Skip to main content
x
‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በኢሕአዴግ አመራሮች የተለመደውን የፖለቲካ ሰዋሰውና መዝገበ ቃላት ቀይረዋል›› አቶ አበባው አያሌው፣ የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ታሪክ መምህርና ተመራማሪ

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በኢሕአዴግ አመራሮች የተለመደውን የፖለቲካ ሰዋሰውና መዝገበ ቃላት ቀይረዋል›› አቶ አበባው አያሌው፣ የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ታሪክ መምህርና ተመራማሪ

አቶ አበባው አያሌው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት ክፍል ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2002 ዓ.ም. በታሪክ መምህርነት ሠርተዋል፡፡ ከ2003 ዓ.ም. በኋላ እስካሁን ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበባትና ዲዛይን ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ ታሪክና በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ታሪክ በመምህርነት እያገለገሉ ናቸው፡፡ አቶ አበባው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በታሪክ ትምህርት፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሥነ ጥበብ ታሪክ አግኝተዋል፡፡ በአብዛኛው በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ታሪክ ጥናት ላይ እየሠሩም ነው፡፡ አቶ አበባው ከመምህርነታቸው ባሻገር በአገሪቱ ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አመለካከት በማንፀባረቅም ይታወቃሉ፡፡ ወቅታዊውን የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ የታየው አለመረጋጋትና አሁን ችግሩን ለመፍታት እየተኬደበት ያለውን መንገድ እንዴት ያዩታል?

አቶ አበባው፡- በአገሪቱ ውስጥ የነበረው ችግር ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የታየው ብቻ አይደለም፡፡ ችግሮቹ ለ26 ዓመታት የቆዩ ናቸው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት አዲስ ነገር ተፈጥሮ አይደለም የፖለቲካ ግጭቶች የጦዙትና እንደገናም ባልተጠበቀ መንገድ ወደዚህ መፍትሔ የተመጣው፡፡ ለ26 ዓመታት የፖለቲካ ውዝፍ ነበረብን፡፡ አገሪቱ ወደ ፌዴራል ሥርዓት ገብታለች፡፡ ወደ ፌዴራል ሥርዓት ስትገባ ተያይዘው በጥንቃቄ መታየት የነበረባቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡ በየወቅቱ ደግሞ መፍትሔ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች በደንብ ሳይጤኑ፣ ውለው አድረው ችግር ያመጣሉ ሳይባል እንዲሁ ተጓተው የመጡ ችግሮች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

አቶ አበባው፡- አንደኛው በክልሎች ያሉ የድንበር ውዝግቦች አሁን ወይም የዛሬ ሦስትና አራት ዓመታት አይደለም የተነሡት፡፡ ቆይተዋል፡፡ እነዚያ ችላ እየተባሉ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በጊዜ የሚያስፈልገውን ድርድር በክልሎች መካከልም ሆነ በፌዴራል በኩል አለመወሰዱ ጭምር ያመጣው ነው፡፡ ክልል ሲካለል እንዲህ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የሕዝብ ይሁንታ ያስፈልገዋል፡፡ ተጠቃሚውም ተጐጂውም ሕዝቡ ነው፡፡ ከመጀመሪያውም የክልል አከላለሎች የዘፈቀደ ናቸው፡፡ ሕዝብ በደንብ የመከረበት መሆን አለበት፡፡ ሁሌም እንደምናየው ይህ አካባቢ የእኔ ነው፣ ይኼ ወረዳ ለእኔ ይገባል፣ ይኸኛው ቀበሌ ለእኔ ይሰጥ እያሉ የሚቆራቆሱ ብዙ አሉ፡፡ የእነዚያ ፍላጐትና ይሁንታ ከመጀመሪያውኑ አልተጤነም ነበር፡፡ እናም ከመጀመሪያ መፈታትና ለሕዝብ ውይይት ቀርቦ ይሁንታዎች ማግኘት ሲገባ፣ የተደረገው የፖለቲካ ኃይሎች ብቻ ተሰባስበው ክልሎች ተከለሉ፡፡ ዘፈቀ የምንለው ይህ ነው፡፡ ዝም ብሎ በይምሰል፣ በይሁን ብቻ የተደረገ ነው፡፡ በሌላው የመብት ጥያቄ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ በአብዛኛው ስለግለሰብ ሐሳብ የመግለጽ መብት፣ የመደራጀት መብት፣ በነፃ የመሰብሰብ መብትና እንዲህ ያሉ የፖለቲካ መብቶችን የሚሰጡ አንቀጾች ተቀምጠዋል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት እንዴት ነው የተተገበረው? ምን ዓይነት መብት ሰጥቷል? በሕገ መንግሥት የተቀመጠን ነገር መተግበር ሲገባና እየተሻሻለ መምጣት ሲገባው እየባሰ ነው የሄደው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በተለይ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ እየባሰ እንጂ እየተሻሻለ አይደለም፡፡ የፕሬስ ነፃነትም እንዲሁ ነው፡፡ የተናገረና የተቸ ጋዜጠኛ፣ እንዲሁም አስተያየት የሰጠ ሁሉ እየታደነ እስር ቤት ይገባል፡፡  

ሕገ መንግሥቱ የሚሰጣቸው የግለሰብና የፖለቲካ መብቶች እየተጓተቱ መሻሻል ሲገባቸው ድሮ ከነበረው የበለጠ መታፈን እየቀጠለ ሄደ፡፡ መጨረሻ ላይ የፖለቲካ ምኅዳሩ ጭራሹን የፖለቲካ ሐሳብን በሰላማዊ መንገድ ማንሸራሸር አቃተው፡፡ በሰላም ጥያቄ የማቅረብ፣ የፖለቲካ፣ የግለሰብ መብትና ማንኛውንም ዓይነት ጥያቄ በሰላም የሚያስተናግድ የፖለቲካ ምኅዳር ከሌለ የሕዝብ አማራጭ የሚሆነው ሕጉ በእጄ ነው የምፈልገውን አደርጋለሁ የሚል ነው፡፡ በኦሮሚያ የታየው ይህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሕጉ በእጄ ነው የሚለው ከምን መነሻ ነው?

