Skip to main content
x
የቀኝ ክንፍ ፖለቲካና የስደተኞች ዕጣ ፈንታ
ጣሊያን ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችና ደጋፊዎቻቸው ፀረ ስደተኛ አቀንቃኞችን ለማውገዝ ሰላማዊ ሠልፍ አድርገዋል

የቀኝ ክንፍ ፖለቲካና የስደተኞች ዕጣ ፈንታ

በፓሪስ ከተማ የሚገኝ አንድ ሕንፃ አራተኛ ፎቅ ላይ አንድ ሕፃን ልጅ ተንጠልጥሎ ያየ አንድ ዜግነት ገና ያላገኘ ስደተኛ ማሊያዊ፣ በሕንፃ ግድግዳ ላይ እየተንጠላጠለ ወጥቶ ሊወድቅ የተቃረበውን ሕፃን ያድነዋል፡፡ ይኼንንም ሲመለከቱ የነበሩ ሰዎች ድርጊቱን በስልካቸው ቪዲዮ በመቅረፅ ያስቀሩታል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያው በስፋት የተዘዋወረው የዚህ ማሊያዊ የጀግንነት ድርጊት ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዘንድ ይደርስና በአድናቆት ተሞልተው አስጠርተው ቢሯቸው ያገኙታል፡፡ እንደ ሽልማትም ዜግነትና በአገሪቱ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል ተቋም ውስጥ ሥራ እንዲያገኝ ያደርጉታል፡፡

ይህ ክስተት ምን ያህል ስደተኞች እንደሚስፈልጉ፣ ለሚሄዱባቸው አገሮች ጥቅም ሊያስገኙ የሚችሉ ሰዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያሳየ እንደሆነ በመጥቀስ በሰፊው ተዘግቧል፡፡

ሕልማቸውን አውሮፓና አሜሪካ ግፋ ሲልም ካናዳ አድርገው የትውልድ ቀዬአቸውን ጥለው የሚሰደዱ ወጣቶች አማካይ ዕድሜያቸው 31 እንደሆነ፣ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ተቋም (IOM) በሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ከእነዚህ ወጣቶች ግን ከሜዲትራንያን ባህር ማዶ ያለ የሕልም አገር ሳይደርሱ ብዙዎቹ በባህር ሰጥመውና የበረሃ እባብ ሲሳይ ሆነው ይቀራሉ፡፡

የቀኝ ክንፍ ፖለቲካና የስደተኞች ዕጣ ፈንታ
የጣሊያን ቀኝ አክራሪ ፋይቭ ስታር ሙቭመንት ፓርቲ መሪ  ወጣቱ ሉዊጂ ዲ ማርዮ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ

 

ከዚህ አስከፊ ክስተት አምልጠው አውሮፓ ለመድረስ የዓረብ አገሮችን ረግጠው ባህር ለሚሻገሩ ስደተኞች ያለሙትን ማግኘት እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም፡፡ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከአፍሪካ አገሮች ለሚተምሙ ስደተኞች በሚደርሱባቸው፣ በተለይ እየተቀያየረ በመጣው የዓለም ፖለቲካ፣ ይልቁንም እየጠነከረ በመጣው የቀኝ ክንፍ ፖለቲካ አራማጆች ምክንያት በእጅጉ አስከፊ እየሆነ መጥቷል፡፡

የቀኝ ክንፍ ፖለቲካ ምንነት ላይ ጥርት ያለ የትርጉም ስምምነት ባይኖርም፣ በብዛት ፖለቲከኞቹ ፀረ ስደተኛ የሆነ አስተሳሰብ የሚያራምዱ፣ ለብዙኃን ተስማሚ የሆኑ አስተሳሰቦችን የሚያንፀባርቁ እንደሆኑ አጠቃላይ ትርጓሜ ይሰጣል፡፡ ይህ በተለይ በአወሮፓ የሚገኙ የቀኝ ዘመም ፖለቲከኞችን ለመግለጽ ቢውልም፣ በሌላ ሥፍራ ያሉ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ፖለቲከኞችን ለመግለጽም ይውላል፡፡

የቀኝ ክንፍ ‹‹ሕዝበኛ›› (Populist) ፖለቲካ የሚያራምዱ አካላት እንቅስቃሴ ከተጀመረ እጅግ የቆየ ቢሆንም፣ ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው በፖለቲካ ፓርቲ ደረጃ መቋቋም የጀመሩት ግን እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ መጀመርያ አካባቢ አንስቶ ነው፡፡ በተለይ በአውሮፓ አገሮች ከፍተኛ ሥፍራን እያገኙና ተቀባይነታቸውም በተለይ በተራው ማኅበረሰብ ዘንድ እየሰፋና እያደገ መጥቶ፣ በተለይ ላለፉት አሥርት ዓመታት በጉልህ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ በሚደረጉ የምርጫ ፉክክሮች የማይናቁ አማራጮች ሆነው ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ይሁንና በምርጫ አሸንፈው ሥልጣን ለመያዝ በሚንቀሳቀሱባቸው በሁሉም አገሮች ማለት በሚያስችል ሁኔታ የነበራቸው ድጋፍ በቂ አልነበረም፡፡ ሆኖም ከሦስት ዓመታት ወዲህ የእዚህ ዓይነት አስተሳሰብ አራማጆች በጉልህ የፖለቲካ ሥልጣን እየያዙ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ ሥልጣን መቆጣጠር ባልቻሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ ጥምር መንግሥታትን ለመመሥረት፣ አልያም አነስተኛ ቁጥር ያላቸውም ቢሆኑ የፓርላማ ወንበሮችን ለመያዝ እየቻሉ ነው፡፡

