Skip to main content
x
‹‹ኢኮኖሚው ወይም አገር ሳይንኮታኮት የምናድንበት ዕድል ከሰጠ ለውጡ ትልቅ ስጦታ ነው›› አቶ አወት ተክኤ፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ

‹‹ኢኮኖሚው ወይም አገር ሳይንኮታኮት የምናድንበት ዕድል ከሰጠ ለውጡ ትልቅ ስጦታ ነው›› አቶ አወት ተክኤ፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ

አቶ አወት ተክኤ የኢኮኖሚ ባለሙያ ናቸው፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በተመሳሳይ በኢኮኖሚክስ ከባንግሎር ዩኒቨርሲቲ (ህንድ) አግኝተዋል፡፡ አቶ አወት በሥራው ዓለም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢኮኖሚ ተመራማሪ፣ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ደግሞ የስትራቴጂክ ፕላኒንግ ስፔሻሊስት በመሆን አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎሜሽን ኤጀንሲ የገጠር ፋይናንስ አገልግሎት ከፍተኛ ኤክስፐርት በመሆን እየሠሩ ነው፡፡ ዳዊት ታዬ ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ በአገሪቱ በኢኮኖሚ ውስጥ ጉዳዮች ዙሪያ እየታየ ያለውን እንቅስቃሴና ሪፎርሞችን በተመለከተ፣ በቅርቡ በጥቁር ገበያውና በመደበኛው የባንክ መገበያያ የውጭ ገንዘቦች የምንዛሪ ዋጋ እየጠበበ ስለመምጣቱና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከጥቂት ወራት ወዲህ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የሚመለከቱ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ በእርስዎ ዕይታ በኢኮኖሚው ላይ ይደረጋሉ ተብለው የሚታሰቡ ለውጦች እንዴት ይታያሉ? በተግባር ለውጥ ይኖራል ብለው የሚያስቧቸው ዋና ዋና ጉዳዮች የትኞቹ ይሆናሉ ብለው ይጠብቃሉ?

አቶ አወት፡- አሁን ይደረጋሉ ብዬ ከማስባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የሚመለከት ነው፡፡ በተለይ እንደ ስኳር፣ ማዳበሪያና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች እስካሁን ባለው አካሄድ አይቀጥሉም፡፡ በእነዚህ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ያሉ ችግሮች በደንብ ተጠንተው፣ በተለይ የፋይናንስ  አቅማቸውና አጠቃቀማቸው ተለያይቶ ወደ ሥራ የሚገቡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ አንዳንዶቹ ከአቅም በላይ የሆኑት ይቋረጣሉ፡፡ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ደግሞ ወደ ግል የሚዘዋወሩበት አሠራር እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በቀጣዩ የበጀት ዓመት ምንም ዓይነት ትልልቅ የሚባሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶች አይኖሩም፡፡ ምክንያቱም ትኩረት የሚደረግባቸው የተመረጡ ፕሮጀክቶች ላይ ብቻ ነው፡፡ ቀደም ብሎ እነዚህ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር የተደፈረውን ያህል ለማጠናቀቅ አልተቻለም፡፡ በድፍረት የተገባባቸው ነበሩ፡፡ ስለዚህ አሁን ትልቁ ሥራ አቅማቸውን ያገናዘበ በተለይም የፋይናንስ ሒደታቸውን ማጥራት ላይ ነው ትኩረት የሚደረገው፡፡ በእነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ በሚደረግ  ጥናት በቀጣይ ምን መደረግ እንደሚኖርበትም ይታወቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አሁን እየተደረገ ባለው ለውጥ በከፍተኛ ሁኔታ ይተገበራል ብዬ የምጠብቀው ከታክስ አስተዳደር ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የታክስ አስተዳደር ምን አዲስ ነገር ሊኖር ይችላል?

