Skip to main content
x
የደቂቅ ዘአካላት እሴቶች

የደቂቅ ዘአካላት እሴቶች

ነገሮች ከመሬት ተነስተው ሲያረጁና ሲበሰብሱ፣ ጤናማው ሰው በበሽታ ሲዳከምና ሞት አፋፍ ሲደርስ፣ በዓይን የማይታዩ ፍጥረታት ለተከሰተው ነገር ሁሉ ማሳበቢያ ይደረጉ የነበረው በ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነበር፡፡ ይህ ከጥርጣሬ ያላለፈ መላምት በ17ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የደቂቅ ዘአካላት መኖር ሲረጋገጥ ለሳይንስ ምርምር እንደ ማዕዘን ድንጋይ የጠነከረ መነሻ ሆነ፡፡ ማይክሮብ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ደቂቅ ዘአካላት ሰፊ ሳይንስ መሆኑ ሳይታወቅ በፊት ተመሳሳይ ዝርያ እንዳላቸው ይታሰብ ነበር፡፡

     ልዩነታቸው ነጥሮ የወጣው የማይክሮ ባዮሎጂ ሳይንስ ራሱን ችሎ ለብቻው የጥናት ዘርፍ ሆኖ ከወጣ በኋላ ነበር፡፡ ባክቴሪያ፣ እርሾ፣ ሻጋታ፣ ፕሮቶዝዋ፣ አልጌና ሪኬቴሲያ በሚል በስድስት የሚከፋፈሉት ደቂቅ ዘአካላት በሰው ልጆች አካል ክፍል ውስጥና ውጪ፣ እንዲሁም በአፈር፣ በአየርና በባህሮች ላይ ይኖራሉ፡፡ በተለያዩ የሥነ ምኅዳር ክፍሎች ውስጥ ጎጂም ጠቃሚም ሆነው ይኖራሉ፡፡

     ከእነዚህ አካላት ማግኘት የሚቻለውን ጥቅም ከፍ፣ ጉዳቱን ደግሞ ዝቅ እንዲል በሚሠራው በማይክሮቢያል ባዮ ቴክኖሎጂ የተባለው የሳይንስ ዘርፍ ስንት ተዓምር የሚመስሉ ግኝቶች በሥራ ላይ ውለዋል፡፡ ተዘጋጅተው ከደቂቃዎች በላይ መቆየት የማይችሉ ምግቦችን ዓመታት እንዲቆዩ የማድረግ ሳይንስ የዚሁ ምርምር ትሩፋት ነው፡፡ ይህ የምርምር ዘርፍ ከተጀመረ ዘመናት ያለፉ ቢሆንም ለኢትዮጵያ ግን አዲስ ነው፡፡ በአንዳንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የግብርና ምርምር ማዕከላት የሚታዩ አንዳንድ ጅምሮች ግን ይበል የሚያሰኝ ውጤቶችን እያሳዩ ይገኛሉ፡፡

      በብሔራዊ ግብርና ባዮቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል የደቂቅ ዘአካላት ምርምር ፕሮግራም ማይክሮቢያል ባዮ ቴክኖሎጂ ፕሮግራም አስተባባሪው አቶ ሙላቱ ዕርቄ በማይክሮ ቢያል ባዮቴክኖሎጂ ፕሮግራም በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የምርምር ሥራዎችን እንደሚሠራ ይናገራሉ፡፡ የመጀመርያው ፉድ ማይክሮቢያል ባዮቴክኖሎጂ ሲሆን፣ የምግብ ደቂቅ ዘአካላት ላይ ትኩረት ያደረገ የምርምር ሥራ የሚሠራበት ነው፡፡ ሁለተኛው በእንስሳት መኖ ላይ የሚሠራው ነው፡፡ የመጨረሻው በአግሮ ኢንዱስትሪያል ዌስት ዩትላይዜሽን ላይ የሚደረገው ምርምር ነው፡፡ በዚህ የምርምር መስክ የግብርናና የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ደቂቅ ዘአካላትን ለማልማት ምርምር ይደረጋል፡፡

