Skip to main content
x
ከሕፃናት የራቀው የፍትሕ ሥርዓት

ከሕፃናት የራቀው የፍትሕ ሥርዓት

በበዓል የተገዛ አዲስ ልብስ ለብሶ ከመሸለል፣ በከረሜላ ጣዕም ከመደነቅ፣ እዚህ ግባ በማይባል ነገር ከመፈንጠዝ፣ እደጅ ወጥቶ ገመድ ከመዝለል፣ ኳስ ከመጠለዝ፣ ትምህርት አልሄድም ብሎ ከማልቀስ ባሻገር የአብዛኞች የልጅነት ትዝታን የሚያመሳስለው ሌላ አንድ ነገር አለ፡፡ አሁን ላይ ቆም ብሎ ሲታሰብ ከምክንያታዊነት የራቀና አንዳንዴም አስቂኝ የሚሆነው የወላጅ ቁጣ፣ ዱላና ተግሳጽ ከልጅነት ትዝታዎች ምናልባትም ትልቁን ድርሻ ሊይዙ ይችላሉ፡፡

ግብረ ገብ ያለው ልጅ ማሳደግ የወላጆች ስኬት መለኪያ ነውና ልጃቸውን በሥነ ምግባር አንጾ ለቁም ነገር የማብቃቱን ሥራ የሚጀምሩት ሕፃኑ ገና ድክድክ ማለት ሲጀምር ነው፡፡ የነገሮችን መንስዔና ውጤት በምክንያት አንተርሶ ከማስረዳት ይልቅ በጭፍን መከልከልን መርሑ ባደረገ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚያድግ ልጅ ለምን ብሎ መጠየቅ ከልብ አውልቅነት ያስቆጥራል፡፡ ለምንን ተከትሎ የሚመጣውን ቁጣና ተግሳጽስ ማን ይችላል? ለምን ከነውር እንደተፈረጁ፣ ከመከልከላቸው ጀርባ ያለውን ምክንያት በግልጽ ሳይታወቅ በአይነኬነታቸው ተስማምተን የማናልፋቸው ብዙ ቀይ መስመሮች ነበሩ፡፡

በአዋቂዎች ጨዋታ መካከል ገብቶ ሐሳብ መስጠት የማይታሰብ ነው፡፡ ሲሳሳቱ ላርማችሁ የሚልን ልጅ ለትልልቆች ክብር የሌለው ተደርጎ ይታሰባል፡፡ በአዋቂዎች ጨዋታ መካከል ገብተው ማውራት የቃጣቸው ስንቶች ኩርኩም ቀምሰዋል? ስንቶች በወንድማቸው ጥፋት ተገርፈዋል? በበርበሬ ታጥነዋል? መናገርም አለመናገርም እኩል በሚያስቀጣበት የወላጅ አስተዳደር ሥር መልስ አትመልሱ ተብለው ጥፊ እንደቀመሱ በዝምታቸው ጥጋበኛ ተብለው ካልቾ የተጨመረላቸው ብዙ ናቸው፡፡ ሲናገር ድምፁ የማይሰማ፣ እንግዳ ሲመጣ ጓዳ የሚደበቅ፣ ልጅ ማሳደግ የወላጆች ሁሉ ህልሙ የሆነ ማኅበረሰብ በራስ መተማመን የራቀው፣ በተሰበሰቡ ሰዎች ፊት ማውራት ሞት የሚሆንበት፣ ራሱን መሸጥ የማይችል ትውልድ ተፈጥሯል፡፡

ስንቶች ያላቸውን ተፈጥሯዊ ብሩህነት ልዩ ችሎታን ከአፈንጋጭነት በሚፈረጅ የአስተዳደግ መዶሻ ተኮርኩመው አጉል ሆነዋል? በዚህ መንገድ ከተቀረፁ ትውልድ መካከል ስኬታማ ሆነው ነጥረው የሚወጡ አስተዳደጋቸው የስኬታቸውን ጫፍ ቀንሶባቸው እንደሆነስ ማን ያውቃል? ራሱን መሸጥ የማይችል ዓይናፋር እንዲሆን ያደረገው የልጆች አስተዳደግ መንገዱ ልክ ባይሆንም ምንጩ የተሻለ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው፡፡

ይህ ከትውልድ ትውልድ መሻሻል ቢታይበትም አሁንም ከችግር ያልፀዳ በልጆች ሥነ ልቦናም ሆነ አካላዊ ጉዳት እስከ ማድረስ ግዝፈት ያለው ማኅበራዊ ችግር ነው፡፡ ልጆች በየዕለቱ የሚደርስባቸውን ነገሮች ተከታትሎ ወላጆችን በሕግ የሚያስጠይቅ ጠንካራ ሥርዓት ቢኖር የስንቶቹ ወላጆች ኑሮ በማረሚያ ቤቶች ሊሆን እንደሚችል መገመት ለአገሬው ተወላጅ ከባድ አይደለም፡፡

