Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ከስብሰባ በኋላ የሻይ ዕረፍት ላይ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው

ክቡር ሚኒስትሩ ከስብሰባ በኋላ የሻይ ዕረፍት ላይ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ወዳጃቸው ይደውሉላቸዋል]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ ሰላም ነኝ አንተ እንዴት ነህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ዕረፍት አለዎት?
 • ይህች አገር እስክትለወጥ ምን ዕረፍት አለ ብለህ ነው?
 • ያው እርስዎ መሥራት የሚችሉትን ብቻ ስለሚሠሩ፣ ለሌላ ቢያስተላልፉ አይሻልዎትም?
 • እሱማ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ይህችን አገር ለዚህ ያበቃናት ሌት ከቀን እየሠራን ነው እኮ፡፡
 • ያው አሁን አገሪቱ ተስፋ ቢጤ እያየች ነው ብዬ ነዋ፡፡
 • እኮ ይኼንንስ ተስፋ ያመጣነው እኛ አይደለን እንዴ?
 • እሱን እንኳን ይተውት?
 • መቼም እናንተ ወርቅ ቢነጠፍላችሁም ፋንድያ አማረን ትላላችሁ፡፡
 • እኔ እንደዚያ እያልኩ አይደለም፡፡
 • ታዲያ ከዚያም ጨቋኝ ሥርዓት አገሪቱን ያላቀቅነው እኛ አይደለን?
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኸው ኢኮኖሚው ተመንድጎ አገሪቷ የምታስጎመጅ አገር ሆናለች አይደል?
 • ስለኢትዮጵያ ነው የሚያወሩት?
 • ሰውዬ አገሪቱን ለዚህ ደረጃ ያበቃናት እኛ ነን፡፡
 • አይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • አገሪቱ ለዚህ የበቃችው በሕዝቡ ትጋት ነው፡፡
 • ምን?
 • ትግላችሁ ራሱ ፍሬ ማፍራት የቻለው ይህ ሕዝብ ስለረዳችሁ ነው፡፡
 • እሱንማ አንክድም፡፡
 • ስለዚህ ያለሕዝቡ የትም ልትደርሱ አትችሉም ነበር፡፡
 • ስማ ይኼ ሁሉ ሀብታም እኛ በገነባነው ሥርዓት እንደተፈጠረ መዘንጋት የለብህም፡፡
 • የተፈጠሩት ሀብታሞች እነማን እንደሆኑ ሁላችንም እናውቃቸዋለን፡፡
 • አንተ ለነገሩ ሁልጊዜ መተቸትና መንቀፍ ነው የምትወደው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ የመተቸትና የመንቀፍ አባዜ ኖሮኝ አይደለም፡፡
 • ታዲያ ምንድነው የምታወራው?
 • እርስዎ እንደሚሉት ተሠርቶ ቢሆን ኖሮ አገሪቱ የት በደረሰች ነበር፡፡
 • ቆይ ግን ምንም አልተሠራም እያልከኝ ነው?
 • እንደዚያ አልወጣኝም፣ ግን ከዚህ የበለጠ መሥራት ይቻል ነበር ነው ያልኩት፡፡
 • ይኼን ሁሉ ልማት እያለ አፍራሽ ነገር የምታወራ ከሆነ ፀረ ልማት ነህ ማለት ነው?
 • ኧረ እንደዚህ አይመፃደቁ ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ እየተመፃደኩ ሳይሆን፣ ከዲክሽነሪ ላይ የረሃብ ምሳሌ መሆኗ እንዲቀር ያደረግን ሰዎች ነን እኮ?
 • እሱን እንኳን ይተውት፡፡
 • ሰውዬ እኔ የምለውን ተውና አንተ የምትቀበላቸውን ሪፖርቶች መመልከት ትችላለህ፡፡
 • የትኞቹ ሪፖርቶች?
 • ይኸው ዓለም ባንክም ሆነ አይኤምኤፍ የመሰከሩልን አለ፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላለፉት አሥር ዓመታት በሁለት አኃዝ እያደገ እንደሆነ መስክረዋል፡፡
 • በዚያው ልክ ዝርፊያውና ስርቆቱም በሁለት አኃዝ እያደገ ነው፡፡
 • አንተ አፍራሽ ነ­­ህ ያልኩህ ለዚህ ነው፡፡
 • ኢኮኖሚውም አደገ ከተባለ ያደገው የአገሪቱ አይደለም፡፡
 • ታዲያ የማን ኢኮኖሚ ነው ያደገው?
 • የእርስዎና የቤተሰብዎ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ሰላም ነህ ወዳጄ?
 • ምን ሰላም አለ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሆንክ ደግሞ?
