Skip to main content
x
‹‹የአፍሪካውያን ፍልሰት በሜድትራኒያን ባህር ከመስጠም በላይ ሌሎች እውነታዎች እንዳሉት መገንዘብ ይገባል››

‹‹የአፍሪካውያን ፍልሰት በሜድትራኒያን ባህር ከመስጠም በላይ ሌሎች እውነታዎች እንዳሉት መገንዘብ ይገባል››

ሙኪሳ ኪቱዬ (ዶ/ር)፣ በተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ዋና ጸሐፊ 

ሙስ ግንቦት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ ይፋ የተደረገው የአፍሪካ ስደተኞችንና ስደትን የተመለከተው ሪፖርት ሌላ ዕይታ ይዞ ብቅ ብሏል። አፍሪካ የጎስቋላ ስደተኞች አመንጪ ማዕከል ብቻም ሳትሆን፣ የስደተኞች ተቀባይና ማረፊያ ስለመሆኗ የሚከራከረው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የንግድና የልማት ጉባዔ (UNCATD) ሪፖርት ነው። ሪፖርቱን  ይፋ ለማድረግ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተገኙት የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ዋና ጸሐፊ ሙኪሳ ኪቱዬ (ዶ/ር) እንዲሁም የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ቬራ ሶንግዌ (ዶ/ር)፣ ናቸው። ሁለቱ ምሁራን ኃላፊዎች እንደሚሞግቱት ስደትና ፍልሰት አፍሪካን በመጥፎ ገጽታ እንዲወከሉ የሚያደርግ የሚዲያ ዘገባና የቀኝ ዘመም ‹‹ሕዝበኝነት›› (Populist) አቀንቃኞች ሚና ትልቅ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው። በስደት ወቅት በሜድትራኒያን ባህር የሚሰጥሙ፣ የሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ሰለባ እየሆኑ ለጉዳትና ለሞት የሚዳረጉ፣ ወዘተ. ትክክለኛውን የአፍሪካን የፍልሰት ገጽታ አያሳዩም የሚሉት ኪቱዬ፣ ‹‹ማይግሬሽን ፎር ስትራክቸራል ኢኮኖሚክ ትራንስፎርሜሽን›› የተሰኘው የተቋማቸውን ጥናታዊ ሪፖርት መነሻ በማድረግ፣ ከጋዜጠኞች ጋር አጭር ቆይታ አድርገው ነበር። ከሪፖርተርና ከሌሎች መገናኛ ብዙኃን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሙኪሳ ኪቱዬ (ዶ/ር) የሰጡትን ምላሽ ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል። 

ሪፖርተር፡- ሪፖርቱ በአብዛኛው ትኩረቱ አፍሪካውያን ስደተኞች በአፍሪካ ውስጥ በሚያደርጉት የስደት እንቅስቃሴ ላይ ያነጣጠረ፣ ይህ ደግሞ ሆን ተብሎ በጥንቃቄ የተመረጠ ርዕሰ ጉዳይ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የአፍሪካ መንግሥታት በአውሮፓውያኑ ጫና እየተደረገባቸውና ሕዝባቸውን በአገራቸው ማቆየት እንዲችሉ፣ ለስደት የሚነሳውን ሰው ሁሉ እዚሁ አፍሪካ ውስጥ እንዲያስቀሩ እየተጠየቁ ነው፡፡ በአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ውስጥ የሚካሄደው ይታወቃል፡፡ የጣሊያን መንግሥት የሚያደርገው ግፊትም የታወቀ ነው፡፡ ጥቂት የአፍሪካ መንግሥታት ባለፈው ዓመት ወደ አውሮፓ በማቅናት ስደተኞችን በአፍሪካ ማስቀረት ላይ ያተኮረ ስምምነት መፈረማቸውም  ይታወሳል፡፡ ከዚህ አኳያ ሪፖርቱ ምን ያህል ከዚህ የአውሮፓውያን ፍላጎት የተለየ ነው?