አቶ አበባው፡- ሕጉ በእጄ ነው ማለት ይኼ ሕግ ለእኔ የማይሠራ ከሆነ፣ የፖለቲካ ሐሳቤንና መብቴን ለማራመድ ጊዜና ቦታ የማይሰጠኝ ከሆነ የፈለግኩትን አደርጋለሁ ነው፡፡ ድንጋይ አስቀምጬ መንገድ እዘጋለሁ፣ ድንጋይ እወረውራለሁ፣ እንዲሁም ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ ማንኛውንም ነገር እያደረግኩ ጥያቄ አቀርባለሁ ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት የታዩት ያለፉት ዓመታት ውዝፍ ጉዳዮች ውጤት ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ውዝፍ ጥያቄዎች አመጡት የተባለው ለውጥ የተፈለገውን ውጤት እያመጣ ነው? ወይም አምጥቷል ማለት ይቻላል? አሁን መጣ የተባለው ለውጥ እንዴት ይታያል? ከሕዝቡ ፍላጐት ጋር የተጣጣመ ነው?

አቶ አበባው፡- አሁንም ለውጥ ብለን ለመናገር የሚያስደፍር ሁኔታ ላይ አይደለንም፡፡

ሪፖርተር፡- ለውጥ መጥቷል ለማለት የሚያስደፍርበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ አበባው፡- አንደኛው የተቀየረው ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ወደሚቻልበት መንገድ እየተጓዝን ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ለውጥ ተብሎ በአብዛኞቹ የሚጠየቀው ከዚህ በፊት በፖለቲካ አመለካከታቸው ወይም በፖለቲካ ተሳትፏቸው ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን መፍታት አንድ ለለውጥ መነሳሳት ነው፡፡ የነበረውን የጦዘና የተካረረ የፖለቲካ አየር ይፈታዋል፡፡ አሁን እንግዲህ ያየነው እሱን ነው፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከመጡ በኋላ ያየነው ይህንን ነው፡፡ ግን የለውጥ ዕርምጃዎቹ ገና ናቸው፡፡ የለውጥ ዕርምጃ የምንላቸው አንደኛ ከዚህ በፊት የፖለቲካ ምኅዳሩን ያጣበቡ አዋጆችና የፖለቲካ ዕርምጃዎችን እንደገና በማጤን ማሻሻል ሲደረግባቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የትኞቹ አዋጆችን ማለትዎ ነው? የፖለቲካ ዕርምጃዎች የሚያስፈልጓቸው የትኞቹ ጉዳዮች ናቸው?

አቶ አበባው፡- አንደኛው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ነው፡፡ ይህ አዋጅ የፖለቲካ አመለካከትንና ሽብርተኝነትን የሚያምታታ ነው፡፡ ለተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የፖለቲካ ተሳትፎን የሚያበረታታ አይደለም፡፡ ሰውን ወደ መሸማቀቅና ወደ ፍርኃት ነው የወሰደው፡፡ ስለዚህ ትልቁ የለውጥ ዕርምጃ መሆን ያለበት የተዘጉ የፖለቲካ በሮችንና የተዘጉ የፖለቲካ መድረኮችን መክፈት ነው፡፡ ይኼ ከሆነ ትልቁ ነገር ተሳትፎ የገደቡና በር የዘጉ አዋጆችን እንደገና ማየት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሁለቱ አዋጆች የግድ መከለስ አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ሁለተኛው አዋጅ የቱ ነው?

አቶ አበባው፡- ሁለተኛው የሲቪል ማኅበረሰብ አዋጅ ነው፡፡ የሲቪል ማኅበራት ከመንግሥታዊ ተቋማት በበለጠ ለዴሞክራሲ መስፈንና ለሐሳብ መንሸራሸር ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ወይ ከተባለ የሕዝብን ንቃተ ህሊና ለማሳደግና (አድቮኬሲ) በመሳሰሉት ጀምረውት የነበረው ሥራ ነበር፡፡ ዴሞክራሲ አድቮኬሲን ይጠይቃል፡፡ መዋቅራዊ ዴሞክራሲ አይሠራም፡፡ ምክንያቱም በየትም አገር ብንሄድ መንግሥት ለዴሞክራሲ መጎልበት ሊያደርገው የሚችለው ሁለት ነገሮች መስጠት ነው፡፡ አንደኛው የመንግሥትን መዋቅር አሳታፊ ማድረግ፣ ሁለተኛው ወካይ ማድረ ነው፡፡ ከእነዚህ ውጪ መቻቻል፣ መግባባትና የመሳሰሉት የሚመጡት በኅብረተሰቡ ነው፡፡ በኅብረተሰቡ የሚመጡ ከሆነ ደግሞ የሲቪል ማኅበራት ትልቅ ሚና አላቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የዚህም አዋጅ ተከልሶ የጠበበው የፖለቲካ ምኅዳር መስፋት አለበት፡፡