 • የአገሪቱ አካሄድ በጣም እያሠጋኝ ነው፡፡
 • ምኑ ነው የሚያሠጋህ?
 • እርስዎ ግን በአገር አሉ?
 • የት እሄዳለሁ ብለህ ነው? ሰሞኑን ብቻ ለቼክአፕ ወጣ ብዬ ነበር፡፡
 • አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እያደረጉ ያሉትን ነገር መቼም ይከታተላሉ?
 • እንግዲህ አገሪቱ ውስጥ ብዙ ነገር ይደረጋል፣ ዋናው በልማት ጎዳና ላይ መሆናችን ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ጉድ እየፈላ ነው፡፡
 • የምን ጉድ ነው?
 • በቅርቡ ሊበረበሩ ነው፡፡
 • ማን ነው የሚበረብረኝ?
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉትን አልሰሙም እንዴ?
 • ምን አሉ ደግሞ?
 • ባለሥልጣናት በውጭ ያስቀመጡት ገንዘብ እየተመረመረ ነው፡፡
 • ኧረ ሰውዬ ትንሽ አስብልኝ?
 • ምን አደረኩዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ለምን እንደዚህ ዓይነት ወሬ እየነገርከኝ ደሜን ከፍ ታደርገዋለህ?
 • ምን ላድርግ እንዲጠነቀቁ ብዬ ነው?
 • ምንድነው ግን ያሉት
 • ባለሥልጣኖቻችን አካውንት ከከፈቱባቸው አገሮች ጋር እየተወያየን ነው ብለዋል፡፡
 • ምንድነው የሚሻለኝ?
 • እኔማ እዚያ የተለመደው ባንክ ደውዬ ብጠይቅ፣ በጉዳዩ ላይ ምንም ምላሽ አንሰጥህም አሉኝ፡፡
 • ኧረ ተው ሌላ በሽታ አታምጣብኝ?
 • ክቡር ሚኒስትር አካሄድዎ ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባል፡፡
 • ኧረ በሰላም ልኑርበት ተውኝ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ እርስዎን ላወዛግብዎት ፈልጌ አይደለም፡፡
 • አሁን ምንድነው ማድረግ የምችለው?
 • ከፍተኛ ጥንቃቄ ነዋ፡፡
 • ስማ ያ ሁላ ዶላር በእኔና በቤተሰቤ ስም እኮ ነው የተቀመጠው፡፡
 • አዝማሚያው አላማረኝም እያልኩዎት ነው፡፡
 • ታዲያ አንደኛዬን ጠቅልዬ ልጥፋ?
 • የት ነው የሚጠፉት?
 • ውጭ ልገዛው ያሰብኩት ቤት ስላለ ቤተሰቤን ይዤ ልጥፋ?
 • ክቡር ሚኒስትር አካውንትዎ ከተበረበረ ንብረትዎትም መበርበሩ አይቀርም፡፡
 • ውጭ ቤት አትግዛ እያልከኝ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር እስር ቤት መግባትዎ ስለማይቀር ውጭ የመሄዱን ሐሳብ ቢተውት ይሻላል፡፡
 • ምን?
 • ቤት መግዛት ከፈለጉም አካባቢውን ከአሁኑ እንዲለምዱት እኔ ጥሩ ቤት እፈልግልዎታለሁ፡፡
 • የት አካባቢ?
 • ቂሊንጦ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት አቅርቡ ተብለው ተደናግጠው አማካሪያቸውን አስጠሩት]

 • ያን ሪፖርት አዘጋጀህ?
 • የትኛውን ሪፖርት ክቡር ሚኒስትር?
 • ባለፈው ያዘዝኩህን ነዋ?
 • ኧረ ምንም አላዘዙኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • አሁን በአንድ ሰዓት ውስጥ ሪፖርት እንድትሠራልኝ እፈልጋለሁ፡፡
 • እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን ቀልድ ነው?
 • ሪፖርት እንዴት ነው በአንድ ሰዓት ውስጥ የሚዘጋጀው?
 • ሌላ ጊዜ በሰላሳ ደቂቃ አልነበር እንዴ የምታቀርብልኝ?
 • አሁን ብዙ ነገር እንደተቀየረ ያውቃሉ አይደል ክቡር ሚኒስትር?
 • እሱማ አውቃለሁ፡፡
 • በአንድ ሰዓት ውስጥ ሪፖርት ማዘጋጀት አይቻልም፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • እንደበፊቱ ኮፒ ፔስት ማድረግ አይቻልማ?
 • አሁን ኮፒ ፔስት ቀረ እያልከኝ ነው?
