Skip to main content
x
‹‹ዘንድሮ በከተማዋ የሚከሰተውን የሞት አደጋ በአምስት በመቶ መቀነስ ችለናል››

‹‹ዘንድሮ በከተማዋ የሚከሰተውን የሞት አደጋ በአምስት በመቶ መቀነስ ችለናል››

አቶ ጅሬኛ ሂርጳ፣ የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር

በመላ አገሪቱ ከሚከሰተው የትራፊክ አደጋ ውስጥ አብዛኛው በአዲስ አበባ ይከሰታል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመንገድ ትራፊክ አደጋ ሁኔታ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በ2007 ዓ.ም. በ443 ሰዎች የሞት አደጋ ሲከሰት፣ በ2008 ዓ.ም. ቁጥሩ ወደ 463 ከፍ ብሏል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ደግሞ 477 ሰዎች በመንገድ ትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን ያመለክታል፡፡ በነዚህ ዓመታት ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የሞት አደጋ በእግረኞች ላይ የተከሰተ ሲሆን፣ ከአደጋ ተጋላጭነት አኳያ 70 በመቶው የሚሆነው አደጋ የተከሰተው የመኪና መንገድ ሲያቋርጡ በነበሩ ሰዎች ላይ ነው፡፡ አብዛኛው የሞት አደጋ የሚከሰተው ከ15 እስከ 44 ዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ  ላይ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የትራፊክ ፖሊስ በዘመናዊ አሠራርና መሣሪያዎች በመደገፍ በከተማው ውስጥ የሚታዩ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቆችን፣ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ እንዲሁም የትራፊክ ደንብና መመርያዎችን በላቀ ሁኔታ በማስፈጸም ችግሩን በበቂ ሁኔታ ይቀርፋሉና ያሻሽላሉ ብሎ ያመነባቸውን የተለያዩ ተግባሮችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ባንክ ባገኘው የረዥም ጊዜ ብድር አማካይነት የከተማ አስተዳደሩ ሥራዎችን በበላይነት እንዲመራ ለአዲስ አበባ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ በሰጠው ኃላፊነት መሠረት ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ማክሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም በ175 ሚሊዮን ብር የገዛቸውን የትራፊክ ቁጥጥሩን ያሳልጣሉ ያላቸውን ተሸከርካሪዎችና ግብዓቶችም ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስረክቧል፡፡  275 የሆኑ ዘመናዊ የትራፊክ ሞተር ብስክሌቶች፣ አራት ፒካፖች፣ ሁለት አምቡላንሶችና 26 ሚኒባሶች ናቸው፡፡ በከተማዋ የሚከሰተውን የመንገድ ትራፊክ አደጋ መከታተልና መቆጣጠር ብሎም መቅጣት የሚያስችል አፕልኬሽን የተጫነላቸው 100 ዘመናዊ ሞባይል ስልኮችም  ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተበርክቷል፡፡ በዕለቱ ከባለድርሻ አካላት መካከል የሆነው የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲም ተወካዮቹን ልኮ ነበር፡፡ ኤጀንሲው የትራፊክ ደኅንነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ትልቅ ሚና ያላቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ከወራት በፊትም በ3.3 ሚሊዮን ብር ወጪ የአልኮል መጠን መለኪያ መሣሪያዎች ግዥ በመፈጸም በተመረጡት ቦታዎች ማሠራጨቱ አይዘነጋም፡፡ ከትራፊክ ደኅንነት አንፃር ችግር በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ሻሂዳ ሁሴን የኤጀንሲውን  ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጅሬኛ ሂርጳን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- በከተማዋ ትራፊክ ፖሊሶች ተንቀሳቅሰው የሚሠሩባቸው ምን ያህል ተሽከርካሪዎች አሉ?

