Skip to main content
x
ሕይወት በጠባቧ ጎጆ
ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው የአቶ ድሪባ ሠቦቃ ልጆች

ሕይወት በጠባቧ ጎጆ

የልጆች መኝታ ክፍል የምታክለው ትንሿ ጎጆ ቤት ሚናዋ እንደ ትልቅ የሀብታም ቪላ ነው፡፡ እንደ ከብቶች ማደሪያ፣ የአዋቂዎችና የልጆች ማደሪያ፣ ዕቃ ቤት፣ ማብሰያ ጓዳና የዘር ማስቀመጫ ጎተራም ነች፡፡ ሊነጋጋ ሲል የቤተሰቡ አለኝታ የሆኑት ከአንድ ግርግም የሚያድሩት በጎች ዕደጅ ወጥተው ሣር እንዲግጡ ሲደረግ ጎጆዋ በትንሹም ቢሆን እፎይ ትላለች፡፡ መሬት ላይ የሚነጠፈው ትልልቅ ትራስ የሚመሳስሉት ሁለት የሣር ፍራሾች ሲነሱ ደግሞ መተንፈሻ ይገኛል፡፡

     ችግሩ የኤሌክትሪክ ምድጃ አልያም የከሰል ማንደጃ በማታወቀው ጠባቧ ጎጆ ውስጥ ጉልቻ ጥዶ በጭስ እየተጨናበሱ ምግብ ማብሰል ሲጀመር ነው፡፡ ይህም ቢሆን የዘወትር ኑሯቸው ለሆነው ለእነ አቶ ድሪባ ሰቦቃ የጉልቻው ጢስ የማይቋቋሙት ደመኛቸው ሳይሆን ቤተኛቸው ነው፡፡

     በግድግዳው ዙሪያ የተሠራው መደብ መሳይ ነገር እንደ መንደርደሪያ ሆኖ ያገለግላቸዋል፡፡ ዳንቴል ጣል የተደረገበት ያረጀው መሶብ ባረጀው በርሜል አናት ላይ ተቀምጧል፡፡ ሊጡ በወጉ ያልታጠበለት ሌማታቸው፣ ጀሪካን፣ ዘምቢል፣ ያረጁ የሣር ፍራሾችና ሌሎችም ወደ አንድ ጥግ ታጉረዋል፡፡ ግድግዳውም በአንድ ጥግ ያደፈ መዘፍዘፊያ፣ የቡና ምጣድና የአቶ ድሪባ የክት ኮፍያ ተሰቅሎበታል፡፡

     አቶ ድሪባ ሞፈርና ቀንበር አልያም ጥማድ በሬ የላቸውም፡፡ ከግርጌያቸው ሆነው ሌሊቱን ሙሉ ሲያመነዥጉ የሚያድሩ በጎችን እንኳን በስጦታ ያገኙት እንጂ በጥረታቸው ያገኙት አይደለም፡፡ ቤታቸው በእርሻ የተከበበ ይሁን እንጂ የኔ የሚሉት የሚያርሱት ቦታ የላቸውም፡፡

      ከአሰላ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ዲገሉናጢጆ ወረዳ የዲገሉ ቦራ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ድሪባ ሕይወታቸውን የሚመሩት መሬት ላላቸው ሰዎች ተቀጥረው እያረሱ በሚያገኙት ጥቅም ነው፡፡ ባለቤታቸውም ቢሆኑ በዚህ የገጠር መንደር ተዘዋውረው እንጀራ እየጋገሩ በሚያገኙት መጠነኛ ገንዘብ ገቢያቸውን ለመደጎም ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ከእጅ ወደ አፍ ለሆነው ኑሯቸውን ተስፋ የምትዘራበት የ13 ዓመቷ ሴት ልጃቸው ነች፡፡ ተስፋ የጣሉት በማህደር (ስሟ ተቀይሯል) ላይ ቢሆንም ድህነት ሳይበግራቸው እስካሁን አምስት ወልደዋል፡፡

