Skip to main content
x
አገርን የማያስቀድም አጀንዳ እርባና የለውም!

አገርን የማያስቀድም አጀንዳ እርባና የለውም!

የአገር ህልውና ለድርድር አይቀርብም፡፡ የአገር ሰላምና ደኅንነት መቼም ቢሆን ለፖለቲካ ሒሳብ ማወራረጃነት መዋል የለበትም፡፡ የአገር ጉዳይ ሲነሳ በቀጥታ የሚመለከተው ከ100 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያንን ነው፡፡ በአገሪቱ አራቱም ማዕዘናት ውስጥ የሚኖሩና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከአያት ከቅድመ አያቶቻቸው የወረሱት ጥልቅ የሆነ የአገር ፍቅርን ነው፡፡ ይህ ወደር የሌለው ፍቅር በመስዋዕትነት ጭምር የተጠናከረ በመሆኑ፣ የእናት አገር ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ ያሳስባል፡፡ ይህ የተከበረ፣ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ የአገሩ ጉዳይ ዛሬም ያሳስበዋል፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ መነጋገሪያ የሚሆኑ  ነገሮች የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ማኅበራት ወይም ግለሰቦች የአገርን ጉዳይ ከጠባብ ፍላጎት አኳያ ሲቃኙ ጠባቸው ከሕዝብ ጋር ነው፡፡ የአገርና የሕዝብ ቁርኝት ይኼንን ያህል መሆኑ ከታወቀ በብሔር፣ በእምነት፣ በፖለቲካ አመለካከትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ዲስኩሮችም ሆኑ መልዕክቶች ጥንቃቄ ያሻቸዋል፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በጣም ከሚወቀስባቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው ለአገር አንድነት የሰጠው አናሳ ግምት ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ በሆነች አገር ውስጥ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ከመጠን በላይ በመሰበኩ በርካታ ጉዳቶች አጋጥመዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገር አንድነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ድምፆች እየተሰሙ ቢሆንም፣ አሁንም ከፍተኛ ጥረት የሚያስፈልጋቸው ቀሪ ጉዳዮች አሉ፡፡ ሥልጣንን ከታማኝነትና ከብሔር አንፃር የመመልከት አባዜ ያመጣው ጣጣ ብቃትንና ተፎካካሪነትን ገፍትሮ በመጣሉ፣ ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ተሽመድምደዋል፡፡ ለሕዝብ መሰጠት ያለባቸው አገልግሎቶች በመጨናገፋቸው ምክንያት ለበርካታ ቅሬታዎች መነሻ ሆነዋል፡፡ ተቋማት ዘመኑ ከደረሰበት ዕድገትና ሥልጣኔ አንፃር ሲታዩ ወደ ኋላ የመቅረታቸው ምክንያት ከልማዳዊ አሠራር መላቀቅ አለመቻላቸው ነው፡፡ ለተማረና ለሠለጠነ የሰው ኃይል የሚሰጠው ትኩረት እዚህ ግባ የማይባል በመሆኑ ብዙዎች የተሻለ ፍለጋ ጥለዋቸው ሄደዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት አመራሮች ቢለዋወጡም ተገቢው ዕውቀት፣ ክህሎትና ልምድ ባለመኖሩ ብዙዎቹ ተቋማት እንደሌሉ ይቆጠራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት አገር ተጎድታለች፡፡

