Skip to main content
x
የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር አርፍዶ ቤታቸው መጣ

የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር አርፍዶ ቤታቸው መጣ

[የክቡር ሚኒስትሩ ልጅ የፈተና ውጤቱን መጥቶ እያሳያቸው ነው፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደዋል]

 • ና አንተ፡፡
 • አቤት ዳዲ?
 • ምን ሆነህ ነው?
 • ምን ሆንኩ?
 • ውጤትህን አይተኸዋል?
 • አሪፍ ነው አይደል ዳዲ?
 • ሳይንስ ያመጣኸው አሪፍ ነው፡፡
 • እንግሊዝኛስ ዳዲ?
 • እሱንም ጥሩ ሠርተሃል፡፡
 • የሶሻል ሳይንስ ውጤቴስ ጥሩ አይደል?
 • እኔ እሱ ላይ ጥያቄ የለኝም፡፡
 • ታዲያ ምን ላይ ነው ጥያቄ ያለህ?
 • ሒሳብ ላይ፡፡
 • ምንድነው ጥያቄህ?
 • ሒሳብ ላይ ያለብህ ችግር ምንድነው?
 • ኧረ ምንም ችግር የለብኝም፡፡
 • ታዲያ እንዴት ነው እንደዚህ ዓይነት ውጤት ልታመጣ የቻልከው?
 • ችግሩ የእኔ አይደለም ዳዲ፡፡
 • የፈተና ውጤትህን እያየሁት እኮ ነው?
 • ችግሩ የእኔ አይደለም አልኩህ እኮ ዳዲ፡፡
 • ከመቶ ስንት እንዳመጣህ አይተኸዋል?
 • እ. . . ዳዲ. . .
 • አሥራ አምስት በመቶ እኮ ነው ያመጣኸው?
 • እሱ እኮ የአስተማሪዎቹ ስህተት ነው፡፡
 • የምን የአስተማሪ ስህተት ነው፣ ስህተቱማ የአንተ ነው፡፡
 • አይደለም ዳዲ እኔ እንዲያውም ትምህርት ቤት ሄደን እንድታስረዳቸው ነው የምፈልገው፡፡
 • ምኑን ነው የማስረዳቸው?
 • መሳሳታቸውን ነዋ፡፡
 • የተሳሳትኸው አንተ ነህ እንጂ እነሱ እኮ አይደሉም፡፡
 • ዳዲ ሙት እመነኝ እነሱ ናቸው የተሳሳቱት፡፡
 • ወረቀትህን እያየሁት እንዴት እነሱ ተሳሳቱ ትለኛለህ?
 • አየህ ዳዲ አንተ ራስህ አልገባህም ማለት ነው?
 • ደግሞ ከመሬት ብቅ ሳትል እኔን ሒሳብ ልታስተምር ትፈልጋለህ?
 • ከተሳሳትክ ባስረዳህ ምን ችግር አለው?
 • ስለሒሳብ ሥሌት ነው እኔን የምታስረዳኝ?
 • ምን ችግር አለው?
 • ይኼ እኮ የሒሳብ መሠረታዊ ነገር ነው፡፡
 • አውቃለሁ ዳዲ፡፡
 • ብታውቅማ እንደዚህ አትሳሳትም ነበር፡፡
 • ዳዲ አንተም አስተማሪዎቹም ያልገባችሁ ነገር ስላለ ነው፡፡
 • ምንድነው ያልገባን?
 • የሒሳብ ሥሌት ነዋ፡፡
 • ቆይ እንጂ ከዘጠኝ ላይ ሦስት ሲቀነስ ስንት ነው?
 • አሥራ ሁለት፡፡
 • ሒሳብ ምንም አትችልም እንዴ?
 • እንዴ ዳዲ?
 • እሺ አሁን አራት ሲባዛ በሁለት ስንት ነው?
 • ስድስት፡፡
 • አሁን በደንብ ነው የገባኝ፡፡
 • ምንድነው የገባህ ዳዲ?
 • መሠረታዊ የሒሳብ ሥሌት ችግር እንዳለብህ፡፡
 • እኔ ደግሞ የገባኝ አንድ ነገር አለ፡፡
 • ምንድነው የገባህ?
 • አንተም አስተማሪዎቼም አዲሱን ለውጥ አትቀበሉም ማለት ነው፡፡
 • የምን ለውጥ?
 • አገሪቱ ውስጥ የመጣውን ለውጥ አትቀበሉትም ማለት ነው?
 • ፖለቲከኛም ሆነኸልኛል ልበል?
 • ዳዲ እኔ እንደተረዳሁት አንተም አስተማሪዎቼም የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎች ናችሁ፡፡
 • እኔ ጠፋሁ፣ ከማን ጋር ነው የምትውልልኝ?
 • ዘመኑ የምን ዘመን መሆኑን ረሳኸው እንዴ?
 • የምን ዘመን ነው?
 • የመደመር!

