Skip to main content
x
ከአሥር ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ወገኖችን ያጠቃው ቫይራል ሄፒታይተስ

ከአሥር ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ወገኖችን ያጠቃው ቫይራል ሄፒታይተስ

ወላጅ እናታቸውን ከ11 ዓመታት በፊት ነበር በሄፒታይተስ በሽታ የተነጠቁት፡፡ እምብዛም የማይታወቀው በሽታው የዚያኔ ነበር በሰው ላይ የሚያሳድረውን ክፉኛ ስቃይ በአዕምሯቸው ያስቀረው፡፡ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ እንደሚተላለፍ እንዳወቁም ተመርምረው ነፃ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጊዜ አልፈጁም ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ የሁለቱም እህትና ወንድም የደም ናሙናቸው ነፃ መሆናቸውን ነበር የሚያሳየው፡፡

 በዚህ ደስተኛ ቢሆኑም እናታቸውን ከሞት ማትረፍ ባለመቻላቸው ሐዘናቸው ከባድ እንደነበር መቅደስ ገብረ ወልድ ትናገራለች፡፡ ሞት ለሁሉም የማይቀር የተፈጥሮ ሕግ መሆኑን ማስተዋል ሲጀምሩ ትንሽም ቢሆን ተፅናንተው ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ እንደ ገና ጭንቅ እንደ ገና ሐሳብ ሆነ፡፡ ተመርምሮ ነፃ የነበረው የመቅደስ ወንድም በሆነው ባልሆነው በሽታ ይጥለው ጀመር፡፡

ደሙ ተመርምሮም ያልጠበቁትን ውጤት ተነገራቸው፡፡ ደሙ የሄፒታይተስ ‹‹ሲ›› ቫይረስ ያሳያል፡፡ በምን አጋጣሚ እንደተፈጠረ እስካሁን እንቆቅልሽ ሆኖ የቀረ ነገር ቢሆንም፣ ፈጥነው ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኝ የቻሉትን ሁሉ ማድረግ ጀመሩ፡፡ በሕክምና መዳን እንደሚችል ማወቃቸው ተስፋ ስለሆናቸው ሕክምናውን በወቅቱ መከታተል ሥራዬ ብለውም ነበር፡፡ ሕመሙ ሳይቆይበት በጊዜ ወደ ሕክምና መሄዱ ጥሩ እንደሆነና ፈውስ የሚሆን መድኃኒት እንደሚያስመጣለት ሐኪሙ የሰጠው ቃልም ተስፋ ሆኖላቸው ነበር፡፡ ከውጭ እንደሚያስመጣለት ቃል የገባላቸው መድኃኒት ግን ሳይደርስ ወራት ተቆጠሩ፡፡

 ‹‹መድኃኒቱን ሳያገኝ በመቆየቱ በውስጡ ያለው የቫይረሱ ክምችት በጣም እየበዛ መጣ፡፡ ከዚያም ታክሞ መዳን የማይችልበት ደረጃ ላይ ደረሰ፤›› የምትለው መቅደስ፣ ለተሻለ ሕክምና ወደ ታይላንድ መሄድ ብቸኛ አማራጫቸው እንደነበር ትናገራለች፡፡ ታክሞ እንደማይድን ቢያውቁም ከመሞቱ በፊት ያሉትን በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ከስቃይ ነፃ ማድረግ ነበር ዓላማቸው፡፡ ‹‹የመጨረሻዎቹ ቀናት በተለይም ሦስቱ ወራት ሕመምተኞቹ ክፉኛ ይሰቃያሉ፡፡ ጉበታቸውን በአፋቸው እየተፉ ነው የሚሞቱት፡፡ በእነዚያ ቀናት ያለውን ሕመም ባለሙያዎች ከምጥ ጋር ነው የሚያወዳድሩት፡፡ አስቢው ያለዕረፍት ሦስት ወራት ማማጥ፤›› አለች መቅደስ ስቃዩን በዓይነ ህሊናዋ ለመሳል እየሞከረች፡፡