      ማይክሮቢያል ባዮቴክኖሎጂ ዕፀዋትንና ደቂቅ ዘአካላትን በመጠቀም የግብርናውን ችግር መፍታት ያስችላል፡፡ በዕፀዋት ላይ የሚከሰቱ ነፍሳትን መከላከልም ሆነ የግርናውን ምርታማነት መጨመር የሚያስችል የምርምር ዘርፍ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በመጠጥ፣ በምግብ፣ በጤናው ዘርፍ፣ በአካባቢ ጤና ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ደቂቅ ዘአካላት ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ፡፡

      የፍልልት ሒደትን የሚያፋጥኑ ደቂቅ ዘአካላት በኢንዱስትሪዎች በቢራ፣ በስኳር፣ በቤከሪ ውስጥ በከፍተኛ መጠን ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ በወተትና የወተት ተዋፅኦዎችን በማቀነባበር ሒደት ውስጥ ዋና ግብዓት ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በተለይ በቢራ ፋብሪካዎች በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው ሳካሮማይሲስ ሰርቪሴ የተባለው የእርሾ ዓይነት አንዱ ነው፡፡ ሳካሮማይሲስ በአገር ውስጥ ስለማይመረት ከውጭ የሚገባ ነው፡፡

     ይህንን የእርሾ ዓይነት ለማምረት አሚሌዝ የተባለውን ኢንዛይም ይጠቀማሉ፡፡ አሚሌዝ በገብስ ውስጥ የሚገኘውን የስታርች ክምችት ወደ ግሉኮስ በመቀየር አልኮል እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ይኼንን ሒደት የሚያፋጥን አሚሌዝ ኢንዛይምን አቶ ሙላቱ በሚያስተባብሩት ፕሮግራም አማካይነት በኢትዮጵያ ውስጥ ሊሠራ ችሏል፡፡

     ‹‹ለፈርመንቴሽን መነሻ የሚሆኑ ደቂቅ ዘአካላትና ኢንዛይሞች በጣም ውድ ናቸው፡፡ አንድ ጊዜ በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ጉባዔ አዘጋጅተን የቢራ ፋብሪካዎችን ጋብዘን ነበር፡፡ ነገር ግን አልመጡልንም፡፡ ለቢራ ኢንዱስትሪው የሚሆኑ የምርምር ሥራዎችንና በእነሱ በኩል ያለውን ፍላጎት ለማስተዋወቅ አስበን ነበር፡፡ ስለዚህም የኢንዱስትሪውን ፍላጎት ማርካት የሚችል ብቃት ያለው ምርምር መሥራትና ቀጥሎ ገበያውን ለመሳብ አስበን መሥራት ቀጠልን፤›› የሚሉት አቶ ሙላቱ በዚህ መሠረት አሚሌዝ፣ ፕሮቴዝና ለአልኮል ጠመቃና ለቤከሪ ኢንዱስትሪዎች የሚውሉ የእርሻ ዓይነቶችን በምርምር ማውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

     እዚህ መመረቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከማዳኑ ባሻገር ሌላ ጥቅም አለው፡፡ ከተለያዩ ቦታዎች የሚመረቱ አሚሊዞች ሚና ተመሳሳይ ቢሆንም፣ እዚህ የሚመረተው አሚሌዝ ከዚሁ ሥነ ምኅዳር መገኘቱም ሌሎች ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ ለምሳሌ ከውጭ የሚገባውና እዚሁ አገር የሚመረተው አሚሎዝ ሙቀትን የመቋቋም አቅሙ የተለያየ ነው፡፡ አሲድንና የተለያዩ አካባቢያዊ ተፅዕኖዎችን የመቋቋም አቅማቸውም እንደዚሁ የተለያየ ይሆናል፡፡

      የፕሮቲን ይዘት ያላቸውን ምግቦች መበጣጠስ የሚያስችል ፕሮቴዝ የተባለ ኢንዛይምም ሠርተዋል፡፡ ፕሮቴዝ ከሚሰጣቸው ጥቅሞች መካከል በቆዳ ፋብሪካ ውስጥ በቆዳው ላይ ያለውን ፀጉር ማስወገድ አንዱ ነው፡፡