ሙኪሳ ኪቱዬ፡- አፍሪካውያን ስደተኞችን ወይም ከአፍሪካ የሚፈልሱ ሰዎችን በተመለከተ በአውሮፓ የሚደረገው ክርክር ፈላሾቹ ሁሉ እንደ መደበኛ ፈላሾች ሳይሆን፣ እንደ ሳይወዱ በግድ ተሰዳጆች ከመመልከት የሚመነጭ የአስተሳሰብ መነሻ አለው፡፡ እኛ ለማሳየት እየሞከርን ያለነው ደግሞ የሚፈልሱት ሰዎች ስደተኞች ቢሆኑም፣ መጠጊያና ደህና ኑሮ ፍለጋ ብቻ የሚጓዙ ስደተኞች እንዳልሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛ አውሮፓ ከአፍሪካ የሚፈልሱ ዜጎች መናኸሪያ እንደሆነች የሚታሰበውን የተሳሳተ አመለካከት በሪፖርቱ ይፋ  አውጥተናል፡፡ አፍሪካውያን ወደ አውሮፓ እየፈለሱ ቢሆንም፣ የሚፈልሱት ሰዎች እንቅስቃሴያቸውን መነሻ በማድረግ የሚፈጸሙት የዘር ወይም ጥላቻና ፍራቻን መሠረት ያደረገ ጥቃት ብዙም እንደማይታይ፣ ይህም የአፍሪካ ባህልና መስተጋብር አካል እንደሆነ ጥናቱ አመላክቷል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ አፍሪካውያን ወደ አውሮፓ እንደሚሄዱ ብቻ ይታሰባል እንጂ፣ በአፍሪካ ውስጥ ስለሚደረገው አፍሪካውያን ከአንዱ አገር ወደ ሌላው አገር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብዙም አይነገርም፡፡ ነገር ግን በርካታ አፍሪካውያን በተለይ ክህሎትና ዕውቀት ያላቸው ከአንዱ አፍሪካ አገር ወደ ሌላው እየፈለሱ ነው፡፡

ለምሳሌ የአይሲቲ ዕውቀት ያላቸው ኬንያውያን ወደ ሩዋንዳ  እየፈለሱ ነው፡፡ ይህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የአፍሪካ የነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት በተግባር ሲተረጎም ደግሞ አውሮፓውያኑ ስለአፍሪካውያን ፈላሾች የሚሉትን ሁሉ መስማት የምናቆምበት ጊዜ ሊያመጣ እንደሚችል ያሳያል፡፡ አፍሪካ ያላትን ዕምቅ የአገልግሎት ዘርፍና የንግድ አቅም በሚገባ መጠቀም ስትጀምር፣ የአገልግሎት እንቅስቃሴን በሕግ አግባብ ስትተገብር፣ ከቦታ ቦታ የሚደረገው የሰዎች እንቅስቃሴ ቀላል ሲሆንና የሰዎች የንግድ ሥራ ፈጠራ ሲበረታታ የፍልሰት ጠቀሜታም ይጎላል፡፡ ሆኖም ሳይወዱ ያለ ፍላጎታቸው በተለያዩ ጫናዎች ሳቢያ የሚሰደዱ በርካቶች እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡ እነዚህን ስደተኞች እዚያው ከሚነሱበት አገር እንዳይወጡ የሚጠይቁ መንግሥታት አሉ፡፡ እኛ እየነገርናቸው ያለው ደግሞ ይህንን በማድረግም ጭምር ጥሩ እየሠራን ስለመሆናችን ነው፡፡ ዘላቂነት ያለው የሰዎች መደበኛ ፍልሰት ጠቃሚ መሆኑ ግን መዘንጋት የለበትም፡፡ በአፍሪካ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዲስፋፋ የሚያስችሉ ኢንቨስትመንቶች መካሄድ አለባቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ስደተኞች እዚሁ አፍሪካ ውስጥ መቆየት የሚችሉባቸው ዕድሎች ሲፈጠሩ፣ ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሲባል ወደ ሌሎች አኅጉሮች የሚደረገው ስደት ይቀንሳል፡፡

ሪፖርተር፡- ስደት ወይም ፍልሰት በከፍተኛ ደረጃ ፖለቲካዊ አጀንዳ እየሆነ ከመጣ  ቆይቷል፡፡ በተለይ አፍሪካውያን መሪዎች ካለባቸው ጫና አኳያ ሪፖርቱ የዘገየ አይመስልዎትም?