ሞት ለማንም የማይቀር ቢሆንም የሚሞትበትን ቀን ማወቅ የሚፈልግ ግን ይኖራል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ የማቱሳላን ዕድሜ የማይመኝ የለምና ዕድሜህ በወራት የተወሰነ ነው ቢባል ቀድሞ ጭንቀቱ የሚገድለው ብዙ ነው፡፡ የመቅደስ ወንድም ግን ጭንቀቱ ድርብ ነበር፡፡ ደቂቃዎች ባለፉ ቁጥር አንድ ዕርምጃ ወደ ሞት እየተጠጋና በወራት የተወሰነ ዕድሜውን እያጋመሰ እንደሆነ ሲሰማው የሚያድርበት ጭንቀትና ውጥረት፣ ይብስ ብሎ ደግሞ አሟሟቱ ለጠላትም በማይመኙት እንደ ምጥ የከበደ ስቃይ ለቀናት ማስተናገድ ነበርና ፈተናዎች ድርብ ነበሩ፡፡

‹‹በሕክምና እንደማይድን ዶክተሩ ሲነግረኝ እንደዛ ተሰቃይቶ እንዲሞት አልፈልግም፡፡ ሌላው ቢቀር ስቃዩን ሳናይ በሰላም እንዲሞት ይሁን አልኩት፤›› ስትል ሰቀቀኑ የበዛባትን ወቅት አስታወሰች፡፡ የወንድሟን ነገር ስታወራ እንባ ይተናነቃታል፣ ነገር ግን ሳትሸነፍ ዋጥ አድርጋ ታስቀረዋለች፡፡

 የሞት ቀጠሮ የቆረጠለትን ይህን ክፉ በሽታ ታክሞ መገላገል ባይችልም ያለውን ጥሪት አሟጦ ግን ስቃዩን ለመቀነስ ከእህቱ መቅደስ ጋር አብረው ወስነው ታይላንድ ሲደርሱ፣ ሌሎች በተመሳሳይ በሽታ ይሰቃዩ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አግኝተዋል፡፡ ዛሬ ነገ መድኃኒት ይሰጥሀል እየተባለ በተስፋ ሲጠባበቅ ጉበቱን ማዳን ከማይቻልበት ደረጃ የደረሰ አንድ ግለሰብም አግኝተው እንደነበር መቅደስ ትናገራለች፡፡

ሰውየው ምናልባት በታይላንድ የሚኖረው ዘመናዊ ሕክምና ሊታደገኝ ቢችል በሚል እምነት ያለውን ገንዘብ ሸክፎ ታይላንድ ቢኖርም፣ ተስፋውን የሚያለመልም ነገር ሳያገኝ ወደ አገሩ በተመለሰ በቀናት ጊዜ ውስጥ ሕይወቱ ማለፉን መቅደስ ስትናር በሐዘን ነው፡፡ ምናልባትም ታይላንድ መሄዱ እንደ እሱ ሄፒታይተስ የሞት ቀጠሮ ከቆረጠላቸው ሌሎች ጋር ተገናኝቶ ስቃዩን እንዲጋሩት ከማድረግ ባለፈ የፈጠረለት አንዳችም ነገር አልነበረም ይሆናል፡፡ ነገር ግን ውዱን የሰውን ልጅ ሕይወት ለማትረፍ እስከ መጨረሻው ጠብታ ድረስ እንደሚታገሉ የሚያሳይ፣ ጤና ከምንም በላይ መሆኑን፣ ጤናማ አዕምሮ ያለው ሰው ሞትን እንደማይፈልግ የሰውን ልጅ ባህሪ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