      በወተት ተዋፅኦዎች ቅንብር ሒደት ውስጥ ትልቅ ሚና ያለውን ላክቲክ አሲድ ባክቴሪያም አምርተዋል፡፡ ይህ ባክቴሪያ ወተት የሚረጋበትን ጊዜ የማፋጠን ተግባር አለው፡፡ ሌሎች ምግብን የሚበክሉ ደቂቅ ዘአካላትን በወተት ውስጥ ያላቸውን መጠን በመቀነስ ወተቱ ሳይበላሽ የሚቆይበትን ሰዓት መጨመር የሚቻልበትም ሳይንስ አለ፡፡ ነገር ግን በምርምር ተቋሙ የተሠራው በወተት ውስጥ የሚገኙ የወተቱን ዕድሜ የሚያሳጥሩ ባክቴሪያዎችን መጠን በማብዛት በአጭር ጊዜ ውስጥ እርጎ ማግኘት የሚያስችል ግኝት ነው፡፡

      ‹‹ቤተሰቦቻችን ወተት ከላሚቷ አልበው እንዲረጋላቸው ሁለትና ሦስት ቀን ይጠብቃሉ፡፡ የእኛ ላክቲክ አሲድ ባክቴሪያዎች ግን ወተትን ከስምንት እስከ አሥር ሰዓት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ማርጋት የሚያስችሉ ናቸው፤›› ይላሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር በምርምሩ የተገኘው ላክቲክ አሲድ ፈልቶ በቀዘቀዘ ወተት ላይ የሚጨመር መሆኑም ሌሎች የጤና ጠቀሜታዎች እንዲኖሩት ያደረገው አጋጣሚ ነው፡፡ ወተት ሲፈላ በውስጡ ያሉ እንዲረጋ የሚያደርጉት ባክቴሪያዎች ስለሚሞቱ የተፈላ ወተት መርጋት አይችልም፡፡ ይህ ላክቲክ አሲድ ግን በመፍላት ሒደት ላይ የሚሞቱ ለወተቱ መርጋት ወሳኝ የሆኑ ባክቴሪያዎችን የያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ወተቱን በማፍላት ከላሚቷ ወደ ሰው ሊተላለፉ የሚችሉ እንደ ቲቢ ያሉ በሽታዎች እንዲሞቱ ማድረግና ጤናማ እርጎ በሰዓታት ውስጥ ማግኘት የሚያስችል በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የመጣል ያህል ድርብ ሚና ያለው ግኝት ነው፡፡

      እነዚህ ላክቲክ አሲድ ባክቴሪያዎች የሚያመነጩ ሌላ ምርቶች (ሜታቦላይቶች) አሉ፡፡ ከሚያመነጯቸው ሜታቦላይቶች መካከል መድኃኒቶችን (አንቲባዮቲክ)፣ ኢንዛይሞች፣ የምግቦችን ዕድሜ ለማርዘም የሚረዱ ነገሮችንም እንዲሁ ያመርታሉ፡፡ የፍልልት ሒደትን ከሚያፋጥኑ አሲዶች ውጪ የምግብን ዕድሜ ለማራዘም የሚረዱ ምርምሮች  እየተካሄዱ መሆኑን አቶ ሙላቱ ይናገራሉ፡፡ ምግብ ሳይበላሽ የሚቆይበትን ዕድሜ የማራዘሙ ምርምርም የኢትዮጵያውያን በማይደራደሩበት እንጀራ ላይ ተጀምሯል፡፡

      ምርምሩ እንጀራን ሊበክሉ የሚችሉ እንደ ሳልሞኔላ ያሉ ፈንገሶችን መከላከል የሚችሉ ደቂቅ ዘአካላትን በብዛት በማምረትና በመቀላቀል እንጀራ ሳይሻግት የሚቆይበት ዕድል መፍጠር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ እነዚህ የፍልልት ሒደትን የማፋጠንና የማዘግየት ሚናን የሚጫወቱ ደቂቅ ዘአካላትን በምግብ ዝግጅት ሒደት ለምሳሌ በእንጀራ ላይ ከሊጡ ጋር አብው የሚቦኩ ናቸው፡፡

      የምርምር ማዕከሉ አንድ እንሰት ባሉ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦችም ላይ የፍልልት ሒደትን ማሳጠር የሚችሉ ምርምሮችም በከፊል ተጠናቀዋል፡፡ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ከምግብ ማዕድ የማይጠፋውን ቆጮ ለማዘጋጀት እስከ ስድስት ወራት ሊፈጅ ይችላል፡፡ የእንሰት ተክልን መፋቅና በላስቲክና ቅጠል ጠቅልሎ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲብላላ መሬት ውስጥ መቀበር ይኖርበታል፡፡

