Skip to main content
x
‹‹የመከላከያ ሠራዊቱ ሕዝብ ከመረጠው ፓርቲ ጋር መቀጠል የሚችል መሆን አለበት››  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

‹‹የመከላከያ ሠራዊቱ ሕዝብ ከመረጠው ፓርቲ ጋር መቀጠል የሚችል መሆን አለበት›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ በተገኙበት ከከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት አዛዦች ጋር ባረደጉት ውይይት፣ ‹‹ኢሕአዴግ ፖለቲካዊ ሥራውን መሥራት አቅቶት በራሱ ስንፍና የወደቀ እንደሆነ፣ የመከላከያ ሠራዊቱ ሕዝብ ከመረጠው ፓርቲ ጋር መቀጠል የሚችል ሠራዊት መሆን አለበት፤›› ሲሉ አሳሰቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የጦር ኃይሉ መጠናከር እንዳለበትና ወደፊት ሊመጡ የሚችሉ የተለያዩ ጥቃቶችን መቋቋም በሚያስችለው ቁመና ላይ መሆን እንዲችል፣ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ ሚናም የሲቪል አስተዳደሩ የለያቸውን ሥጋቶች ለመመከት በላቀ ብቃት ግዳጁን መፈጸም እንዳለበት፣ ዋነኛ ዓላማውም የሕዝብን ጥቅሞች በማስጠበቅ የአገርን ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት መከላከያ ሠራዊቱ የብሔር ብሔረሰቦች ነፀብራቅ መሆኑን፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት መፅዳት እንዳለበት፣ ለሲቪል አስተዳደርና ለሕገ መንግሥቱ ታዛዥ መሆን እንዳለበት፣ የአገር ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ ተልዕኮ የተሰጠው በመሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ባህሪውን ይዞ መቀጠል እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡

ዓርብ ግንቦት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተደረገውን ውይይት አስመልክተው በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽሑፍ ያሠፈሩት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመከላከያ ሪፎርምን በተመለከተ ያላቸውን ራዕይ ለጄኔራሎች አጋርተዋል፡፡ የመከላከያ ኃይል ዋነኛ ተግባር ሕገ መንግሥቱን በከፍተኛ ደረጃና የሙያ ሥነ ምግባር መጠበቅ ነው፡፡ መከላከያ የኢትዮጵያን ጥንካሬ በሚያሳድግ ደረጃ እንዲደራጅ ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፤›› ሲሉ ጽፈዋል፡፡

አቶ ፍፁም አክለውም፣ ‹‹ኢትዮጵያ ያሉባት የደኅንነት ሥጋቶች ውስብስብና በየጊዜው የሚለዋወጡ ናቸው፡፡ ይህም በጦር ሜዳ ያሉ ጠላቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ እያደገ የመጣው ሳይበርና ያልተለመዱ ዓይነት ጥቃቶችም ጭምር ናቸው፡፡ የአገሪቱን ደኅንነት ለመጠበቅ ቀጣይነት ያለውና ፈጣን የሆነ የመቋቋም አቅምን መገንባት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመከላከያ ኃይሉ በአፍሪካ ደረጃ ያለውን የበላይነት፣ በተለይም በአየር ኃይልና በምድር ኃይል ያለውን ቀደምትነት በባህር ኃይልም አቅሙን ሊያሳድግና በዚያም ሊደግመው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ቢሉም ኤርትራ ስትገነጠል ኢትዮጵያ የባህር በር በማጣቷ ሳቢያ፣ የባህር ኃይል የሌላትና ከኤርትራ መገንጠል በፊት የነበረው የባህር ኃይል አባላት መበተናቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዴት የባህር ኃይል እንዲኖረው እንዳሰቡና እንዴት ተፈጻሚ ሊደረግ እንደታሰበ አልታወቀም፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱ ከማኅበረሰቡ ጋር አብሮ እያደገ የመጣ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሉዓላዊነትን ለማስከበር በጣም በርካታ አገሮች ያደረጉትን ሙከራ ማክሸፍ የቻለ ተቋም ነው ሲሉ አሞካሽተውታል፡፡

‹‹ውትድርና ጀግንነት፣ አገር ጠባቂነትና አርዓያነት ከሆነባቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ . . . የደከምነው ለፍሬ ነው፣ ፍሬው መሬት ሳይወድቅ ጥቅም ላይ መዋል አለበት የሚል አስተሳሰብ ለመፍጠር የሚያስችለውን ለውጥ ማካሄድ የሚቻለው በዚያ ደረጃ የአተያይ ብቃት የፈጠርን እንደሆነ ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመከላከያ ኃይሉ ውስጥ የሚደረጉ ለውጦች እንደሚኖሩ ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህ ለውጦች በዋናነት የሠራዊቱን ሙያ (ፕሮፌሽናሊዝም) ማሳደግ እንደሚሆኑም አስምረውበታል፡፡

የመከላከያ ኃይሉ የሥርዓት ለውጥን ተቀብሎ መቀጠል የሚችል ከሆነ መላመድና መቀጠል የሚችል ነው ማለት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ኃይለ ማርያም ተነስቶ ዓብይ ሲመጣ መቀበል የሚችል ሠራዊት ከሆነ ለውጥን መላመድ የሚችል ነው ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በዕለቱ ከቀትር በኋላ ከቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስተር ቶኒ ብሌር ጋር በመሆን፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተውጣጡ ባለከፍተኛ ውጤት ተማሪዎች ጋር ውይይት አድርገው ነበር፡፡