Skip to main content
x
‹‹በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ ብዙ ነገሮችን እንድንመረምር ያደረገን ይመስለኛል››

‹‹በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ ብዙ ነገሮችን እንድንመረምር ያደረገን ይመስለኛል››

ግሩም ዓባይ፣ በሩሲያ የኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደር

በሲቪዬት ኅብረት ዘመን ነበር ወደ ሩሲያ ያቀኑት፡፡ በ1971 ዓ.ም. በሩሲያ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ጀምረው በ1977 ዓ.ም. አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀጥረው በተለያዩ የሥራ እርከኖች ለ30 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ዘመን ቆይታቸውም ሁለተኛ ጸሐፊ፣ አንደኛ ጸሐፊ፣ ካውንስለርና ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጄኔራልና አምባሳደር ሆነው ሠርተዋል፡፡ በአውሮፓ ኅብረት መምርያ በሥራ ላይ እያሉ 1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ በ1984 ዓ.ም. በብራሰልስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ፡፡ ከዓመታት ቆይታ በኋላም በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰውም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነውም አገልግለዋል፡፡ ከዚያም ዳግም ወደ ጣሊያን በአምባሳደርነት፣ የአውሮፓና የአሜሪካ ዲፓርትመንት ለሁለት ሲከፈል በዋና ኃላፊነት አገልግለው፣ ከመጋቢት 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሾመው በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡ አምባሳደር ግሩም ዓባይ በቅርቡ በቤልጂየም ብራስልስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል፡፡ በሩሲያ ስለነበራቸው ቆይታና ስለአዲሱ ሹመታቸው በሩሲያ የዓለም ዋንጫ ወቅት ሞስኮ ያገኛቸው ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ከተሾሙ ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖዎታል፡፡ በቆይታዎ ወቅት ሩሲያና ኢትዮጵያ የነበራቸውን ግንኙነት ቢያብራሩልን?

አምባሳደር ግሩም፡- ኢትዮጵያና ሩሲያ ያላቸው ግንኙነት በአራት የተለያዩ ጉዳዮች ይከፈላሉ፡፡ አንደኛው የፖለቲካና የዲፕሎማሲ፣ የገጽታ ግንባታ፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚና የዳያስፖራ ዘርፎች ናቸው፡፡ ቀሪው የአስተዳደርና ፋይናንስ ሆኖ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር ያለው ነው፡፡ በፖለቲካና በዲፕሎማሲ ባለፉት ዓመታት ምንም እንኳ በባህልና በታሪክ ጠንካራ ግንኙነት አለን ቢባልም፣ ከሶቪየት ኅብረት መፍረስ በኋላ ይኼ አገር ወደ ውስጥ መመልከት ነው የጀመረው፡፡ እንደ ድሮ አቅም ያለው አገር መሆን አልቻለም፡፡ የሩሲያ ፌዴሬሽን ሲቋቋም ብዙ ነገር ተቀየረ፡፡ ሩሲያውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበራቸው ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖ በዚያው መጠን ቀንሶ ነበር፡፡ ወደ ውጭ ለመመልከት አሥር ዓመታት ገደማ ወስዶባቸዋል፡፡ እኛም ዘንድ መንግሥት ከተለወጠ በኋላ ትኩረታችን ወደ ውስጥ ነበር፡፡ ስለዚህ ይኼን ማስተካከል ነበረብን፡፡ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮችን ማስተካከል ነበረብን፡፡ በሚያገናኙን ክልላዊም ሆነ አኅጉራዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ የምንሠራበት ጉዳይ ላይ መሥራት ነበረብን፡፡ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ምንድነው የሚያገናኝ ብለን ቁጭ ብለን ወስነን አቅጣጫ አስቀምጠን ስንሠራ ነበር፡፡ በመሠረቱ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ የቀይ ባህር፣ የዓረብ ባህረ ሰላጤ፣ የፀረ ሽብርተኝነትና የተባበሩ መንግሥታት ድርጅት ጉዳዮች ያገናኙናል፡፡ በዓለም አቀፍ መድረክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ላለፉት ሁለት ዓመታት ተለዋጭ አባል መሆናችንን ተከትሎ፣ እዚያ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ የሚሠሩትን ነገሮች በጋራ ለይተን ነበር፡፡ አባል ስንሆንም ሩሲያ ውስጥ ከኒውዮርክና ከአዲስ አበባ የልዑካን ቡድኖች መጥተው፣ ሩሲያን በተመለከተ በፀጥታው ምክር ቤት መድረክ ላይ በሚነሱ የጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተናል፡፡ በዚህም መሠረት አሜሪካና ሩሲያን የሚያገናኛቸውን፣ ነገር ግን ለእኛ ቅርብ የሆኑትን በጥንቃቄ ተመልክተን ተወያይተንባቸዋል፡፡ በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሩሲያ የመንግሥት ተቋማትና የውጭ ጉዳይ አካላት ጋር የነበራችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