      ከራሱ እንሰት፣ ከእንጀራ፣ ከጠላ፣ ከጠጅ፣ የተለዩ ከእርሾ ዝሪያዎች የተውጣጡ በቆጮ ላይ ፈጣን ፍልልት ማካሄድ የሚችሉን መለየት ተችሏል፡፡ የተሻለ ተብሎ በምርምር ማዕከሉ የተዘጋጀው እርሾ ቆጮ ለማዘጋጀት የሚወስደውን እስከ ስድስት ወራት የሚደርስ የተንዛዛ ጊዜን ወደ 15 ቀናትና ከዚያ በታች የሚያወርደው ነው፡፡

     በምግብ ኢንዱስትሪ ላይ የእሽግ ምግቦችን ዕድሜ ለማራዘም ደቂቅ ዘአካላት ዓይነተኛ ግብዓት ቢሆኑም በቀላሉ ስለማይገኙና ዋጋቸውም ወደድ ስለሚል በብዛት ሌሎች ኬሚካሎች በጥቅም ላይ እንደሚውሉ የሚናገሩት አቶ ሙላቱ፣ በብዛት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የታሸጉ ምግቦች ዕድሜያቸው በኬሚካል እንዲረዝም የተደረጉ መሆናቸውን አይሸሽጉም፡፡ በደቂቅ ዘአካላት ምትክ ኬሚካል የተጨመረባቸው ምግቦች ውሎ ሲያድር በጤና ላይ የሚያደርሱት ጉዳት መኖሩ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ለምግብ ዕድሜ ማራዘሚያ ተብለው የሚጨመሩ ደቂቅ ዘአካላት ከዚያው ከምግቡ ውስጥ የሚወሰዱ በመሆኑ በኬሚካሎች ከሚታከሙት በተቃራኒ በጤና ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት አይኖርም፡፡

      ማይክሮ ቢያል ባዮቴክኖሎጂ ሰፊ የምርምር ዘርፍ ነው፡፡ ከምግብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የእንስሳት መኖ አዘገጃጀትና አያያዝ ማሻሻልና ማጎልበት የሚችሉ የደቂቅ ዘአካላት ምርምር የሚካሄድበትም ነው፡፡ በእንስሳት መኖ ላይ የሚከሰቱ መርዛማ ነገሮችን ለመከላከል የሚደረግ የደቂቅ ዘአካላት ምርምር ጋርም የተቆራኘ ነው፡፡ የግብርናና የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶችን ጥቅም ወዳለው ምርት መቀየር የሚያስችል የምርምር ዘርፍ ነው፡፡

      ወደ አካባቢ ቢለቀቁ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ተረፈ ምርቶችን ወደ ባዮ ጋዝና ሌሎች ተለዋጭ የኃይል ምንጮች የመቀየር ሥራም ይሠራበታል፡፡ ከአካባቢ ደኅንነት ጥበቃ ጋርም በተያያዘም ጠቃሚ ምርምሮችን ያመጣል፡፡ ከኢንዱስትሪዎች የሚወጡ በካይ ፍሳሾችን በደቂቅ ዘአካላት በማከም መርዛማነታቸውን የመቀነስ ሥራ የሚሠራው በማይክሮቢያል ባዮ ቴክኖሎጂ ነው፡፡

      ለምሳሌ ከቆዳ ፋብሪካዎች የሚወጡ ቆሻሻዎች የመርዛማ ንጥረ ነገር ይዘታቸው በተለይም የሄቪ ሜታል ክምችታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ወደ አካባቢ ሲለቀቅ በጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ እንዲህ ያሉ ከኢንዱስትሪ የሚወጡ መርዛማ ፍሳሾችን ናቸው በደቂቅ ዘአካላት የሚታከሙት፡፡