አቶ አወት፡- እስካሁን ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ታክስ እየተሰበሰበ አይደለም፡፡ እየተሰበሰበ ያለው ከታሰበው በታች ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ ሁለት ነገሮች እንደሚሠሩ አምናለሁ፡፡ አንዱ የታክስ አሰባሰብ ሥራውን ማዘመን ነው፡፡ ዜጎች በአግባቡ የታክስ ግዴታቸውን እንዲወጡ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ይደረጋል፡፡ ይኼም ብቻውን ሳይሆን የሚጠበቅባቸውን ግብር በማይከፈሉት ላይ ደግሞ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይመስልኛል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ዕርምጃ የታክስ ሥርዓቱን ግልጽ በሆነ አሠራር እንዲቃኝ ያደርገዋል፡፡ ሌሎች ከኢኮኖሚው ጋር የተያያዙ ለውጦችም አሉ፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው ለውጥ ያመጣቸዋል ወይም እንደሚተገብራቸው የሚታመነው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የበጀት አስተዳደርና ቁጥጥር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛ የሆነ ቁጥጥር በማድረግ ለአንድ ሥራ የተመደበ በጀት በትክክል ለተፈለገው ዓላማ መዋሉ የሚያረጋግጥበት ተቋማዊ የሆነ አሠራር ይኖራል፡፡ ይህ አሠራር ተጠያቂነትን ጭምር ሲኖረው፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ችግሮችን ገልጾ ማለፍ ብቻ ሳይሆን ችግር የተገኘበት ሰው የሚጠየቅበት ነው፡፡ የተሰጠውን ሥራ በአግባቡ አለመሥራቱ ከተረጋገጠ በኃላፊነቱ የሚቀጥልበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ሥራው ሳይሠራ የቀረው በማን ድክመት ነው? ተብሎና ተለይቶ ዕርምጃ የሚወሰድበት አሠራር ይኖራል፡፡ እስካሁን በነበረው አካሄድ ብዙ ነገሮችን በአንዴ ለመሥራት ታስቦ እንዲተገበር ይደረግ ነበር፡፡ ይህ የራሱ የሆነ ስኬቶችና ውድቀቶች ነበሩበት፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ሪፎርም የሚደረግበት ይሆናል ብዬ የማምነው ትኩረት አጽንኦት የሚሰጥበት አሠራር ነው፡፡ ኢኮኖሚው ትኩረት የተደረገባቸው ሥራዎች ላይ ብቻ አነጣጥሮ፣ እነዚህም ተለይተው በአግባቡ የመሥራትና የማጠናቀቅ ሥራ ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

አቶ አወት፡- ለምሳሌ ግብርናው ላይ ስንመጣ የኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ማምረት፣ የሆልቲካልቸር ግብርናን ማስፋፋት፣ ግብርናን ደግሞ ወደ ዘመናዊ አሠራር ማስገባትና የመስኖ ሥራ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡  ሌላው የወጪ ንግድን የተመለከተ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሁልጊዜ ኢኮኖሚው ኤክስፖርት መር ነው እያልን ቆይተናል፡፡ ግን ኤክስፖርት የመሪነት ሚናውን ሊጫወት አልቻለም፡፡ ስለዚህ በኤክስፖርት ላይ ያሉ መዋቅራዊ ችግሮችምን በመለየት መሠረታዊ መፍትሔ የሚመጣባቸው ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ይሠራል፡፡ በኢንዱስትሪ ረገድም ማኑፋክቸሪንግ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ቢሆንም፣ አምራቾች ለምርቶቻቸው የሚጠቀሙዋቸው አብዛኞቹ ግብዓቶች ከውጭ የሚገቡ ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ ለወጪ ንግዱ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ምክንያቱም የሚያመጡትን የውጭ ምንዛሪ መልሰው ለግብዓት መግዣ የሚያወጡ በመሆኑ ነው፡፡ አንድ ኢንዱስትሪ የአገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀም ካልቻለ ጠቃሚነቱ እምብዛም ነው፡፡ ስለዚህ በአገር ውስጥ ምርት የሚጠቀም ኢንዱስትሪ የሚበረታበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ወይም ደግሞ ለኢንዱስትሪዎቹ የሚሆኑ ግብዓቶችን በሰፊው ማምረት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርበት አሠራር ይዘረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በፓርላማ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መንግሥት ከአገር ውስጥ ግብዓት የሚጠቀሙትን እናበረታታለን ብለዋል፡፡ ይህ አባባላቸው እንዴት ይገለጻል? በዚህ ረገድ የሚለወጥ ነገር ይኖራል?

