Skip to main content
x

ተፈናቃይ አርሶ አደሮች አክሲዮን ማኅበር መሠረቱ

ከአዲስ አበባ ከተማ በተለይም ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በልማት ምክንያት የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች አክሲዮን ማኅበር አቋቋሙ፡፡

‹‹ፊንፊኔ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችና ዳያስፖራዎች ንግድ›› የሚል ስያሜ ያለው አክሲዮን ማኅበር የተቋቋመው በ180 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሲሆን፣ በ40 ሔክታር መሬት ላይ በተለያዩ ዘመናዊ የግብርና ምርቶች ለመሰማራት እየተዘጋጀ ነው፡፡

      አሥራ አምስት የልማት ተፈናቃዮች ያቋቋሙት አክሲዮን ማኅበር በጥምር የከተማ ግብርና፣ በሪል ስቴትና በስፖርት መስክ ኢንቨስትመንት ውስጥ በስፋት የመግባት ዕቅድ አውጥቷል፡፡ የፊንፊኔ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችና ዳያስፖራዎች ንግድ አክሲዮን ማኅበር ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ለሚ ታዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቅርቡ የአክሲዮን ሽያጭ በይፋ ይጀመራል፡፡

      ነገር ግን አክሲዮን ማኅበሩ ከወዲሁ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ተግዳሮቶች እየገጠሙት መሆኑን አስታውቋል፡፡ ማኅበሩ በመጀመሪያው ሥራው  እንቅስቃሴ የጀመረው በክፍለ ከተማው ወረዳ አንድ ሀንሰም ግላስ ፋብሪካ አጠገብ ባለው 40 ሔክታር መሬት ላይ ነበር፡፡

      በዚህ ቦታ ላይ የሚገኙ 80 የሚጠጉ አርሶ አደሮችን በማስተባበር አፕልና ካዝሚርን ጨምሮ የተለያዩ የግብር ምርቶችን ማልማት ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ክፍለ ከተማው ቦታውን ለሌላ ልማት የሚፈልገው መሆኑን በመግለጽ ሲፈናቀሉ የቆዩ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ሊያፈናቅል መሆኑ ተገልጿል፡፡

      ይህ የክፍለ ከተማው አካሄድ ያልተዋጣለት አዲሱ አክሲዮን ማኅበር ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ማክሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ይዞታው ላይ ምንም ግንባታ እንዳይገነባና ወደ ሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ አስወስኗል፡፡

      የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ አባል ጂሬኛ ግንዳቦ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አክሲዮን ማኅበሩ በቦታው ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን በሚፈቅደው መሠረት የትኛውንም ግንባታ ለማካሄድ አቅም አለው፡፡

          በአዲስ አበባ ከተማ በልማት ምክንያት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ተፈናቅለዋል፡፡ በእርግጥ አርሶ አደሮቹ ከቦታቸው በሚነሱበት ወቅት ተለዋጭ ቦታና ካሳ የሚከፈላቸው ቢሆንም፣ ተለዋጭ ቦታው ለእርሻ ሥራና ለኑሮ አመቺ አለመሆንና ካሳውም አነስተኛ በመሆኑ በርካታ አርሶ አደሮች ለከፍተኛ ችግር ሲዳረጉ መቆየታቸው ይገለጻል፡፡

      አዲሱ ማኅበር ተፈናቃይ አርሶ አደሮች በቢዝነስ ሥራዎች ተሰማርተው ራሳቸውን እንዲያቋቁሙ፣ ብሎም ከሚያውቁት የግብርና ሥራ ሳይርቁ ሥራ እንደሚፈጥር አስታውቋል፡፡