     በግብርናው ዘርፍም ደቂቅ ዘአካላት ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ በአፈር ውስጥ ያለው ውስን የናይትሮጅንና የፎስፈረስ ክምችት በምርምር በማገዝ ምርታማነትን ለማሳደግ እንደ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ የሚያገለግለውን ማዳበሪያ መተካት ይቻላል፡፡ ዕፀዋት በመሬት ውስጥ የሚገኘውን ናይትሮጂን እንጂ በከባቢ አየር ውስጥ ያለውን መጠቀም አይችሉም፡፡ መጠቀም የሚችሉት ናይትሮጂንን ወደ ናይትሬት ከተቀየረ በኋላ ነው፡፡ ናይትሮጂን ወደ ናይትሬትነት የሚቀይሩትም ደቂቅ ዘአካላት ናቸው፡፡ ናይትሮጂን ለዕፀዋት ዕድገትና ምርታማነት ወሳኝ ግብዓት ነው፡፡ አርሶ አደሩ ለዩሪያና ኤንፒ ኤስ የሚያወጣውን ወጪ በደቂቅ ዘአካላት መተካት መቻል ሌላ ለግብርናው ዘርፍ እመርታ ይሆናል፡፡

     ሌላው ደቂቅ ዘአካላት በግብርናው ዘርፍ ያላቸው ጠቀሜታ ዕፀዋትን ከተባዮች መጠበቅ መቻላቸው ነው፡፡ በዕፀዋት ላይ የሚከሰቱ ተባዮችን ደቂቅ ዘአካላትን በመጠቀም መቆጣጠር ተቻለ ማለት ለፀረ ተባይ የሚመጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተቻለ ማለት ነው፡፡

      የደቂቅ ዘአካላት ምርምር በጤናውም መስክ ትልቅ ሚና አለው፡፡ አብዛኛዎቹ አንቲባዮቲኮች የሚሠሩት ከደቂቅ ዘአካላት በተለይም ከፈንገስና ከባክቴሪያዎች እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሙላቱ፣ በፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪዎች ላይ የደቂቅ ዘአካላት ተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በቀላሉ በላብራቶሪ ውስጥ መባዛት መቻላቸው፣ እንዱሁም ጠቃሚ ተብለው የተለዩ ደቂቅ ዘአካላት የኋላ ኋላ የሚያስከትሉት የጤና ጉዳት ባለመኖር በመድኃኒት ምርት እንደ መሠረታዊ ግብዓት ሆነው እንዲያገለግሉ ያደርጋቸዋል፡፡

      ምርምር ታክሎባቸው በየዘርፉ በመዋል፡፡ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጡ ደቂቅ ዘአካላት እንደ የሚሰጧቸው ጥቅሞች እየታዩ ግብዓት ይደረጋሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ለግብርና የሚውሉ ደቂቅ ዘአካላት የመድኃኒት ምርት ግብዓት መሆን አይችሉም፡፡ ከዚህም ባሻገር ጠቃሚና ጎጂ ተብለው የሚለዩበት አግባብ እንደ ምርምሩ ዓላማ የተለያየ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የወተትን መርጋት የሚያፋጥን የማይክሮቢያል ባዮቴክኖሎጂ ውጤት ለማግኘት በሚደረግ ምርምር ሒደት ወተት ይዘቱን ጠብቆ እንዲቆይ ዕገዛ የሚያደርጉ ባክቴሪያዎች እንደ ጎጂ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ምርምሩ በተቃራኒው ሲሆን ደግሞ ጠቃሚ የተባሉት ጎጂ ይሆናሉ፡፡

      ኢትዮጵያ ደጋ፣ ወይና ደጋ፣ ቆላ የተባሉ የአግሮ ኢኮሎጂ ዞኖች ባለቤት መሆኗ በርካታ ዓይነት ደቂቅ ዘአካላት መገኛ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡ ለምሳሌ በቆላው አካባቢ በሚገኝ የእርሻ ማሳ ላይና በወይና ደጋ አካባቢ የሚገኘው ማሳ ላይ የሚገኙ ደቂቅ ዘአካላት የተለያዩ ናቸው፡፡ በአንዱ አካባቢ ከፍተኛ ሙቀትን መቋቋም የሚችሉ፣ በሌላው ደግሞ ቅዝቃዜን መቋቋም የሚችሉ የደቂቅ ዘአካላት ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ሁለቱም ደቂቆች በግብርናው ላይ የሚውሉ ነገር ግን የተለያየ ተፈጥሯዊ ባህሪ ያላቸው ናቸው፡፡