ለአንድ አገር ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ ፍትሕ ነው፡፡ ፍትሕ ሊሰፍን የሚችለው የሕግ የበላይነት በተረጋገጠበት አገር ውስጥ ብቻ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በመጥፋቱ ግን ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው ሹማምንትን ይለማመጣሉ፡፡ የተጻፈ ሕግ ባለበት አገር ውስጥ ያልተጻፈ ሕግ የበላይ ይሆናል፡፡ ሕግ የዜጎች መብትና ጥቅም ማስከበሪያ መሆን ሲገባው፣ ማጥቂያ መሣሪያ እየሆነ ብዙዎችን አሳር አሳይቷል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሕግ ፊት እኩልነታቸው መረጋገጡ በሕገ መንግሥቱ ቢሰፍርም ይህ እየተጣሰ በርካታ በደሎች ደርሰዋል፡፡ ፍትሕ እንደ ሸቀጥ በገንዘብ እየተሸጠ ንፋስ አመጣሽ ባለሀብት ደሃውን ቀልዶበታል፡፡ ባለ ጉልበቱ አቅመ ደካማውን አጥቅቶበታል፡፡ መብቴ ይከበርልኝ ያለው ሰንሰለት ጠልቆለታል፡፡ ይህ ዓይነቱ የታሪክ ምዕራፍ ተዘግቶ ኢትዮጵያውያን በሕግ ፊት እኩልነታቸው ሊረጋገጥ የግድ ይላል፡፡ ባለ ሀብቱ በገንዘቡና በሚመካበት ባለሥልጣን ተማምኖ እንዳሻው የሚሆንባት አገር ቅራኔን በማባባስ የበለጠ አመፅ ትጋብዛለች፡፡ በብሔርና በእምነት እየተቧደኑ ፍትሕን መናድ ካልቆመ እየታየ ያለው አንፃራዊ ሰላም ይደፈርሳል፡፡ ለአገር የማይጠቅሙ ድርጊቶች ይቁሙ፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በፈለጉበት ሥፍራ የመዘዋወር፣ የመኖርና ሠርተው ሀብት የማፍራት መብታቸው በሕግ የተረጋገጠ ቢሆንም አሁንም ችግሮች አሉ፡፡ የገዛ ወገናቸውን እንደ ባዕድ ወራሪ ኃይል የሚመለከቱና በጭካኔ የሚያፈናቅሉ፣ የአገር አንድነትና ኢትዮጵያዊ ማንነት ምንም የማይመስላቸው፣ ራሳቸውን በክልል ማንነት አጥረው ሰፋ አድርገው ማገናዘብ የቸገራቸው በአገርና በሕዝብ ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ዓይቶት የማያውቀው ጥላቻ በዚህ ዘመን ሲቀነቀን መስማት ያሳፍራል፡፡ ከልዩነት ይልቅ ለአንድነት ትልቅ ቦታ ሰጥቶ አገሩን ከአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች በመከላከል ደማቅ ታሪክ ያለው አስተዋይና ጀግና ሕዝብ በበቀለባት ኢትዮጵያ፣ ሕዝብን በብሔርና በእምነት ለመከፋፈል በሚዳዳቸው ቅስቀሳ በርካታ ግፎች ተፈጽመዋል፡፡ አሁንም የገዛ ወገናቸውን የብሔሬ አባል አይደለህም በማለት ከኖረበት ቀዬ እየዘረፉ የሚያፈናቅሉ አሉ፡፡ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥን አሳፋሪ ድርጊት ሲፈጸም፣ ክልሎችን ከሚመሩ ጀምሮ እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ እንዳላየና እንዳልሰማ ሲታለፍ ያስገርማል፡፡ ይህ ዓይነቱ የአውሬ ድርጊት ለታሪካዊቷ አገር ኢትዮጵያና ለአስተዋዮቹ ኢትዮጵያዊያን አይመጥንም፡፡

ሰሞኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነስቷል፡፡ ለማንም ጤነኛ ሰው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መኖር እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ እዚህ ጣጣ ውስጥ ከአንድም ሁለቴ የተገባው ባለፉት ሦስት ዓመታት ባጋጠሙ ተቃውሞዎች ምክንያት ቢሆንም፣ ቀደም ባሉት ዓመታት መንግሥት በፈጸማቸው አጉል ድርጊቶች መሆኑ ግን ሊሰመርበት ይገባል፡፡ መንግሥት ሕዝብን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት አገሪቷ ከባድ ቀውስ ውስጥ ገብታ ነበር፡፡ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በርካቶች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ብዙዎች የእስራት ሰለባ ሆነዋል፡፡ መጠኑ በውል የማይታወቅ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ደግሞ ጊዜያዊ አንፃራዊ ሰላም የተገኘ ቢመስልም፣ በሕዝብ ላይ በግልጽ የታዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ የአገሪቱ የቱሪዝም፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ኪሳራ አጋጥሟቸዋል፡፡ ታይቶ የማይታወቅ የውጭ ምንዛሪ ዕጦት አጋጥሟል፡፡ የዋጋ ግሽበት ከነጠላ ወደ ድርብ አኃዝ ተሸጋግሯል፡፡ ይህ ሁሉ ፈተና ያጋጠመው ሕዝብን በአግባቡ አዳምጦ ላቀረባቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዘለቄታ ያለው ሰላም እንደማያመጣ በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ሕዝብ በሚፈልገው መንገድ እየተጓዙ ዘላቂ ሰላም ማረጋገገጥ ብቻ ነው፡፡ ለአገር የሚበጀውም ይኼው ብቻ ነው፡፡

አሁን ኢትዮጵያ ለዚህ ዘመን የሚመጥን አስተሳሰብ ነው የሚያስፈልጋት፡፡ ይህ አስተሳሰብ ከየትኛውም አቅጣጫ ሊመጣ ይችላል፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ ግን ተወዳዳሪና የሕዝብ ቀልብ መግዛት መቻሉ ነው፡፡ ሕዝብ ደግሞ የተሻለውን ሐሳብ የሚወስደው ለአገር ካለው ጥልቅ ፍቅር አንፃር ስለሆነ፣ ከየቦታው የተቃረመ ዘመን ያለፈበት ርዕዮተ ዓለም በማቀንቀን ማደናገር አይቻልም፡፡ በተለይ ለዚህ ትውልድ የማይመጥኑና ፖለቲካዊ ፋይዳቸው እዚህ ግባ የማይባሉ አጀንዳዎችን ተሸክሞ መዞር ለባለቤቱም ጥቅም አይሰጥም፡፡ ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት የነገሠባት፣ ፍትሕ የሚናኝባት፣ ዴሞክራሲ የሚለመልምባት፣ ሰብዓዊ መብት የሚከበርባት፣ ሁሉንም ልጆቿን በእኩልነት ማስተናገድ የሚቻልባትና ልክ እንደ ታላቁ የዓደዋ ድል አሁንም አርዓያ መሆን የምትችል የነፃነት አገር እንድትሆን የጋራ መግባባት ሊኖር ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ ለአገር የማይጠቅምና ሕዝብን ማዕከል ያላደረገ አጀንዳ ማራመድ እርባና የለውም!