[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር አርፍዶ ቤታቸው መጣ]

 • አንተ ስለአዲሱ አለቃ ነግሬሃለሁ አይደል እንዴ?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንደዚህ እያስረፈድከኝ ልታስጠምደኝ ነው?
 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼኔ ማታ አንቡላህን ስትልፍ አምሽተህ ነው፡፡
 • ኧረ በፍፁም፡፡
 • ምን ሆነህ ነው ታዲያ ያረፈድከው?
 • የዓለም ዋንጫ ሳይ አምሽቼ ነው፡፡
 • አሁን ምን ኳስ አለ ብለህ ነው?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • አንጋፋዎቹ ቡድኖች ተባረው ምንም የዓለም ዋንጫ አይመስልም እኮ?
 • ዋናው እሱ አይደል እንዴ?
 • እንዴት ማለት?
 • አይነኬ የሚባሉት ቡድኖች እየተዋረዱ ምድባቸው እንኳን ሳይቀር ማለፍ ተስኗቸው ሲታዩ አያስገርምም?
 • ወጣት ሲባል እኮ ግንፍልተኛ ነው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ስማ የዓለም ዋንጫን እኮ የዓለም ዋንጫ ያስባሉት ቡድኖች እነዚህ ናቸው፡፡
 • የትኞቹ?
 • እነ ጀርመን፣ ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ስፔንን የመሳሰሉት፡፡
 • ይኸው ከብራዚል ውጪ ሁሉም ከውድድሩ ተሰናብተዋል፡፡
 • ለዚህ ነው እኮ አንጋፋዎቹ የሌሉበት የዓለም ዋንጫ ምን የዓለም ዋንጫ ነው የምልህ?
 • ክቡር ሚኒስትር እነ ክሮሺያና ቤልጂየም የመሳሰሉ ቡድኖች ሲጫወቱ ግን አይተዋቸው ያውቃሉ?
 • የፈለገ ነገር ብትለኝ አንጋፋዎቹ የሌሉበት የዓለም ዋንጫ አንገሽጋሽ ነው፡፡
 • ሕዝቡ ግን ይኼኛውን የዓለም ዋንጫ በጣም በትኩረት ነው እየተከታተለ ያለው፡፡
 • እንደ አንተ ዓይነት ኳስ የማያውቅ ሰውማ ሊወደው ይችላል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ከዘመኑ ጋር ሊለወጡ ይገባል እኮ፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • አንጋፋዎቹ እኮ ከውድድሩ የተባረሩት አዳዲሶቹ ላቅ ያለ የእግር ኳስ ችሎ ስላላቸው ነው፡፡
 • እንዳይመስልህ አትሳሳት፡፡
 • ታዲያ በምንድን ነው አንጋፋዎቹ የተባረሩት?
 • በአሻጥር፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ስመለከትዎ እርስዎ ከሚያውቁት ውጪ የሆነ ነገር አይወዱም፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • ይኸው በአገሪቱ ውስጥ የመጣውን ለውጥ ራሱ መቀበል አይፈልጉም፡፡
 • አንጋፋዎቹ የሌሉበትን ለውጥ አልቀበለውም፡፡
 • እንደዚያ ከሆነ የእኔ ምክር አንድ ነው፡፡
 • ምንድነው ምክርህ?
 • በጊዜ ቢቆርጡ ይሻልዎታል፡፡
 • ምንድነው የምቆርጠው?
 • ትኬት ነዋ፡፡
 • የምን ትኬት?
 • የስንብት!