ልጆች አካባቢያቸውን እስኪረዱ፣ በአካል ጎልብተው፣ በአዕምሯቸው በስለው ራሳቸውን እስኪችሉ የወላጆች ጥገኛ ሲያልፍም የማኅበረሰቡ ኃላፊነት ናቸው፡፡ ህልውናቸው ግን በወላጆች በጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ መሆን የለበትምና እነዚህ ተጋላጭ የማኅበረሰቡን ክፍሎች የሚጠብቁ፣ ሲያጠፉ ደግሞ የሚዳኙበት ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች እንዲሁም የፍትሕ ሥርዓቶች ተዘረግተዋል፡፡

በዚህ ረገድ በግባር ቀደምትነት ከሚጠቀሰው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መካከል እ.ኤ.አ. በ1985 የወጣው ዘ ቤጂንግ ሩልስ አንዱ ነው፡፡ የሕፃናት የፍትሕ ተደራሽነት ላይ ያተኮረ የመጀመርያው ዓለም አቀፍ ድንጋጌ እንደሆነ የሚነገርለት የቤጂንግ ሩልስ ሕፃናት በሕግ የሚጠየቁበትን አግባብ እንደ ዕድሜያቸውና የብስለት መጠናቸው አገሮች ስታንዳርድ እንዲያወጡ ያደረገ ነው፡፡ ወይም ድንግጋጌው ሕፃናት በሠሩት ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑበት የዕድሜ ጣራ አገሮች እንዲያወጡ ያስገድዳል፡፡ የሚጣልባቸው የቅጣት መጠንም እንዳደረሱ የጉዳት መጠንና ቅጣት የመቀበል አቅማቸው ተመጣጣኝነት ይኖረዋል፡፡ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ልጆች ሌላ አማራጭ ካልጠፋ በስተቀር ማረሚያ ቤት እንዲገቡ ማድረግ የመጨረሻ አማራጭ ይሆናል የሚሉ መሰረታዊ ጉዳዮችን ያካተተ ነው፡፡

ቀጥሎ እ.ኤ.አ. በ1989 የወጣው ዘዩኤን ኮንቬንሽን ኦንዘራይት ኦፍ ዘ ቻይልድ ነወ፡፡ ይህ ድንጋጌ የሕፃናቱን መብት ማስከበር ላይ ያተኮሩ ልዩ ልዩ አንቀጾችን ያካተተ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ማንኛውም ሕፃናትን የተመለከቱ ጥያቄዎች በየትኛውም የግልግል ሥርዓት ቢታዩ ሁሉም ግን የሕፃናቱን ጥቅም በተሻለ መጠን ማስከበር ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ የሚያዘው አንቀጽ ሦስትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አስገዳጅ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ በስተቀር ሕፃናት ከቤተሰቦቻቸው መለየት እንደሌለባቸው፣ ማንኛውም የእነሱን ጥቅም በሚነኩ ጉዳዮች ላይ ከተቻለ ራሳቸው ቀርበው ካልሆነ ደግሞ በተወካያቸው በኩል የሚሉት ሊደመጥ ይገባል የሚሉ የተለያዩ አንቀጾችን ያካተተ ነው፡፡ የሕፃናትን ልዩ ልዩ የመብት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ሌሎችም ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችም አሉ፡፡

ሕፃናት በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ በመሄድ እነዚህን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ተመሥርተው በተዘጋጁ የሕግ አግባቦች ይዳኛሉ፣ ይገለገላሉ፡፡ ልጆች ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ወይም የወንጀል ድርጊት ሰለባ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ ምስክር ሆነውም ችሎት ፊት ይቀርባሉ፡፡ ራሳቸውም በወንጀል ድርጊት ተሳታፊ ሆነው ክስ ተመሥርቶባቸው ፍርድ ቤት ሊቆሙ ይችላሉ፡፡ በፍትሐ ብሔር የመብት የንብረት፣ በውርስና በመሳሰሉት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከልጆች መብት ጥያቄ ጋር በሚገናኙ ጉዳዮችም እንደ አንድ የጥቅም ተጋሪ ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ ሕፃናት እንዲቀርቡ ይሆናል፡፡