ሙኪሳ ኪቱዬ፡- እኔ በበኩሌ ዘግይቷል ብዬ በምንም ሁኔታ አላስብም፡፡ ሪፖርቱ ወቅታዊ ብቻም ሳይሆን፣ አዎንታዊነት ያላቸው ምክክሮች በፍልሰት ላይ እንዲደረጉ የሚጋብዝ ጭምር ነው፡፡ እርግጥ በርካታ ዘገባዎች ያለ ፍላጎት በጫና በሚደረጉ የስደት እንቅስቃሴዎች ላይ ሲያጠነጥኑ እየታየ ነው፡፡ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በሜድትራኒያን ባህር እየታየ ያለው አስከፊ የስደተኞች እልቂት ትልቅ ሽፋን እያገኘ መሆኑና ስደተኞቹ ትኩረት እንዲያገኙ ማገዙ ባይካድም፣ የአፍሪካ ፍልሰት ግን በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ በርካታ አዎንታዊ ጎኖች ያሉት የፍልሰት ታሪክ ሲገለጽ ግን አንሰማም፡፡

ሪፖርተር፡- በአፍሪካውያን ስደተኞች ላይ የሚደረገው ተፅዕኖና ጥቃት እንዳለ ሆኖ፣ በአገሮች ደረጃ በተለይ በምዕራባውያኑ አገሮች ዘንድ በተለይም በመንግሥታቱ ደረጃ ሆን ተብሎ የሚካሄድ የፖሊሲ ዕርምጃ እንደሚኖር ይታመናል፡፡ ይኸውም አብዛኞቹ አገሮች የሕዝብ ቁጥር ዕድገታቸውና የውልደት መጠናቸው ባለበት እየቆመ በመሆኑ፣ በስደተኞችና በፈላሾች እንዳይጥለቀለቁ በመፍራት አፍሪካውያን አገሮች ዜጎቻቸው እንዳይወጡ እያስገደዱ ነው ለማለት አያስችልም?

ሙኪሳ ኪቱዬ፡- የሕዝብ ቁጥር መቀነስ ወይም ባለበት መቆሙ እንዲያውም ለሌሎች ዜጎች ድንበራቸውን ለመክፈት የሚያነሳሳቸው ነገር ነው፡፡ የሕዝብ ቁጥር እየቀነሰ ከሆነ አገሮች በፍላጎታቸው ይህንን የሕዝብ ቁጥር መቀነስ ለመግታትና ለኢኮኖሚያቸው አስፈላጊ የሆነውን የሰው ኃይል ለማግኘት፣ ወደ ሌሎች አገሮች ዜጎች ማተኮራቸው አይቀርም፡፡ ፖለቲከኞች የሚያደርጉት ጥላቻና ፍራቻ ላይ መሠረት ያደረገ ቅስቀሳ መነሻው የሕዝበኝነት አመለካከት ነው፡፡ ይህ አመለካከት ፍራቻን በመጠቀም የሚራመድ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ የፖለቲካ ተቀባይነት ለማግኘት ሲባል ሰዎች ፍራቻን መጠቀሚያ አድርገውታል፡፡ በመሆኑም የቀኝ ዘመም ሕዝበኝነት አቀንቃኞችና አራማጆችን ማንሰራራት ተከትሎ፣ በበርካታ የአውሮፓ አገሮች የተስተዋለውን ዓይነት ፍራቻን መሠረት ያደረገ ጥቃት በመመልከት ሥጋት ውስጥ መውደቅ አይገባንም፡፡ የሕዝብ ቁጥራቸው እየቀነሱ ያሉ አገሮች ድንበራቸውን ለመዝጋት ግንብ እንገነባለን እያሉ ነው፡፡ ይሁንና እነዚህ አገሮች እየቀነሰ ያለውን የሕዝባቸውን ቁጥር ሊያካክስላቸው የሚችለው ዘላቂነት ያለው ትክክኛውን መንገድ የተከተለ የሰዎች ፍልሰት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአፍሪካ ስደተኞችን በሚመለከት በአውሮፓውያን ዘንድ ያለው ምልከታ አፍሪካውያኑ ሥራችንንና ኑሯችንን ሊቀሙን መጡ የሚል እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ ይህ ምልከታ የሚዲያውና የማኅበረሰቡ ብቻም ሳይሆን፣ እንዲህ ያለውን ሐሳብ የሚያቀነቅኑ መንግሥታትና ፖለቲከኞችም መጥተዋል፡፡ እንዲያውም ቀኝ ዘመም አዳዲስ መንግሥታትና የፖለቲካ ሰዎች በፍልሰት ላይ ጥብቅ ፖሊሲ እንደሚከተሉ ሲገልጹ እየተሰማ ነው፡፡