      ‹‹በእንቅርት ላይ…›› እንዲሉ ከሁለቱ ልጆቻቸው በስተቀር ሦስቱ ልዩ እንክብካቤ የሚሹ አካል ጉዳተኞች ናቸው፡፡ ዘንድሮ 18 ዓመት ይሞላት የነበረችውን የመጀመሪያ ሴት ልጃቸው የተወለደችው ከአካል ጉዳት ጋር ነበር፡፡ ስትወለድ ጀምሮ የዓይን ብርሃን የላትም፡፡ መራመድ አትችልም፡፡ ትስማ አትስማ ግን እርግጠኛ አይደሉም፡፡ ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያደበዘዘው የልጃቸው የዝምታ ዓለም ከድህነታቸው ጋር ተደምሮ ከባድ ቢሆንም ሌላ ልጅ ከመውለድ አላገዳቸውም፡፡

      ባለቤታቸው ወ/ሮ ጫልቱ አበራ ሁለተኛ ልጃቸውን ፀነሱ፡፡ ስትወለድ ግን ልክ እንደ መጀመሪያ ልጃቸው ከተደራራቢ የአካል ጉዳት ጋር ነበር፡፡ ትንሿ ልጅ እንደ እህቷ አታወራም፣ አትንቀሳቀስም፣ አትሰማም፣ የሚያበሏት፣ የሚያጠጧት፣ ሽንት ቤት የሚወስዷት ወላጆቿ ናቸው፡፡

      ቀጥሎ የተወለደችው ማህደር ግን ጉዳት አልባ ሆና ተወለደች፡፡ የማህደር ጉዳት አልባ መሆን ለወላጆቿ ትልቅ የምስራች ቢሆንም ለሷ ግን ጫናው የበረታባት ስለመሆኑ ገፅታዋን አይቶ መገመት አይከብድም፡፡ ድህነት ከሥራ ጫና ጋር ተጋግዘው ልጅነቷን የነጠቋት ማህደር ወደ መቀንጨር ያለች፣ ብርድና ፀሐይ የተፈራረቀባት ገፅዋ የተጎሳቆለ ነው፡፡ ደረቷ አካባቢ የተቀደደው ቀሚሷ የደረቷን አጥንት ያስቆጥራል፡፡ እንደ ነገሩ የተጎነጎነው ሹሩባዋና እጇ አመድ መስለዋል፡፡ የተጫማችው አሮጌ ኮንጎ ጫማ የቅያሪ ያለህ ቢልም ከእጅ ወደ አፍ የሆነው የእነ ወ/ሮ ጫልቱ ገቢ ለማህደር ቅያሪ ኮንጎ ለመግዛት የሚፈቅድ አይደለም፡፡

       ያለሰዎች ዕርዳታ መንቀሳቀስ፣ ምግብ መብላትም ሆነ መናገር የማይችሉ ታላላቆቿን እንዲሁም ትንሹ ወንድሟን የመንከባከብ ኃላፊነት በልጅነቷ የተጣለባት ማህደር የየዕለት ውሎዋ ከማዕድ ቤት ወደ ትምህርት ቤት በሚደረግ ሩጫ የተሞላ ነው፡፡ እኩዮቿ አባሮሽ ሲጫወቱ እሷ ደቂቃዎችን እያባረረች ወደ ሥራ ትቀይራቸዋለች፡፡ የልጅነት ደስታ የራቀው የማህደር ፊት የተከፋ ነው፡፡

     ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው እህቶቿ የፀሐይ ብርሃን ነክቷቸው አያውቅም፡፡ እንደ ነውረኛ ቤት ውስጥ ተደብቀው ይውላሉ ያድራሉ፡፡ ፀሐይ ነክቶት የማያውቅ ቆዳቸው እንደ ማህደር የተጎሳቆለ ሳይሆን ባህር ማዶ እንደሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ቆዳ ጥርት ያለ ነው፡፡ በእግራቸው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ባይኖርም መቆምና መራመድ ባለመልመዳቸው ቁጭ ብለው ይውላሉ ያድራሉ፡፡

