Skip to main content
x
የሰንሻይን ፋውንዴሽን የአሥር ዓመታት በጎ ተግባራት

የሰንሻይን ፋውንዴሽን የአሥር ዓመታት በጎ ተግባራት

በሪል ስቴት፣ በመንገድ ግንባታዎችና በሆቴል ኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማራው ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ግሩፕ፣ በሥሩ ከሚያስተዳድራቸው የንግድ ሥራዎች ባሻገር ያለ ትርፍ ለበጎ ተግባር የተቋቋመው ሰንሻይን ፋውንዴሽንም የኩባንያው መለያ ነው፡፡

ፋውንዴሽኑ አቅም የሌላቸውን ቤተሰቦች ለመደገፍና ልጆቻቸውንም ለማስተማር በማሰብ ሥራውን የጀመረው ከአሥር ዓመታት በፊት በነቀምት ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የገነባው ትምህርት ቤት፣ 200 ተማሪዎችን ከእነ ሙሉ ወጪያቸው በመሸፈን ማስተማር የጀመረበት ምዕራፍ ነው፡፡  

ከነቀምት በተጨማሪ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን፣ አገና ከተማ በገነባው ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች የዓመቱ የትምህርት ዘመን ማጠናቀቁን መነሻ በማድረግ በተዘጋጀው ፕሮግራም ወቅት ለተማሪዎች ልዩ ልዩ ማበረታቻ ተበርክቷል፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በነቀምት፣ በአክሱምና በአገና በተገነቡ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1,350 ተማሪዎችን ተቀብሎና ሙሉ ወጪያቸውን ችሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ፋውንዴሽኑ አስታውቋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ሽልማት ያበረከቱት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለቤትና ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ፣ ፋውንዴሽኑ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ በመጥቀስ አወድሰውታል፡፡ ከፋውንዴሽኑ በቀረበው ማብራሪያም እስካሁን በፋውንዴሽኑ የተገነቡት ሦስት ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ የግንባታ ወጪያቸው ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ይገመታል፡፡ በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎች ቤተሰቦች በየወሩ 200 ብር የኪስ ገንዘብ እየከፈለ ልጆቻቸውን እያስተማረ እንደሚገኝ ፋውንዴሽኑ አስታውቋል፡፡

የፋውንዴሽኑ መረጃ፣ ለሦስቱ ትምህርት ቤቶች ሥራ ማስኬጃና ለተማሪዎች የሚሰጠው ቋሚ የገንዘብ ድጋፍ ሲታከሉ በየወሩ ከ800 ሺሕ ብር በላይ ወጪ እያደረገ እንደሚገኝ ያመላክታል፡፡ በዚህም መሠረት ፋውንዴሽኑ እስካሁን ድረስ ከ127 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንዳደረገና ወደፊትም የፋውንዴሽኑ ዓመታዊ ወጪ ከእጥፍ በላይ እንደሚያድግ ተጠቁሟል፡፡  

የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ፕሬዚዳንትና የፋውንዴሽኑ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለኑሮ ችግር የተዳረጉ ልጆችን ለመደገፍ በደብረ ብርሃን ከተማ  350 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችልና ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚያደርግበትን ትምህርት ቤት መገንባት ይጀምራል፡፡ ይህ ግንባታ ሲጠናቀቅ ፋውንዴሽኑ በአራቱም ትምህርት ቤቶች የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ቁጥር 1,700 የሚደርስ ሲሆን፣ ለትምህርት ቤቶች የሥራ ማካሄጃያና ለተማሪዎች ቤተሰቦች የሚደረገው ወርኃዊ ድጋፍ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ ተጠቅሷል፡፡  

ለኑሮ ችግር የተዳረጉ ልጆችን እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ድረስ ከማስተማር ጎን ለጎን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባገኘው ቦታም 500 አረጋውያን የሚጦሩበት ማዕከል ግንባታ እያካሄደ እንደሚገኝ የፋውንዴሽኑ መረጃ ይጠቁማል፡፡ የዚህ ማዕከል ግንባታ 85 በመቶ መጠናቀቁም ገልጿል፡፡

እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ፣ 65 ሚሊዮን ብር የሚፈጀው የአረጋውያን ማዕከል በሚቀጥለው ዓመት ተመርቆ ለአገልግሎት በሚበቃበት ወቅት ለአረጋውያኑ ክብካቤና ለሥራ ማስኬጃ በየወሩ ግማሽ ሚሊዮን ብር ወይም በዓመት ስድስት ሚሊዮን ብር ወጪ ይጠይቃል፡፡