በእነዚህ አጋጣሚዎች ሁሉ ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ ሲቀርቡ ከሕንፃው አወቃቀር፣ ከችሎት አደረጃጀት ጀምሮ ጥንቃቄ ይፈልጋሉ፡፡ ከሕፃናቱ ጋር መግባባት የሚችሉ የሥነ ልቦናና የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች መኖር ግዴታ መሆኑን የሚናገሩት፣ ወ/ሮ ገነት ሹሜ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕፃናት ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ጊዜያዊ አስተባባሪ ናቸው፡፡

ጥቃት ተፈጽሞባቸው ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ የሚሄዱ ሕፃናትን ሥነ ሥርዓቱ እንኳንስ ለሕፃናት ለአዋቂዎች በሚያስጨንቀው በመደበኛ ችሎት ፈት መሆን የለበትም፡፡ ከዋናው ችሎት ጋር በሲሲቲቨ የሚገናኙ ክፍሎች ውስጥ በአሻንጉሊቶችና በልዩ ልዩ መጫወቻዎች እየተጫወቱ እንግድነት ሳይሰማቸው የደረሱባቸውን እንዲናገሩ ይደረጋል፡፡

በሆነው ባልሆነው የሚበታተን ትኩረታቸውን በመላ በጥበብ እየሳቡ፣ እያግባቡ የሚያናግሯቸው የማኅበራዊ ሳይንስና የሥነ ልቦና ባለሙያዎች መኖርም ግዴታ ነው፡፡ ከዋናው ችሎት የሚሰነዘሩ መስቀለኛ ጥያቄዎችን በጆሯቸው ደብቀው በሚይዙት ማዳመጫ ጥያቄዎቹን ለልጆች በሚመጥን ቋንቋ እያቀለሉ መጠየቅ ከባለሙያዎቹ ይጠበቃል፡፡ የፍትሕ ሥርዓት ሕፃናትን ያካተተ ነው የሚባለው ይህን ሁሉ ነገር ሲያሟላ ነው፡፡

ወ/ሮ ገነት እንደሚሉት፣ በወንጀል ድርጊት ተሳትፈው ሕግ ፊት የሚቀርቡ ልጆች የችሎት ሒደትም ከመደበኛ በተለየ ለልጆች የተመቸ መሆን አለበት፡፡ ዳኛው ችሎት ላይ ሲሰየም የክብር ልብሱን ጥቁሩን ካባ ሳይለብስ መሆን አለበት፡፡ በክፍሉ ውስጥ መኖር ያለባቸውም ተከላካይ ጠበቃ እንዲሁም የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያና የልጁ የቅርብ ዘመዶች ብቻ ሆነው በዝግ ችሎት የሚታይ ነው፡፡

የሕፃናት ጉዳይ የሚታየው ዘቤጂኒግ ሩልስ በሚያዘው መሠረት በኢትዮጵያ ሕፃናት በሠሩት ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑት ከስንት ዓመታቸው ጀምሮ መሆን አለበት የሚለውን መስፈርት አውጥታለች፡፡ በመስፈርቱ መሠረት ከዜሮ እስከ ዘጠኝ ዓመት ድረስ ያሉ ሕፃናት በሠሩት ወንጀል አይጠየቁም፡፡ ከዘጠኝ ዓመት በላይ የሆኑ ግን ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡

‹‹እስከ ዘጠኝ ዓመት ድረስ መሆናቸው ከታወቀ ከመነሻውም ክስ አይመሠረትም፡፡ ከዘጠኝ እስከ 15 ያሉትንና ከ15 ዓመት እስከ 18 የሆኑትን የወንጀል ሕጉ ለይቶ ነው የሚመለከታቸው፡፡ ከዘጠኝ እስከ 15 ዓመት ድረስ ያሉ ልጆች በወንጀል ተሳታፊ ሆነው ሲገኙ፣ የሚጠየቁበት የችሎት ሒደት ጥንቃቄ በተሞላበትና በዝግ እንዲሆን ግድ ነው፡፡ ከ15 እስከ 18 ያሉት ግን እንደ አዋቂ ታይተው በመደበኛ ችሎት የሚዳኙ ይሆናል፡፡

‹‹በወንጀል ሕጋችን መሠረት ነው እንጂ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች ከ18 ዓመት በታች ያሉትን በሙሉ እንደ ሕፃናት ነው የሚቆጠሩት፤›› ይላሉ ወ/ሮ ገነት፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ የሚሄዱ አብዛኞቹ ተከሳሾች የስርቆት፣ የነጠቃ ወንጀሎች ፈጽመው ነው፡፡ ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸውና አድርሰው ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ የሚሄዱም ጥቂት አይባሉም፡፡ ‹‹አስገድዶ መድፈርና መሰል ወሲባዊ ጥቃቶች ደርሰውባቸው ወደኛ የሚመጡ ሕፃናት ብዙ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በጉልበት ብዝበዛ፣ ከአቅም በላይ በሆነ ሥራ እንዲሰማሩ የተገደዱም ይመጣሉ፤›› ይላሉ፡፡

