Skip to main content
x
የኢ ቪዛ አገልግሎት መስጠት ተጀመረ 
አዲሱ የኢ-ቪዛ ማዕከል ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የማዕከሉ ባለሙያ ለመንግሥት ኃላፊዎች ማብራሪያ ሲሰጡ

የኢ ቪዛ አገልግሎት መስጠት ተጀመረ 

ከተለመደው የቆየ አሠራሩ ወጣ በማለት ዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጥ መከተል የጀመረው የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምርያ፣ የውጭ ዜጎች ቪዛ ለማግኘት በድረ ገጽ መጠቀም የሚችሉበትን አሠራር መተግበር ጀምሯል፡፡

ዋና መምርያው የኤሌክትሮኒክ ቪዛ (ኢ ቪዛ) አገልግሎትን ለማስጀመር ካቀደ ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ግን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር በሙከራ ደረጃ ሲተገብረው የቆየውን የኢ ቫዛ አገልግሎት በይፋ ማስጀመሩን አስታውቋል፡፡

እንግዳ የሆነውን የኢ ቪዛ አገልግሎት ማስጀመሩን በማስመልከትም ቅዳሜ ሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ወቅት እንደተገለጸው፣ ቪዛ ፈላጊው ሰው የሚጠበቅበትን መረጃ አሟልቶ ለተቋሙ ሲልክ፣ የኢ ቪዛ አገልግሎቱ በደቂቃዎች ውስጥ ማግኘት የሚችልበት አዲስና ፈጣን አሠራር ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል፡፡ ሁሉንም የቪዛ ዓይነቶች በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ማግኘት የሚያስችለው አሠራር መተግበሩ በተለይ የውጭ ዜጎች ሳይጉላሉ በቅልጥፍና እንዲስተናገዱ እንደሚረዳ የመምርያው ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረ ዮሐንስ ተክሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መናኸሪያ በመሆኗም ጭምር ወደ ኢትዮጵያ ለሚደረጉ ምልልሶች የሚያስፈልገውን የቪዛ አገልግሎት ደረጃ ከፍ ማድረጉ ለአገሪቱ የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል የሚኖረው  አስተዋጽኦ ሰፊ ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡

አገልግሎቱ እንዲጀመር በርካታ ተገልጋዮች ይወተውቱ እንደነበር የመምርያው ኃላፊ አስታውሰው፣ የተገልጋዮችን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ እንደተቻለ በመጥቀስ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ዜጎች በአዲሱ አሠራር ያለ ውጣ ውረድ መስተናገድ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡ የውጭ ዜጎች ቪዛ ለማግኘት በሚመጡባቸው አገሮች ወደሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በመሄድ የሚያጠፉትን ጊዜ ከማስቀረቱም በላይ፣ ኤምባሲዎች በሌሉባቸው አገሮች ውስጥ የሚገኙ ቪዛ ጠያቂዎችንም ያለ ችግር ለመስተናገድ የዋና መምርያውን ድረ ገጽ በመጠቀም የኢ ቪዛ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ዕድል ስለመፈጠሩ ተብራርቷል፡፡   

በተዘረጋው የኢ ቪዛ አገልግሎት አማካይነት ከየትኛውም የዓለም ጫፍ ወደ ኢትዮጵያ መግባት የሚፈልጉ ዜጎች፣ መምርያው ለአገልግሎቱ ባመቻቸው ድረ ገጽ ተጠቅመውና ጥያቄቸውን አቅርበው መስተናገድ ይችላሉ፡፡ አገልግሎቱ በይፋ ከተጀመረበት ግንቦት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ መምርያው የኢ ቪዛ ጠያቂዎችን ማስተናገድ ጀምሯል፡፡ በሙከራ ጊዜውም ቢሆን አገልግሎቱን ማግኘት የቻሉት ተገልጋዮች ብዙ ሲጠብቁት የነበረ በመሆኑ መደሰታቸውን እንደገለጹ መመርያው አስታውቋል፡፡

 አራት ኪሎ አካባቢ ለኢ ቪዛና ለውጭ ዜጎች አገልግሎት መስጫነት በተከፈተው ማዕከል ውስጥ በተደረገው የምረቃ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን እንደገለጹት፣ የኦንላይን ቪዛ አገልግሎት መጀመሩ ለአገሪቱ የቱሪስት ፍሰት ዕድገት ሁነኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም ሚናው እንደሚጎላ ሚኒስትሯ ጠቅሰው፣ የአገልግሎቱ መጀመር ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር ለማድረግ አጋዥነቱ እንደሚጎላ አብራርተዋል፡፡

የኢ ቪዛ አገልግሎት ራሱን ችሎ በተናጠል እንዲደራጅ የተደረገ ሲሆን፣ አራት ኪሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ሕንፃ ውስጥ የውጭ ዜጎች በግንባር ቀርበው የሚስተናገዱበትን አሠራርም እንደተዘረጋ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት ፍጥነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ለማድረግ፣ ቀድሞ ከነበረው የቢሮ አደረጃጀት ይልቅ ለዚሁ አገልግሎት በሚስማማ አኳኋን መዘጋጀቱን  አቶ ገብረ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡ የውጭ ዜጎች የመምርያውን አገልግሎት የሚያገኙበት እንደሆነ የተገለጸው ይህ ማዕከል፣ በአንድ መስኮት ሁሉንም አገልግሎት የሚያገኙበት ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የኢ ቪዛ ለማግኘት አመልካቹ ሙሉ መረጃዎቹን በኢሜይል መላክ ይጠበቅበታል፡፡ መረጃዎቹ የተሟሉ መሆናቸው ሲረጋገጥና ቪዛ ለማግኘት የሚያበቁት ሆነው ሲገኙ፣ በኢሜይል አድራሻው ቪዛ ማግኘቱን የሚያረጋግጥ ምላሽ ይላክለታል፡፡ በመሆኑም ወደ ኢትዮጵያ በሚመጣበት ወቅት ኤርፖርት ላይ ቪዛው እንዲመታለት ይደረጋል፡፡ መምርያው እንዲህ ያሉ ዘመናዊ አገልግሎቶችን ለማስፋት ጥረቱን እንደሚገፋበት ጠቅሷል፡፡ ከአንድ ወር በፊትም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ለአገልግሎቱ በተዘጋጁ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በመሄድ የአገልግሎቱን ክፍያና ወረፋ ለመያዝ የሚያበቃቸውን መረጃዎች በመስጠት መገልገል የሚችሉበትን አሠራር መዘርጋቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይህ አሠራር በተለይም ፓስፖርት ለማውጣትና ለማሳደስ ከዚህ ቀደም ይፈጠር የነበረውን መጨናነቅ እንደሚያስቀር ተስፋ ተደርጎበታል፡፡ በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ ውጭ የሚኖሩ ፓስፖርት ፈላጊዎችም ባሉበት አካባቢ ሆነው ፓስፖርት እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር ቀድሞም የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከተከፈቱት የክልል ቅርንጫፎቹ ባሻገር በዚህ ሳምንት መጀመርያ በጅግጅጋ የሚገኘውን ቅርንጫፉን ሥራ እንዳስጀመረ ለማወቅ ተችሏል፡፡