Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር ቢሯቸው እያወሩ ነው

ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር ቢሯቸው እያወሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ ለሌላ ሚኒስትር ጓደኛቸው ስልክ ይደውላሉ]

 • እኔ የምልህ አንድ በጣም እየከነከኝ ያለ ጉዳይ አለ፡፡
 • ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • በዚህ ፕሮጀክት ሊሰበሰብ የሚችለው ገንዘብ ቀላል አይደለም፡፡
 • የትኛው ፕሮጀክት?
 • የትረስት ፈንዱ ነዋ፡፡
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ስማ በቀን አንድ ዶላር ማለት ለዳያስፖራው ምንም አይደለም፡፡
 • እሱማ ቀላል ነው፡፡
 • እንዲያውም አንዳንዶቹ አሥርም ማድረግ እንችላለን እያሉ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ለአገር እኮ ምንም ሊደረግ ይችላል፡፡
 • አሁን በአሜሪካ ብቻ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ ይኖራል?
 • ልክ ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይህ ማለት በየቀኑ አንድ ሚሊዮን ዶላር ከዚያ ይሰበሰባል ማለት ነው፡፡
 • በትክክል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በዓመት ደግሞ 365 ሚሊዮን ዶላር ማለት ነው፡፡
 • አልተሳሳቱም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በአገር ውስጥ ገንዘብ ሲሰላ ደግሞ ወደ አሥር ቢሊዮን ብር ገደማ ነው፡፡
 • እሱን እንኳን አላሰላሁትም ነበር፡፡
 • በአሥር ዓመት ደግሞ መቶ ቢሊዮን ብር ማለት ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼን ያህል ሒሳቡ ምነው አስጨነቀዎት?
 • ምን ነካህ በአሥር ዓመት እኮ ሌላ ህዳሴ ግድብ መሥራት እንችላለን ማለት ነው?
 • እ. . .
 • ሌላው ቢቀር የማዳበሪያ ፋብሪካው ብትል የቆሙ የስኳር ፋብሪካዎችን ማንቀሳቀስ ይቻላል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ስለእነሱ ፕሮጀክቶች ግን ሲያወሩ አያፍሩም?
 • ምን ያሳፍረኛል?
 • በእርስዎ ምክንያት መሰለኝ ተሰነካክለው የቀሩት?
 • ይኼኛውም ፕሮጀክት እንዳይሰናከል ሐሳብ ስላለኝ እኮ ነው፡፡
 • ምን ዓይነት ሐሳብ?
 • ይኼንን ፈንድ የሚያንቀሳቅሱት ሰዎች በጥንቃቄ ሊመረጡ ይገባል፡፡
 • በዳያስፖራው በኩል ፈንዱን የሚያንቀሳቅሱት ሰዎች እኮ የሚታመኑና ኃላፊነት የሚሰማቸው ተብለው ነው የተመረጡት፡፡
 • ገንዘቡ ወደዚህ ሲላክ እንዳይባክን እዚህም የሚታመኑና ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች ሊመረጡ  ይገባል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ገንዘቡ እኮ የሚላከው በባንክ ነው፡፡
 • ቢሆንም ፈንዱ እዚህ ሥራ ላይ ሲውል እንዳይባክን ተመሳሳይ ኮሚቴ ያስፈልጋል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ምን እያሰቡ እንደሆነ አልገባኝም?
 • ስማ እዚህ የሚመሠረተው ኮሚቴ ውስጥ አንተና እኔ መግባት አለብን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በእጃችን ላይ የያዝናቸውን ሥራዎች እንኳን መቼ በሚገባ ተገበርናቸው?
 • ማወቅ ያለብህ ነገር ለእያንዳንዱ ልፋታችን እኮ ተገቢውን ጥቅም እናገኛለን፡፡
 • ምን ዓይነት ጥቅም ነው?
 • ኮሚሽን እንወስዳለና፡፡
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ትንሽ ይፈሩ?
 • ለምንድነው የማፍረው? መጽሐፉም እኮ ጥረህ ግረህ ብላ ነው የሚለው፡፡
 • ክቡር ሚኒትር የስኳሩና የማዳበሪያው አልበቃ ቢልዎት ትረስት ፈንዱንም መብላት ያምርዎታል?
 • እዚህ ላይ እንዳትሳሳት፣ እኔ ብቻዬን ተጠያቂ ልሆን አልችልም፡፡
 • ምን?
