Skip to main content
x
‹‹ባለ ጋሪው››
በአሰላ ከተማ ውር ውር የሚሉት ጋሪዎች እንዲህ በየመንደሩ እየገቡ አገልግሎት ይሰጣሉ

‹‹ባለ ጋሪው››

ዓለም እንደ ወገብ ስፋቷ፣ መቀነቷ ርዝመት፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ዋልታ ያላት ርቀት በልኬት በማይታወቅበት የሰዎች ሕይወት በቴክኖሎጂ ባልቀለለበት በዚያ ዘመን ከአንዱ የሠፈር ጥግ ወደ ሌላው ለመጓዝ ቀናት ብሎም ወራት ሊፈጅ ይችል ነበር፡፡ ኩታ ገጠም በሚባሉ ግዛቶች መካከል እንኳ ከአንዱ ወደ ሌላው መልዕክት ለማድረስ በበቅሎና በፈረስ የሚደረገው ጉዞ አታካች ነበር፡፡ በአንድ ስልክ ጥሪ ብዙ ማለት ሲቻል ያኔ ግን ከወዲያና ወዲህ የሚደረገው የመልዕክተኞች ጉዞ መንፈቅ ሊፈጅ ይችላል፡፡

      መኪና፣ አውሮፕላን፣ ድሮን፣ ስልክ፣  ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ያሆና ጂሜይል የመሳሰሉት ዓለምን ወደ አንድ መንደርነት በመቀየሩ ረገድ የየድርሻቸውን እየተወጡ ያሉ ቴክኖሎጂዎች እንደልብ ባልሆኑበት ዘመን በትንሹም በትልቁም ስንቅ ቋጥሮ ጉዞ የተለመደ ነገር ነበር፡፡ በዚህ አድካሚ ጉዞ እንደ መኪና ነዳጅ፣ እንደ ኢንተርኔት መረብ መብራት የማይሉት አቀበት ቁልቁለቱን ሳይሉ ጢሻ በጥሰው ቁልቁለቱን ተንደርድረው፣ አቀበቱን አዝግመው የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩት በቅሎና ፈረስ የቀድሞ ኢትዮጵያውያን ባለውለታዎች ነበሩ፡፡

     በመኪናና በተለያዩ ተሽከርካሪዎች እስኪተካ ድረስ የፈረስ ግልቢያ ስፖርትም ትራንስፖርትም ነበር፡፡ ሙሽሮች የሚንሸራሸሩበት ቄንጠኛው ሰረገላ፣ በአንዴ እስከ ሦስት ሰዎችን ጭኖ ሰከም ሰከም የሚለው ጋሪም የዚሁ ትራንስፖርት ቅሪት ነው፡፡ ይህ የትራንስፖርት ዘርፍ ሲበላሽ የሚያድስ ጋራጅ፣ በየጊዜው አዲስ ሞዴል እያወጣ ደንበኛን የሚያቋምጥ ኩባንያ ሳያስፈልግ በተፈጥሮና በአንድ ፈረሰኛ ብልኃት የተቃኘ ነው፡፡ ሣር ሲግጥ የኖረን ፈረስ ከመግራት፣ የለገመን ፈረስ እስከ መለማመጥ የሚደርሰው የፈረሰኞቹ ተግባር እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትልልቅ ከተሞች የወጣ ይምሰል እንጂ በከተሞች ዙሪያና እንደ አሰላ ባሉ ከተሞች ደግሞ እንደዋነኛ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ ሆነው አሁንም ድረስ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡

     ተራራማ መልክዓ ምድር ላይ ጉብ ያለችውን የከተማዋን አውራ ጎዳናዎችና መንደሮች የሚጋልቡት ጋሪዎች የአሰላ ልዩ ገጽታ ናቸው፡፡ ወደ ታችና ወደ ላይ ሲሮጡ በየፈረሶቹ አንገት ላይ የሚታሰሩት ቃጭሎችና ኮቴያቸው ሙዚቃዊ ቃና ባይኖረውም ምቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ጋሪዎቹ ለከተማው ነዋሪዎች ዋነኛ መጓጓዣ እንደ አቤኔዘር ተስፋዬ ላሉ ባለጋሪዎች ደግሞ መተዳደሪያ ናቸው፡፡  