አቶ አወት፡- ማበረታቻ የነበረ ነው፡፡ ነገር ግን የበለጠ ትኩረት የሚደረግበት መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡ ለምሳሌ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለምርታቸው የሚሆኑ ግብዓቶችን ከውጭ የሚያስገቡ ከሆነ፣ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ መልሰው እየተጠቀሙበት ጥቅሙ ትንሽ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች እንዲራመዱ ለማድረግ ግብዓቶቻቸውን ከአገር ውስጥ እንዲገዙ ማበረታቻ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ለእነሱ የሚሆነውን ግብዓት በሰፊው ማምረት ነው፡፡ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሊሆኑበት የሚያስችላቸው ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብላቸው ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ነው፡፡ ስለዚህ ከመንግሥት የሚሰጠው ማበረታቻ ግብዓቶቻቸውን ከአገር ውስጥ እንዲገዙ ማድረግ መሆኑን ያሳያል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ አነጋጋሪ የሆነ አንድ ክስተት ተፈጥሯል፡፡ ይህም ባልተጠበቀ ሁኔታ በጥቁር ገበያውና በመደበኛው የባንክ አገልግሎት የውጭ ገንዘቦች የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት ጠቧል፡፡ እንዲህ ያሉ ለውጦች ለመከሰታቸው በትክክል ምክንያቱም ምንድነው ሊባል ይችላል?

አቶ አወት፡- በባንክና በጥቁር ገበያ ምንዛሪ ዋጋ ላይ ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ነበር፡፡ አሁን የተወሰነ መረጋጋት ይታያል፡፡ ልዩነቱ እየጠበበ እየመጣ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ  መረጋጋት የመጣባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ በመጨመሩ ይሆናል፡፡ ይህም በዕርዳታ የተገኘ ገንዘብ ገብቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ከተለያዩ ሌሎች ምንጮችም ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ሲጨምር ወደ ጥቁር ገበያ ሄዶ ይገዛ የነበረው ተጠቃሚ ወደ ባንክ ስለሚያደላና አስተማማኝ ስለሚሆን የጥቁር ገበያው እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ግን ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ ጨምሯል ማለት ይቻላል? በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ እንዲቀንስ ምክንያቱ ወደ ብሔራዊ ባንክ  የውጭ ምንዛሪ በመግባቱ ብቻ ነው?

አቶ አወት፡- ለጥቁር ገበያ ዋጋ መቀነስ ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው የውጭ ምንዛሪ ብቻ አይደለም፡፡ ለጥቁር ገበያው ዋጋ መቀነስ ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ ምን? ምን?