 • አሁንማ እያንዳንዱ መስመር ነው የሚነበበው፡፡
 • ቢነበብስ ታዲያ?
 • ሁሉንም ነገር አመንጭተን ነው መጻፍ ያለብን፡፡
 • ስማ አመንጭተህም ቢሆን ኮፒ ፔስት አድርገህ፣ በአንድ ሰዓት ውስጥ ሪፖርቱን እንዳገኘው፡፡
 • እሱ የማይሆን ነገር ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንተ የታዘዝከውን ሥራ ለምንድነው የማትሠራው?
 • ክቡር ሚኒስትር የማይሠራ ነገር እንዴት እሠራለሁ?
 • በጣም ተናንቀናል ልበል?
 • የመናናቅ ጉዳይ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስማ ጠዋት ስንት ሰዓት ገብተህ ለምሳ ስንት ሰዓት እንደምትወጣ አውቃለሁ፡፡
 • ምን አጠፋሁ ታዲያ?
 • ከሥራ የምትወጣበትንም ሰዓት ሆነ የምታመሽበትን ቤት በሚገባ ነው የማውቀው፡፡
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ሪፖርቱን መሥራት ያልፈለግከው የመጠጥ ሰዓትህን ስለሚነካብህ ነዋ፡፡
 • አይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስማ ታታሪ ሠራተኛ ብትሆንማ ኖሮ ቀን ተሌት ሠርተህ ሪፖርቱን ታዘጋጅ ነበር፡፡
 • ያሉት ሪፖርት እኮ እንዲህ ቀላል አይደለም?
 • ቅዳሜና እሑድ በመሥሪያ ቤት መኪና ደብረ ዘይት እንደምትዝናና አውቃለሁ፡፡
 • ምን ችግር አለው?
 • ከዚያም ባለፈ ፊልድ ስትወጣ ከሾፌሩ ጋር ተመሳጥረህ ከሰል ጭነህ እንደምትመጣም አውቃለሁ፡፡
 • አሁን ግራ እያጋቡኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ለምንድነው ግራ የተጋባኸው?
 • ይኼ ሁሉ ከሪፖርቱ ጋር ምን አገናኘው?
 • ይገናኛል እንጂ፡፡
 • እኮ እንዴት?
 • ሪፖርቱን መሥራት ያልፈለግከው ለምን እንደሆነ እየነገርኩህ እኮ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሪፖርቱ እኮ እንደ ድሮ ዝም ተብሎ ስለማይሠራ ነው፡፡
 • ታዲያ ከእኔ ምንድነው የምትፈልገው?
 • ሐሳብ እንዲያመነጩ ነዋ፡፡
 • ከዚህ በላይ ምን ዓይነት ሐሳብ ላመንጭልህ?
 • ለነገሩ እርስዎ ሐሳብ አመንጪ እንዳልሆኑ አውቃለሁ፡፡
 • ታዲያ ምንድነኝ?
 • አቃቂር አውጪ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከስብሰባ በኋላ የሻይ ዕረፍት ላይ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው]

 • በሰላም ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አልገባኝም?
 • ማታ አመሹ እንዴ?
 • ምን ለማለት ፈልገህ ነው? መጠጥ እንደማልጠጣ ታውቃለህ አይደል?
 • ጤንነትዎስ ሰላም ነው?
 • ኧረ ፍጹም ጤነኛ ሰው ነኝ፡፡
 • አልመሰለኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን እያልክ ነው ሰውዬ?
 • ከጠዋት ጀምሮ ስብሰባው ላይ እያንቀላፉ እኮ ነው፡፡
 • ለምን አንከባበርም?
 • ይኸው ፎቶ አንስቼዎታለሁ፡፡
 • ማሸለብ ብርቅ ነው?
 • ኧረ ሙሉ ስብሰባውን ነው የተኙት፡፡
 • አሁን አንተ ንቁ ነኝ እያልክ ነው?
 • እኔማ ስብሰባው የእርስዎን መሥሪያ ቤት ስለሚመለከት ብዙ አስተያየት ይሰጣሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡
 • ስማ እኔ ተኝቼ ሳይሆን እያሰላሰልኩ ነበር፡፡
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስቅሃል?
 • ለማንኛውም ሁኔታዎን ሳየው እንዲያው የደከምዎት ይመስለኛል፡፡
 • ማን ነው የደከመው?
 • እርስዎ ነዎታ፡፡
 • ለዚህ ሥርዓት እኮ እኔ አድራጊ ፈጣሪ ነኝ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን ግን አድራጊ ፈጣሪ አይደሉም፡፡
 • እና ምንድነኝ?
 • ተጧሪ!