የቀኝ ክንፍ ፖለቲካና የስደተኞች ዕጣ ፈንታ
የጣሊያን ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ

 

የዚህ አንዱ ማሳያ እ.ኤ.አ. በ2016 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞችን እየተሳደቡና እያንቋሸሹ መንበረ ሥልጣን መጨበጥ የሚያስችላቸውን ድምፅ ማግኘታቸው ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በመጀመርያው ዓመት የሥልጣን ጊዜያቸው የወሰዱት ትልቁ ዕርምጃ ተደርጎ የሚጠቀሰውም፣ በተለይ ከሙስሊም አገሮች ወደ አሜሪካ የሚገቡ ዜጎች ላይ ገደብ መጣላቸው ነው፡፡ ቀጥሎም ምንም እኳን ግልጽ የድርጊት መርሐ ግብር ስለሌለው ተፈጻሚነት ሊገኝ አልቻለም እንጂ፣ በአሜሪካና በሜክሲኮ ድንበር ላይ ሊገነባ የታሰበው የድንበር አጥር ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሥልጣን በያዙ ማግሥት በአውሮፓ ያሉ ተመሳሳይ ዓላማ ያነገቡ ግለሰቦች ወደ ምርጫ ፉክክሮች በሙሉ ኃይል መምጣት ጀምረዋል፡፡ ይሁንና ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያን ጨምሮ ሌሎች ከአሜሪካ በኋላ ምርጫ ያካሄዱ የአውሮፓ አገሮች እንደዚህ ዓይነት ክስተቶችን አስተናግደዋል፡፡

በፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ቀኝ አክራሪዋን ማሪን ሊፒን ማሸነፋቸው፣ በጀርመንም ቻንስለር አንገላ መርከል መንግሥት ለመመሥረት ድምፅ ያሳጧቸውንና የጥምር መንግሥት እዲመሠርቱ ካደረጓቸው የቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች ጋር ተፋልመው በስተመጨረሻም መንበረ ሥልጣናቸውን ሳይለቁ መቆየታቸው የቀኝ ዘመም ፖለቲካ ተስፋ የሌለው ጎራ ሆኑ እንዲታይ አድርጎ ነበር፡፡ በተመሳሳይም በኔዘርላንድስ፣ በቡልጋርያ፣ በማልታ፣ በእንግሊዝ፣ በአውስትሪሊያና በቼክ ሪፐብሊክ የተካሄዱ ምርጫዎች የቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች መሸነፍ በተለይ ለአውሮፓ ኅብረት ደጋፊ አቀንቃኞች ዕፎይታን የፈጠረና የቀኝ ክንፍ ፖለቲከኞች መዳከም አመላክቷል ተብሎ የታሰበ ክስተት ነበር፡፡

ነገር ግን ቁጥሮች እንደሚያሳዩት፣ ምርጫ በተደረገባቸው የአውሮፓ አገሮች የቀኝ ክንፍ ፖለቲከኞች የሚያገኙት ድምፅ በመቶኛ እያደገ መጥቷል፡፡ ይሁንና ሰሞኑን በጣሊያን የተደረገው ምርጫ ይዞት የመጣው ውጤት፣ እነዚህ አመለካከቶች ምን ያህል መሠረተ ቢስ እንደነበሩና የስደተኞችን ተስፋ የሚያጨልም ክስተት ነበር፡፡

በጣሊያን መንግሥት የመሠረቱት የፋይቭ ስታር እንቅስቃሴና ሰሜናዊው ሊግ (ሊግ) መሪዎች ሉዊጂ ዲ ማርዮና ማቲዮ ሳልቪኒ መመረጥ ምክንያት ስደተኞች ለሥጋት መጋለጣቸው እየተነገረ ነው፡፡ የፋይቭ ስታርስ እንቅስቃሴው መሪ ሳልቪኒ በፌስቡክ ገጻቸው በለቀቁት ቪዲዮ አማካይነት አገሪቱን ከወንጀለኞች እንደሚያፀዷትና የቀድሞው መንግሥት ለስደተኞች ማስተናገጃ ያስቀመጠውን የ50 ሚሊዮን ዩሮ በጀት እንደሚያስወግዱ ተናግረዋል፡፡

በሃንጋሪም የተደረገው ምርጫ በተመሳሳይ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር፡፡ ይባስ ብሎም በእንግሊዝና በፈረንሣይ ያሉ ስደተኞች ከፍተኛ ግፊት እየደረሰባቸው ሲሆን፣ ፈረንሣይ የሚገኙ ስደረኞች በጊዜያዊነት ይዘውት የነበረው የመጠለያ ጣቢያ እንዲፈርስ መደረጉ አገሮቹ ለስደረኞች ያላቸው ትዕግሥት እየተሟጠጠ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት እነዚህን ስደተኞች የሚቃወሙና ለማስወገድም እንሠራለን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኙ መጥተዋል፡፡ 

የቀኝ ክንፍ ፖለቲካና የስደተኞች ዕጣ ፈንታ
በጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ የሚመራው የመጀመርያው ‹‹ሕዝበኛ›› (Populist) መንግሥት ቃለ መሃላ የፈጸመበት ሥነ ሥርዓት