ሙኪሳ ኪቱዬ፡- በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ እንዲህ ያለው ጉዳት ሥጋት መደቀኑ እንደማይቀር የሚታመን ነው፡፡ በስደት የሚመጣው ሰው በበዛ ቁጥር ለመገደብ መነሳት ብዙም የሚያነጋግር ጉዳይ ላይሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ወደ ጣሊያን የሚያቀናው ስደተኛ ቁጥር ማስተናገድ ከሚቻለው በላይ እየሆነ ከመጣ ኢኮኖሚው ላይ ጫና ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ጀርመንና ስዊድን ያሉ አገሮች ያደረጉትን መመልከቱም ተገቢ ነው፡፡ የሚፈልሱ ሰዎች እንደ ቧንቧ፣ ኤሌክትሪክና ግንባታ ሥራ ባሉት መስኮች ላይ ሙያዊ ሥልጠና የወሰዱ ስደተኞች በኢኮኖሚዎቹ ውስጥ የሚታየውን የሰው ኃይል ክፍተት እያሟሉ ነው፡፡ በቴክኒክ ሙያ ዘርፍ በእነዚህ አገሮች ብቻም ሳይሆን፣ በሌሎችም የሚታየውን ክፍት እየሸፈኑ ያሉት በአብዛኛው ስደተኞች ናቸው፡፡ አዎንታዊው እንዲህ ያለው ታሪክ ግን በአሉታዊው እየተሸፈ፣ ሕዝበኝነትን ተገን በማድረግ ጽንፈኝነትን የሚያቀነቅኑ አካላት ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ስለሚያገኙ፣ የስደተኞችን መልካም አስተዋጽኦ ማየት አዳጋች እየሆነ መጥቷል፡፡ ሰሞኑን ታዋቂው ኮሜዲያን ትሬቨር ኖህ እንዳለው፣ በፈረንሣይ ሕንፃ ጫፍ ተንጠልጥሎ የነበረውን ሕፃን ያዳነው አፍሪካዊ ስደተኛ ማማዶ ባደረገው መልካም ነገር ሳቢያ፣ አፍሪካውያን ስደተኞች በጎ ገጽታ ያለው ትርክት በየሚዲያው እንደሚያገኙ በመጥቀስ ቀልድ ቀመስ ቁምነገር ተናግሯል፡፡ አውሮፓውያኑ በአኗኗራቸው ቆሻሻ አፍሪካውያን ሥራችንን ሊወስዱብን መጡብን ማለታቸውን ይተው ይሆን የሚል ቀልድ ነበር ትሬቨር ኖህ ሲናገር የነበረው፡፡ የፀጥታ ችግር ሲኖርና የሽብር ጥቃት ሲፈጸም በአብዛኛው ሲያያዝ የሚታየው ከአፍሪካውያንና ከትውልደ አፍሪካውያን ጋር ነው፡፡ እንዲህ ያለው አሉታዊ ምልከታ ከአዎንታዊው ጋር ሚዛናዊ ሆኖ እንዲቀርብ ማድረግ ይገባል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የአፍሪካውያን ፍልሰት፣ በሜድትራኒያን ባህር ሲሰጥሙ የሚያሳየውን ዓይነት ብቻም ሳይሆን ከዚህ ሁሉ በላይ እውነታዎች እንዳሉት መገንዘብ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- አፍሪካውያን መንግሥታት ጫና ውስጥ እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ በሪፖርታችሁ ደግሞ፣ ሀቅን አዎንታዊ እውነታዎች እንዳሉ እየሞገታችሁ ነው፡፡ 

ሙኪሳ ኪቱዬ፡- አፍሪካውያን መሪዎች አዎንታዊ እውነታዎችን በመንተራስ ከተከላካይነት ይልቅ ሐቆችን የተንተራሰ ክርክርና ውይይት እንዲያደርጉ ሪፖርቱ ትልቅ እገዛ ያደርግላቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ከአኅጉሪቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚደረገው ፍልሰት በአፍሪካ የኑሮ ደረጃን እያሻሻለ እንደሚገኝ ለማሳየት ሞክረናል፡፡ ፍልሰቱ እንዲቀንስ ካስፈለገም በአፍሪካ ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንዲኖር ማድረግ፣ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ኢንቨስትመንቶች እንዲካሄዱ ማድረግ ይገባል፡፡ እንዲህ ያለውን እንቅስቃሴ ለማስፋፋት አፍሪካ ድጋፍ ያስፈልጋታል፡፡ አፍሪካውያንም በገዛ አገሮቻቸው ውስጥ ለውጥ ሲኖር፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ሲረጋገጥ ወደ ሌሎች አገሮች የመጓዝ ተነሳሽነታቸው ሲቀንስ፣ በጎረቤት አገሮችና በሌሎችም የአፍሪካ አካባቢዎች ለውጥ ሲኖር ወደ እነዚያ ቦታዎች መሄድን እንደማይመርጡ ዓይተናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህ ሪፖርት አፍሪካውያን በሚኖሩባቸው በአውሮፓና በሌሎች አገሮች ውስጥ ስለሚያደርጓቸው መልካም አስተዋጽኦዎችና ልዩ ልዩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ምን ያህል ይዳስሳል?

