Skip to main content
x
‹‹በፍላጎቴ ሁለት መቶ ብር እከፍላለሁ የሚሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የቀይ መስቀል አባላት እንዲኖሩን ምኞታችን ነው››

‹‹በፍላጎቴ ሁለት መቶ ብር እከፍላለሁ የሚሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የቀይ መስቀል አባላት እንዲኖሩን ምኞታችን ነው››

አቶ አበራ ቶላ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዚዳንት

ከ150 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የዓለም ቀይ መስቀል ማኅበር በተቋቋመ በዓመቱ ነበር በ12 የአውሮፓ አገሮች ተቀባይነትን ያገኘው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ደግሞ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዋዜማ ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት የተጎዱ ወታደሮችን ለማከም ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ያለው ቀይ መስቀል በኢትዮጵያ በቋሚነት ተደራጅቶ  ሲያገለግል 83 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበራት ፌዴሬሽን የአመራር ቦርድ አባል ሆኖ ከተመረጠ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የኢትዮጵያን ሕዝብ እያገለገለ የሚገኘው ማኅበሩ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የተለያዩ ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን በማድረግ ይታወቃል፡፡ በጥቂት በጎ ፈቃደኞች በመታገዝ የሚሰራውን ሥራ ይበልጥ ለማጎልበት ወጣቱን ለመሳብ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ቀርፆም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የድጋፍ ሠልፍ በተደረገበት ዕለት በተከሰተው የቦንብ ፍንዳታ ለተጎጂዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ላደረጉ በጎ ፈቃደኞችና የማኅበሩ አባላትም ከቀናት በፊት ዕውቅና ሰጥቶ ነበር፡፡ የማኅበሩን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን ፕሬዚዳንቱን አቶ አበራ ቶላን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በመላ አገሪቱ ያለው ተደራሽነት ምን ያህል ነው?

አቶ አበራ፡- ቀይ መስቀል በመላ አገሪቱ ነው የሚሠራው፡፡ በሁሉም ክልሎች፣ በዞኖችና በወረዳዎች ቅርንጫፎቹ ከፍቶ ይሠራል፡፡ ለምሳሌ በአማራ ክልል በ11 ዞኖች፣ በኦሮሚያ በ14 ዞኖች፣ በትግራይ በአራት ዞኖችና ወረዳዎች የቀይ መስቀል ማኅበር የተለያዩ ሥራዎች ይሠራል፡፡ የአምቡላንስ አገልግሎትና የመጀመርያ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ድንገተኛ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ እንሰጣለን፡፡ ማንኛውም የድንገተኛ አደጋ በደረሰበት ቦታ ላይ ማኅበሩ ይደርሳል፡፡ ለምሳሌ የመሬት መንሸራተት በደቡብ ክልል በደረሰበት ጊዜ የመጀመርያው ደራሽ ቀይ መስቀል ነበር፡፡ የቆሼ አደጋ እንዳጋጠመም ቀይ መስቀል ቀድሞ በመድረስ ፍራሽና ምግብ ለተጎጂዎች አድሏል፡፡ በጌድኦ፣ በሐዋሳና በሞያሌ ለተፈጠረው ችግርና በባህር ዳር ለሚገኙ ተፈናቃዮች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ችግሮች በተፈጠሩበት ቦታዎች ሁሉ ደርሶ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በዚህ ዓመት ከሁለት ሚሊዮን ላላነሱ ዜጎች ደርሷል፡፡ ሲደርስ ደግሞ በሙሉ ዕርዳታ ነው፡፡ መጠለያና ምግብን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል አምቡላንሶች አሏችሁ?