እናታቸውን ቀድሞ የነሳቸውን ባለጋራ የሆናቸውን ሄፒታይተስ ታግለው እንደማያሸንፉት ስለሚያውቁ ስቃዩን ለመቀነስ ሲሉ በታይላንድ ሕክምና ከ700 ሺሕ ብር በላይ አውጥተዋል፡፡ የጉበት ንቅለ ተከላ ሕክምና እንዳለ ቢያውቁም ክፍያው እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር ስለደረሰ እሱን ለባለሀብቶች ብለው ትተውታል፡፡ በታይላንድ የተደረገለትን ሕክምና ጨርሶ ወደ አገሩ በተመለሰ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ነበር ሕይወቱ ያለፈው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ስቃዩን አለማየቷን እንደ ትልቅ ድል የምትቆጥረው መቅደስ፣ በዚህ ደስታም ሐዘንም ብቻ የተደበላለቀ ስሜት ይታይባታል፡፡

ይህ እንደ ክፉ ባለጋራ አሉኝ የምትላቸውን እናቷንም ወንድሟን ተመላልሶ የቀማትን ሄፒታይተስ ለመዋጋት ቆርጣ እንድትነሳ አደረጋት፡፡ መቅደስ ብዙ ስለምታነብ ስለበሽታው ከሐኪሞች ባልተናነሰ ታውቃለች፡፡ ከባዱን ስቃይ ስትገልጽም ታማ የምታውቅ ያህል ነው፡፡ ታይላንድ በቆየችባቸው ጊዜያት የተለያዩ ከሕመሙ ጋር አብረው ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ተዋውቃ ስለነበርም፣ ስለበሽታውና ሕመምተኞቹ ብዙ ማለት ትችላለች፡፡ የሚያሳዝነው ነገር አውቃቸዋል ከምትላቸው ሰዎች መካከል ‹‹አሁን ሞቷል›› የምትላቸው መብዛታቸው ነው፡፡ በሽታው ሌሎችን ከማጥቃቱ በፊት አስቀድሞ መከላከል ላይ የመሥራት ህልም ያላት መቅደስ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የሚሠራና ሕመሙ የሕመምተኞቹ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ጉዳዬ ብሎ የሚረባረብበት አገራዊ ጉዳይ ማድረግ የሚያስችላትን የሄፒታይተስ ማኅበር ለመመሥረት ደፋ ቀና ማለት ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡

ጉበት በአልኮልና በመድኃኒት ብዛት ሊታመም ይችላል፡፡ ከመጠን ባለፈ ውፍረት፣ በከፍተኛ የኮሌስትሮል ክምችት፣ በዓይነት ሁለት የስኳር በሽታ ምክንያት በሚከሰተው በነን አልኮሊክ ፋቲ ሊቨር ዲዚዝ ጉበት ሊጠቃም ይችላል፡፡ ከፍተኛ አልኮል በመጠጣትም እንደዚሁ ጉበት ሊታመም ይችላል፡፡ ሌሎችም ጥቂት የማይባሉ ጉበትን የሚያጠቁ ሕመሞች ሲኖሩ፣ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘው ግን ሄፒታይተስ ነው፡፡ በንጽህና ምክንያት የሚከሰቱት ሄፒታይተስ ‹‹ኤ›› እና ‹‹ኢ›› የተባሉት ጊዜያዊ ሕመም ሲሆኑ፣ በሕክምና ይድናሉ፡፡ አደገኛ የሚባሉት በቫይረስ የሚከሰቱት ቫይራል ሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› እና ‹‹ሲ›› ናቸው፡፡