ሙኪሳ ኪቱዬ፡- ሪፖርቱ በርካታ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ስላካተተ እስካሁን ካልነው በተጨማሪ ሪፖርቱን ማንበቡ ብዙ ሐሳብ እንደሚያካፍል መናገር ይቻላል፡፡

ስፓኒሽ ኒውስ ኤጀንሲ፡- ፍልሰት ወደ አፍሪካ ከሚደረገው ስደት አኳያም ያለውን አንድምታ ማየት ይገባል፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ በክረምቱ ወራት በቆሎ በየመንገዱ ዳርቻ እየተጠበሰ ይሸጣል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የተሠራጨ አንድ ምሥል ነበር፡፡ ይኸውም ቻይናውያን የተጠበሰ በቆሎ ከሚሸጡ ጋር እየተከራከሩ ሲገዙ ያሳያል፡፡ ይህ የሚያሳየው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቻይናውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተለየች አይመስለኝም፡፡ በሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚታየው ተመሳሳይ ነው፡፡ በመሆኑም ወደ አፍሪካ የሚደረገው የቻይናውያን ፍልሰትን በተመለከተ ሪፖርቱ ምን ያሳያል?

ሙኪሳ ኪቱዬ፡- የቻይና የአፍሪካ ፍልሰትን በተመለከተ በሪፖርቱ በመጠኑ ልዩነት ያለበት አቀራረብ አለው፡፡ የሪፖርቱ አብዛኛው ትኩረት በአፍሪካውያን ፈላሾች ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡ 19 ሚሊዮን ሰዎች ከአፍሪካ እንደሚፈልሱ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ በዚያው ልክ ከ5.5 ሚሊዮን በላይ ወደ አፍሪካ የሚመጡ የሌላ አገር ሰዎች እንዳሉም ተረጋግጧል፡፡ የአፍሪካ ስደተኞች ወይም ፈላሾች ከሚነሱባቸው አገሮችና ከሚደርሱባቸው አገሮች አኳያ ምን አስተዋጽኦ አላቸው የሚለው ጉዳይ የሪፖርቱ የትኩረት ነጥብ ነው፡፡ ይሁንና በርካታ ቁጥር ያላቸው ቻይናውያን ወደ አፍሪካ እንደሚገቡ የታወቀ ነው፡፡ አንዳንድ አገሮች ወደ አገራቸው የሚገቡ የሌሎች አገሮች ዜጎች ማሟላት ስለሚገባቸው የሥራ ፈቃድና ሌላውም ጉዳይ ላይ ጠበቅ ያለ ሕግ ሲኖራቸው፣ ሌሎች አገሮች ግን ይህ ብዙም የሚያሳስባቸው አይመስሉም፡፡ በአንዳንድ አገሮች ያለው የቻይናውያን ቁጥር ከሕዝቡ ብዛት አኳያ ሲታይ በጣም አሳሳቢ ሊባል የሚችል ከፍተኛ ደረጃ ይዞ የሚገኝበት ጊዜም አለ፡፡ ጥቂት የሕዝብ ቁጥር ያላቸው የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቻይናውያን ከሚገኙባቸው አገሮች ውስጥ ናሚቢያ ትጠቀሳለች፡፡ ምን ያህል ቻይናውያን በዚያች አገር ውስጥ እንደሚገኙ እንኳ በአግባቡ አይመዘገቡም፡፡ እንዲህ ያሉ የተለያዩ ጉዳዮች አሉ፡፡ በዚህ ላይ ያተኮሩ ምክክሮች ሊደረጉ እንደሚገባ ይታመናል፡፡ ሆኖም እኛ ካደረግነው ጥናት አኳያ የተነሳው ጉዳይ ትንሽ ለየት ያለ ነው፡፡ በፖሊሲ መፍትሔ ሐሳብነት ካቀረብናቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ እንደየፍልሰቱ ሁኔታ የተለያየ የፖሊሲ አቅጣጫ መከተል እንደሚገባ የሚጠይቀው ይገኝበታል፡፡ 5.5. ሚሊዮን ሰዎች ከአውሮፓ፣ ከእስያና በተለይም ከህንድ ፈልሰው ወደ አፍሪካ መጥተዋል፡፡ ይህ ቁጥር ግን ከሚታሰበው ይልቅ አነስተኛውን ግምት በመውሰድ የቀረበ ነው፡፡ ፆታ ተኮር የፍልሰት ፖሊሲዎች በአግባቡ መተግበር ይኖርባቸዋል፡፡   