አቶ አበራ፡- ማኅበሩ የሚሠራቸውን የበጎ አድራጎት ሥራዎች በአብዛኛው የሚሠራው በአምቡላንሶቹ ነው፡፡ የአምቡላንስ አገልግሎት የምንሰጠው በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች እንዲሁም በአገሪቱ በሚገኙ በእያንዳንዱ ወረዳዎች ነው፡፡ በአገሪቱ ከ300 በላይ ፖስቶች ያሉን ሲሆን፣ በእነዚህ ፖስቶች የሚሠሩ ከ450 በላይ አምቡላንሶች አሉን፡፡ ካለው ፍላጎት አንፃር ሲታይ ያሉት አምቡላንሶች የሚሰጡት አገልግሎት ኢምንት ነው፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ካስቀመጥናቸው ዕቅዶች መካከል የአምቡላንሶቻችን ቁጥር መጨመር ነው፡፡ በሚቀጥሉት ሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ አሁን ላይ ያለውን የአምቡላንስ ቁጥር ቢያንስ በ30 እና በ40 በመቶ ለማሳደግ እናስባለን፡፡ ይህም ተደራሽነታችንን እስከ 30 በመቶ ይጨምርልናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ በትግራይ ክልል ያለውን አጠቃላይ አምቡላንሶችን ማኅበሩ እንዲያስተዳድራቸው ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር እየተነጋገርንም እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በቀጣይ ለመሥራት ያቀዳቸው ስትራቴጂክ አቅጣጫዎች አስቀምጧል?

አቶ አበራ፡- ሰባት ስትራቴጂክ አቅጣጫዎች አስቀምጠናል፡፡ አዲስ የተዋቀረው ቦርድ ምን አዲስ ነገር ለማድረግ አስቧል? የሚለውን እንመልከት፡፡ የቀይ መስቀል ዋና ተግባር መታደግ፣ ለድንገተኛ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት፣ ጥራት ያላቸው አገልግሎቶችን ማቅረብ ነው፡፡ ሁሉም ነገር የሚጠቃለለው በእነዚህ ተግባራት ዙሪያ ነው፡፡ ይህንን አገልግሎት የምንሰጥበትን ጥራት ማሻሻል ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡ ያለውን የአገልግሎት ጥራት ለመጨመር ሠራተኞቹን፣ ሎጂስቲኩን ሁሉ ማሻሻል አለብን ማለት ነው፡፡ ይህንን ለማድረግም የገንዘብ ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ የቀይ መስቀል አብዛኛው በጀት ከውጭ ዕርዳታ የሚገኘው ገንዘብ ነው፡፡ በመርህ ደረጃ ግን ቀይ መስቀል ማኅበር የማኅበረሰብ ስለሆነ በሕዝቡ ነው መቆም ያለበት፡፡ በመንግሥት ቻርተር የተቋቋመ፣ በመንግሥት የተቋቋመ፣ የመንግሥት አካል ነው፡፡ ማኅበሩ ለዚህም መንግሥት በየዓመቱ እስከ 20 ሚሊዮን ብር አግኝተናል ከመንግሥት፡፡ ዘንድሮም ይህንኑ ያህል ገንዘብ እንጠይቃለን፡፡ አብዛኛው ገንዘብ የሚገኘው ግን ከውጭ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ከውጭ ዕርዳታ እስከ 700 ሚሊዮን ብር አግኝተናል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ እስከ 900 ሚሊዮን ብር እናገኛለን ብለን ዕቅድ ይዘናል፡፡ ግን በዚህ መልኩ መቀጠል የለብንም ማኅበሩ የራሱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማኅበር ነው፡፡ ሕዝቡ ራሱን መቻል አለበት፡፡ ማኅበሩ ከተቋቋመ 83 ዓመታትን ያስቆጠረ፣ ልምድ ያካተበ ትልቅ ተቋም ነው፡፡ ይህንን ስሙን ተጠቅመን ከመላ ሕዝቡ ገንዘብ ለማሰባሰብ እያሰብን ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የመሥራት አቅም ያለው 60 ሚሊዮን ሕዝብ ቢኖረን ከእያንዳንዱ አሥር ብር ብንሰበስብ በዓመት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ማግኘት እንችላለን፡፡ ሌላው ነገር የቀይ መስቀል መሠረት ማኅበረሰቡ ነው፡፡ ያሉንን የበጎ ፈቃደኞች ቁጥር ማብዛት ይኖርብናል፡፡ አሁን ያሉን በጎ ፈቃደኞች በአገር አቀፍ ደረጃ 3,000 ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ወደ ሦስት ሚሊዮን ከፍ ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ ይህም ትንሽ የሚባል ነው፡፡ የቀይ መስቀልን ንቅናቄ የወጣቱ ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ ወጣቱ ባለው ሙሉ ኃይል እንዲሳተፍ እንዲመራው እንፈልጋለን፡፡ በአገራችን እምብዛም የሆነውን የበጎ ፈቃደኝነት ባህል እንዲጎለብት እንፈልጋለን፡፡ በውጭ አገሮች ወጣቶች ሥራ ለመቀጠር ወይም ከአንድ ትምህርት ደረጃ ወደ ሌላው ለመዘዋወር ምን ዓይነት የበጎ ፈቃድ ሥራ ሠርተሃል? ተብለው ይጠየቃሉ፡፡ ይህንን ዓይነት አሠራር ወደ ኢትዮጵያ ብናመጣ የበጎ ፈቃደኝነት ባህሉን ማዳበር ያስችለናል፡፡ ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት ከማኅበሩ ጋር ሲሠሩ ቤተሰብ ይሆናሉ፡፡ ስለበጎ ፈቃድና ስለሰብዓዊነት ያወራሉ፡፡ ስለሰው ልጅ ደኅንነት፣ መልካምነት፣ አዕምሮና ዕውቀት እንዲያወሩ ሲሆን፣ የታነፀ ትውልድ ይኖረናል ማለት ነው፡፡ የበጎ ፈቃደኝነት ርዕዮተ ዓለም በወጣቱ ልብ ውስጥ መጨመር የሰዎችን እኩልነት፣ መልካም ተግባርን የሚሰብክ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው፡፡ ከበጎ ፈቃደኞች ጎን ለጎን የቀይ መስቀል አባላትንም ማብዛት ያስፈልጋል፡፡ የ20,000 ብር ደመወዝተኛ የሆነ አባል በወር ሁለት መቶ ብር ቢሰጥ በጣም ብዙ ሕይወትን ያድናል፡፡ እኔ እኮ ከመንግሥት ግብር በተጨማሪ በፍላጎቴ ሁለት መቶ ብር እከፍላለሁ የሚሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የቀይ መስቀል አባላት እንዲኖሩን ምኞታችን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የጌድኦና ጉጂ ተፈናቃዮች ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ተፈናቃዮች ከመጠለያ ጀምሮ የተለያዩ መሠረታዊ ፍላጎታቸው ባለመሟላቱ ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገዋል፡፡ ቀይ መስቀል ማኅበር ለተፈናቃዮች ምን እያደረገ ይገኛል?