በአጠቃላይ ለሕዝብ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴም ሆነ ለግለሰቦች ፖለቲካዊ አስተዋጽኦ መሠረት ሊኖራቸው የሚችለው፣ ከዚህ በፊት በተለይ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የመጡ አዋጆችን እንደገና መከለስ ያስፈልጋል፡፡ መጀመሪያውን እነዚህ አዋጆች ሲረቁና ሲሳቡ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማጥበብ ሆን ተብለው የተፈጠሩ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ የግድ በሽብርተኝነት መፈረጅ የለባቸውም፡፡ እኔ መቼም አሸባሪ የፖለቲካ ድርጅት እዚህ አገር ውስጥ አለ አልልም፡፡ ብረት ያነሳ የፖለቲካ ድርጅት አሸባሪ ሊባል አይችልም፡፡ ብረት ወደ ማንሳት የሄደው ሰላማዊው መንገድ ስለተዘጋበት ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት በውጭም ያለ ሊሳተፍበት የሚችል የፖለቲካ ምኅዳር መፈጠር አለበት፡፡ ሌላው ደግሞ የእስረኞቹ መፈታት ለምን መባል አለበት፡፡ ብዙ ሰዎች ለረጅም ጊዜ ታስረው ነበር፡፡ ከእነዚህ እስረኞች ገዘፍ ያለ የፖለቲካ ዕውቅና ያላቸውም አሉ፡፡ ለምሳሌ እነ መራራ ጉዲናን፣ አንዳርጋቸው ጽጌን፣ በቀለ ገርባ መውሰድ እንችላለን፡፡ ጋዜጠኞችም ተፈትተዋል፡፡ ግን ስም የሌላቸውና የማይታወቁ፣ በየምክንያቱ ወይም በሚያቀርቡት የፖለቲካ ጥያቄ ምክንያት በየቀበሌው፣ በየወረዳው አንተ የእከሌ ፓርቲ አባል ነህ፣ ደጋፊ ነህ ተብለው የታሰሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በእርግጥ እየተፈቱ ያሉ አሉ፡፡ ግን አሁንም ያልተፈቱ አሉ፡፡ መፍታት ብቻ ግብ ነው ወይ? ሰዎችን መፍታት ለመነጋገር መሆን አለበት፡፡ ለመወያየት መሆን አለበት፡፡ የታሰሩት በስርቆት ወንጀል አይደለም፡፡ በነፍስ ማጥፋት አይደለም፡፡ የታሰሩት በፖለቲካ አቋማቸው ነው፡፡ ይኼ ከሆነ እነዚህን ሰዎች ፈትቶ አንድ ነገር ማስከተል ያስፈልጋል፡፡ ይህም አገራዊ የሆነ የፖለቲካ መግባባትን ሊፈጥር የሚችል ድርድር ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ነፃ በሆነ መንፈስ መሆን አለበት እንጂ የይስሙላ ድርድር መሆን የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ከእስር መልቀቅ ትልቅ ዕርምጃ ቢሆንም ከዚህ ጎን ለጎን ግን እርስዎ እንደጠቀሱት ቀጣይ ድርድሮችን ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉም አሉ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ወደ ድርድር ለመግባት የሚያሳዩ ምልክቶችም እየታዩ ነው ይባላል፡፡ ለምሳሌ የእነ አቶ ሌንጮ ለታ መምጣት፣ አቶ አንዳርጋቸውን ፈትቶ ቤተ መንግሥት ጠርቶ ማነጋገርና የመሳሰሉት ጉዳዮች ሲታዩ፣ መንግሥት ድርድር ስለመሻቱ ምልክት ናቸው ይባላልና የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

አቶ አበባው፡- በእርግጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁኔታ ወደዚያ ይመስላል፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የሚሳተፉበትን መድረክ መፍጠርና መግባት ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ እስካልሆነ ድረስ ግን እርግጠኛ ልሆንበት አይችልም፡፡ ግን ተጨባጭ ምልክቶች ናቸው፡፡ አሁንም ግን ሁለት ነገሮችን ማሰብ አለብን፡፡ እነ አቶ ሌንጮ መጥተዋል፡፡ ነገ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ማለትም በወጣቱ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች መጨመር አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ? ሊጠቅሱልኝ የሚችሉት እነ ማንን ነው?