 • ከበፊቱም ቀስ እያልን እንብላ የሚል ሐሳብ ባቀርብም፣ የሚሰማኝ አጥቼ ነው በአንዴ አገሪቱ መቀመቅ ውስጥ የገባችው፡፡ እንደዚያ ያደረጉት ሌሎች ናቸው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ አሁን እንደዚህ ዓይነት ነገር ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡
 • አሁን ያመጣሁት ሐሳብ በጣም አስታራቂ ነው፡፡
 • የምን አስታራቂ ሐሳብ ነው?
 • ለአገልግሎታችን የምንጠይቀው ክፍያ በጣም አነስተኛና ተመጣጣኝ ነው፡፡
 • ምን ያህል ነው?
 • ከአንድ ዶላር አንድ ሳንቲም!

[በአሜሪካ የሚገኝ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለላቸው]

 • ክቡር ሚኒስትር እንዴት ነዎት?
 • አንተ በሕይወት አለህ?
 • አሁንማ እንደ አዲስ የተፈጠርኩ ያህል ነው እየተሰማኝ ያለው፡፡
 • ምን ተገኝቶ?
 • መቼም እንደሚያውቁት እኔና እርስዎ ያኔ ነው ዩኒቨርሲቲ የምንተዋወቀው፡፡
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • እንግዲህ ይኸው ከአርባ ዓመታት በላይ ትግል ውስጥ ነበርኩ፡፡
 • የምን ትግል ነው? የኑሮ ትግል ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ሕዝቤን ነፃ ለማውጣት ስንትና ስንት መስዋዕትነት ስከፍል ነበር፡፡
 • ከአርሊንግተን እስከ መሀል ዲሲ ድረስ ታክሲ መንዳት ነው ትግል?
 • እ. . .
 • ማታ ማታ ደግሞ የሐበሻ ምግብ በልቶ የማር አረቄ መጠጣት ነው እንደ ትግል የተቆጠረው?
 • ክቡር ሚኒስትር ስለእኔ የትግል ሕይወት ምንም የሚያውቁት ነገር የለም፡፡
 • ለመሆኑ በርገርና ፒዛ እየበላህ ታገልኩ ስትል ትንሽ አታፍርም?
 • ክቡር ሚኒስትር ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ለመጣው ለውጥ ዋነኛ መንስዔ እኔ ነኝ፡፡
 • ኪኪኪ. . . ወደው አይስቁ አሉ?
 • ክቡር ሚኒስትር ከአርባ ዓመታት በላይ ነው እኮ የታገልኩት፡፡
 • ለመሆኑ በፓርቲህ ውስጥ ኃላፊነትህ ምንድነው?
 • የዲሲን፣ የሜሪላንድንና የቨርጂኒያን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የምመራው እኔ ነኝ፡፡
 • ፓርቲያችሁ ስንት አባላት አሉት?
 • ዲሲ ላይ ሁለት አሉ፣ ሜሪላንድ ላይ በዕጩነት የያዝናት አንድ እሳት ልጅ አለች፣ ቨርጂኒያ ደግሞ እኛን ለመቀላቀል በቋፍ ላይ ያሉ ሁለት አሉ፡፡
 • አምስት ሰው ይዘህ ነው ፓርቲ የምትመራው?
 • ክቡር ሚኒስትር እንዳይታለሉ፣ ዌስት ኮስት ላይም ሌሎች አሉ፡፡
 • ዌስት ኮስት ላይ ስንት አባል አላችሁ?
 • እዚያ ደግሞ ሁለት ወሳኝ ሰዎች አሉን፡፡
 • እና ሰባት ሰው ይዛችሁ ነው አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ ያመጣችሁት?
 • ክቡር ሚኒስትር ክርስትናን እኮ በዓለም ላይ ያስፋፉት 12 ሰዎች መሆናቸውን አይዘንጉ፡፡
 • እ. . .
 • ስለዚህ እኛም ሰባት ሆነን በድፍን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሐሳባችንን ማንሰራፋት እንችላለን፡፡
 • እንደዚህ እያሳቅከኝ ግን ሆዴን እንዳታሳምመኝ?
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን እኛም ጠንከር ማለት አለብን ብለን ከሌሎች ሁለት ፓርቲዎች ጋር ልንጣመር ነው፡፡
 • ከእነማን ጋር?