     ከደቂቃዎች በፊት በጣለው ዝናብ ጋሪው እንደ መርጠብ ያለው የ22 ዓመቱ አቤኔዘር ሥራ ጨርሶ ወደ ቤቱ ከመግባቱ በፊት አንድ ሁለት ጊዜ ተመላልሶ ተጨማሪ ገንዘብ ለመሥራት ላይና ታች ይላል፡፡ ሁለቱን ጎማዎች የሚጎትተው የአቤኔዘር ፈረስ ቀኑን ሙሉ ሲሠራ ውሎ ደክሞታል፡፡ ስለዚህም እንደ መሪ በሚያገለግለውና በፈረሱ አናት ላይ በታሰረው ገመድ እንዲንቀሳቀስ ምልክት ቢሰጠውም እንዳልሰማ እየሆነ ያስቸግረው ይዟል፡፡ መንቀሳቀስ የሚጀምረው አቤኔዘር ከጎኑ የሚያስቀምጣትን አለንጋ አንስቶ ለአመል ያህል ገረፍ ሲያደርገው ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ በየጉዞው መሀል አልታዘዝ እያለ መዞር ያለበት ቦታ አልዞር፣ ዳገትማ የሆነ ቦታን አልወጣ ብሎ ያሳብደዋል፡፡

      ትምህርቱን ከአሥረኛ ክፍል አቋርጦ ወደ ጋሪ ነጂነት የገባው አቤኔዘር የየዕለት ውሎው አመለኛ ከሆነው ፈረሱ ጋር እየታገሉ ገንዘብ መልቀም ነው፡፡ ወደ ጋሪ ሥራ ከመግባቱ አስቀድሞ መኪና ላይ ረዳት ሆኖ ይሠራ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ወደ እዚህ ሥራ ገባው በቅርቡ ነው፡፡ አይረባም የሚለው ከሲታ ፈረሱን በ2,000 ብር፣ ጋሪውን ከሰው ላይ በ12,000 ብር ነበር የገዛው፡፡ የፈረስ ዋጋ እንደየ ወቅቱ የሚዋዥቅ ሲሆን፣ ገበያው ጥሩ ነው በሚባልበት እንደ ዘንድሮው የሳቡሬ (ከከተማው ወጣ ብላ የምትገኝ ገበያ) ‹‹የማይረባ ፈረስ ከ800 ብር ጀምሮ ይገኛል፡፡ ምርጥ የሚባለው ደግሞ እስከ 4,000 ብር በጣም የተለየ ከሆነ ደግሞ እስከ 8,000 ብር ድረስ ይገኛል፤›› ይላል፡፡

     ከአምስት ብር በታች ጉዞ የለም የሚለው አቤኔዘር፣ በቀን ከወጪ ቀሪ ‹‹በልቼ ጠጥቼ 70 ብር እሠራለሁ፡፡ በየቀኑ 50 ብር ዕቁብ እከፍላለሁ ይላል፡፡›› መሀል መንገድ ደርሶ አልሄድ ብሎ ከለገመ ፈረሱ እየታገለ፡፡ የፈረሱን ምግብ ወደ ሚገዛበት ለመሄድ ገና አንድ ጉዞ የሚቀረው ቢሆንም አይረባም የሚለው ፈረሱ እልህ የያዘው ይመስላል፡፡ ለነገሩ ከጠዋት ጀምሮ ሲሠራ ስለቆየ እግሮቹ አልፈረጥጥ ቢሉ አይፈረድበትም፡፡

       ቀኑን ሙሉ ሲሠራ የሚውለው ፈረሱ በየመሀሉ ሣር አይግጥም ወይም ሌላም ምግብ አይሰጠውም፡፡ ምሣ አያውቅ መክሰስ የለው፡፡ ከኑን ሙሉ የሚውለው ሌሊቱን ሲበላ ባደረው ፉሩሽካ ኃይልና ቀን ላይ በሚጠጣው ውኃ ኃይል ነው፡፡ አንድ ኪሎ ፍሩሽካ በስምንት ብር እየገዛ የሚሰጠውን ፉሩሽካ ሌሊቱን እስከ አሥር ኪሎ ቡን አድርጎ ያድራል፡፡ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ውኃ ያጠጣውና ሥሩ በላሜራ መቀመጫው ደግሞ በሣር ፍራሽ የተደለደለውን ጋሪ ወደ መጎተት ይገባል፡፡ አቤኔዘርም ማልዶ ጋሪውን በትኩስ ኃይል ይዞ ይወጣል፡፡

     ‹‹ባለጋሪው ባለጋሪው

     ቶሎ ቶሎ ንዳው  . . .

     ተብሎ በአንድ ወቅት የተዜመላቸው እንደ አቤኔዘር ያሉ ባለጋሪዎች አሁንም ድረስ በአሰላ ከተማ ላይ ታች ሲሉ ይውላሉ፡፡ ትራንስፖርት በማያውቁ ጉራንጉሮች እየተንገጫገጩ፣ መንገድ የሌላቸውን ጢሻዎች እየበጠሱ በየትኛውም የከተማዋ ክፍሎች ውር ውር ይላሉ፡፡ ተሳፋሪዎች በማይመቸውን የጋሪው ወንበር ለመቆናጠጥ ይወራጫሉ፣ ሾፌሮቹ አመለኛ ፈረሶቻቸውን እያግባቡ፣ የሚንሸራተት ጎማቸውን ከአስፓልቱ እያስታከኩ፣ ከወዲያና ወዲህ የሚያማታቸውን የተቦረቦሩ የመንገድ እንቅፋቶችን በመላ እያለፉ ከመንገደኞች በሚለቅሙት ገንዘብ የዕለት ጉርሳቸውን፣ የዓመት ልብሳቸውን ሲያልፍ ደግሞ የነገ ህልማቸውን ዕውን ሊያደርጉ ማልደው ይወጣሉ፣ አምሽተው ይገባሉ፡፡