አቶ አበባው፡- ይህንን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሲመሩ የነበሩ የውጭ የፖለቲካ አክቲቪስቶችን መውሰድ እንችላለን፡፡ አሁን እየተፈጠረና እየተግለበለበ ባለው የአማራ ብሔርተኝነት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ አክቲቪስቶች በውጭ አሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ እነዚህም መሳተፍ አለባቸው፡፡ እነዚህ እንደ አንድ የፖለቲካ ኃይል መወሰድ አለባቸው፡፡ እነዚህን ነው አዳዲስ ኃይሎች የምላቸው፡፡ ምክንያቱም አንደኛ የወቅቱን መንፈስ ሊያስረዱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ከእነዚህ ጋር መግባባት ለወደፊቱ ትልቅ ኃይል ይሆናል የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡ ሌላው በእውነት የአገር ውስጥ ፖለቲካውን ስንወስደው፣ እንዲያውም በእርቅና በስምምነት ላይ ከተወሰኑት በስተቀር ሌሎቹን እንደ ፓርቲ ልናያቸው የምንችላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ መኢአድ፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ ኅብረት፣ ኦፌኮና የመሳሰሉት ድርጅታዊ አቋም ያላቸው ናቸው፡፡ ስም መጥቀስ ባያስፈልግም አንዳንዶቹ በግለሰብ ብቻ የቆሙ ናቸው፡፡ ድርድር ሲባል ሁልጊዜ ቀድመው የሚገኙትና ወንበር ላይ የሚሰለፉት እነዚህ ድርጅታዊ አቋም የሌላቸው፣ አንድ ግለሰብ ብቻ ከላይ የሚታይባቸው ናቸው፡፡ እነዚህን እንደ ፓርቲ መጀመሪያ ሊያስቀጥል የቻለ የምርጫ ሕግ መፈተሽ አለበት፡፡ ይህ ከጀርባው መሰሪነት ያለ ይመስላል፡፡ ስለዚህ የአገር ውስጥ የፖለቲካ ድርጅት ሲባል ሚዛን የሚደፉት የትኞቹ ናቸው ብሎ መፈተሽ አለባቸው እንጂ፣ ዝም ብሎ 94 ፓርቲዎች አሉ ማለቱ አያዋጣም፡፡ ጽሕፈት ቤት የሌለው ፓርቲ እኮ አለ፡፡ ምርጫ ቦርድ እንዴት ዕውቅና እንደሚሰጣቸው ግራ በሚገርም ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የአገር ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ ሲባል በሆደ ሰፊነት ለይስሙላ ያሉትን ይዞ እሹሩሩ ማለት ሳይሆን፣ እውነተኛ ድርድር ሁነኛ በሚባሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና በሕዝብ ልብ ላይ ተስፋን በፈጠሩ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስተር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የአብዛኛውን ሕዝብ ድጋፍ አግኝተዋል የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር መሆናቸው የተዘነጋ ይመስላል፡፡ እሳቸው የሚናገሩትን ነው እየሰማን ነውና የሚመሩት ኢሕአዴግ ምን እየሆነ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ አበባው፡- እንግዲህ ትልቁ ነገር የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች የሚሳተፉበት፣ ሁሉም ተቻችሎ ሕዝብና ኢትዮጵያን ብቻ ዋና መሠረት አድርጐ መደራደር ይገባል፡፡ ይህ የሁሉም ስሜት ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይ. . . ዶ/ር ዓብይ ቢባልም ያው የኢሕአዴግ አባልና ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ትልቁ ፈተና የሚሆነው ኢሕአዴግ ውስጥ ገና ያልተሠራ የቤት ሥራ መኖሩ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በዚህ ወቅት የኢሕአዴግ ትልቅ የቤት ሥራ ተደርጐ የሚወሰደው ምንድነው? የአራቱ ዋና ዋና ድርጅቶችስ ሚና እንዴት ይታያል? ቀጣይ ጉዟቸውስ?

አቶ አበባው፡- አራቱን ድርጅቶች ስንወስዳቸው ገና ያልተሠራ የቤት ሥራ እንዳለ እናያለን፡፡ ኦሕዴድ ተራማጅ ኃይሎችን ፈጥሮ ለለውጡ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከሞላ ጎደል በኦሮሚያ ሕዝብ ዘንድ ይጠላ የነበረው ኦሕዴድ፣ በሌሎች የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች በጥርጣሬ ሲታይ የነበረው ኦሕዴድ ለሕዝቡ ቆሞ ሕዝቡን ማሠለፍ ችሏል፡፡ እንደገና ከሌሎች ተቀባይነት ከነበራቸው በተለይ ከኦነግ የበለጠ ሕዝባዊነት አግኝቷል፡፡ ስለዚህ በኢሕአዴግ ውስጥ የመደራደር አቅሙ ትልቅ ነው ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ መሪዎቹም በክብ ጠረጴዛ እኩል መብት ኖሮን እንከራከር እንጂ፣ ከላይ እንደፈለጋችሁ የምትሸነቁጡንና በሉ ዝም በሉ አፋችሁን ያዙ የምትሉን አይደለንም ወደሚል ደረጃ ደርሰዋል፡፡ ይኼን ዓይነቱ ለውጥ በብአዴን ውስጥ እየተፈጠረ ነው፡፡ ምክንያቱም ብአዴን ከመጀመሪያው ጀምሮ እንዲያው የሕወሓት የክርስትና ልጅ ነበር የሚመስለው፡፡ እውነት አመራሮቹም እንዲያው ከአማራ ሕዝብ የወጡ ናቸው ወይ? በማለት ሕዝቡ ጥያቄ ያነሳ ነበር፡፡ አሁን የማንነት ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያነሳ የለም፡፡ ሌላው እንግዲህ ከፌዴራል ሆኖ እንደገናም ከብአዴን ፓርቲ በላይ ሆኖ ሲሸነቁጥና ሲቆነጥጥ የነበረው ኃይል አሁን እየተዳከመ እየመጣ ነው፡፡