በዓለም ዙሪያ 325 ሚሊዮን ሰዎች በቫይራል ሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› እና ‹‹ሲ›› ተጠቅተዋል፡፡ሥርጭቱ  ከኤችአይቪ ሥርጭት ጋር ሲነፃፀር ዘጠኝ ዕጥፍ ይበልጣል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. 2000 እስከ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ በቲቢ፣ በኤችአይቪ፣ በወባናጉበት ሕመም የሚደርሰውን ሞት ቁጥር በንፅፅር ሲያስቀምጥ በቲቢ ኤችአይቪናወባ ምክንያት የሚከሰተው ሞት በየዓመቱ መቀነስ ሲያሳይ በጉበት ሕመም የሚከሰተው ሞት ቁጥር ጭማሪ እያሳየ እንደሚገኝ ያስረዳል፡፡ ቫይራል ሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› እና ‹‹ሲ›› ለጉበት ካንሰር መፈጠር ዋነኛ መንስዔዎች ናቸው፡፡ ሕመምሙ ምልክት ሳያሳይ ለረዥም ዓመታት ማለትም ለ30 እና ከዚያ በላይ ዓመታት ተደብቆ ሊቆይ ይችላል፡፡ የሕመም ምልክት ሳያሳይ ጉበትን በማጥቃት በጉበት ላይ ጠባሳ መፍጠር ይጀምራል፡፡

‹‹በሽታው ዓይንን ቢጫ በማድረግ ነው የሚታወቀው፡፡ በእኛ አገር የወፍ በሽታ ነው ተብሎ ስለሚታመን ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ብዙዎች አያውቁም፡፡ የሌሊት ወፍ ሸንታብኝ ነው የታመምኩት ብለው ስለሚያስቡ፣ ወደ ባህላዊ እንጂ ወደ ዘመናዊ ሕክምና  አይመጡም፡፡ ወደ እኛ የሚመጡት አጣዳፊ ሕመም ሲይዛቸው አልያም ጉበታቸው ከጥቅም ውጪ ከሆነ በኋላ ነው፤›› የሚሉት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የጨጓራ፣ የአንጀትና የጉበት ሕክምና አስተባባሪው ተባባሪ ፕሮፌሰርና የክፍሉ ኃላፊ ዶክተር ኃይለ ሚካኤል ደሳለኝ ናቸው፡፡  

ሄፒታይተስ ‹‹ቢ››ን ማዳን ባይቻልም የቫይረሱን ሥርጭት በመቀነስ በጉበት ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን በጊዜ ሊደረስበት ካልተቻለ ሕክምናው ምንም ሊፈጥር አይቻልም፡፡ ችግሩ በሽታው ምልክት ሳያሳይ ለረዥም ዓመታት የሚቆይበት ሁኔታ ሰዎች መታመማቸውን ሳያውቁ ጉበታቸው ከጥቅም ውጭ እስኪሆን መንቃት አለመቻላቸው ነው፡፡

 ‹‹ምልክት የሚያሳዩት ከ100 ሰዎች መካከል 11ዱ ብቻ ናቸው፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉት በሽታውን ለሰው እያስተላለፉ ጤናማ መስለው ይኖራሉ፤›› የሚሉት ዶክተር ኃይለ ሚካኤል፣ ምልክት አለማሳየቱ በሽታው ሥር እንዲሰድና በሕክምና መዳን የማይችልበት ደረጃ እንዲደርስ ዕድል እንደሚፈጥርለት ይናገራሉ፡፡

 የሄፒታይተስን ጉዳይ ነገሬ ብላ የምትሠራው መቅደስ ደግሞ ‹‹ታመን ስላልተኛን ጤናማ ነን ማለት አይደለም፡፡ በሽታው ምልክት ማሳየት የጀመረ ጊዜ አበቃልን የመዳን ዕድላችን ጠበበ ማለት ነው፤›› ስትል ማንም ሰው ከበሽታው ነፃ መሆኑን ተመርምሮ እስካላረጋገጠ ድረስ እርግጠኛ መሆን እንደማይችል ትናገራለች፡፡

የሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› ሥርጭት ከዚህ ቀደም በጤና ተቋማት በተሠራ የዳሰሳ ጥናት 7.4 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ወደ 9.4 በመቶ ማሻቀቡን ዶክተር ኃይለ ሚካኤል ይናገራሉ፡፡ የሄፒታይተስ ‹‹ሲ›› ሥርጭት ደግሞ በፊት ከነበረበት 3.1 በመቶ ወደ አንድ በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ የሥርጭት መጠኑ ከቦታ ቦታ የተለያየ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተሩ፣ ከፍተኛው የሥርጭት መጠን ያለው በአፋር ክልል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት የሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› ሥርጭት በአፋር 28 በመቶ፣ በአዲስ አበባ አሥር በመቶና በትግራይ 11 በመቶ መሆኑን አክለዋል፡፡