አቶ አወት፡- አንዱ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት በዕርዳታም ሆነ በብድር ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው ዶላር መጨመር ነው፡፡ መንግሥትም ዳያስፖራዎችን በማግባባት ወደ አገር ቤት የሚልኩትን ገንዘብ በባንክ እንዲልኩ የተለያዩ የማግባቢያ ሥራዎችን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ስለተሠሩ ይህ ቅስቀሳ በባንክ የሚላከውን የውጭ ምንዛሪ እንዲጨምር ሊያደርገው ይችላል፡፡ ሌላው ለሰሞኑ ለጥቁር ገበያ መቀነስ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ጥሪ ነው፡፡ ግለሰቦች ቤታቸው ውስጥ ገንዘብ በማስቀመጥ፣ በዚህ ገንዘብ ወደ ጥቁር ገበያ ሄደው ሲገዙ ብዙ ዶላር ፈላጊ አለ ማለት ነው፡፡ አሁን ግን እነዚህ በየቤታቸው ብርም ሆነ ዶላር ያስቀመጡ ሰዎች ወደ ባንክ እንዲያስገቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር ማበረታቻ ስለተሰጠና ሕጋዊ ዕርምጃ ሳይመጣባቸው ገንዘባቸውን በሕጋዊ መንገድ የሚያስቀምጡበት መልዕክትም ስለተላለፈ፣ እነዚህ ሰዎች ወደ ባንክ ሄደው ማስቀመጥ መጀመራቸው የጥቁር ገበያውን ፍላጎት ይቀንሳል፡፡ እነዚህ የውጭ ምንዛሪ የሚያስቀምጡ ሰዎች ምንም ዓይነት ንግድ ላይ የሌሉም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የማያስፈልጋቸውም ይሆናል፡፡ አስቀምጠውት አተርፍበታለሁ በማለት የያዙም ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ወደ ባንክ ሲሄዱ የጥቁር ገበያውን ፍላጎትና አቅርቦት ሊቀንስ ይችላል፡፡ በቤታቸው ያለውን ገንዘብ ወደ ባንክ ያላስገቡ ሰዎች ደግሞ ገንዘቡን ሸሽገው በማስቀመጣቸው ሕጋዊ ዕርምጃ ስለሚኖር፣ እሱን በመፍራት ያላቸውን ወደ ባንክ አስገብተውም ሊሆን ይችላል፡፡

ሌላው እንደ ትልቅ ምክንያት የሚቆጠረው የመንግሥት ውሳኔ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ከፍተኛው የውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚ ራሱ መንግሥት ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ፕሮጀከቶች ስላሉት የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በቀጣዩ በጀት ዓመት አዳዲስ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የሉኝም፣ የተጀመሩትን ለመጨረስና ለማጥራት ነው የምሠራው ብሎ መወሰኑ በራሱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ መንግሥት አዳዲስ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የለኝም ካለ፣ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱ ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚነቱ ከቀነሰ ደግሞ፣ የውጭ ምንዛሪው የባንክ ሥርዓት ውስጥ ስለሚገባ የተረጋጋ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ እንዲሁም ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት የውጭ ጉዞዎች እየቀነሰ በመምጣቱ ይህም የራሱ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው፣ ባንክና ጥቁር ገበያ ላይ የነበረው ጫና ይቀንሳል፡፡ ኤክስፖርትን ለማበረታታት ሲባል የተወሰዱ ዕርምጃዎች ነበሩ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ የቱሪስት ፍላጎት ይጨምራልና ከዚህ ዘርፍ ገቢ ስለሚኖር፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ከፍ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ከዚሁ  ጋር መረሳት የሌለበት ጉዳይ ደግሞ ሰዎች ራሳቸው የአገሪቱ መጪ ጊዜ መልካም ይሆናል፣ ብሩህ ነገር ይታየናል የሚል ሐሳብ ካላቸው ወደ ጥቁር ገበያ ሄዶ ዶላር እየተሻሙ አይገዙም፡፡ አይመነዝሩም፡፡ ይህም የጥቁር ገበያ ዋጋ እንዲወርድ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ እንዲረጋጋ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ በርከት ያሉ ምክንያቶች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በጠቀሱዋቸው ምክንያቶች የውጭ ምንዛሪ ገቢ ሊያድግ ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት የጥቁር ገበያ የምንዛሪ ዋጋ ሊቀንስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ አካሄድ ቀጣይ ይሆናል? የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትንስ ለማሟላት አሁን በተጀመረው እንቅስቃሴ ብቻ ሊሳካ ይችላል?

