Skip to main content
x
የአገር ሸክም የሚቃለለው በተቋማት ግንባታ ነው!

የአገር ሸክም የሚቃለለው በተቋማት ግንባታ ነው!

የዘመናት የአገር ሸክምን ለማቃለል ሲባል መጠነ ሰፊ የሆነ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እየተገባ ነው፡፡ ይህ ለውጥ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ በማጠንጠን ኢትዮጵያን ከነበረችበት ቀውስ ውስጥ ለማውጣት ላይ ታች እየተባለ ነው፡፡ ለዚህም በአገር ውስጥ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት ምኅዳር ለመፍጠር ጠንካራ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡ ዕርምጃዎቹ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን በሥልጡን መንገድ ለመጀመር ያግዛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህ የለውጥ ጅማሮ ላይ ሆነን የኋላ ታሪካችንን በወፍ በረር ስንመለከት፣ ትልቁ የአገር ችግር ለተቋማት ግንባታ የተሰጠው ትኩረት በጣም አናሳ መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት ከሥርዓት ወደ ሥርዓት ስትሸጋገር የገጠሟት ሕመሞች ይታከሙ የነበሩት በማስታገሻዎች እንጂ፣ ዘላቂ ፈውስ በሚያመጡ መድኃኒቶች አልነበረም፡፡ መድኃኒቶቹ ጠንካራ ተቋማት መሆን ሲገባቸውና በሕግ ማዕቀፍ መመራት ሲኖርባቸው፣ ግለሰቦችና ቡድኖች እንዳሻቸው በመፈንጨታቸው በአገር ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሷል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ የዘመናት ማጥ ውስጥ በመውጣት አሁን ስለተቋማት ግንባታ መነጋገር ይገባል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው በአንድነት እንዲቆሙ፣ እርስ በርስ እንዲዋደዱ፣ ለሰላም በፅናት እንዲቆሙና ያለፉትን በደሎች በመተው በፍቅርና በይቅርታ ለበለፀገች ኢትዮጵያ ትንሳዔ እንዲነሱ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ንግግር ሚሊዮኖችን ከዳር እስከ ዳር እንዲነቃነቁ አድርጓል፡፡ በዚህ ስሜት የተነቃቁ ኢትዮጵያውያን ደግሞ አገራቸው ከደመነፍሳዊ አስተዳደር ወደ ሥርዓት ያለው አስተዳደር እንድትሸጋገር ለተቋማት ግንባታ መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለአገራችን ቀርቶ ከአፍሪካ ቀንድ አልፈን ለአፍሪካ ጭምር መድኅን መሆን እንደምንችል ታሪካችን ይመሰክራል፡፡ ታላቁን ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓደዋ የድል ታሪክ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ታሪካዊ ወቅት ደግሞ ይህንን ታላቅ የአገር አደራ የመሸከም ብቃት እንዳለን ማሳየት የምንችለው፣ እርስ በርስ ከመተናነቅ ወጥተን የተቋማት ግንባታ ላይ ስናተኩር ነው፡፡ ተቋማት ሲጠናከሩና ሥራዎች በሕግ ማዕቀፍ ሲመሩ ግለሰቦች ላይ መንጠልጠል ይቆማል፡፡ ሥልጣን በሕጋዊ መንገድ ብቻ ሲያዝ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትም ግዴታ ይሆናሉ፡፡ በየወቅቱ የሚካሄዱ ምርጫዎችም ሰላማዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ሆነው መሪዎች ይፈራረቃሉ፡፡ የኢትዮጵያውያን እያንዳንዷ ድምፅ ዋጋ ይኖራታል፡፡ ይህ ግን የሚገኘው ጠንካራ ተቋማት ሲገነቡ ብቻ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ተቋማት ማለትም ምርጫ ቦርድ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ዕንባ ጠባቂ ተቋምና ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ተፅዕኖ ነፃ ወጥተው በገለልተኝነት መደራጀታቸው እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ከእነዚህ ተቋማት በተነፃፃሪነት ከዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በስተቀር ብዙዎቹ በመሽመድመዳቸው የደረሰውን ችግር አገር ያውቀዋል፡፡ የሕግና የፍትሕ ሥርዓቱ ነፃነቱ በመጣሱና የአስፈጻሚው ተላላኪ በመደረጉ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሕ እንደ ውኃ ጠምቶታል፡፡ መብቶቹ ተገፈው የሹም መጫወቻ ሆኗል፡፡ የሲቪክ ማኅበራት ተሰነካክለው እንደሌሉ ይቆጠራሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት መሥራት የማይችሉበት አሳዛኝ ሁኔታ ተፈጥሮ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ ተቋማቱ ከፓርቲ ተቀጥላነት ሳይላቀቁ፣ ነፃና ገለልተኛ ሆነው ሳይደራጁና በባለሙያዎች ሳይመሩ ሲቀሩ ስለዴሞክራሲም ሆነ ስለሰብዓዊ መብት መነጋገር አይቻልም፡፡ ሕግ አውጭው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው አንዱ ሌላውን የሚቆጣጠርበት አሠራር ባመስፈኑና መናበብ ባለመቻላቸው፣ የአስፈጻሚው ጡንቻ ብቻ እየፈረጠመ የደረሰው ምስቅልቅል ይታወቃል፡፡ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ገነው በመውጣት አገርን ምን እንዳደረጓት በሚገባ ከመታወቁም በላይ፣ በአገር ላይ ለተፈጠረው ቀውስ ዋነኛ መንስዔ ነው፡፡ ጠንካራ ተቋማት ተገንብተው ቢሆን ኖሮ ግን ይህ ሁሉ ብልሽት ባላጋጠመ ነበር፡፡