 ቫይራል ሄፒታይተስ በአንድ ወቅት አንገብጋቢ አገራዊ አጀንዳ ከነበረው ኤችአይቪ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ማየት ይቻላል፡፡ በማንኛውም ፈሳሽ የሚተላለፍ ሲሆን፣ ቫይረሱ የሚቆይበት ዕድሜም ከኤችአይቪ አንፃር በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ700 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ከኤችአይቪ ጋር አብረው የሚኖሩ ሲሆን፣ ከሄፒታይተስ ጋር አብረው የሚኖሩ ዜጎች ቁጥር ግን ከአሥር ሚሊዮን በላይ ሆኖ ሳለ ጉዳዩ ቸል መባሉ እንቆቅልሽ ነው፡፡      

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ ላይ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የጉበት ሕመም በኢትዮጵያ ካሉ ዋነኛ የጤና ጠንቆች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በሽታው አብዛኛውን አምራች የኅብረተሰብ ክፍል እያጠቃ ይገኛል፡፡ ቫይራል ሄፒታይተስ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፍ ሲሆን፣ በተጨማሪም ልቅ በሆነ ግብረስጋ ግንኙነት፣ በስለት በተለይም ንቅሳት በሚሠራባቸው ቁሳቁሶች ይተላለፋሉ፡፡

ኢትዮጵያ የጉበት ሕመም ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብሎም 2030 ለማስወገድ የተለያዩ ሥልቶችን በመንደፍ በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡ ለዚህም በሽታውን አስቀድሞ ተመርምሮ ማወቅና አስፈላጊውን ሕክምና ማድረግ መቻሉ ትልቅ ተስፋ ሆኗታል፡፡ 95 በመቶ የሚሆነው በሽታው በሕፃንነት ዕድሜያቸው በተያዙ ሰዎች ላይ ነው ክሮኒክ (የማይድን ሥር የሰደደ) የሚሆነው የሚሉት ዶክተሩ፣ በአዋቂዎች ላይ ሲከሰት የመዳን ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡

ለዚህም በሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› ከተያዙ እናቶች የሚወለዱ ሕፃናት ወዲያውኑ እንዲከተቡ በማድረግ ከበሽታው ነፃ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች በተለይም የሕክምና ባለሙያዎችም ይህ ክትባት እንዲደርሳቸው እየተደረገ ይገኛል፡፡ ሚሊዮኖችን ከመጥፋት የሚታደገውን ይኼንን ክትባት ለብዙኃኑ ማድረስ ከባድ በመሆኑ በነፃ የሚሰጠው ለባለሙያዎችና ለሕፃናት ብቻ ቢሆንም፣ አንዳንድ የግል ሆስፒታሎች ተመርምረው ከቫይረሱ ነፃ የሆኑ ሰዎችን እስከ 1,000 ብር እያስከፈሉ ክትባቱን እንደሚሰጡ መቅደስ ትናገራለች፡፡

በገዳይነታቸውና በተላላፊነታቸው ግንባር ቀደም ሆነው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን እያሽመደመዱ የሚገኙት ቫይራል በመባል የሚታወቁት ሁለቱ ሄፒታይተሶችን ሥርጭት አስቀድሞ በሚደረግ ጥንቃቄ መቆጣጠር ቀላል ቢሆንም፣ ሒደቱን የሚያከብዱ ውስብስብ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ ማኅበረሰቡ ስለሄፒታይተስ ያለው ግንዛቤ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ የሚሆኑበት ዕድልም ሰፊ ነው፡፡ ሄፒታይተስ ‹‹ቢ››ን በክትባት አስቀድሞ መከላከል ቢቻልም የክትባቱ ተደራሽነት አናሳ መሆን፣ እንዲሁም ቅድመ ጥንቃቄ የማድረግ ባህሉ ዝቅተኛነት ችግር ሆኗል፡፡