አቶ ጅሬኛ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ወደ 1,000 የሚሆኑ ትራፊክ ፖሊሶች አሉ፡፡ ነገር ግን ይህ የሰው ኃይል ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ይቸገራል፡፡ ተሽከርካሪዎች ላሉት አባላቶች ቀርቶ ለትራፊክ ፖሊስ ኮማንደሮች እንኳ አይደርሱም፡፡ በከተማዋ ትልቅ ማኅበራዊ ችግር የሆነውን የትራፊክ አደጋ ባለው የፖሊስ ኃይል እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ መቆጣጠር ባይቻልም፣ የተለያዩ አደጋውን መቀነስ የሚችሉ አማራጮችን እየተጠቀምን እንገኛለን፡፡ ጠጥቶ ማሽከርከርን ለመቆጣጠር 20 የሚሆኑ የፍጥነት ራዳሮች ገንብተናል፣ የአልኮል መጠንን በትንፋሽ መለካት የሚችሉ መሣሪያዎችን ገዝተን አከፋፍለናል፡፡ እንዴት ተደርጎ ነው ቁጥጥር የሚደረገው? የትራፊክ አደጋ የሚቀነሰው? ፖሊሶች እንዴት ቢሠሩ ነው ያለውን የመንገድ ደኅንነት ችግር መቅረፍ የሚቻለው? የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ በሌሎች ጉዳዮችም ዙሪያ እንዲሁ ተባብረን እየሠራን ነው፡፡ ይህም የትራፊክ አደጋን በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ ዘንድሮ በከተማዋ የሚከሰተውን የሞት አደጋ በአምስት በመቶ መቀነስ ችለናል፡፡ በትራፊክ አደጋ ይሞቱ የነበሩ 21 ሰዎችን ታድገናል ማለት ነው፡፡ በየዓመቱ በስድስት በመቶ እየጨመረ የሚሄደውን በትራፊክ አደጋ የሚከሰተውን ሞት በአምስት በሞቶ መቀነስ ትልቅ ነገር ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ቀንሶ አያውቅም፡፡ ይህ ለእኛ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይህንን ስኬት ማስመዝገብ የተቻለውም ተቋማት በጋራ መሥራት በመቻላቸው ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከመንገድ ጥገና ጋር በተያያዘ እንዲሁም ግንባታን በተመለከተ ተናቦ የመሥራት ችግር ግን በስፋት ይታያል፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ጅሬኛ፡- አለመቀናጀቱ ሰፍቶ የሚታየው በቢሮ ደረጃ ባሉ መሥሪያ ቤቶች ጋር ሳይሆን ውኃ፣ መብራት፣ ስልክና ሌሎችም አገልግሎቶችን ከሚያቀርቡ ድርጅቶች ጋር ነው፡፡ ተቀናጅተው በጋራ ፕላን ካላወጡለት በከፍተኛ የገንዘብ ብድሮች የሚሠሩ የመሠረተ ልማቶች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እንዲያመዝን ይሆናል፡፡ የዚች ደሃ አገር ሀብት በጥንቃቄ ነው ሥራ ላይ መዋል ያለበት፡፡ 

ሪፖርተር፡- በከተማዋ ያሉ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ መንገዶችስ ምን ያህል በቂ ናቸው?

አቶ ጅሬኛ፡- በዚህ ረገድ ያለው ችግር ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ከተማችን ስታድግ በዘፈቀደ እንጂ በፕላን አይደለም፡፡ የመንገዶቻችን ስፋትን፣ ሕንፃዎች ከመንገዶች ምን ያህል መራቅ እንዳለባቸውና የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን በተመለከተ ተጠንቶ አይሠራም፡፡ ለምሳሌ መንገድ ለእንቅስቃሴ እንጂ ለፓርኪንግ ተብሎ አይገነባም፡፡ ስለዚህም መኪኖች ፓርክ ሲደረጉ ለእንቅስቃሴ ቦታ እንዲጠፋ እየሆነ ነው፡፡ ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ ሥርዓት የእግረኞች፣ የፓርኪንግ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት ፓርኪንግን ያካተተ ነው፡፡ በእኛ አገር ያለው ዕድገት በፕላን ተስተካክሎ ጥናትን መሠረት አድርጎ ባለመሆኑ ትልቅ የትራፊክ አስተዳደር ችግር ሆኖብናል፡፡ ኤጀንሲው እነዚህ ተፅዕኖዎች የሚፈጥሩትን ጫና ለመቀነስ ነው የሚሠራው፡፡ በእኛ አገር እኮ የትራፊክ ደንብ ጥሰቶች እንደ ጥፋት ሳይሆን እንደተለመደ ተራ ድርጊት ነው የሚታዩት፡፡ ሕጎች ተከብረው ስለማያውቁ ማኅበረሰቡ ሕግን መጣስ ለምዷል፡፡ የእግረኛ መሻገሪያ መንገድ ላይ መኪና ማቆም ተለምዷል፡፡ እየተቀጡበትም አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነት ባህል ስለሚፈጠር ነው ችግር እየበዛ ያለው፡፡ እኛ ይህንን ለመቀነስ ነው እየሠራን ያለው፡፡ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ደግሞ መንገዶች የፈጣን መንገዶች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ምንን መሠረት አድርገው ነው የሚገቡት የሚለውንም ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ እግረኛም ተሽከርካሪም ተቀላቅሎ ቢንቀሳቀስባቸው ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ረዘም ያሉ ኪሎ ሜትሮችን እግረኛው በእግሩ መሄድ የሚገደድባቸው መንገዶች ላይ የእግረኛ መንገዶች መገንባት አለባቸው፡፡ በተጨማሪም ማዞሪያ ቦታዎች፣ መታጠፊያዎችና የመሳሰሉትን መቀነስ ግድ ይላል፡፡ መጋጠሚያ መንገዶች ጋር ያለውን የመብራት ችግር ለእግረኞች ተገቢን መሻገሪያ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡ የቀለበት መንገዶች ላይ የሚገነባው አጥር በራሱ ሰዎች እንዲሻገሩበት የሚፈቅድ ነው ይኸም መሻሻል አለበት፡፡  

ሪፖርተር፡- የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን የማዘጋጀት ሥራ በስፋት መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ምን ያህሉ ተጠናቀው ወደ ሥራ ተገብቷል?