አምባሳደር ግሩም፡- በሩሲያ ካሉት የመንግሥትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አካላት ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለን፡፡ በቋሚነት በየወሩ ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአፍሪካ መምርያም ሆነ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች መምርያ ጋር እንገኛለን፡፡ በሦስት ወራት አንዴ ከምክትል ሚኒስትሩ ጋር በቋሚነት የምንገናኝበት መድረክ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር የፓርላማ ጉዳይን በተመለከተም ከሁለቱም የሩሲያ ምክር ቤቶች ጋር ግንኙነት ለማጠናከር ተሞክሯል፡፡ የተለያዩ ስምምነቶችን ለመፈረም ጫፍ የደረስንበት ሁኔታ አለ፡፡ የረቂቅ ስምምነቶች ልውውጥ ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ እነዚህም ረቂቆች ከኢትዮጵያ ከመጡ የፓርላማ ልዑካን ቡድኖች ጋር በጋራ ለመሥራት የተፈራረሙትን ስምምነቶች ይዘዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በፀጥታ ጉዳዮች፤ በፖለቲካና በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጋራ የሚሠሩ አሉ፡፡ የአገር መከላከያን በተመለከተም ከሶቪዬት ኅብረት ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ ሠራዊት የታጠቀው የሩሲያን መሣሪያ ነው፡፡ ስለዚህ የረዥም ጊዜ ግንኙነታችን እንደቀጠለ ነው፡፡ በሰው ኃይል ሥልጠና በመከላከያ ዘርፍም ሆነ በሲቪል ሰርቪስ ተማሪዎችም የሚካሄድ ሥራ አለ፡፡ ባለፉት ዓመታት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጀምሮ የተለያዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና በሚኒስትር ደረጃ ኃላፊነት ያላቸው ባለሥልጣናት በሩሲያ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፎች በሁለቱ አገሮች መካከል ተቀዛቅዞ የነበረውን ግንኙነት ለማስተካከል ተሞክሯል፡፡  

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል የተሠራው የገጽታ ግንባታ ምንድነው?

አምባሳደር ግሩም፡- የገጽታ ግንባታን በተመለከተ ዋናው ትኩረት የነበረው የሩሲያ ኅብረተሰብ ስለኢትዮጵያ ምን ያውቃል የሚለው ሥራ ነበር፡፡ በሶቪየት ኅብረት ዘመን የነበረው ትውልድ ስለኢትዮጵያና አፍሪካ በተወሰነ ደረጃ ያውቃል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ግን ብዙ አያውቅም፡፡ ስለዚህ አሁን ትኩረት መሰጠት ያለበት ይኼኛው ትውልድ ላይ ነው፡፡ የአሁኑ ትውልድ ላይ ለመሥራት ደግሞ ዋና ትኩረት ያደረግነው ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ በመገኘት፣ ከተለያዩ የሚዲያ አካላት ጋር በጋራ በፕሮሞሽን የተለያዩ ጽሑፎች እንዲወጡ በማድረግ፣ በእኛ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ ስለኢትዮጵያ እንዲያውቅ በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ከዚህ አኳያ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የነበረንን ግንኙነት በተመለከተ፣ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲፕሎማቶች ማሠልጠኛ ተቋም አላቸው፡፡ ይኼም የዲፕሎማቶች ማሠልጠኛ ተቋም ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወጣት ዲፕሎማቶች ሥልጠና ለመስጠት የዛሬ ሦስት ዓመት ስምምነት ተፈራርመን ሒደቱ ሲታይ ቆይቶ፣ በመስከረም ወር 20 ወጣት ዲፕሎማቶች ሩሲያ ይመጣሉ፡፡