አቶ አወት፡- እንዲህ ያሉ ነገሮች ዘላቂ እንዲሆኑ ዋናው የውጭ ምንዛሪ ከዕርዳታና ከሌሎች ምንጮች ይልቅ ዋናው የኢኮኖሚ ዘርፍ ማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና እና አገልግሎት የሚያመነጩት ነው መረጋጋት የሚፈጥረው፡፡ ዘላቂነት ያለው እሱ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ እንዲቀጥል በብርቱ መሠራት ያለበት በነዚህ በጠቀስኳቸው ዘርፎች ላይ በአትኩሮት በመሥራት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርብ ለውጥ ይደረግባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የፋይናንስ ዘርፉን የሚመለከት ነው፡፡ ይህ ሪፎርም እስከምን ድረስ ሊደርስ ይችላል ብለው ያስባሉ? በዚህ ዘርፍ መሆን አለበት ብለው የሚያምኑትስ ምንድነው?

አቶ አወት፡- በፋይናንስ ዘርፉ ሪፎርም እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡ በተለይ ብሔራዊ ባንክ ራሱን በማዘመን በባንኮች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥርም ሆነ የባንኮችን አሠራር ማስተካከል አለበት፡፡ በባንኮች ውስጥ የተበላሹ አሠራሮች ካሉ እነሱንም የማስተካከል ሥራዎች የሪፎርሙ አካል መሆን አለበት፡፡ በተለይ በብድር አሰጣጥ፣ በውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምና ማስተናገድ ላይ፣ እንዲሁም ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ረገድ መሠራት አለበት፡፡ ለውጡም ከዚህ አንፃር መቃኘት አለበት፡፡ ለኅብረተሰቡ የሚቀርቡትን የፋይናንስ ፕሮጀክት የምንላቸውን ተደራሽነት ለማሻሻል በሰፊው የሚያግዙ የፖሊሲ አቅጣጫዎችና መመርያዎችን ያወጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ በሚቀጥለው ዓመት የነበሩ ጉድለቶችን በማየት ማስተካከያ የሚወሰድባቸው ይሆናል፡፡ አንዳንድ ከጊዜው ጋር የማይራመዱ መመርያዎችንም ይቀይራል፡፡ ስለዚህ በፋይናንስ ዘርፍም ሆነ በሌሎች የተወሰኑ የኢኮኖሚ ዘርፎ ችግሮች ቢኖሩም በጥሩ ሁኔታ መጥተዋል፡፡ አሁንም የኢኮኖሚያዊ ዕድገት ፍጥነቱ ጋብ እንዳይል ሊረዱ የሚችሉ ሥራዎች የተመረጡ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ የፖሊሲ ማሻሻያዎችና ሥራዎችን ለማቀላጠፍ  የሚያስችሉ አሠራሮች ላይ ያነጣጥራል ብዬ አስባለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ግዙፍ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ፕራይቬታይዝ ማድረግ የለውጡ አካል ነው፡፡ ነገር ግን ቀድመው መሠራት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ይታመናል፡፡ በተለይ ስቶክ ማርኬት ሳይኖር እነዚህን ድርጅቶች መሸጥ አይታሰብም እየተባለ ነው፡፡