ይህ ከሆነ ብአዴንም በአጭር ጊዜ ኦሕዴድ የደረሰበት እንደሚገኝ የማይቀር ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የብአዴንም ጥያቄ እኩል እንደራደር፣ የምንፈልገውን ፓርቲ እንደግፋለን ወደሚል መጥቷል፡፡ በተለይ አሁን እየጠነከረ የመጣውን የአማራ ብሔርተኝነት ይዞ የሚሄድ ይመስለኛል፡፡ ባለፈው በተደረገው የኢሕአዴግ ምርጫም የምንፈልገውና የሚያግባባን ነገር ካለ አንድ ላይ ብንሠራ ወደሚል እየመጡ ይመስላል፡፡ ሕወሓት በአንፃሩ ልክ እንደተፈጠረ ቁጭ ብሏል፡፡ አንደኛ አዳዲስ የፖለቲካ ኃይሎች ያልተፈጠሩበት ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ ብንወስድ ያኔ ትግል ላይ የነበሩና ባለፉት 27 ዓመታት በፓርቲ ውስጥ ተፅዕኖ ሲፈጥሩ የነበሩ ግለሰቦችን ብቻ ነው የያዘው፡፡ አንድ ሁለት ሰዎች እንኳን ቢኖሩ ይኼን ያህል ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሕወሓት ካለው የአገሪቱ ንፋስ ጋር፣ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እኩል ሊጓዝ አልቻለም፡፡ ደኢሕዴን ምናልባት ውሎ አድሮ ኦሕዴድና ብአዴን የተጓዙበትን መንገድ ሊከተል ይችላል፡፡ ይኼ ማለት እንግዲህ ዞሮ ዞሮ ኢሕአዴግ የምንለው ፓርቲ ለውጥ ፈላጊዎችና ለውጥ አያስፈልግም በጥንቃቄ እንሂድ የሚሉ ይታያሉ፡፡ አሁን ሰሞኑን እንሰማ እንደነበረው የፖለቲካ አካሄዱ ፈር ለቋል የሚሉ አሉ፡፡ አይ የፖለቲካ አካሄዱ ትክክል ነው የሚሉ አሉ፡፡ የፖለቲካ አካሄዱ ፈር ለቋል፣ መስመር ለቋል የሚሉ አሉ፡፡ ትክክል ነው የፖለቲካ አካሄዱ እንዲህ እንዲሆን ነው የሚፈለገው የሚሉ አሉ፡፡ ዶ/ር አብይ ከለውጥ ፈላጊዎቹና አዲስ የፖለቲካ መስመር፣ አዲስ የፖለቲካ ግብና ስትራቴጂ መከተል አለብን የሚሉ ዓይነት ሰው ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ለዘመናት ሲመራበት የነበረውን ማዕከላዊነትንም ይህንን ያህል ከቁብ የቆጠሩት አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ደፈር ያሉ ብርቱ ውሳኔዎችን እየወሰኑና እንዲወሰን ተፅዕኖ እያደረጉ ይመስለኛል፡፡ ይኼ የፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትና ውሳኔዎችን በጋራ የማስተላለፍ ነገርም ውሎ አድሮ ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ አሁን ትልቁ ነገር ኢሕአዴግ ምን ያህል ወደ አዲስ ነገር ይጓዛል የሚለው ነው፡፡      

ሪፖርተር፡- የእርስዎ ግምት ምንድነው?

አቶ አበባው፡- እንደ ትንበያ ከተወሰደ አንደኛው ነገር ሕወሓት ውሎ አድሮ መቀየሩ አይቀርም፡፡ መቀየር የግድ ነው፡፡ አንድን ፖለቲካዊ ስትራቴጂ፣ አንድን ፖለቲካዊ መስመር (መስመር የምለው ርዕዮተ ዓለም ስለማይሉ ነው) ይዞ ያለ ለውጥ መቆየት አይችልም፡፡ ስለዚህ ለአርባ ዓመት የተጠቀመበትን ፖለቲካዊ ባህል፣ ፖለቲካዊ ስትራቴጂና መስመር የሚባለውን ርዕዮተ ዓለም አሁን ሊቀጥልበት አይችልም፡፡ ካልቻለ ደግሞ የግድ በውስጡ ከሌላው ለውጥ ፈላጊና አዲስ የፖለቲካ ፍኖት ከሚፈልገው ኃይል ጋር ሊተባበር የሚችል ኃይል መፈጠር አለበት፡፡ ደግሞም የግድ ይፈጠራል፡፡ የትውልድም ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕወሓትን የፈጠሩትና በኋላም በአምሳያቸው የቀረፁት ሰዎች በጊዜያቸው ጠንካራ ፖለቲከኞች ነበሩ፡፡ ግን እዚያው ቀርተዋል፡፡ አሁን ላሉት ለውጦች ዝግጁ ይሆናሉ ወይ? አይሆኑም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰፊ የለውጥ ፋና ወጊ በመሆን አገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ የመምራት፣ በተለይ ሊያናቁሩ የሚችሉ አንገብጋቢ የሆኑ የፖለቲካ ጉዳዮችን ለምሳሌ የብሔር ፖለቲካን በጊዜ አክሞና አስታሞ አገሪቱ ወደ ጥሩ መንገድ እንድትገባ የማድረግ ዕድል የነበረው እንደ ኢሕአዴግ ያለ ማንም አልነበረም፡፡ የነበሩትን ጦርነቶች ስናስባቸው በጣም ትንሽ ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ ይህንን ማድረግ ካልቻለ መለወጥ አለበት፡፡ ስለዚህ አሁን ትልቁ ነገር ኢሕአዴግ ምን ያህል ዶ/ር ዓብይ ወደፈለጉት የለውጥ አቅጣጫ ይጓዛል የሚለው ነው፡፡ ተወደደም ተጠላ ወደዚያ ሊጓዝ ይችላል፡፡  

ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ አሁን ለውጥ ላይ ነው የሚለውን የሚቀበሉም የማይቀበሉም አሉ፡፡ ኢሕአዴግ ቀድሞ ከነበረው አካሄዱ ተለውጧል፣ ወይም ይለወጣል ተብሎ ቢታመን እንኳ አዲሱ ገጽታውን ይዞ ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ሊኖረው የሚችለው ግንኙነት ምን ዓይነት ይሆናል? ቀጣዩ ምርጫ እንዴት ይሆናል ብለው ይገምታሉ?

