አያወጣም የሚለው አስተያየት ተቀባይነት እንደሌለውና ትክልል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹በአጠቃላይ መሠረታዊ የግጭቱ መንስዔና ግጭቱ እንዲባባስ ያደረገበትን ምክንያት አስመልክቶ ተጠያቂነትንና የሕግ የበላይነትን ሊያረጋግጥ በሚያስችል መንገድ ሪፖርቱ ተሠርቶ ለምክር ቤት የተላከው በጥር ወር ነው፡፡ ስለዚህ ምክር ቤቱ አቅርቡ ሲለን እናቀርባለን፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱ አቅርቡ ካላለን ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ ምክር ቤቱ አቅርቡ እስኪለን መጠበቅ አለብን፤›› በማለት በሁለቱ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት የተጠናከረው ሪፖርት ይፋ እንዲሆን፣ የምክር ቤቱ ጥሪ እየተጠበቀ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ዜጎች በየትኛውም ሥፍራ ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸው መከበር አለበት ብሎ እንደሚያምን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ከዚህ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ያካተተ ሪፖርት ለምክር ቤቱ መላካቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ዜጎች በየትኛውም ሥፍራ ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸው መከበር አለበት ብለን አናምናለን፡፡ በተግባር ስንፈትሽ ግን አንዳንድ ቦታዎች ላይ ይህ ሕገ መንግሥታዊ መብት እየተጣሰ እንደሆነ የምርመራ ሪፖርታችን አመላክቷል፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

በሪፖርቱ ላይ ምክር ቤቱ ከተወያየ በኋላ ሰፊ የሆነ ማብራሪያ ለመገናኛ ብዙኃን እንደሚሰጥ ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ ታስረው የሚገኙ ዜጎችን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ደግሞ፣ ‹‹የምናጠናቅረው ሪፖርት ባለመጠናቀቁ በዚህ ወቅት የሪፖርቱን ሁኔታ መግለጽ የሚቻል አይደለም፡፡ ነገር ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢታወጅም ባይታወጅም ኮሚሽኑ መደበኛ ሥራውን የማካሄድ መብት አለው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መሠረት በየአካባቢው ያለውን የእስረኞችና የተጠርጣሪዎች ጉዳይ በተመለከተ ከሰብዓዊ መብት አኳያ ኮሚሽኑ እየተከታተለ እንደሚገኝ፣ ውጤቱንም ሪፖርቱ እንደተጠናቀቀ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

በሶማሌ ክልል በምርመራ ሥራ ላይ የነበሩ የክልሉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ጀማል መሐመድ ላይ ባለፈው ሳምንት በደረሰ ጥቃት፣ የክልሉ መንግሥት ኃላፊዎች እጅ እንዳለበት ዋና ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡  

‹‹በጅግጅጋ ባለው ቅርንጫፋችን የሚሠሩት ኮሚሽነር የምርመራና የክትትል ሥራ ለማከናወን በሚጥሩበት ወቅት ይህ ምርመራ እንዲከናወን ያልፈለጉ አካላት ጥቃት አድርሰውባቸዋል፡፡ በዋናነት ግን ጥሰቱን የፈጸሙት የመንግሥት አካላት ናቸው፡፡ ይህንንም ኮሚሽኑ አውግዞታል፤›› በማለት ስለሁኔታው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አሥር ትልልቅ ተቋማት የኮሚሽኑን ውሳኔ አንቀበልም በማለታቸው ኮሚሽኑ ለምክር ቤቱ ባለፈው ሳምንት በጻፈው ደብዳቤ ማሳወቁን ገልጸው፣ እነዚህ ተቋማት ለሕግ ተገዥ የማይሆኑ ከሆነ ለምክር ቤት ከማሳወቅ ባለፈ በመገናኛ ብዙኃን የተቋማቱ ማንነት ይፋ እንደሚያደርጉ ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