አቶ አወት፡- እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ኩባንያዎች ወደ ግል ሲዞሩ ከፍተኛውን የአክሲዮን ድርሻ መንግሥት ይዞ ቀሪውን ለመሸጥ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ የእነዚህ ኩባንያዎችን አክሲዮን ለመግዛት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሌለው ሰው በአቅሙ እንዲገዛና ባለቤት የሚሆንበት አሠራር አለ፡፡ ለዚህም ሲባል የአክሲዮኖች ግዥና ሽያጭ የሚስተናገድበት ሰከንደሪ ማርኬት ወይም ካፒታል ማርኬት የምንለው አለ፡፡ ይህ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ  የለም፡፡ ስለዚህ ይህንን ማቋቋምና ወደ ሥራ ለማስገባት ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ አንደኛ መንግሥትም ብር የሚያስፈልገው ከሆነ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአቅማቸው አክሲዮኖችን በመግዛት፣ በትልልቅ ኩባንያዎች ላይ ባለቤት የሚሆኑበት ዘዴ ይፈጠራል፡፡ የካፒታል ማርኬት መፈጠር ገንዘብን የምታመነጭበት ነው፡፡ ለሌላውም ይጠቅማል፡፡ ስለዚህ የአየር መንገድና የቴሌ የአክሲዮን ሽያጫቸው ለትልልቅ ገዥዎችም ክፍት ቢሆን፣ በትክክለኛ ዋጋ መገበያየት እንዲቻል የካፒታል ማርኬት ጠቃሚ ነው፡፡ ለምሳሌ እስካሁን ድረስ በባንኮችም ሆነ በሌሎች ኩባንያዎች አክሲዮን ገዝተህ ለመሸጥ ብትፈልግ የሚያስተናግድህ የለም፡፡ ስለዚህ አክሲዮኖች እንደ ማንኛውም የንግድ ዕቃ የሚለዋወጡበት፣ ዛሬ ገዝተህ ነገ ካሽ ሲያስፈልግህ የራሱ ፈተና ቢኖረውም ጠቀሜታም ስላለው ወደዚህ መግባት መልካም ነው፡፡ አሁን ባለው የአገሪቱ የፋይናንስ ሕግ መሠረት ይህንን ማቋቋም ይቻላል፡፡ በእርግጥ የተወሰኑ ሕጎችን መለወጥ የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ ካፒታል ማርኬት ማቋቋም ትችላለህ፡፡ አሁን ደግሞ ምርት ገበያውም አለ፡፡ አሠራሩ በተወሰነ ደረጃ ልዩነት ቢኖረውም፣ ከዚያ ልምድ በመነሳት ካፒታል ማርኬት መፍጠር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በፋይናንሱም ሆነ በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተጨባጭ መሬት ላይ ለማዋል አስፈላጊ ናቸው ተብለው ከሚታመኑ ነገሮች አንዱ የሚደረገውን ለውጥ በጊዜ ገደብ ማስቀመጥ ነው፡፡ ይኼ ነገር በዚህ ጊዜ ውስጥ መደረግ አለበት፡፡ ይህ ለውጥ ደግሞ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ መተግበር አለበት የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ እስካሁን የጊዜ ገደብ የተቀመጠላቸውን አዳዲስ አሠራሮች ባናውቅም፣ በእርስዎ እምነት እነዚህ አዳዲስ አሠራሮች ከጊዜ ገደብ አንፃር እንዴት ይተገበራሉ?

አቶ አወት፡- ማንኛውም ዕቅድ የጊዜ ገደብ ከሌለው ዕቅድ ሳይሆን ህልም ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ዕቅድ በጊዜ የታቀፈ መሆን አለበት፡፡ አሁን የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ ሲባል ጊዜ አለው፡፡ በፋይናንስም መስክም  እንደሚወጣለት ነው፡፡ እስካሁን ያጋጠመን ችግር ይኼ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ይህንን እንሠራለን፣ በረዥም ጊዜ ደግሞ ይህንን እንፈጽማለን በማለት የጊዜ ገደብ ይበጅላቸዋል፡፡ አሁን የጊዜ ገደብ ያልወጣላቸው አንዳንድ ሥራዎች እየተጠኑ በጥናቱ ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ በመውሰድ የማስተካከያ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ መስተካከል ያለባቸው ፖሊሲዎች በጥናት ላይ ስለሆኑ እነዚህ ጥናቶች ሲያልቁ የጊዜ ገደብና የሥራ ዝርዝሮች ይወጣሉ፡፡ እነዚህን በ2011 ዓ.ም. እናያለን ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ የማስተካከያ ዕርምጃዎች ምን ያህል ውጤታማ ይሆናሉ ብለው ያስባሉ? እርስዎ መደረግ ይኖርባቸዋል ብለው የሚሞግቱት ነገር አለ?