የተቋማት ተጠናክሮ መውጣት መሪዎች አገርን በሥርዓት እንዲመሩ፣ ሥልጣናቸው ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖርበት፣ ከአንድ አሠራር ወደ ሌላ ሲሸጋገሩ በነሲብ ሳይሆን በሕግ ብቻ እንዲመሩ ይረዳል፡፡ አለበለዚያ ግለሰቦች የነገሡበት የእንዳሻህ አሠራር እየሰፈነ ሕዝብ ሲቆጣ ኃይል ይከተላል፡፡ ለምሳሌ በልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና የቆረበ የመንግሥት ፖሊሲ ሕዝብ ላይ ተጭኖ፣ ባለሥልጣናት ግን በኒዮሊበራል አቋራጭ መንገድ ራሳቸውንና ቢጤዎቻቸውን በሀብት ሲያበለፅጉ ተስተውለዋል፡፡ ሌብነትና ዝርፊያ ከሚታሰበው በላይ ሆኖ ኢትዮጵያ መተንፈስ እስኪያቅታት ድረስ ዕዳ ውስጥ ስትዘፈቅ፣ እዚህ ግባ የሚባሉ ተቋማት አለመኖራቸው የችግሩን ክብደትና መጠን ያሳየናል፡፡ በልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ፍልስፍና የመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ መጠን ያለው የአገር ሀብት እያገላበጡ፣ በአገር ላይ የደረሰው ጉዳት ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት የጎደለውና ተጠያቂነት ስሌለበት የአገር ሀብት እንዴት እየባከነ እንደሆነ፣ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን ሪፖርቶች ማገላበጥ በቂ ነው፡፡ ጠያቂና ሞጋች ኅብረተሰብ መፍጠር የሚችሉ ተቋማት ስለሌሉ አገር የግለሰቦች መጫወቻ ሆናለች፡፡ ይህ የውድቀት ማሳያ ነው፡፡ የተፈጠረው ምስቅልቅልም ከበቂ በላይ ይናገራል፡፡