[ለክቡር ሚኒስትሩ በአገሪቱ አሸባሪ የተባለ ድርጅት አባል ከውጭ ስልክ ደወለላቸው]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሰላም ነህ?
 • አገሪቱ ውስጥ ትክክለኛ ለውጥ መኖሩን እየተረዳሁ ነው፡፡
 • በምኑ ነው የተረዳኸው?
 • ስልኬን ራሱ ማንሳትዎ የለውጡ አካል አድርጌ ነው የቆጠርኩት፡፡
 • የምን ለውጥ ነው?
 • ይኸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራችሁ መጥታችሁ ተደመሩ እያሉን አይደል እንዴ?
 • እንግዲህ እናንተ ስትደመሩ እኛ እንቀነሳለን፡፡
 • ምን ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ለመሆኑ ሬሲሊንግ ዓይተህ ታውቃለህ?
 • በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንድ ተፋላሚ ወደ ሪንጉ ሲገባ ሌላውን በእጁ እንደሚጨብጠው፣ እኛም እናንተ ስትገቡ ተጨባብጠን አገሪቱን ለቀን እንወጣለን፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔና አንተ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ላይ መኖር አንችልም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ዘመኑ የመደመር እኮ ነው?
 • በምንም ሥሌት እኔ ከአንተ ጋር ልደመር አልችልም፡፡
 • የድሮ ሥርዓት ናፋቂ ነዎት ልበል?
 • ነገርኩህ እኮ እኔና አንተ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ላይ መኖር አንችልም፡፡
 • አይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማለት?
 • ኢትዮጵያ እንኳን ለእኔና ለእርስዎ ለሌሎች ትተርፋለች፡፡
 • ይኼን ፕሮፓጋንዳህን ወሬ ለተጠሙ ጓደኞችህ ንገራቸው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በፍቅርና በይቅርታ እኮ ለአገራችን ሰላም ማምጣት እንችላለን፡፡
 • ስማ ይኼው እዚህ ራሱ ያሰርናቸው አሸባሪዎች ተፈትተው ሰላም የነበረችው አገር እየተበጠበጠች ነው፡፡
 • እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን ቀልድ ነው?
 • ለሦስት ዓመታት አገሪቱ ታምሳ አሁን አይደል እንዴ ከመፍረስ የተረፈችው?
 • ስማ ለእኔ ግን ከነበረችበት የበለጠ ማጥ ውስጥ እየገባች ያለችው አሁን እየተደረጉ ባሉ ነገሮች ነው፡፡
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • አሸባሪዎቹ ሲለቀቁ ሰላም የነበረችው አዲስ አበባ ውስጥ ቦምብ ፈነዳ፡፡
 • ቦምብ ያፈነዱት እኮ የለውጡ ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡
 • አሸባሪን መልቀቅ ለውጥ ከሆነ እሱን ቢቃወሙ ምን ችግር አለው?
 • ክቡር ሚኒስትር እውነተኛ አሸባሪ እኮ መንግሥት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ተናግረዋል፡፡
 • የማልቀበለው እኮ ይኼንን ነው፡፡
 • ምኑን?
 • እኛ አሸባሪዎች እናንተ ሰላማዊ መሆናችሁን፡፡
 • ሀቁ ግን እሱ ነው፡፡
 • ስለዚህ እኛም የእናንተ ዕጣ እንዳይደርሰን በጊዜ እንወጣለን፡፡
 • ከየት?
 • ከአገር!

[ክቡር ሚኒስትሩ ፀጉር ቤት እየተስተካከሉ ከፀጉር ቆራጫቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር እንዴት ላድርገው ፀጉሩን?
 • እንደ ሁልጊዜው ነዋ፡፡
 • እኔማ ለወጥ ያለ ቁርጥ ልቆርጥዎት አስቤ ነበር፡፡
 • ሰውዬ ምንም ዓይነት ለውጥ አልፈልግም፡፡
 • ሽበትዎን ለማጥፋት ፈልጌ ነበር፡፡
 • ለምን ተብሎ?
 • ያው አርጅተዋል ምናምን ብለው ከፖለቲካው እንዳያባርርዎት ብዬ ነዋ፡፡
 • ማን ነው የሚያባርረኝ?
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ከተባረሩ እኔ ራሴ እጎዳለሁ፡፡
 • እንዴት?
 • የፀጉር ቤቴ ገቢ ሊቀንስ ይችላል፡፡
 • ለምን ይቀንሳል?
 • ያው አሁን ሚኒስትሩ የሚስተካከሉበት ፀጉር ቤት እየተባለ ገቢዬ ቀላል አይደለም፡፡
 • አንተ ግን ለእኔ ኮሚሽን አትከፍለኝም?
 • ይኸው አሁን በሚቀጥለው በጀት ዓመት የፀጉር ቤቴን ስም ሚኒስትሩ ፀጉር ቤት ልለው ወስኛለሁ፡፡
 • እሱ ምን ያደርግልኛል?
 • ያው አንጋፋዎቹ ለቀው በወጣት ይተኩ እየተባለ ስለሆነ፣ አንድ ሐሳብ ነበረኝ፡፡
 • የምን ሐሳብ?
 • እርስዎን ወጣት ማስመሰል እችላለሁ፡፡
 • እንዴት አድርገህ?
 • የፀጉርዎን ቀለም በመቀየር፡፡
 • እሱን ፈጽሞ እንዳታስበው፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ከተማ ውስጥ አዲስ አደን ተጀምሯል፡፡
 • ምንድነው የሚታደነው?
 • ፀጉረ ልውጥ!