 • ከእኛ የፖለቲካ አመለካከት ጋር አንድ ዓይነት አመለካከት ያላቸውን ሁለት ፓርቲዎች መርጠናል፡፡
 • ለመሆኑ እነሱ ስንት አባል አላቸው?
 • አንደኛው እንደነገረኝ ሦስት የአጎቶቹ ልጆችና ሁለት የአክስቶቹ ልጆች የፓርቲው አባል ናቸው፡፡
 • ምን አልከኝ?
 • የሚገርመው ክቡር ሚኒስትር እነዚህ የአጎቶቹና የአክስቶቹ ልጆች ከማኅበራዊ ድረ ገጽ ጋር ከፍተኛ የሆነ ቁርኝት አላቸው፡፡
 • ለመሆኑ በፌስቡክ ምን ያህል ተከታይ አላቸው?
 • በቅርቡ አንድ ሺሕ ተከታዮች እንደሚኖራቸው ነግሮኝ፣ ለዚያም ትልቅ ድግስ ደግሰው ቀኑን እንደሚዘክሩት አጫውቶኛል፡፡
 • ፓርቲው ከተመሠረተ ስንት ዓመቱ ነው?
 • 27 ዓመቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሌላኛውስ?
 • እሱኛው ፓርቲ ደግሞ ከመሪው ስምንት ቤተሰቦች ውስጥ አምስቱ በፕሮግራሙ አምነው አባል ሲሆኑ፣ ሦስቱ በቅርቡ አባል ይሆናሉ ተብለው ይጠበቃሉ፡፡
 • በጣም ነው ያሳቅኸኝ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አይሳቁ፣ በቅርቡ ትልቅ ግንባር ነው የምንፈጥረው፡፡
 • ለእናንተ ያለኝ ምክር ከግንባር ይልቅ በሌላ ነገር ብትደራጁ የሚል ነው፡፡
 • በምን ክቡር ሚኒስትር?
 • በጥቃቅንና አነስተኛ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ምሳ እየበሉ እያወሩ ነው]

 • ከቢሮ እየተመለስኩ አንድ በጣም አሪፍ ሐሳብ ነው የበራልኝ፡፡
 • የምን ሐሳብ?
 • ለመሆኑ በዳያስፖራውና በአገር ውስጥ መካከል ያለውን ትስስር እየተከታተልሽ ነው?
 • ምን ሚዲያው በጠቅላላ ስለእሱ ነው የሚያላዝነው ሰለቸኝ እኮ?
 • ይኼማ ሊሰለችሽ አይገባም፡፡ ለእኔና ለአንቺ መረጃ ማለት እኮ ገንዘብ ማለት ነው፡፡
 • አልገባኝም?
 • ያኔ ለሕዝቡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ይገንባ ሲባል፣ እኛም በተጓዳኝ ለቤቶቹ ፊኒሺንግ የሚሆኑ ዕቃዎችን ማስመጣት በመጀመራችን ምን ያህል እንደከበርን ታውቂያለሽ?
 • እሱማ ሚሊየነር ያደረገን ቢዝነስ ነው፡፡
 • አሁንም ተለቅና ረቀቅ ያለ ነገር መጥቷል፡፡
 • ምን ዓይነት ነገር?
 • ሰሞኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግሮች ሰምተሻቸዋል?
 • ያው ሁሌም እንደሚሉት መደመር፣ ፍቅር፣ ይቅርታና አንድነት አይደል እንዴ?
 • ስሚ በእነዚህ ቃላት እኮ እኛም ተጠቃሚ መሆናችንን አትርሺ?
 • እንዴት ሆኖ?
 • ይኸው የይቅርታ ዘመን ስለሆነ አይደል እንዴ ያን ሁሉ ዘርፈን ዝም የተባልነው፡፡
 • እንዳይመስልህ፡፡
 • ማለት?
 • እስሩ ከተጀመረ አይደለም የአገር ውስጥ የጎረቤት አገርም እስር ቤት አይበቃም ብለው ነው ዝም ያሉት፡፡
 • አንቺ ደግሞ እስኪ ደግ ደጉን አስቢ፡፡
 • እንግዲህ ጊዜው ሲደርስ ታየዋለህ፡፡
 • ለማንኛውም ይኼኛው አጋጣሚ እንዲያልፈኝ አልፈልግም፡፡
 • የምን አጋጣሚ ነው?
 • ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንቡ ፈርሶ ድልድይ ይሠራ እያሉ ነው፡፡
 • ምን ማለት ነው እሱ?
 • ያኔ የአሜሪካኑን ፕሬዚዳንት ግንብ እገነባለሁ ብለው ይኸው ሥልጣን ላይ ሲወጡ ግንቡን ለማስገንባት ደፋ ቀና እያሉ ነው፡፡
 • ምን እያልክ ነው ታዲያ?
 • የአሁን ጊዜ መሪዎች ፊት ለፊት ነው የሚናገሩት፡፡
 • አልገባኝም?
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በቃ ሰሞኑን ድልድዮች መሠራት ይጀምራሉ፡፡
 • የምን ድልድይ?
 • ክልልን ከክልል፣ ክፍለ ከተማን ከክፍለ ከተማ፣ ዞንን ከዞን፣ ወረዳን ከወረዳ የሚያገናኙ ድልድዮች ይሠራሉ፡፡
 • ሰውዬ ለየልህ አይደል?
 • ነገርኩሽ የእሳቸው ንግግር ቀጥተኛ ነው፡፡
 • ለማንኛውም ጤንነትህን ብትመረመር ጥሩ ነው፡፡
 • አንቺ ደግሞ ቶሎ ብለሽ ፈቃድ ብታወጪ ደስ ይለኛል፡፡
 • የምን?
 • የኮንስትራክሽን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር ቢሯቸው እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር ጋዜጠኞቹ ተጠርተዋል፡፡
 • የምን ጋዜጠኞች?
 • ባለፈው የምንሠራቸውን ሥራዎች ማሳወቅ ስላለብን ፕሬስ ኮንፈረንስ ይጠራ ብለውኝ ነበር፡፡
 • ታዲያ ሳታማክረኝ ነው የምትጠራቸው?
 • እኔማ አሁን ትክክለኛው ጊዜ ነው ብዬ አስቤ ነበር፡፡
 • እንዴት?
 • ያው ከተሾሙ መቶ ቀናት ስለሞላዎት በዚህ ጊዜ ያከናወኗቸውን ነገሮችን ነዋ ጋዜጠኞቹ የሚጠይቁዎት፡፡
 • በእነዚህ በመቶ ቀናትማ ፍቅር፣ መደመርና ይቅርታ ላይ ነዋ የሠራነው፡፡
 • እሱ ላይ ታዲያ እርስዎ ምን ሠርተዋል?
 • እንደምታውቀው የሻይ ቤታችን ሠራተኛና ጥበቃችን ለረዥም ዓመት ተኮራርፈው፣ እኔ ነኝ መካከላቸው ገብቼ ያስታረቅኳቸው፡፡
 • እ. . .
 • ከዚያም ባለፈ በግምጃ ቤቱ ኃላፊና በሾፌሩ መካከል የተከሰተው አለመግባባት ወደ ቡድን ግጭት ተሻግሮ በርካታ የመሥሪያ ቤታችንን ሠራተኞች ተሳትፈው እኔ ነኝ በሰላም እንዲቋጭ ያደረግኩት፡፡
 • ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለዚህም ተግባሬ ሠራተኞቼ የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት ይገባሃል ሲሉኝ፣ ከእሱ ይልቅ ይቅርታ እንዲያደርጉልኝ መጠየቄን መቼም ሰምተሃል?
 • የምን ይቅርታ?
 • በፊት የሰረቅኩትን ገንዘብ እዳልሰረቅኩ ተቆጥሮ ይቅርታ እንድባል ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር መሥሪያ ቤታችን እኮ ሊያስፈጽማቸው የሚገባቸው ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡
 • እሱንም አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አቅጣጫ ድልድዮች እንዲገነቡ ልናደርግ ነው፡፡
 • የምን ድልድይ ነው?
 • ሻይ ቤትን ከጥበቃዎች የሚያገናኝ፣ እንዲሁም ግምጃ ቤቶችን ከሾፌሮችና እንደ ሁኔታው ወደፊት ሌሎች ድልድዮችንም እንጨምራለን፡፡
 • በዚህ ዓይነትማ በመቶ ቀናት ያከናወኗቸው ተግባራት ከመቶ ሲፈተኑ ውጤቱ ይታወቃል፡፡
 • ስንት ነው?
 • ዜሮ!