አቶ አበባው፡- ሁልጊዜ የእኔም ጥያቄ ይኼ ነው፡፡ መደራደር ሊኖር ይችላል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችን ይቅር እያሉ ማምጣቱ ይቻላል፡፡ በኢሕእዴግ ውስጥ የዴሞክራሲ ባህል እስካሁን ጫፉም አልታየም፡፡ ዓብይ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ በሕወሓትም፣ በኦሕዴድም፣ በብአዴንም ሆነ በደኢሕዴን ሥልጣንን ለሌላ ፓርቲ አሳልፎ መስጠት አይደለም ፍላጎት ይታሰባል ወይ? እሱ ነው ትልቁ ጥያቄ ለእኔ የሚሆነው፡፡ በአገሪቱ መረጋጋት ሊኖር ይችላል፣ የፖለቲካ መብቶች ተግባራዊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ግን ቁልጭ ያለ እኩል መድረክ ተፈጥሮ በእኩል መወዳደርና ሽንፈትን መቀበል ሊኖር ይችላል ወይ ነው? በ2012 ዓ.ም. የሚደረገው ምርጫ የዚህ ጥያቄ መፍቻ ነው፡፡ እንግዲህ በሚቀጥለው ዓመት ብዙ የፖለቲካ ኃይሎች ሊመጡ ይችላሉ፡፡ መድረኮችም ሊከፈቱ ይችላሉ፡፡ ግን ኢሕአዴግ ውስጥ የሥልጣን ነገር ከህልውና ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ዴሞክራሲያዊ ሰብዕና ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በአመለካከቱ ላሸነፈ ሥልጣን ብንሰጥስ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ግን ኢሕአዴግ የመንግሥት መዋቅሩን ይዞታል፡፡ መዋቅሩን መያዝ ብቻ ሳይሆን፣ የአንዳንድ ሰዎች ህልውና ከኢሕአዴግ ሥልጣን መያዝ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የሚያስቸግር ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን አባባል ሊያፍታቱልኝ ይችላሉ?

አቶ አበባው፡- ይህንን በቀላሉ ላስረዳህ፡፡ ኦሕዴድን እንውሰድ፡፡ በየአስተዳደሩ ያለው የኦሕዴድ አባል ነው፡፡ ኦፌኮ ነገ ልትወዳደር ትችላለህ ተብሎ ቢወዳደር ካድሬው ኦፌኮ የሚወድቅበትን መሰናክል ነው እንጂ የሚፈልገው እኩል እንወዳደር አይደለም የሚለው፡፡ አንተም ኦሮሚያ ውስጥ የምትንቀሳቀስ ፓርቲ ነህ፣ እኔም ኦሮሚያ ውስጥ የምንቀሳቀስ ፓርቲ ነኝ ብለው እኩል እንወዳደር አይሉም፡፡ ምክንያቱም ለእነዚያ ሰዎች እንጀራቸው ነው፡፡ አሁን ፖለቲካን ከሥራና ከሌሎች ጉዳዮች አላላቀቅነውም፡፡ አንዱ የኢሕአዴግ መውደቅ ህልውናዬ ነው ይልሃል፡፡ የቀበሌው ሊቀመንበርም እንዲህ ሊል ይችላል፡፡ ከዚህ ባለፈ የፖለቲካ ሥርዓታችንና ሕይወታችን እንዲሁም ኢኮኖሚው አንድ ላይ ተጋብተዋል፡፡ ስለዚህ የኦሕዴድ አባላት ኦፌኮ ይወዳደር እንጂ በምንም ሁኔታ አንድ ወረዳ እንዲያሸንፍ አይፈልግም፡፡ ምክንያቱም ሥራ የሚለው እዚያ ያለው ነው፡፡ እናም ትልቁ ፈተና ለኢሕአዴግ ነው የሚሆነው፡፡ ሥልጣን እንካችሁ የሚሉት የበላይ አመራሮች ቢወስኑ እንኳን፣ በዞንና በቀበሌ ያለው ካድሬ የህልውና ጉዳይ አድርጐ ይወስደዋል፡፡ እናም መሟገታቸው አይቀርም፡፡  

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለው አመለካከት የሚለወጥበት ዕድል ሊኖር አይችልም?

አቶ አበባው፡- እንግዲህ አንደኛ ቀስ በቀስ መሄድ ነው፡፡ ለምሳሌ በ1997 ዓ.ም. ያመለጠ ነገር አለ፡፡ እንኳን በአብዮታዊ መንገድ በምርጫ እንኳን ቢሆን ሥርዓት መለወጡ ይጎዳል፡፡ ለምሳሌ ማንኛውም የፖለቲካ ኃይል ይመጣና ሙሉ በሙሉ ምርጫ አሸንፎ ይችን አገር እረከባለሁ ቢል እንኳን ከኢሕአዴግ ጋር አብሮ እየሠራ ካልሆነ ሌላ ችግር ውስጥ ነው የሚገባው፡፡ ሌላ ፈተና አለው፡፡ ጎን ለጎን እኩል የመጓዝ ነገሮች መኖር አለበቸው፡፡ በ1997 ዓ.ም. ቅንጅት አዲስ አበባን ቢወስድ ኖሮ የመቆራቆስም አብሮ የመሥራት ዕድልም ይኖረው ነበር፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ይህንን ከያዘ ነው እያሳደገ፣ እያሳደገ የሚሄደው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የፖለቲካ ባህሉ ከላይ የተወካዮች ምክር ቤትን ይዤ ሥልጣን እይዛለሁ፣ ከዚያ ሁሉን ነገር በአንድ ጊዜ እመነጣጥራለሁ ማለት ሳይሆን፣ ወረዳ ላይ ካሸነፍክ ያቺን ወረዳ እንዳለ ይዘህ መቆየት እንጀራና ፖለቲካ የተጋባትን ነገር ፈታ እያደረገው ይመጣል፡፡ አዲስ የፖለቲካ ባህል መለመድ አለበት፡፡ ሰው በሙያው ይቀጠር፡፡ እንዳለ የመንግሥት ሠራተኛ ፖለቲከኛ መሆን፣ አባል መሆን የለበትም፡፡ በደርግም ጊዜ አስተማሪው፣ ዳይሬክተሩ የአንበሳ ግቢ ሥራ አስኪያጅ፣ ስፖርተኛው ሁሉ የፓርቲ አባል ነበር፡፡ አሁንም እንዲህ ነው፡፡ እንዲህ መሆን ግን የለበትም፡፡ ፖለቲከኞቹ ለፖለቲካው ሥራ ብቻ ይሁኑ፣ ሌላው ሙያተኛ በፖለቲካ መሾም የለበትም፡፡  