ሁለተኛ በሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር ራሱን የቻለ፣ የሞስኮ ዓለም አቀፍ የግንኙነት ዩኒቨርሲቲ የሚባል አለ፡፡ ስለዚህ ከዚህ ተቋም ጋር የዛሬ ሁለት ዓመት ስምምነት ተፈራርመን፣ እዚያ በሚሰጡ ሥልጠናዎች ኢትዮጵያውያን ዕድሉን እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ አከናውነናል፡፡ ሥልጠናው በክፍያ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ግን በነፃ እንዲማሩ ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ የሩሲያን ሚዲያ በተመለከተ ብዙ ጊዜ እንደ ምዕራባውያን አገር ሚዲያዎች ለሌሎች አገሮች ትኩረት አይሰጡም፡፡ የዜና ሥርጭታቸውን ብንመለከት 80 በመቶ የራሳቸውን ጉዳይ ብቻ ነው የሚያካትቱት፡፡ በተለይ አፍሪካ ላይ ምንም ዓይነት ሽፋን አይሰጡም፡፡ እኛ ግን በሦስት ወር አንዴም ስንገናኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተከናወኑት ጉዳዮች ለማሳወቅ እንሞክራለን፡፡ ወደ አገር ውስጥም ሄደው የተለያዩ ዘገባዎችን እንዲሠሩልን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን እንዲያሳዩልን ሞክረናል፡፡     

ሪፖርተር፡- በሁለቱ አገሮች መካከል የተከናወነ የቢዝነስ ግንኙነት ካለ?

አምባሳደር ግሩም፡- ቢዝነስን በተመለከተ አስቸጋሪው ዘርፍ ነበር፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ የሩሲያ ኩባንያዎች በመንግሥት እጅ ውስጥ ናቸው፡፡ ከፍተኛ ትኩረታቸውም በጋዝ፣ በዘይት፣ በማዕድንና በተወሰነ ደረጃ የመሣሪያ ሽያጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በጋዝና በዘይት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ አትከተልም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ዓይን ለዓይን የምትተያይበት ደረጃ ላይ አልደረሰችም፡፡ እኛ ያተኮርነው የንግድ ዘርፉን ግንኙነቱን ማጠናከር፣ ባህላዊ የሆኑ ምርቶችን ኤክስፖርት ማድረግና ነባር ገበያውን ማስጠበቅ ነው፡፡ አዳዲስ ገበያዎች መፈላለግ ከጀመርን ሰነባብተናል፡፡ ግን በሩሲያውያን በኩል የሚነሳ ችግር ቢኖርም፣ በእኛም በኩል ችግር ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት እንዳስፈላጊነቱ ማስኬድ አልተቻለም፡፡

ሪፖርተር፡- በእኛ በኩል ያለው ችግር ምንድነው?

አምባሳደር ግሩም፡- በኢትዮጵያ በኩል ያለው ችግር የኮንትራትን ስምምነት በአግባቡ ያለማክበር፣ በተባለው መጠንና የጥራት ምርቶችን ያለማቅረብ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሁለተኛ ችግር ደግሞ ቀጥታ የአየር በረራ አለመኖር ነው፡፡ ቀጥታ በረራ ባለመኖሩ ምርቶቻችን በሦስተኛ ወገን በኩል ነው የሚገቡት፡፡ ለምሳሌ የአበባ ምርታችን በጣም ተፈላጊ በመሆኑ ከሆላንድ በመኪና ይገባል፡፡ ስለዚህ የንግድ ግንኙነቱን ለማንቀሳቀስና ለማቀላጠፍ ስንል፣ ላለፉት ዓመታት ስንደክም የነበረው በሁለቱ አገሮች መካከል ቀጥታ በረራ እንዲኖር ማድረግ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ጥረታችን ተሳክቶ በረራው ተጀምሯል፡፡ ከዚህ በኋላ ምርቶቻችንን በቀላሉ ማጓጓዝና ለገበያ ማቅረብ ያስችለናል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ ሩሲያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በቀዳሚነት ስሟ ይጠቀሳል፡፡ ኢትዮጵያም ከሩሲያ ጋር ካላት ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያ ግንኙነት ባሻገር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላት ግንኙነት እንዴት ይገለጻል?