      መኪና የመግዛት ህልም ያላቸው እንደ ገመቹ በቀለ ያሉት ደግሞ በቀን የሚያገኙት ገንዘብ ትንሽ ጠርቀም እስኪል ላይ ታች ይላሉ፡፡ ገመቹ ወደ ጋሪ ሥራ ሲገባ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን እንኳን ሳያጠናቅቅ ነው፡፡ በሥራው ሰባት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ አራት እህቶች ያሉት ገመቹ ለቤተሰቡ አንድ ወንድ ነው፡፡ በሚያገኘው ገንዘብ አናጢ አባቱን፣ ከዚህም ከዚያ የሚገኘውን አብቃቅተው ቤተሰባቸውን የሚንከባከቡ የቤት እመቤት እናቱን ይደግፋል፡፡

     ከጠዋት 3 ሰዓት ጀምሮ እስከ 11፡30 አንዳንዴም እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ገፋ አድርጎ ፈረሱን ሲያሯሩጥ በቀን ከ100 ግፋ ሲል እስከ 300 ብር ድረስ ይሠራል፡፡ በቀን ይህንን ያህል ገቢ የሚያስገኝለት ፈረሱን እንደማንኛውም ባለጋሪ ሌሊቱን ሲበላ የሚያድረውን ፉሩሽካ ይገዛለታል፡፡ ለፉሩሽካ ብቻ በቀን 60 ብር እንደሚያወጣ የሚናገረው ገመቹ የተረፈውን ቀን እንደሚያበላው ሲናገር በኩራት ነው፡፡ ‹‹ብዙ ስለማሯሩጠው ቀኑን ሙሉ ቢሠራም ይህንን ያህል አይደክመውም፤›› ይላል፡፡

     ከሚያገኘው ገንዘብ ላይ በየሳምንቱ 300 ብር ዕቁብ ይጥላል፡፡ ከዚህ ቀደም በተከታታይ የወጡለትን ዕቁቦች ተከታትሎ ባንክ ያስገባ ሲሆን፣ በዚህኛው ዙር የሚወጣለትንም እንደዚሁ ወደ ባንክ ደብተሩ የሚያስገባት ሐሳብ አለው፡፡ በየቀኑ የሚያገኛትን ቁጥ ቁጥ ገንዘብ አጠራቅሞ ዕቁብ እየጣለና ወደ ባንክ በማስገባት የሚያገኘውን በዋዛ ፈዛዛ ላለማጥፋት በዚህ መልኩ ጥረት ያደርጋል፡፡ መኪና መግዛት የሚችል ገንዘብ እስኪጠራቀምለት መቆጠቡን አያቆምም፡፡ ጋሪውን በጥሩ ዋጋ የሚገዛው ሰው ካገኘም አትርፎ ስለሚሸጥ ገንዘብ ማግኛ መንገዱ ሊሰፋለት ይችላል፡፡

     ለሰባት ዓመታት ያህል ሲሠራ የተለያዩ ገጠመኞችን አስተናግዷል፡፡ ለነገሩ ሥራቸው ከደንባራና ጋግርታም ፈረስ ጋር የሚያውላቸው ስለሆነ ውሏቸው በገጠመኝ የተሞላ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ በአንድ ወቅት ለሰዓታት ሲያስጋልበው የነበረ ፈረስ መሀል መንገድ ላይ ድንገት እምቢ ይለዋል፡፡ ቁም ብሎ እንደመሪ የሚጠቀሟትን ገመድ ቢጎትት አልሰማ አለው፡፡ ሲንደረደር ሄዶም ከመኪና ጋር ተጋጭቶ አረፈው፡፡ የዚህ ጋግርታም ፈረስ መዘዝም 3,000 ብር አስከፍሎት ማለፉን ባለጋሪው ገመቹ ያስታውሳል፡፡ ይኽኛውም ፈረስ ሳይለግምበት አሳርፎ ሊመግበው ወደ ቤቱ እስኪደርስ ምናልባት ደቂቃዎች ቢቀሩት ነው፡፡ የሚያንገጫግጭ በኮብልስቶን የተሠራውን መንገድ ጨርሶ ከአንዱ ጥግ መንገደኞቹን አውርዶ መሪውን ጠምዝዞ ፈትለክ አለ፡፡