Skip to main content
x
አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ የግል ባንኮች ባሉባቸው ችግሮችና መፍትሔዎች ዙሪያ እያነጋገሩ ነው

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ የግል ባንኮች ባሉባቸው ችግሮችና መፍትሔዎች ዙሪያ እያነጋገሩ ነው

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የግል ባንኮች ፕሬዚዳንቶችንና ሥራ አስፈጻሚዎችን በተናጠል ማነጋገር ጀመሩ፡፡

የባንኩ ገዥ የሁሉንም ባንኮች ኃላፊዎች በማነጋገር ላይ የሚገኙት ለሁሉም ባንኮች ባስተላለፉት ጥሪ መሠረት ሲሆን፣ የየባንኮቹ ኃላፊዎችም በተያዘላቸው ፕሮግራም መሠረት ከገዥው ጋር ለሰዓታት ውይይት ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ካለፈው ዓርብ፣ ሰኔ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. የጀመረው በተናጠል የግል ባንኮች ኃላፊዎችን የማወያየት ሒደት እስከ መጪው ሳምንት እንደሚዘልቅ ይገመታል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር  በተናጠል የውይይት መርሐ ግብር የጠሩበት ዋናው ዓላማ፣ የአገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ሪፎርም ለማድረግ የሚረዳ ግብዓት ለማሰባሰብ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ስለአገሪቱ ወቅታዊ የፋይናንስ ሁኔታና የግል ባንኮች አሉብን በሚሏቸው ችግሮች ዙሪያ ከኃላፊዎቹ ጋር ሐሳብ ለመለዋወጥ ነው፡፡ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ እንዴት አብሮ መሥራት ይቻላል? የሚለው የመወያያ አጀንዳ እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት የመመካከርና የመነጋገር ዕድል ባለመኖሩ በአዲሱ ገዥ የተጀመረው ምክክር በገዥው ባንክና በሚቆጣጠራቸው ተቋማት መካከል በኢንዱስትሪው ውስጥ ተግባብቶ ለመሥራት ጥሩ ጅምር ስለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

በብሔራዊ ባንኩ በኩል የሚታዩ ችግሮች ምንድን ናቸው? የሚሉ መጠይቆችም ለውይይት ከሚነሱ ነጥቦች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ታውቋል፡፡ የባንኮቹ ኃላፊዎች  አጠቃላይ በኢንዱስትሪው ከሚታየውና ከራሳቸው አንፃር ችግሮች ናቸው በሚሏቸው መስኮች ሐሳባቸውን እየሰነዘሩ ሲሆን፣ በየተራ ከገዥው ጋር የሚገናኙ ኃላፊዎችም የየራሳቸው የመፍትሔ ሐሳብ ጭምር እያቀረቡ እንደሚገኙም ታውቋል፡፡   

በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ መሻሻል አለባቸው ተብለው በባንክ ባለሙያዎችና በኢኮኖሚ ተንታኞች ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ፣ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተመሳሳይ ተቋማት የተለያዩ መመርያዎች ወጥቶላቸው እንዲሠሩ መደረጉ አግባብ አለመሆኑ ነው፡፡ የባንኮቹ ኃላፊዎች ለገዥው ከጠሷቸው ችግሮች ዋነኛው እንደሆነም ተሰምቷል፡፡

የብሔራዊ ባንክ መመርያዎች በአብዛኛው የግል ባንኮች ላይ ጫና በመፍጠር እንዲተገብሯቸው የሚያስገድዱ ናቸው እየተባለ ገዥው ባንክ ሲተች ቆይቷል፡፡ በግል ባንኮች ላይ አስገዳጅ ሆነው የሚተገበሩት መመርያዎች ግን በመንግሥት ባንኮች የማይተገበሩ በመሆናቸው፣ የውድድር ሜዳውን ለመንግሥት ያደላ እንዲሆን ያደረጉ ናቸው በማለት እንዲህ ያሉት አሠራሮች መስተካከል አለባቸው የሚሉ ጥያቄዎችም ለገዥው ቀርበውላቸዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ ኃላፊ፣ ለወቅቱ የሚመጥን ማዕከላዊ ባንክ እንዲኖር እንፈልጋለን በማለት ስለምክክሩ ገልጸው፣ በተናጠል በሚደረገው ውይይትም ይህንኑ የሚያንፀባርቅ ሐሳብ ማንሳታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መንግሥታዊ ተቋም እንደመሆኑ አገራዊ ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ የግል ባንኮችም እንደየአቅማቸው ከንግድ ባንክ ያልተናነሰ ሊያበረክቷቸው የሚችሏቸው ጉዳዮች በመኖራቸው በገበያው ውስጥ በእኩል ዓይን ታይተው እንዲሠሩ የሚያደርግ አሠራር መዘርጋት እንዳለበት እየተጠየቀ ነው፡፡ በብሔራዊ ባንክና በግል ባንኮች መካከል ያለው ግንኙነት ‹‹የገዥና የተገዥ፣ የአዛዥና ታዛዥ ነው፤›› እየተባለ ሲብጠለጠል ቆቷል፡፡ ይህ በመሆኑም የመንግሥትና የግል ባንኮችን ያለአድልኦ የሚመለከትና ለማደግ የሚረዳቸውን አጋዥ አሠራር እንዲከተል ማድረግ  እንደሚገባም የባንክ ኃላፊዎች እያሳሰቡ ስለመሆናቸው ተሰምቷል፡፡

 በአሁኑ ወቅት የግል ባንኮችን ሸብበው የያዙ መመርያዎች እንዲሻሻሉ ለአዲሱ ገዥ ሐሳብ እያቀረቡ ያሉት የንግድ ባንኮች ኃላፊዎች፣ እስካሁን ከገዥው ጋር የተነጋገሩ ኃላፊዎችም ይህንኑ ጥያቄ ስለማቅረባቸው ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ብሔራዊ ባንክ እንቅስቃሴ በመጀመሩ ባንኩን ሪፎርም ለማድረግ የሚያግዙ ሐሳቦችን ለማሰባሰብ የግል ባንኮችን ማነጋገር መጀመሩ በበጎ ጎኑ ታይቷል፡፡ በመነጋገርና መመካከር ላይ የተመሠረተ ለውጥ ወደፊት በጋራ ለመሥራት ዕድል ከመስጠቱም በላይ፣ በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም ተዋናዮች ተገቢውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መንገዱን እንደሚጠርግ ከገዥው ጋር የተወያዩ የባንክ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኃላፊዎቹ እንደገለጹት፣ ብሔራዊ ባንክ ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ ብሎም ራሱን ለማሻሻል ያለውን ፍላጎት ያመለከተበትን የለውጥ መንገድ ጀምሯል፡፡ ይበል፣ ይቀጥል ባሉት ጅምር መሠረት፣ የተናጠል ምክክሩ እንዳበቃ አጠቃላይ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ተዋናዮች የሚሳተፉበት የጋራ መድረክ በብሔራዊ ባንክ እንደሚጠራና መሰናክል የሆኑት የባንኩ መመርያዎች በየደረጃው ጊዜ ሳይፈጁ እንደሚሻሻሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