ለሦስቱ ትምህርት ቤቶች በዓመት የሚያስፈልጋቸውን ወጪ ፋውንዴሽኑ እስካሁን ሲሸፍን የቆየው መስቀል አደባባይ አካባቢ ከሚገኘው የኮንስትራክሽን ኩባንያው ሕንፃ ዓመታዊ ኪራይ ሲሆን፣ የኪራይ ገቢውን ለዚህ በጎ አድራጎት ሥራ ሲያውል መቆየቱን አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል፡፡

በመጪው ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገባ ለሚጠበቀው የአረጋውያን ማዕከል ዓመታዊ ወጪ መሸፈኛ ይሆን ዘንድ፣ ከማዕከሉ አጠገብ ከአዲስ አበባ አስተዳደር በተፈቀደለት ቦታ ላይ ባለ ሁለት ወለል ሕንፃ በመገንባት ከሕንፃው ኪራይና ሌሎች አገልግሎቶች የሚገኘውን ገቢ ለማዕከሉ መደጎሚያነት እንደሚያውለው አስታውቀዋል፡፡

ለገቢ ምንጭነት የሚውለው ሕንፃ ግንባታም ከአረጋውያን ማዕከሉ ግንባታ ጋር አብሮ በመጪው ዓመት የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ለበጎ አድራጎት ፋውንዴሽኑ ድጋፍ የሚሰጠውን እንዲህ ያለ የገቢ ምንጭ መመሥረት ያስፈለገበትን ምንክንያት አቶ ሳሙኤል ሲያስረዱ፣ በቢዝነስ ዓለም ውስጥ ማትረፍና መክሰር ስለሚያጋጥም በእንዲህ ያለው አጋጣሚ የፋውንዴሽኑ ተግባራት ሳይተጓጎሉ እንዲጓዙ ለማድረግ በማስፈለጉ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ብዙ ጊዜ በባንክ ብድር ጭምር ስለምንሠራ፣ የገንዘብ እጥረት የሚያጋጥምበት ወቅትም ስለሚኖር እንዲህ ያለው ዘዴ አረጋውያኑና ተማሪዎቹ ሳይበተኑ የሚደረግላቸው ድጋፍ ዘላቂ እንዲሆን ያስችላል፤›› ያሉት አቶ ሳሙኤል፣ ይህንን አባባላቸውን ለማጠናከር እንደ ምሳሌ የጠቀሱት ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ የሚገነባው ማሪዮት ሆቴል ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ በማብራራት ነበር፡፡ የሆቴሉ ግንባታ ወጪ ሁለት ሦስተኛው በባንክ ብድር የተሸፈነ በመሆኑ፣ የባንክ ብድር በመክፈልና በሌሎችም ወጪዎች ሳቢያ የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥም የበጎ አድራጎት ሥራው እንዳይተጓጎል የሚያግዙና በየራሳቸው ገቢ የሚተዳደሩ ተቋማት እንዲሁኑ ማድረጉ ተመራጭ ሆኖ መገኘቱን አብራርተዋል፡፡

የቢዝነስ ተቋማት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንደ መደበኛ የሥራ ድርሻቸው መያዝ አለባቸው የሚል እምነት ያላቸው አቶ ሳሙኤል፣ ፋውንዴሽናቸውን ይበልጥ በማጠናከር ከአንድ ዓመት በኋላም በአዲስ አበባ እንደተገነባው ዓይነት የአረጋውን ማዕከል በደሴ ከተማ እንደሚገነቡ ገልጸዋል፡፡ በደሴ የሚገነባው ማዕከል 500 አረጋውያንን ለመንከባከብ የሚችልበት አቅም እንደሚኖረውም ተጠቅሷል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከ2,500 በላይ ሠራተኞች ያሉት ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ ሠራተኞቹን ለመደገፍ በየአምስት ዓመቱ በሥራቸው ከፍተኛ ውጤት ለሚያስመዘግቡ 40 ሠራተኞች የመኖሪያ ቤትና የገንዘብ ሽልማት በመስጠት ሠራተኞች በማበረታታት እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል፡፡

በ2010 ዓ.ም. በከፍተኛ ውጤታማነታቸው ከተመረጡት 40 ሠራተኞች ውስጥ 10 ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት፣ ቀሪዎቹ ደግሞ እንደ ሽልማት ከሚሰጣቸው ቤት ውስጥ 40 በመቶውን እነሱ፣ 60 በመቶውን በኩባንያው ወጪው ተሸፍኖላቸው እንደሚሸለሙ ታውቋል፡፡ ይህም የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት ተግባር ጋር እንደሚያያዝና በየአምስት ዓመቱ አንድ ጊዜ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

እንዲህ ዓይነት የበጎ አድራጎት ተግባር በመደገፍ በአገርና የፋውንዴሽኑ ተማሪዎች ምረቃ ላይ የተገኙት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፉት ወ/ሮ ሮማን ለመማር ዕድል በማግኘታችሁ ልትደሰቱ ይገባል ብለዋል፡፡