ሪፖርተር፡- አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እያራመዱት ያለው ሐሳብና ንግግራቸው ከዚህ ቀደም ከታዩት የኢሕአዴግ አመራሮች የተለየ ነው፡፡ እንደ እሳቸው ሊናገር የሚችል ወይም በእሳቸው አስተሳሰብ ሊራመድ የሚችሉ አመራሮች በዙሪያቸው የለም የሚሉ አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የእሳቸው ብቻ እንዲህ መሆን የተዘበራረቀ ስሜት ይፈጥራል ይላሉ፡፡

አቶ አበባው፡- እንግዲህ ዶ/ር ዓብይ በፖለቲካ ንግግራቸው ለየት ያሉ ይመስላሉ፡፡ እውነትም የተለዩ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በኢሕአዴግ አመራሮች የተለመደውን የፖለቲካ ሰዋሰውና መዝገበ ቃላት ቀይረውታል፡፡ በማይታመን ሁኔታ ነው የቀየሩት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አገራችን እንጂ ኢትዮጵያ የሚል እንኳ ካፋቸው አይወጣም ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዲያው አገር የመወድድ ወደ ሕዝብ የማዘንበል አዝማሚያ ቢታይባቸውም፣ እሳቸውም የተለመደውን የፓርቲ ቋንቋና የፓርቲ ሰዋሰው ነው ሲናገሩ የነበሩት፡፡ የዶ/ር ዓብይ ለየት የሚለው እዚህ ላይ ነው፡፡ እውነትም ጠንካራ የፖለቲካ ሰብዕና ያላቸው ይመስለኛል፡፡ ባህሉን ለመለወጥ የሚሞክሩ ይመስለኛል፡፡ ይህንን ለምንድነው ብለን ያለውን የፖለቲካ ባህል መመልከት አለብን፡፡ አንድ ሰው የኢሕአዴግ አባል ሲሆን እንግዲህ ቀጥታ የሚገባው ኢንዶክትራሄሽን (መጠመቅ) ውስጥ ነው፡፡ በሥልጠናውና በመሳሰሉት ወደዚህ ይገባል፡፡ የፓርቲ አባል ይሆኑና ጓደኞቻችንም ሆኑ ሌሎች ሰዎች በሁለትና በሦስት ዓመት ውስጥ ሌላ ሰው ነው የሚሆኑት፡፡   

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ አበባው፡- አንደኛው አነጋገራቸው፣ ሁለተኛ ሐሳባቸውና ነፃ አመለካከታቸው ስለሚጠፋ ነው፡፡ ወደ ሥጋት የሚገቡም አሉ፡፡ ራሳቸውን ከኅብረተሰቡ የሚነጥሉ አሉ፡፡ እኚህ ሰው ከአፍላ ወጣትነታቸው ጀምሮ እስካሁን ድረስ ኢሕአዴግ ውስጥ ነው የነበሩት፡፡ በውትድርናም መስክ ቢባል ነበሩበት፣ በሌላው ዘርፍ ውስጥም ነበሩ፡፡ ያ ሁሉ የአንዶክትሬሽንና የሥልጠና ማዕበል አልወሰዳቸውም፡፡ ከነፃ መንፈሳቸውና የለውጥ አስተሳሰባቸው አዲስ ነገር ለመቀበል የተዘጋጁ እንጂ፣ የኢሕአዴግ መስመር ነው ትክክል ወደሚለው የገቡም አይመስለኝም፡፡ ይህንን መቋቋም አንደ ትልቅ የፖለቲካ ሰብዕና ነው፡፡ ምክንያቱም የሶሻሊስት ፓርቲዎችና ድርጅቶች ትልቁ የፖለቲካ ችግር ነፃነት ማጣት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ካነሳሱ ሶሻሊዝምን ባጠኑና የሙጥኝ ባሉ ሰዎች የመጣ ነው፡፡ የትም አገር ብትሄድ ሶሻሊዝም ከሊብራሊዝም ጋር ጠብ ነው፡፡ ለሶሻሊስት ፓርቲዎች ይኼ መስመር ብቻ ነው አማራጭ፣ ሌላ መስመር የለም ነው የሚሉት፡፡ ይህንን እዚህም ኢሕአዴግ ላይ ታይበታለህ፡፡ የዶ/ር ዓብይ ትልቁ የፖለቲካ ችሎታና ስጦታ ይህንን መቋቋምና ነፃ አዕምሮህን ይዘህ መቆየት ማለት ነው፡፡ ሰዎች በዙሪያቸው አሉ ወይ ብለን ስንመለከት ዓናይም፡፡ እንግዲህ ዶ/ር ዓብይን ሕዝብ ያወቃቸው በዚህ ዓመት ነው፡፡ የፖለቲካ ሰውም አልነበሩም፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ ቦታውም ያን ያህል የሚያስተዋውቅ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ቴክኖሎጂና ሳይንስ አፈር ድሜ በበላበት አገር የዚያ መሥሪያ ቤት ሚኒስትር ሆንክ ማለት ይህንን ያህል ታዋቂ አያደርግህም፡፡ ኦሮሚያ በነበሩበትም ወቅት ያን ያህል ታዋቂ አልነበሩም፡፡ ምናልበት በቅርብ የሚያውቁዋቸው ካልሆኑ በቀር፡፡ ነገር ግን ድንገት መጥተው ሁሉንም ነገር ሲቀያይሩ ትልቅ የፖለቲካ ሰው ነው የሆኑት፡፡ በእሳቸው ዙሪያ ያለውን ሰው አቅምና አመለካከት ግን እጠራጠራለሁ፡፡ ገና ቀስ ብሎ የሚመጣ ነው፡፡ በኦሮሚያና በአማራ አካባቢ በብአዴንና በኦሕዴድ የተወሰኑ ተደማጭነት እያገኙ፣ እንደገና አዲስ ለውጥ የመሻትና ጥሩ አማራጭ ካለ ያንን ይዘን የማንሄድበት ምክንያት የለም የሚሉ ሰዎችም አሉ፡፡ ግን ኢሕአዴግ ከምንለው ከዋናው ስብሰብ አንደኛ በአንደበቱ፣ ሁለተኛ በግርማ ሞገሡ፣ በአቋምም (የአቋም ፅኑነትን ይጠይቃል) ጠንከር ያለ ከኢሕአዴግ ሰዎች በዙሪያቸው ያለ አይመስለኝም፡፡   