አቶ አወት፡- የአገራችን ኢኮኖሚ ባለፉት አሥር ዓመታት በጥሩ ሁኔታ የመጣ ነው፡፡ አሁን ደግሞ የቀድሞው ፖሊሲ ያመጣቸውን ጥሩ ነገሮች በሚያስቀጥል ሁኔታ ያሉትን ችግሮች ደግሞ የሚፈታ ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የቀድሞው ፖሊሲ ያስገኘልህ ጥሩ ነገር ያለ ቢሆንም፣ ችግሮችም የነበሩበት ስለሆነ እስካሁን የመጣህበትን ፖሊሲ ከነችግሮቹ ይዘህ መጓዝ የለብህም፡፡ ድክመቶቹን ሊቀንስና ጥንካሬዎቹን ሊያስቀጥል የሚችል፣ ኢኮኖሚው ዕድገቱን እንዲቀጥልና እንደ አዲስ እንዲነቃቃ የሚያደርግ ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በተለይ የውድድር ሜዳውን ፍትሐዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡  ገበያው ውስጥ የመጫወቻ ሜዳው ፍትሐዊ እንዲሆን ማድረግ የግድ መሆን አለበት፡፡ መንግሥት የመጫወቻ ሜዳውን ምቹ የማድረግና ለዚህ የሚያግዝ ፖሊሲና መሣሪያዎች ጉድለት ነበረበት፡፡ ስለዚህ የውድድር ሜዳውን ምቹ የሚያደርግ አሠራር ሊዘረጋ ይገባል፡፡ ይህንን ማድረግ ከተቻለ ሰዎች የመጫወቻ ሜዳው ምቹ በመሆኑ ተበረታተው ይሠራሉ፡፡ ውድድሩ ፍትሐዊ ከሆነ ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው፡፡ ሰዎች ሠርቼ ሊያልፍልኝ ይችላል የሚል እምነት ኖሯቸው እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በገበያ ጨዋታ አሸናፊና ተሸናፊ ይኖራል፡፡ ግን ምቹ የውድድር ሜዳ ካለ የተሸነፍኩት በትክክለኛ ውድድር ነው የሚል እምነት እንዲፈጠር ሁነኛ መፍትሔው፣ የውድድር ሜዳውን ፍትሐዊ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ጥሩ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ኢትዮጵያ በአካባቢው ካሉ አገሮች ወደቦች ጋር በጋራ የማልማት ስትራቴጂ ውስጥ የሚያሳዩ የተለያዩ ስምምነቶች እየተደረገ ነው፡፡ ይህ አዲስ ነገር ሲሆን እንዲህ ዓይነት ሒደት ምን ያመለክታል?