ስፓኒሽ ኒውስ ኤጀንሲ፡- በርካታ ቻይናውያን ወደ አፍሪካ በመጡ ቁጥር ከአገሬው ጋር የኑሮና የሥራ ዕድል ጋር መሻማታቸው አይቀሬ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም እንዲህ ከነዋሪው የዕለት ኑሮ ሒደት ጋር ሽሚያ ከጀመሩ ምን ያህሉ አፍሪካዊ የኑሮ ጫና ውስጥ ገብቷል? በዚህም ለፍልሰት እየተዳረገ ነው የሚለውን ጉዳይ ሪፖርቱ አሳይቷል ወይ?

ሙኪሳ ኪቱዬ፡- የተነሳው ጥያቄ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ ቀድሜ እንዳልኩት ግን ስለጉዳዩ መነጋገር ይገባል፡፡ ጉዳዩ ለመነጋገር በሚያስገድድ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የቻይና ፍልሰትን በሚመለከት ከሥራ ፈቃዳቸው፣ ከኢኮኖሚ ሁኔታና ከሌሎች ሕጋዊ ጉዳዮች በመነሳት እንዴት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው መነጋገር ይገባል፡፡ ሆኖም እኛ ከተነሳንበት መከራከሪያ ጭብጥና ጥናት አኳያ የተለየ ጉዳይ ነው፡፡ ምናልባት ወደፊት በሌላ ምዕራፍ መታየት ሳይኖርበት አይቀርም፡፡ የአፍሪካውያንን የሥራ ዕድል እየተቀራመቱ ነው? ወይስ ለአፍሪካውያን የሥራ ዕድል ምቹ አጋጣሚ እየፈጠሩ ነው? የሚለው ወደፊት ሊታይ የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ ይፋ ካደረግነው የጥናት ሪፖርት ተከታይ ክፍል ሆኖ ወደፊት ይታይ ይሆናል፡፡  

ጥያቄ፡- ከ21 በላይ የአፍሪካ አገሮች በፖለቲካና በሌላም ዓይነት ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ ሊቢያ በከባድ ቀውስ ውስጥ ነች፡፡ ስደተኞች በዚያች አገር ውስጥ የሚደርስባቸው ነገር እየታየ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ እነዚህ አገሮች ለስደተኞች እንዴት ምቹ ሊሆኑ ይችላሉ?

ሙኪሳ ኪቱዬ፡- በመጀመሪያ ቀውስ ውስጥ የሚገኙ አገሮች ለራሳቸውም ዜጎች ፈታኝ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ በቀውስ ውስጥ የሚገኙ አገሮች ብዙውን ጊዜ ዜጎች ሳይፈልጉ እንዲሰደዱ ያስገድዳሉ፡፡ በዚህ ሳቢያ በአገር ውስጥ የሚፈናቀሉትም ሆኑ ወደ ውጭ የሚሰደዱት በርካቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ስደተኞች ናቸው ከአፍሪካ የሚፈልሱ ሰዎች በሙሉ  በሰፊው በአሉታዊ ገጽታ እንዲታዩ ትልቁን አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉት፡፡ ቀውስ ባለበት ቤት ውስጥ ምንም ጥሩ ሊባል የሚችል ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ለረጅም ጊዜ ከቀውስ ነፃ ልትወጣ ያልቻለች አገር ነች፡፡ ሌሎችም ሊጠቀሱ የሚችሉ አገሮች አሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች የአፍሪካን ዘላቂ ዕድገትና የወደፊት ለውጥ የሚቃኘውና ‹‹አጀንዳ 2063›› የተሰኘው ትልቅ ዕቅድ ትኩረት እንዳያገኙ የሚያደርጉ ናቸው፡፡