አምባሳደር ግሩም፡- የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሌላው ትልቅ ትኩረት የሰጠንበት የዕውቀት ሽግግር ነው፡፡ በዚህም ዘርፍ ከሩሲያ ጋር የኑክሌር ኃይልን ለሰላማዊ አገልግሎት ለመጠቀም የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ በ2009 ዓ.ም. ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ የኑክሌር ኃይል ለሰላማዊ ጥቅም እናውላለን ስንል ለኢነርጂ አቅም እንዲሆነን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ኢነርጂ የምትጠቀመው ከውኃ ነው፡፡ ግድቦችን ብቻ እየገነባን አንዘልቅም፡፡ ግድቦች ብንገነባም ከአየር ንብረት መለወጥ ጋር በተያያዘ የዝናብ እጥረት ቢያጋጥመን አዳጋች ነው፡፡ ስለዚህ በተፈጥሮ ላይ ብቻ ከማተኮር እንዲህ ዓይነት አማራጮችን መፈለግ ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህ ቀዳሚ ያደረግነው ኑክሌር መገንባት ሳይሆን የሰው ኃይልን ማሠልጠን ነው፡፡ ምክንያቱም ከተገነባ በኋላ በውጭ ዜጎች ሳይሆን በራሳችን ባለሙያዎች መተግበር ስላለበት፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በባቡር ሐዲድ ኢንጂነሪነግ መስክ የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ ከካሊንግራድ ከተማ 40 ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ተመርቀዋል፡፡ እነሱም በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ተጨማሪ ተማሪዎችም በቀጣይ ሥልጠና እንደሚወስዱ ተነጋግረናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሩሲያ መንግሥት ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የሚሰጠው የትምህርት ዕድል ላይ አንዳንድ ችግሮች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ምክንያቱም ምንድነው?

አምባሳደር ግሩም፡- የሩሲያ መንግሥት በየዓመቱ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ሰፊ የትምህርት ዕድል ይሰጣል፡፡ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የትምህርት ዕድል ለመስጠት ዝግጁ እንደሆኑ ይገልጹልናል፡፡ ስለዚህ ትምህርት ሚኒስቴር ጉዳዩን በአትኩሮት ሊመለከተው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ትምህርት ሚኒስቴር ዘንድ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የሩሲያን ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ ለመጋበዝ ምን ተሠርቷል?

አምባሳደር ግሩም፡- ኢትዮጵያ የምትከተለው የኢንቨስትመንት አሠራር በቂ የሆነ የሰው ኃይል መጠቀም የሚያስችልና በማንፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የሩሲያ ኢንቨስተሮች ይኼንን ደረጃ አልፈውታል፡፡ እነሱን ወደ ኢትዮጵያ ለመጋበዝ እንደ ቱርክና ህንድ ኢንቨስተሮች ቀላል አይደለም፡፡ የሩሲያ ኢንቨስተሮች ትኩረት ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ላይ ነው፡፡ ለጊዜው ግን እሱን ትተን በኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ እንዲያስቡ እያደረግን ነው፡፡ ስለዚህ በምግብ ዘርፍ ውጥስ የሚገኙ ኢንቨስተሮች በኢንዱስትሪ ፓርኩ እንዲሳተፉ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ብዙ የቤት ሥራዎች ግን ይጠብቁናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሶቭየት ኅብረት ዘመን ጀምሮ ኑሯቸውን በሩሲያ አድርገው ጎጇቸውን ከቀለሱና የትምህርት ዕድል ካገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር ኤምባሲው ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል?