አቶ አወት፡- ወደ ኢኮኖሚ ትስስር የሚመሩን ናቸው፡፡ አሁን እንደሚታየው አፍሪካውያን የእርስ በርስ የንግድ ልውውጣቸው እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ በአብዛኛው አፍሪካውያን የሚነግዱት ከአፍሪካ ውጭ ካሉ አገሮች ጋር ነው፡፡ ኬንያና ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳና ኬንያ የመሳሰሉት የአፍሪካ አገሮች ከአውሮፓ ጋር ነው የሚነግዱት፡፡ በቀጣናችን መደጋገፍ እንደሚያስፈልገን፣ ከተለያየን ደግሞ ሁላችንም እንደምንጎዳ ነው፡፡  ኢኮኖሚውን ካስተሳሰርን በማንኛውም ነገር የማንነጣጠል እንሆናለን፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ወደቦች አካባቢ እየተሠራ ያለው የባቡር መስመር ዝርጋታና የመንገድ ግንባታ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች በሙሉ ለእኛ ለኢትዮጵያውያንም ጥሩ ናቸው፡፡ እኛ ጥሩ ስንሆንና  ስናድግ ያኛውም ያድጋል በማለት ማሰብ አለብን፡፡ ቢሮክራሲያዊ የሆኑ እንደ ድንበር ያሉና ሌሎች ነገሮችን የሚያጠፋልህና ምንም ዓይነት ልዩነት እንደሌለ የሚያደርግልህ፣ ኢኮኖሚ ውስጥ ገብቶ ሲጠቀምና ሲተሳሰር ነው፡፡ አሁን በዓለም ላይ ትንሽ አገር ሆነህ ከምትደናበር አብረህ ሆነህ ብትወዳደር ትልቅ ተወዳዳሪና ተጠቃሚ ትሆናለህ፡፡ ምክንያቱም የአንድ አገር መጎሳቆል የሌላውም መጎሳቆል ይሆናል፡፡ አሁን ዓለም ላይ ብቻህን ሆነህ ከምትወዳደር አብረህ ትልቅ ሆነህ ብትወዳደር ትልቅ ተጠቃሚ ትሆናለህ፡፡ ትስስሩ የኢኮኖሚውን ዕድገት ያፋጥናል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በተለያዩ ወደቦች በጋራ ለማልማት እጇን ስታስገባ የምንፈልገው ቦታ እየተጠቀምን እንሄዳለን፡፡ ለምሳሌ በምሥራቅ በኩል የጂቡቲን ወይም የበርበራን ወደብ ትጠቀማለህ፡፡ በምዕራብ በኩል የሱዳን ወደብ፣ በሰሜን የኤርትራ ወደቦችን እየተጠቀምክ ዋጋ የሚቀንስልህን አሠራር እየተከታተልክ ትሠራለህ፡፡ የትራንስፖርት ወጪህን የሚቀንስልህን እየተጠቀምክ አማራጭህን ታሰፋለህ፡፡ ‹ሁሉንም እንቁላሎችህን አንድ ቅርጫት ውስጥ አታስቀምጥ› እንደሚባለው፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች ተመልክተህ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምህን ታኛለህ ማለት ነው፡፡ በዚህም በምሥራቅ አፍሪካ አንድ ትልቅ የኢኮኖሚ ኃይል ይፈጥራል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ለውጥ ይደረግባቸዋል ተብለው የሚጠበቁ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በጥቅል ሲታዩ መልካም ዕድሎቹና ሥጋቶቹ ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

አቶ አወት፡- እንዲህ ያሉ ለውጦች ሲደረጉ የምናወራው ስለኢኮኖሚ ነውና ኢኮኖሚ በትንሹም በቀዛቀዝ እንደ ትልቅ መልካም ዕድል ነው የሚታየው፡፡ ተቀዛቅዞም የተኖረ ነው፡፡ ስለዚህ ያሉትን ችግሮች ለማወቅ ዕድል ሰጥቶናል፡፡ ያሉትን ውስብስብ ችግሮች ለማወቅ ረድቶናል፡፡ ከዚህ አንፃር ያለነው ጥሩ ቦታ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢኮኖሚያዊ ዑደቱ ዝቅ ይላል፣ ከፍ ይላል፡፡ ይኼ ያለ ነው፡፡ ኢኮኖሚው ወይም አገር ሳይንኮታኮት የምናድንበት ዕድል ከሰጠ ለውጡ ትልቅ ስጦታ ነው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያችን አዝግሟል ባልንበት ጊዜ እንኳን ዕድገቱ ከማንኛውም ጊዜ በላይ ነው፡፡ አዘቅዝቆም ቢሆን ለይቶ ለማየት ዕድል ሰጥቶናል፡፡ ትልቁ ተግዳሮት የሚሆነው እነዚህን ችግሮች መፍታት አለመቻል ነው፡፡ ስለዚህ የግድ ይላል ማለት ነው፡፡ የመውደቅና የመነሳት ዕጣ ፈንታህን ይወስናል፡፡ ስለዚህ አሁን ችግሮችን ለማወቅ ግማሽ መንገድ መሄድና ለመፍታት ተባብረን መሥራት አለብን፡፡ ስለዚህ የእኛ ብቃት የሚፈተሽበት ወቅት ነው ማለት ነው፡፡