አቶ አበራ፡- በጌድኦ ዞን ለሚገኙ ተፈናቃዮች መጠለያ እያዘጋጀን ነው፡፡ መጠለያ ላገኙ ደግሞ ምግብ እያቀረብን እንገኛለን፡፡ ይህንን ሥራ በመደበኛነት የሚሠራው የክልሉ ቀይ መስቀል ነው፡፡ እኛ ደግሞ ከዚህ ከማዕከሉ የሚጎሉ ነገሮችን እያቀረብን ነው፡፡ እነዚህን የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ለመሥራት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩን አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ ከትራፊክ ጀምሮ የተለያዩ ዓይነት አደጋዎች በየቀኑና በየሰዓቱ ይከሰታሉ፡፡ ቀይ መስቀል አብዛኛውን ጊዜውን የሚያጠፋው ለየትኞቹ አደጋዎች ምላሽ ሲሰጥ ነው?

አቶ አበራ፡- አሁን ያለው ትልቁ የቀይ መስቀል ወጪ ለተፈናቃዮች የሚወጣው ነው፡፡ በፊት በተፈጥሮ መዛባት የሚከሰት እንደ ድርቅ ያሉ ችግሮች የሚያስከትሉትን አደጋ ለመቀነስ ነበር ብዙ የምንሠራው፡፡ ከወራት በፊት በዕርዳታ ማስተባበሪያ በተደረገ ጥሪ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች አስፈላጊውን ዕርዳታ እያደረግንም ነው፡፡ አሁን ግን በጣም ገኖ የወጣውና የኛንም አብዛኛውን ኃይል እየወሰደ ያለው በግጭቶች የሚከሰቱ መፈናቀሎች ናቸው፡፡ በሞያሌ በተከሰተው ግጭት ለተጎዱ ዜጎች በመጠለያ ለሚገኙም ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡ በጌድኦና በባህር ዳር ለሚገኙ የግጭት ውጤት ለሆኑ ተፈናቃዮች የምናደርገው ድጋፍ ያመዝናል፡፡ በፊት ግን ያለንን አብዛኛውን አቅም የሚወስድብን በተፈጥሮ አደጋ በጎርፍ፣ በድርቅና በመሬት መንሸራተት የሚከሰቱ አደጋዎች ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ምን ያህል መድኃኒት ቤቶች አሉት? የሚያቀርባቸው መድኃኒቶች ለማኅበረሰቡ ምን ያህል ተደራሽ ናቸው?