ሌላው በቫይራል ሄፒታይተስ ከተያዙ በኋላ በሽታው ስለሚያስከትለው የጤና ቀውስ ተረድቶ በጊዜ አስፈላጊውን ሕክምና ማድረግ ላይም ችግር አለ፡፡ ከዚህም ባሻገር ሕክምናውን ለማድረግ ምርመራውን ከማካሄድ ጀምሮ ትልቅ የአቅም ችግር ያታያል፡፡ ‹‹የላቦራቶሪ ችግሮች አሉብን፡፡ ከዚህም ባሻገር መድኃኒቶችን ማስገባትም በዚሁ መጠን ፈታኝ ነው፤›› የሚሉት ዶክተሩ፣ ሕክምናውም ቢሆን ቀላል አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡  ቫይራል ሄፒታይተስ ‹‹ቢ››ን ሥርጭት በደንብ መቆጣጠር እስከተቻለ ድረስ መድኃኒት እየወሰዱ በመቆየት ጤናማ ሕይወት መኖር ይቻላል፡፡ ‹‹ሲ››ን ደግሞ አስቀድሞ ከታወቀ ጉበት ላይ ጠባሳ ከመጣሉ በፊት ለሦስት ወራት በሚወሰድ መድኃኒት መፈወስ ይቻላል፡፡ ችግሩ አስቀድሞ ቢያውቁም ምርመራው አገር ውስጥ ባለ የላቦራቶሪ ግብዓት ማካሄድ ስለማይቻል ናሙናው ሌላ አገር መላክና ውጤት መጠበቅ ግድ ማለቱ ነው፡፡ ባህር ማዶ የሚደረገው ምርመራ በደም ውስጥ ያለውን የቫይረስ መጠን ምን ያህል እንደሆነ መለየትና ምን ዓይነት ሕክምና እንደሚያስፈልገው የመወሰን ሚና አለው፡፡ ችግሩ ግን ምርመራው አልቆ ወደዚህ እስኪላክ ባለው ጊዜ ውስጥ በሕመምተኛው ደም ውስጥ የሚገኘው የቫይረስ መጠን በአንዴ በመቶ ሺዎችና በሚሊየኖች ከፍ ብሎ መቆየቱ ላይ ነው፡፡

‹‹ከወንድሜ የተወሰደው የደም ናሙና ውጤት የሚያሳየው የቫይረሱ ሥርጭት በመቶ ቤት እንደነበር ነው፡፡ ታይላንድ በሄደበት ወቅት ግን የቫይረሱ መጠን በመቶ ሺዎች ገብቶ ነበር፤›› የምትለው መቅደስ፣ በሌሎች ታማሚዎች ላይም መሰል ሁኔታዎች በብዛት እንደሚከሰቱ ትናገራለች፡፡ ሆኖም ግን መድኃኒቱን በጊዜ መጀመር የቫይረሱ ሥርጭት የቱንም ያህል ከፍ ቢል መልሶ ዝቅ እንዲል ያደርገዋል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን መድኃኒቶቹንስ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል? የሚለው ነገር ነው፡፡

ለቫይራል ሄፒታይተስ የሚሆኑትን ‹‹ሀርቮኒ›› እና ‹‹ቪሪያድ›› የተሰኙ መድኃኒቶች የባለቤትነት መብት ያለው ጊሊያድ የተባለ ዓለም አቀፍ የፋርማሱቲካል ድርጅት ነው፡፡ ሀርቮኒ ለሄፒታይተስ ‹‹ሲ››፣ ቪሪያድ ደግሞ ለሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› የሚያገለግሉ መድኃኒቶች ናቸው፡፡ እነዚህን መድኃኒቶች ለማምረት ጊሊያድ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ገንዘብ ያፈሰሰ ሲሆን፣ ያወጣበትን ወጪና ማግኘት ያለበትን ጥቅም አስቦ የሚሸጥበት ዋጋ የማይቀመስ ነው፡፡