አምባሳደር ግሩም፡- ከሶቪየት ኅብረት በኋላ በሩሲያ የሚኖሩ ኢዮጵያውያን ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡ በየዓመቱ ወደ ሩሲያ የሚመጡትን ኢትዮጵያውያን ማንነት የሚገልጽ መረጃ እንይዛለን፡፡ በዚህም መረጃ መሠረት በሩሲያ ፌዴሬሽን፣ ዩክሬንና ቤላሩስ የሚኖሩ በአጠቃላይ 313 ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በሩሲያ ፌዴሬሸን ውስጥ የሚገኙ 210 ናቸው፡፡ አመጣጣቸውም ለትምህርት ሆኖ እዚሁ የቀሩ ናቸው፡፡ የቁጥራቸው አናሳ መሆን ምክንያቱ የሩሲያ መንግሥት ስደተኞችን አለመቀበሉ ነው፡፡ በየዓመቱ የነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው የሚመጡት የግልና የመንግሥት ተማሪዎች 12 ናቸው፡፡ ቁጥራቸው አይጨምር፣ አይቀንስም፡፡ እዚህ ካሉት ጋር በጋራ እንሠራለን፣ በተለያዩ ዝግጅቶችም እንገናኛለን፡፡ እነሱም ለኤምባሲው ቅርብ ናቸው፡፡  አንድ ቡድን አለ፡፡ በዚህ ቡድን ውስጥ የተለያዩ ችግሮች ሲኖሩ እየተወያየን እንፈታለን፡፡ ድጋፍ ሲኖር እንደግፋለን፣ ከተማሪዎች ኅብረት ጋር እንገናኛለን፡፡ እኛም ድጋፍ ከእነሱ ስንፈልግ አሳፍረውን አያውቁም፡፡

ሪፖርተር፡- በሩሲያ ዩኒቨርሰቲዎች የትምህርት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ እዚህ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ እንደማያገኙ ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ ሌሎች የአፍሪካ አገር ተማሪዎች በኤምባሲ ውስጥ ገብተው የመሥራት ዕድል እንዳላቸው ይነገራል፡፡  በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አሠራር ቢያብራሩልን?

አምባሳደር ግሩም፡- ከሌላ አፍሪካ አገሮች የትምህርት ዕድል ያገኙ ዜጎች በኤምባሲያቸው ውስጥ የመቀጠር ዕድል ተፈጥሮላቸዋል የሚለው ሐሳብ እንደ የአገሩ አሠራሩ ሊለያይ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዚህ ዓይነት አሠራር የለውም፡፡ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ አንደኛ ዲፕሎማቶች ናቸው፡፡ ዲፕሎማቶች ደግሞ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው የሚመጡት፡፡ ሁለተኛ ከዚህ የሚቀጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህም የሩሲያ ዜጎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ወይም ደግሞ በሩሲያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ከኢትዮጵያ የሚመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ የአምባሳደሩ ምግብ ቤት አብሳይ፣ ሾፌር፣ ፅዳትና የጽሕፈት ቤት ሠራተኛ ሆነው የቀጠሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ትምህርት ላይ ያሉና ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ በቀጥታ ኤምባሲ የሚቀጠሩበት አሠራር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲሱ የመንግሥት የሥልጣን ሽግሽግ መሠረት በቤልጂየም የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል፡፡ ስለሹመቱና ቀጣይ ሥራ ምን ይላሉ?