አቶ አበራ፡- ከመድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር አንዳንድ አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒቶች በኛ በኩል እንዲቀርቡ ለማድረግ በቅርቡ ስምምነት አድርገናል፡፡ የሚታየውን የመድኃኒት እጥረቶች ለማስወገድና ወሳኝ የሆኑ መድኃኒቶች በቀይ መስቀል ፋርማሲዎች በኩል ለሕዝቡ ለማድረስ እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመርያ ዕርዳታ በመስጠት የሰዎችን ሕይወት መታደግ በኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ነው፡፡ የመጀመርያ ዕርዳታ ወሳኝ መሆኑን ተረድቶ ሥራዬ ብሎ የሚማሩም አይታዩም፡፡ ይህ በምን ያህል ደረጃ ችግር ሆኗል? ማኅበሩስ ምን እያደረገ ነው?

አቶ አበራ፡- ቀይ መስቀል የመጀመርያ ዕርዳታ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ አብዛኛዎቹ ሠልጣኞቻችንም በጎ ፈቃደኞች ናቸው፡፡ የወደቀን ሰው እንዴት ነው የሚነሳው፣ አምቡላንስ ውስጥ ከገባ በኋላ የሚደረግለት የመጀመርያ ዕርዳታና ምን ይመስላ የሚሉና የመሳሰሉትን ተግባት ያሠለጥናል፡፡ ለምሳሌ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ የቀይ መስቀል አባላት ለተጎጂዎች ተገቢውን ዕርዳታ አድርገዋል፡፡ ሠልፉ እንደሚካሄድ ሲረጋገጥ ቀይ መስቀል ሳይጀመር ማኅበሩ ሦስት ቦታዎች ላይ አምቡላንሶችን አቁሞ ነበር፡፡ በየአምቡላንሶቹ ከነርስ ጀምሮ የተለያዩ ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ቦንቡ የፈነዳው አምቡላንሶቻችን ባሉበት አቅራቢያ ስለነበር በጎ ፈቃደኞች ተጎጂዎችን ሮጠው በማንሳት የመጀመርያ ዕርዳታ እንዲያገኙ አስችለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በበጀት እጥረት ምክንያት የታጠፉ ፕሮግራሞች ካሉ ቢገልጹልን?

አቶ አበራ፡- በበጀት እጥረት ምክንያት የሚታጠሩ ፕሮራሞች የሉንም ማለት እችላለሁ፡፡ እንዲያውም አዳዲስ ፕሮጀክቶችን መጀመር ነው የምንፈልገው፡፡ ለምሳሌ የትራፊክ አደጋን የመንገድ ደኅንነት ትምህርት በመስጠት ለመከላከል ሮድ ሴፍቲ የሚል ፕሮግራም ተጀምሯል፡፡ ይህንን ፕሮግራም ያስጀመረው ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር ሲሆን፣ እኛም ይህንን በመጋራት ሮድ ሴፍቲ በኢትዮጵያ እንዲጀመር አድርገናል፡፡ ፕሮግራሞቻችን አይታጠፉም፡፡ እንዲያውም አዳዲስ ፕሮግራሞችን ለማስቀጠል የገቢ ምንጭ ማሰባሰብ ላይ ነው የምናተኩረው፡፡ ለምሳሌ ፍል ውኃ አካባቢ መንግሥት በሰጠን 2,000 ካሬ ቦታ ላይ ባለ 30 ፎቅ ሕንፃ ግንባታ ጀምረናል፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራውን የሚያሳርፍበት፣ 1,000 ብርም ይሁን አንድ ብር አዋጥቻለሁ ብሎ የሚኮራበት ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት መሠረቱ የወጣ ሲሆን፣ በዚህ አራት ዓመታት ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ሥራ እንደሚጀምር እናምናለን፡፡ የቆመው የከተማዋ እምብርት ቦታ ላይ ስለሆነ ለኛ ጥሩ ነው፡፡ ዲዛይኑ ቢሮዎች፣ ማረፊያ ቤቶችንና ሱቆችን ያካተተ ነው፡፡ አጠቃላይ ወጪው አንድ ቢሊዮን ብር ይጠጋል፡፡