ሕፃናት ሴቶች፣ ከጉዳት ጋር የሚኖሩ ታዳጊዎች፣ በገጠር የሚኖሩ፣ ስደተኞች፣ የሕገወጥ የሕፃናት ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሕፃናት፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች በብዛት ለጉደት የተጋለጡ መሆናቸውን የአፍሪካ የሕፃናት ፖሊሲ መድረክ በቅረቡ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያሳያል፡፡ እነዚህ ሕፃናት በቤተሰብ አባላት፣ በጠባቂዎቻቸውና በሌሎች ያልበሰለ አዕምሮአቸውን ከሚጎዳ ያልተገባ ንግግር ጀምሮ ድብደባ ሲያልፍ ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ጥቃት ብለው በሚፈርጇቸው እያንዳንዱ ድርጊቶች ጥቃት ፈጻሚዎቹ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራር ቢኖር ትውልድ በሙሉ የጥቃት ሰላበ፣ መሆኑ በተረጋገጠ ነበር፡፡ ተግሳጽና ሌሎች ያልተገቡ ንግግሮች የሚታይ አካላዊ ጉዳት ባያደርሱም የሚፈጥሩት የሥነ ልቦና ጫናና ቀውስ በርካቶች በራሳቸው እንዳይተማመኑ፣ ራሳቸውን መግለጽና መሸጥ እንዳይችሉ ማድረጉ ጥርጥር የለውም፡፡

በሕፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃት ከየት እስከየት መሆኑን በመውል ባልተረዳ ማኅበረሰብ ውስጥ ልጅህን የምታስተዳድርበት መንገድ ልክ አይደለም ብሎ ወላጅን በሕግ መጠየቅ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊብስ እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል በሕፃናት ላይ ጉዳት አደረሱ ተብለው በሕግ የሚጠየቁ ግለሰቦች በብዛት አካላዊ ጉዳት፣ ፆታዊ ጥቃትና የመሳሰሉትን ከባድ ጥቃቶች ያደረሱ የሚሆኑት፡፡ ይህ በጥናት የተረጋገጠ ባይሆንም ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ እውነታው ከዚህ የተለየ አለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ከባድ ጥቃቶት ምን ያህሉ ሪፖርት እንደሚደረጉ መገመት ይቻላል፡፡ በልጄ ላይ እንዲህ ያለ ጉዳት አድርሻለሁ ብሎ እጁን የሚሰጥ ወላጅ፣ ጾታዊ ትንኮሳ አድርሻለሁ ብሎ ሪፖርት የሚያደርግ ጎረቤት፣ ሕፃኑ ጥቃት የደረሰበት ይመስላል ብሎ በራሱ ተነሳሽነት ክትትል አድርጎ ጥፋተኞችን የሚያስቀጣ የተደራጀ የፍትሕ ሥርዓት በሌለበት ሁኔታ ምን ያህሉ በሠራው ወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆን አጠያያቂ ነው፡፡ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተሳታፊ የሚሆኑትን ሕፃናት ጉዳይስ በአግባቡ ሪፖርት ተደርጎ ተገቢው የእርምት ዕርምጃ ይወሰድባቸው ይሆን የሚለውም ጉዳይ በዚሁ መጠን ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው፡፡

የአፍሪካ የሕፃናት ፖሊሲ መድረክም በመደበኛውና በኢመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ሕፃናት ብዙ ቦታ እንደሌላቸው ይመሰክራል፡፡ በሁለቱም ወገን ያሉት የፍትሕ ሥርዓቶች ሕፃናትን ታሳቢ ያላደረጉ አዋቂዎችን መሠረት አድርገው መዋቀራቸውን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

‹‹በአዲስ አበባ ከዘጠኝ እስከ 15 ዓመት ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣት ታራሚዎች የሚቆዩበት አንድ የተሃድሶ ተቋም አለ፡፡ ወደ ተቋም መግባት የመጨረሻው አማራጭ ቢሆንም ወደ ተቋሙ መግባት የሌለባቸው ማኅበረሰቡ ውስጥ ሆነው መታረም የሚችሉ ሁሉ እንዲገቡ ይደረጋል፤›› በማለት በማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮግራሞች ውስጥ ሆነው መታረም የሚችሉ ሕፃናት አማራጭ ሲጠፋ በተቋም እንዲቆዩ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ፡፡