       እግራቸውም ልክ እንደ አራስ ልጅ ያልጠነከረና እንደ ቲማቲም የቀላ ነው፡፡ ቢርባቸው፣ ቢጠማቸው፣ ቢያማቸው፣ ሽንት ቤት መሄድ ቢያምራቸው ብስጭትጭት ይላሉ ያለቅሳሉ፡፡ “ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወደ ደጅ የወጡት ከወራት በፊት ነበር፡፡ የፀሐይ ብርሃን የማያውቁት እነዚህ ተደራራቢ የአካል ጉዳት ሰለባ የሆኑት ልጆች በሁኔታቸው ተደናግጠው ያለቅሱ ነበር፡፡

      ፀሐይም ሆና ብርድ መቋቋም የማይችል ሰውነታቸው ውጪ ሲወጡ ክፉኛ ይንቀጠቀጣል፣ የፀሐዩን ብርሃን መቋቋም ስለማይችሉም ፊታቸውን በእጃቸው ሸፍነው እንደ መጮኸ ይላሉ፡፡ የመንደሩ ነዋሪዎች እነሱን እንደ ትንግርት ሲመለከቷቸው ማህደር ታዝናለች፡፡ ክፉና ደጉን ያላየው እንደ ማህደር ከጉዳት ነፃ ሆኖ የተወለደው ትንሹ ወንድማቸው እሱም እንደ ጎረቤቱ እህቶቹን በግርምት ቆሞ ያያቸዋል፡፡ በተለይ ከወራት በፊት በድንገተኛ ሕመም ስለሞተች ትልቋ እህቷ ስትጠየቅ እንባ ይይዛታል፡፡ ምን እንዳመማት የምታውቀው ነገር ባይኖርም “ሆስፒታል ተወስዳ በንጋታው ነው የሞተችው” ትላለች፡፡  

       የተሰአት ተማሪ የነበረችው ማህደር እህቶቿን ከመንከባከብ ጎን ለጎን ቤቱን አፀዳድታ ጨርሳለች፡፡ ክዳኑ ሳይቀር ጥላሸት በበላው ድስት የምትሠራው ወጥም ለምሳ ደርሷል፡፡ የቀራት ነገር ቢኖር እንደነገሩ ተጣጥባ በ30 ደቂቃ ውስጥ ወደ ትምህርት ቤት ለመድረስ መሮጥ ነበር፡፡

      ምቾት የማያውቀው የእነማህደር ሕይወት በድጋፍ ለማቅናት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ እንዲህ ባለ በድህነት አረንቋ ውስጥ የሚገኙ ድሆችን ማኅበረሰቡን በማስተባበር የዕለት ጉርስ እንዳይቸገሩ ሲያልፍም የመቋቋሚያ ድጋፍ እንዲሰጣቸው እየተደረገ ይገኛል፡፡ አቶ በዻዻ ወርቁ በዚህ ሥራ የተሰማራው “የእኛ ለእኛ ዕርዳታ” ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ድጋፉ የሚገኘው ከዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይሆን አቅሙ ያላቸውን የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስተባበር ነው፡፡

       በዓይነትና በገንዘብ የሚደረገው ድጋፍ ተረጂዎችን ከድህነት የማውጣት አቅም ባይኖረውም የሚበሉት አጥተው እንዳይራቡ ያደርጋሉ፡፡ እንደ ማህደር ላሉ ቤተሰቦች በጎችን ገዝቶ በመስጠት አራብተው እንዲጠቀሙ ይደረጋል፡፡ በወርልድ ቪዥን አስተባባሪነት የተጀመረው የእኛው ለኛ ፕሮግራም በዲገሉና ጢጆ በሚገኙ 18 ቀበሌዎች የሚገኙ ተጋላጭ ልጆችን ለይቶ መሥራት ከጀመረ ሁለት ዓመታት ማስቆጠሩን የሚናገሩት በወርልድ ቪዥን የሕፃናት ከለላ ፕሮግራም አስተባባሪዋ ወ/ሮ ቤተልሔም ጥላሁን ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ቀበሌ የሚገኙ ከ50 እስከ 70 የሚደርሱ ሕፃናትን ለይቶ የማገዝ ወላጆቻቸውንም መርዳቱ የዓመት የሕክምና አገልግሎት፣ ቀለብ፣ አልባስና ሌሎችንም መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላትን እንደሚያካት አስተባባሪዋ ገልፀዋል፡፡