ሪፖርተር፡- አሁን ባለው አካሄድ የአገሪቱን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል ብለው ያስባሉ? ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥልና የምትፈለገውን ኢትዮጵያ ለማየት ምን መደረግ አለበት?

አቶ አበባው፡- ትልቁ ነገር ምሕረት መስጠትን፣ ከፖለተካ አሳልፈን ዕርቅ ማውረድ ከጊዜያዊ ፖለቲካ መፍቻ አሳልፈን መመልከት አለብን፡፡ አንዳርጋቸው ተፈቷል፡፡ በቀለ ገርባና ሌሎችም ተፈተዋል፡፡ ነገር ግን ሌሎችን ፈልጎ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ በየእስር ቤቱ ብዙ አሉ፡፡ እውነቱን ለመናገር በዚህ አገር ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ኦነግ ነህ ተብሎ ብዙ ሰው ታስሯል፡፡ የሞተው ሞቷል፡፡ ግን በየእስር ቤቱ ፋይሉ ተረስቶ፣ ጉዳዩ ተረስቶ ዝም ብለው የተቀመጡ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ከክልላቸው ውጪም ተወስደው የታሰሩ አሉ፡፡ የፀረ ሽብር ሕጉ ከወጣ በኋላ ደግሞ በተለይ በአማራ ክልል የግንቦት ሰባት አባል ነህ ተብለው የታሰሩ አሉ፡፡ የእነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጉዳይ ለየት ያለ ስለሆነ ነው፡፡ ያልተፈቱ አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች መፈታት አለባቸው፡፡ የአቶ አንደርጋቸው መፈታት የፖለቲካ ጠቀሜታ አለው፡፡ ለኢሕአዴግ ይጠቅማል፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም ይጠቅማል፡፡ ከዚህ ባለፈ መፈታትን የእውነት እናድርገው፡፡ እነዚያን እስረኞች ከየእስር ቤቱ ፈልጎ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ቢቻል በአዋጅ ምሕረት መስጠት ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ሁለት ሦስት ስለተባለ የሚያልቅ ስለማይሆን ነው፡፡ ሁለተኛው የፖለቲካ ድርጅቶች የግል ፍላጎታቸውንና አቋማቸውን ትተው ለሕዝብና ለአገር ሲሉ ከግማሽ መንገድ በላይ መሄድ ይችላሉ፡፡ ለሕዝብና ለአገር ሲባል አንድ ስንዝርም አለመሄድ ይቻላል፡፡ አሁን የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው በአብዛኛው በሶሻሊስት ባህል ያደጉ ናቸው፡፡ ንባባቸውና ዕውቀታቸው ከመጀመሪያው ጀምሮ በዚህ የተቃኘ ነው፡፡ ስለዚህ የፓርቲ አቋም የሚለውን ነገር ከሕዝብና ከአገር ጋር አመዛዝኖ የፖለቲካ ስምምነት መፍጠር ይቻላል፡፡

ሕዝብና አገርን የሚጎዳ ከሆነ አንድ ስንዝርም አለመሄድ፣ ሕዝብና አገርን የሚጠቅም ከሆነና የፖለቲካ መሪዎችን ጉዳት ላይ የሚጥል ከሆነ ለምን 90 በመቶ ወደፊት አይኬድም? እንዲያውም ድርድር፣ ዕርቅ፣ አገራዊ ስምምነት ሲባል ሁልጊዜ መታሰብ ያለበት ለአገርና ለሕዝብ ያለው ፋይዳ ነው፡፡ ምክንያቱም የተሰቃየ ሕዝብ ነው ያለው፡፡ በደርግ ጊዜ አላረፈም፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜ እስካሁን አላረፈም፡፡ እፎይ ያላለ ሕዝብ ነው፡፡ እናም ሕዝቡን ታሳቢ በማድረግ መደራደር ሦስተኛውና ይጠቅማል ያልኳቸው ናቸው፡፡ ለዴሞክራሲ እንቅፋት የሆኑ የፖለቲካ ምኅዳሩን ያጠበቡ አዋጆችንና ሕጎች መሰረዝ ያስፈልጋል፡፡ ትልቁ ደግሞ የምርጫ ሕጉ ይሻሻል፡፡ የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ በሆነ አካል ይመራ፡፡ ሚናውን ይወጣ፡፡ ምናልባት ለተጀመሩት ነገሮች ይኼ ነው ለማለት ገና የወራት ዕድሜ ነው ያለው፡፡ የሚመሠገኑ፣ የሕዝብን አንጀት ያራሱ፣ የሁሉንም ህሊና ከጭንቀት የፈቱ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ መልካም ናቸው፡፡ ግን ይኼ ነው ለማለት ገና ብዙ ነገር ይቀራል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ይህች አገር አዲስ ነገር መጀመሯ የሚታወቀው እነዚህ ነገሮች ተስተካክለው በ2012 ዓ.ም. ለዴሞክራሲ ተስፋ ሊሰጥ የሚችል ምርጫ መካሄድ ሲችል ነው፡፡ ያኔ በሚገባ ልንገመግም እንችላለን፡፡