የሕፃናት የሕግ ጥበቃ በአገሪቱ የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ፣ የቤተሰብ ሕግ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ፣ ኢትዮጵያ የተቀበለችው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ተግባራዊነቱ ላይ ግን ለጉዳዩ ከሚሰጠው ትኩረት ጀምሮ፣ ብዙ ክፍተቶች አሉ፡፡ ለዘርፉን የሚያዝለት በጀት አነስተኛ ከመሆን ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡  ወንጀል ተብለው የተለዩ ድርጊቶች አሁንም ድረስ በስፋት ይፈጸማሉ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መብት ድንጋጌ ጋር የማይሄዱ ሕጎችን የሚያወጡ አገሮች እንዳሉ ከአፍሪካ ሕፃናት ፖሊሲ መድረክ የተወከሉ አንድ ባለሙያ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት ድንጋጌ መሰረት ሕፃናት ብሎ የሚባሉት ከ18 ዓመት በታች ያሉትን ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ አገሮች ይኼንን በመተላለፍ ከ14 ዓመት ጀምሮ ልጆች እንዲዳሩ ይፈቅዳሉ፡፡ ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ወንጀል ሠርተው ቢገኙም ወደ ማረሚያ ተቋማት መላክ የለባቸውም የሚል ሕግ ቢኖርም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ብዙ አገሮች የዕድሜ ገደቡን እስከ ዘጠኝ ዓመት እንደሚያወርዱና ይህም ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡

በፖሊሲና በሕግ የተደነገጉ ሕግጋትን ከማስፈጸም አኳያ የተሻለ ሥራ የተሠራ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ ያለው ክፍተት በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱን ለሕፃናት ተደራሽ ከማድረግ አኳያም ብዙ ጉድለቶች አሉ፡፡ እነዚህን ሽንቆሮች ለመድፈን ይሆናሉ ያላቸውን ምክረ ሐሳቦች የአፍሪካ ሕፃናት ፖሊሲ መድረክ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

የአጥፊ ወይም የተጠቂ ሕፃናት ልዩ የጊዜያዊ ማቆያ ሥፍራዎችን በማዘጋጀትና  የሕፃናትን በተለይም ተጋላጭ የሆኑትን ደህንነት ማስጠበቅ፣ የሕፃናት ፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓትን ማዋቀርና በተለያዩ የሕፃናት የአገልግሎት መስጫ መስኮች የሠለጠኑ ባለሙያዎችን ማቅረብ መቻል፣ እንደ አስፈላጊነቱ እየታየ የሕፃናት የፍትሕ አገልግሎት መስጫ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋምና ሌሎች አስፈላጊ የአሠራር ሥልቶችን ሥራ ላይ በማዋል የሕፃናትን የፍትሕ ተደራሽ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡

እንደ አካላዊ ቅጣት ያሉ በሕግ የተከለከሉ የመቅጫ ዘዴዎች ፈጸሞ እንዲወገዱ ጥረት ማድረግ፣ ለሕግ አስፈጻሚዎች፣ ለወሲብ ጥቃት ወንጀል መርማሪዎች፣ ለዳኞችና ሌሎች በሕፃናት ፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ ተግባር ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ሕፃናት ተኮር የፍትሕ አፈጻጸም ሥልጠና መስጠትም እንደሚያስፈልግ አስምረዋል፡፡

የኢመደበኛ መደበኛ የዳኝነት ሥርዓቶች አንድ ላይ ተቀናጅተው በአገር አቀፍ ደረጃ በሥራ ከዋለው የዳኝነት ሥርዓት ጋር በመደበኛነት አገልግሎት መስጠት መስጠት የሚችሉበትን መድረክ መፍጠርም የትኩረት አቅጣጫ መሆን ይኖርበታል፡፡

የሪፈራል አገልግሎት በማቋቋምና በተቋማት መካከል ቅንጅት በመፍጠር የተጠቁ፣ የተበዘበዙና የተጎዱ እንዲሁም የተዘነጉ ሕፃናት ሕልውናቸው የሚጠበቅበትና ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኝበትን ሥርዓት ማዋቀር፣ የመጨረሻ የዳኝነት ምርጫ ሆኖ ካልተገኘና ተገቢው ክትትል እየተደረገለት ካልሆነ በስተቀር ተጋላጫ ሕፃናት ምንም ዓይነት ክልከላ እንዳይደረግባቸው ነፃነታቸውን እንዳይነፈጉ ብርቱ ጥረት ሊደረግ ይገባል የሚሉት በምክረ ሐሳቡ ከተካተቱ ዋናዋና ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