ለምሳሌ ሀርቮኒ የሚባለው የሄፒታይተስ ‹‹ሲ›› መድኃኒት ለሦስት ወራት የሚወሰድ ሲሆን፣ የሚሸጠውም በ84 ሺሕ ዶላር ነው፡፡ ይኼንን መድኃኒት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ባለድርሻ አካላትና የወገን ስቃይ የሚሰማቸው አንዳንድ ግለሰቦች ጊሊያድን ደጅ መጥናት ነበረባቸው፡፡ እንኳንስ የድህነት መገለጫ ለሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ቀርቶ፣ ሀርቮኒ ኢኮኖሚያቸው የስኬት ጫፍ ላይ ለደረሰው ምዕራባውያን ዋጋው በጣም ውድ ነው፡፡ ሆኖም ሀርቮኒ በቅናሽ ዋጋ ኢትዮጵያ እንዲገባ ማድረግ ተችሏል፡፡

 ከጊሊያድ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መድኃኒቶች አስተባባሪ ሆነው የሚያገለግሉት አቶ በኃይሉ ዘለቀ፣ አንዱ መድሐኒት መጀመርያ ላይ 99 ሺሕ ዶላር እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ግን ሳይቀንስ እንደማይቀር ወደ ኢትዮጵያ የሚገባውም 99 በመቶ ቅናሽ ተደርጎበት በ1,000 ዶላር አካባቢ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በጣም ውድ የሚባለው ለቫይራል ሄፒታይተስ ‹‹ሲ›› የሚታዘዘው በ1,000 ዶላር የሚሸጠው መድኃኒት እስከ ሦስት ወራት ድረስ ብቻ የሚወሰድ ነው፡፡

 ለሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› የሚታዘዘው ቪሪያድ ግን ሐኪሙ ካላዘዘ በስተቀር የማይቋረጥና ለረዥም ጊዜ የሚወሰድ መድኃኒት ነው፡፡ ቫይራል ቢ ያለባቸው ታማሚዎች መድኃኒቱን ለማግኘት በየወሩ 1,000 ብር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ በየወሩ ተከፋፍሎ ሲታይ አነስተኛ ይምሰል እንጂ ለዓመታት የሚቆይ ስለሆነ ገንዘቡ ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ አቅሙ የሌላቸው በሕይወታቸው ላይ ፈርደው የሚተውትም ነው፡፡

በሚሊዮን ከሚቆጠሩ የቫይራል ሄፒታይተስ ተጠቂዎች መካከል በምርመራ ራሳቸውን አውቀው መድኃኒቱን የሚከታተሉ በቁጥር ናቸው፡፡ ‹‹ቪሪያድን ከአንድ ሺሕ እስከ አራት ሺሕ ፓኮ እናስመጣለን፡፡ ሀርቮኒንም እስከ 600 ፓኮ ድረስ እናስመጣለን፤›› የሚሉት አቶ በኃይሉ፣ የሚመጣው መድኃኒት መጠን በሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ መጠን እንደሚወሰን፣ እንዲሁም ያለው ፍላጎት ከታማሚዎች አንፃር በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግር ሳይኖር በፊት በየወሩ እንደሚያስገቡ፣ ባጋጠመው እጥረት ሳያመጡ እስከ ስድስት ወራት ድረስ ቆይተው እንደሚያውቁ ይናገራሉ፡፡