በፖለቲካ መስክ የደረሰው ጥፋት ዋናው የአገር ጎዶሎ ነው፡፡ መንግሥትና ፓርቲን ለመለየት እስኪያስቸግር ድረስ በመቀላቀላቸው ግለሰቦች ከሕግ በላይ ሆነዋል፡፡ ሕግን የመሰለ የሰው ልጆች ከለላና አለኝታ የግለሰቦችና የቡድኖች ማጥቂያ መሣሪያ ሆኗል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ገለልተኛ መሆን ይገባቸው የነበሩ ዴሞክራቲክ ተቋማት፣ የፀጥታ መዋቅሮች፣ የሲቪክና የሙያ ማኅበራትን በማዳከም እንደ ግል ንብረት የተጫወተባቸው፣ ተጠያቂነት የሌለበት ሥርዓት ገንብቶ እንዳሻው ለመሆን ነው፡፡ ተቃዋሚዎቹንና የሰላ ትችት የሚያቀርቡትን በሰበብ አስባቡ እያሰረና እያሳደደ ከመድረኩ ገለል በማድረግ፣ የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ኦና አድርጎታል፡፡ መንግሥትና ፓርቲ ዳር ድንበራቸው እስከማይታወቅ ድረስ መንግሥታዊ ተቋማት የካድሬ መጫወቻ ሆነዋል፡፡ ግለሰቦች ከሕግ በላይ እየሆኑ እንዳሻቸው በሥልጣን ባልገዋል፡፡ ከእነሱ በላይ ምንም ነገር የሌለ ይመስል በርካታ ኃጢያቶች ተፈጽመዋል፡፡ ሕዝባዊ አመፁ ገንፍሎ በመውጣት ላለፉት ሦስት ዓመታት ያህል ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለው፣ ሕዝብ ተረስቶ ግለሰቦች ስለነገሡ ነው፡፡ ተቋማት ተሽመድምደው ሃይ ባይ በመጥፋቱ ነው፡፡ ሥርዓት ራሱ ግለሰብ ላይ ተንጠልጥሎ ተቋማት መገንባት ሲያቅተው ነቀዝ እንደበላው  ዛፍ ይገነደሳል፡፡ ጣጣውም ለአገር ይተርፋል፡፡

ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ሁለገብ ለውጥ መሠረታዊ መሆን አለበት ሲባል፣ ለውጡ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ አንድምታ ሊኖረው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን በግንባር ቀደምትነት ለመምራት የሚያስችላትን መደላድል ለመፍጠር ለውጡ ግዙፍ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ታላላቆቹ ኃያላን አገሮችና የዓረብ ባህረ ሰላጤ ሀብታም አገሮች በአካባቢው የበላይነት ለመያዝ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ የኢትዮጵያን ብቁና ንቁ ሆኖ የመገኘት ራዕይ አጥብቆ ይሻል፡፡ በርካታ ታላላቅ አገሮች ወደ አካባቢው ሲዘልቁ የኢትዮጵያን ጥንካሬና ወሳኝነት ስለሚጠይቅ፣ ተቋማት ተጠናክረው እንዲወጡ የግድ ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚያስተምረው በአካባቢው ገናና ሆኖ መውጣት አለመቻል ለእርስ በርስ ግጭት ከመዳረጉም በላይ፣ ግለሰቦች አምባገነን እንዲሆኑና ደካማ አገር እንድትፈጠር ያመቻቻል፡፡ ድህነትን ያባብሳል፡፡ ኢትዮጵያውያን በሠለጠነ መንገድ ልዩነታቶቻቸውን በመፍታት ትክክለኛው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ፈቃደኝነታቸውን ካሳዩ፣ ኢትዮጵያ የተበላሸ ገጽታዋ በአዲስ ተስፋ ተተክቶ እንደገና ትወለዳለች፡፡ ያለፉት ዘመናት ክፉ ውርሶችን ለታሪክ መዛግብት በመተው አገርን ማስቀደም ከተቻለ፣ እንኳን ለሕዝባችን ለአፍሪካውያን የሚተርፍ ታሪክ መሥራት ይቻላል፡፡ አገር ከምንም ነገር በላይ በመሆኗ ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ይሰጥ፡፡ ግለሰብ አገርን መተካት አይችልም ይባል፡፡ የአገር ሸክም የሚቃለለው በተቋማት ግንባታ ነው!