አምባሳደር ግሩም፡- እኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የቆየን ሰዎች አምበሳደርነትን እንደ መከላከያ ነው የምንመለከተው፡፡ የታዘዝንበት ቦታ እንሄዳለን፡፡ ስለዚህ ይኼ ሌላ ተጨማሪ ተልዕኮ ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ ከፍተኛ ኃላፊነት ነው፡፡ ምክንያቱም ብራሰልስ ቤልጂየም ብቻ አይደለም፡፡ ብራሰልስ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እስካሁን ባለው ሁኔታ ቤልጄም፣ ሆላንድና ላክዘንበርግ አጠቃሎ ይሠራል፡፡ ከዚያ ባሻገር የአውሮፓ ኅብረት ተቋማትን ይሸፍናል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ተቋማት ሦስት ናቸው፡፡ የአውሮፓ ኮሚሽን፣ ካውንስልና ፓርላማ ናቸው፡፡ ሌላው የአፍሪካ ካሪቢያን ፓስፊክ ድርጅት ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ ኃላፊነት ወስዶ በትኩረት መሥራት ያሻል፡፡ እዚያ መዘዋወር በአንድ በኩል እንደ ማንኛውም ሥራ ተልዕኮ ይቆጠራል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ እዚያ ያለው ሥራ ቀላል አልነበረም፡፡ ከዚህ ቀደም እዚያ መሥራት ለእኔ አዲስ አይደለም፡፡ ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቀኝና ትልቅ ግምትም እንደሚኖረው አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር ነው፡፡ በየዓመቱ የሚገኘው ገንዘብ ቀላል አይደለም፡፡ ሌላው በፖለቲካና በዴሞክራሲያዊ ሥራዎችና በፀጥታ ጉዳዮች በኩል ከተቋማት ጋር መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ስለዚህ ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩም እንደ ኃላፊነት ተቀብየዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሩሲያ ከሚገኙት የሃይማኖት መሪዎች ጋር ተገናኝተው ነበር፡፡ በሁለቱ አገሮች የሃይማኖት መሪዎች መካከል የነበረው ቆይታ ምን ነበር?

አምባሳደር ግሩም፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ በሩሲያ ያደረጉት ጉብኝት ሁለት ዓይነት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ አንደኛው መንፈሳዊ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ፖለቲካዊ አንድምታ ነበረው፡፡ ፖለቲካዊ አንድምታ ነበረው ያልኩበት ምክንያት፣ በጉብኝታቸው ወቅት የፖለቲካ ተቋማትን አግኝተዋል፡፡ አንደኛው ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቨሮቭ ጋር ከ45 ደቂቃ በላይ ተወያይተዋል፡፡ በውይይታቸው ወቅት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የሚያጠናክሩ ጉዳዮችና የሃይማኖት ተቋማት መወጣት ያለባቸው ኃላፊነት ላይ ተነጋግረዋል፡፡ በእርግጥ ፓትርያርኩ ወደ ሩሲያ የመጡት በአገሪቱ ፓትርያርክ ኪሪ ግብዣ ነው፡፡ ይኼ ጉብኝት ወደ ሩሲያ ሲደረግ ከ17 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ፓትርያርኩ ከሩሲያ ፓርላማ የላይኛው ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔው ጋር ተገናኝተው፣ ከሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ጋር በተያያዘና በፓርላማ ደረጃ ሊሠሩ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ተወያይተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ከሩሲያ ፓትርያርክ ጋርም የተለያዩ ገዳሞችን በመጎብኘት፣ ከዚህ ቀደም ተቋርጦ የነበረው የሃይማኖት ትምህርት እንዲቀጥል ተስማምተዋል፡፡ ስለዚህ የፓትርያርኩ ጉብኘት ራሱን የቻለ መንፈሳዊ ተልዕኮ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የፖለቲካ ለውጥ እንዴት ተመለከቱት?

አምባሳደር ግሩም፡- በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ ብዙ ነገሮችን እንድንመረምር ያደረገን ይመስለኛል፡፡ ወዴት ነው እየሄድን ያለነው? ምን ዓይነት ሥራዎች ነበር እየሠራን የነበረው? የሚለውን ነገር ማየት ችለናል ባይ ነኝ፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም በየፊናው የራሱን ተልዕኮ መወጣት አለበት፡፡ የኢትዮጵያን ጉዳይ ለተወሰኑ ቡድኖች፣ ድርጅቶችና ፓርቲዎች የሚተው አይደለም፡፡ ሁሉም ዜጋ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡ አሁን ከድሮ የተሻለ ደረጃ ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ግን እስካሁን ከጫካ ወጥተናል ማለት አይቻልም፡፡ ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡ እነዚያን ሥራዎች ለማከናወን የጋራ የሆነ አንድ አዕምሮ ያስፈልገናል፡፡ አንድ አገር ስላለችን ሁላችንም ለአንድ አገሩ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ መሥራት ያስፈልገናል፡፡ አሁን የተሻሉ ነገሮች አሉን፡፡ እነዚህን ነገሮች ይዘን ወደ ፊት መሮጥ ያስፈልገናል፡፡