ይህም ሰዎች ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከፊሎቹ በኮንትሮባንድ የሚገቡ መድኃኒቶችን ለመጠቀም ሲገደዱ፣ የተቀሩት ደግሞ ተመሳሳይ መድኃኒቶችን ማሳደድ ይይዛሉ፡፡ ‹‹ለቫይራል ሄፒታይተስ የሚሰጠው መድኃኒት ከኤችአይቪ መድኃኒት ጋር ይመሳሰላል፡፡ ስለዚህም ሰዎች ይኼንን መድኃኒት እንዲታዘዝላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ነገር ግን የኤችአይቪ ቫይረስ በደማችሁ ውስጥ ካልተገኘ አይሰጣችሁም ይባላሉ፤›› በማለት ዶክተር ኃይለ ሚካኤል፣ ተመሳሳይ መድኃኒቶችን እንኳ ለማግኘት ከባድ መሆኑንና በርካቶች የመዳን ተስፋቸው እየጨለመ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡

ከዚህም ባሻገር አንዳንድ ለሙያው ያልተገዙ ሐኪሞች መድኃኒቱን በኮንትሮባንድ እያስገቡ ለመቸርቸር እንዲመቻቸው ሲሉ ታካሚዎች ከሌላ ቦታ መድኃኒት ሳይጀምሩ እንዲቆዩ እንደሚያደርጉ መቅደስ የታዘበችውን ትናገራለች፡፡ ይህም በሽታው ሥር እንዲሰድና የማይድኑበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ እያደረጋቸው የሚገኝ ሲሆን፣ ወንድሟና ጥቂት የማይባሉ ሌሎች በዚህ ምክንያት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ትናገራለች፡፡

በኢትዮጵያ የጉበት ሕመምን ለመከላከልና ለመቆጣጠርና ብሎም ለማስወገድ የቫይራል ሄፒታይተስ ፕሮግራም ለማጠናከር አገር አቀፍ ስትራቴጂክ ዕቅድ እንዲሁም የሥራ መመርያ ቅድሚያ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መግባት ተችሏል፡፡ በቫይረሱ አማካይነት ስለሚከሰት የጉበት ሕመምና ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶች በማዘጋጀት ተሰራጭተዋል፡፡

 የቫይራል ሄፒታይተስ ምርመራና ሕክምና አገልግሎት 49 ሆስፒታሎች ለማጠናከርና ለማስፋፋት ለጤና ባለሙያዎች (ሐኪሞች፣ ፋርማሲስቶችና የላቦራቶሪ ባለሙያዎች፣ የክልል ኅብረተሰብ ላብራቶሪ ባለሙያዎችና ክልል መድኃኒት ፈንድ ቅርንጫፍ ባለሙያዎች) በአዲስ አባባ፣አማራ፣አፋር፣ትግራይኦሮሚያ፣ደቡብ፣ጋምቤላ፣ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በሶማሌ፣ድሬዳዋናሐረር ክልሎች ለተውጣጡ ተሳታፊዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

ከእነዚህ 13 የመንግሥትና አሥር የግል ሆስፒታሎች አገልግሎት የጀመሩ ሲሆን፣ ቀሪዎች በቀጣይ አገልግሎት እንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡ በዕቅዱ መሠረትም ሁሉም ሥልጠናዎች ሙሉ ለሙሉ ተከናውነዋል፡፡ የሕክምና መድኃኒት በመድኃኒት ፈንድ በኩል ግዢ በማከናወን ቀደም ብለው አገር ውስጥ የገቡ መድኃኒቶች ለሆስፒታሎች ተሰራጭተው ሕክምና ጀምረዋል፡፡

የዓለም የጉበት ሕመም ቀን በየዓመቱ ሐምሌ 21 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ‹‹የጉበት ሕመም፣ መመርመር፣ መታከም፤›› በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡ የበዓሉ ዋና ዓላማ የዓለም ጉበት ሕመም ቀንን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም የማኅበረሰቡን በጉበት ሕመም ዙሪያ ያለውን የመከላከልና መቆጣጠር ግንዛቤ ማዳበር ነው፡፡