      ‹‹ያለው ተለያይነት ኢትዮጵያ የደቂቅ ዘአካላት ክምችት ሀብቷ ትልቅ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከዚህ በፊት የማይታወቁ ዓይነት ደቂቅ ዘአካላትን ሁሉ ልናገኝ እንችል ይሆናል፤›› ሲሉ የክምችት መጠኑ ከፍተኛ እንደሆነ፣ በመስኩ የሚደረጉ ምርምሮችም አገሪቱን ዕድገት ጎዳና የሚመሯት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በዘርፉ የሚደረጉ ምርምሮች ገና ጅምሮች መሆናቸውና ሌሎች ምርምሩን የሚተናነቁ የግብዓት አቅርቦትና ሌሎች ችግሮች ፈተና ሆነዋል፡፡

     በኢትዮጵያ የደቂቅ ዘአካላት ምርምር ገና በጅምር ላይ የሚገኝ ሳይንስ ነው፡፡ በአንዳንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተጀመሩ ሥራዎች ቢሆሩም በብሔራዊ ደረጃ ተቋቁሞ ምርምር መደረግ የተጀመረው በቅርቡ በሆለታ የምርምር ማዕከል ነው፡፡ በጅምር ላይ በሚገኘው ደቂቅ ዘአካላት ምርምር አበረታች የሚባሉ ውጤቶችን፣ በጨለማ ጭላንጭል ብርሃን የመሰሉ የምርምሮች ነጥቦችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ ይህ የምርምር ሒደት ውስጥ ግን ከሠለጠነ የሰው ኃይል ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች የተጋረጡበት ነው፡፡

      የምርምር ሥራዎች ወደ ተጠቃሚው ማድረስ ራሱን የቻለ ሌላ ሥራ ነው፡፡ ነገር ግን እንኳንስ መሰል ምርምሮችን የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ለሆነው ግብርና በቀጥታ ግብዓት የሚሆኑ ምርጥ ዘሮችን ተቀብሎ በበቂ ማዳረስ ላይ ያለው ችግር የሚታወቅ ነው፡፡ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ላይ ግብዓት በመሆን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን የሚችለው የማይክሮ ባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ትኩረት ተደርጎበት ወደ ሥራ የተገባው በቅርብ እንደሆነ አቶ ሙላቱ ይናገራሉ፡፡

     የማዕከሉ ግኝት የሆኑ ሥራዎች መደርደሪያ ማሞቂያ ሆነው እንዳይቀሩ በራሳቸው በቤተ ሙከራ እያባዙ ለተጠቃሚዎች የማሠራጨት ሐሳብ መኖሩን ገልጸዋል፡፡ የደቂቅ ዘአካላት ባለሙያ ካልሆነ በስተቀር ቴክኖሎጂውን እንደተፈለገ በማንም ሰው ማባዛት አይቻልም፡፡ ከዚህ ባለፈ አገሪቱ በማይክሮ ቢያል ባዮቴክኖሎጂ ምርምር ያላትን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ መሥራት  ግድ ነው፡፡

      ‹‹የኬሚካል ራኤጀንቶች ችግር አለብን፡፡ ለምርምሮቹ የሚያስፈልጉ ሪኤጀንቶች ከውጭ የሚገቡ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ያሉ አቅራቢዎች በጣም ውስን ናቸው፡፡ እኛ ምንፈልጋቸውን ሪኤጀንቶች ቶሎ ማግኘት አንችልም፡፡ በዚያ ላይ የሚመጡት ሪኤጀንቶች የአገልግሎት ጊዜያቸው በጣም አጭር ነው፡፡ አቅራቢያዎቹ አምጥተው ቶሎ ካልተወሰደላቸው ይከስራሉ፡፡ ስለዚህ በምንፈልገው መጠን አያመጡልንም፡፡ የዋጋው ውድነት ከውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ጋር ተደምሮ በጣም ችግር ሆኗል፤›› በማለት ምርምሮችን ለመሥራት ፍላጎት ቢኖርም የግብዓት ችግር መኖሩ ውጤታማነታቸው ላይ መንጓተት እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