አቶ ጅሬኛ፡- በከተማዋ ወደ 60 የሚሆኑ ቦታዎች ለፓርኪንግ ተብለው ተለይተዋል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች የተለያዩ ግንባታዎችም ተጀምረዋል፡፡ ለምሳሌ መገናኛ አካባቢ የተገነባው ስማርት ፓርኪንግ ሥራ ጀምሯል፡፡ መገናኛን የመረጥነውም በርካታ ሰዎች ላይ ታች ሲሉ የሚውሉበት ስትራቴጂክ ቦታ በመሆኑ ነው፡፡ እዚሁ ከመገናኛ ሳንወጣ ሌላ ተጨማሪ ሰርፌስ ፓርኪንግ እየተገነባ ነው፡፡ መርካቶና ወሎ ሠፈርም እንዲሁ እየተሠራ ነው፡፡ መኰንን ድልድይ አካባቢም ስማርት ፓርኪንግ በዚህ ዓመት እንጀምራለን ብለን እናስባለን፡፡ ከመሬት ይዞታ ጋር በተያያዘ ያሉትን ሥራዎችንም አጠናቀናል፡፡ ስማርት ፓርኪንጎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስመጣት የውጭ ምንዛሪ ችግር አለ፡፡ ሌላው ትልቁ ችግር ግን መንግሥት የፓርኪንግ ቦታዎችን አልምቶ ማዳረስ አይችልም፡፡ እያንዳንዱ ሰው ሕንፃ ሲገነባ በቂ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ወደ ላይ 12 ፎቅ ያለው ሕንፃ ሲገነባ ተጠቃሚዎቹንም ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡ ወደ ሕንፃው የሚያስገባቸውን ደንበኞች መኪና መንገድ አይችላቸውም፡፡ ሪፖርተር፡- ጉቦ የሚሰጡ አሽከርካሪዎችም ሆኑ ትራፊክ ፖሊሶች የሚቀጡበት ጠንካራ አሠራር አለ?

አቶ ጅሬኛ፡- ማንኛውም ሰው ከጠቆመና በማስረጃ ሲረጋገጥ አጥፊው በሕግ ይቀጣል፡፡ ከሕግ ውጭ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ያልተገባ ነገር የሚፈጽም ሁሉ መቀጣት አለበት፡፡ በዚህ ረገድ በመረጃ ጥፋተኛ መሆናቸው በተረጋገጠባቸው አባላት በየጊዜው ዕርምጃ እንደሚወሰድም አውቃለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተሠራ ያለው ግን የትራፊክ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡ አሠራሩም ራሱን የቻለ ሥርዓት እንዲከተል ማድረግ ላይም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ ለምሳሌ በመጪው ዓመት ተግባራዊ የሚደረግ ‹‹ፖይንት ፔናሊቲ ሲስተም›› የሚባል አሠራር አለ፡፡ ይህ አሠራር ትራፊክ ፖሊሱ በእጁ የሚይዘው ሬዲዮ ይኖራል፡፡ አሽከርካሪዎችን ሲያናግር ሬዲዮኑን ያበራል፡፡ ሬዲዮውን አብርቶ ቅጣት ሲሰጥ እሱን የሚከታተለው አካል ሁሉንም ሒደት ይመዘግባል ማለት ነው፡፡ ለትራፊኮች አዲስ የታደሉ ወደ 100 የሚሆኑ ሞባይሎችም አሉ፡፡ ቅጣት የሚመዘግቡት በስልኩ ሲሆን፣ አንድ ጊዜ ከመዘገቡ በኋላ መልሰው ማጥፋት አይችሉም፡፡ ወደ ኋላ መመለስ ቢፈልግ ራሱ ለአለቆቹ በቂ ምክንያት ተናግሮ አሳምኖ እንጂ እዚያው ተደራድሮ መቀየር አይችልም፡፡ ዋናው ነገር ከተማዋ በጣም ሰፊ ነች፣ በጣም ብዙ የትራፊክ ጥሰቶች ይሠራሉ፣ ፖሊሶች ግን በዚያ መጠን ተደራሽ አይደሉም፡፡ ሁሉንም ጥሰት መከታተል ስለማይችሉ እየመረጡ ነው የሚሠሩት፡፡ ስለዚህም የአባላቱን ቁጥር ማብዛት፣ አስፈላጊ የሆኑ ተሽከርካሪዎችና ቁሳቁሶችን ማሟላት ግድ ይላል፡፡ አንድ ሰው በተሽከርካሪ መንቀሳቀስ ሲጀምር ብዙ ቦታዎችን መሸፈን እንደሚችል ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡ ተገቢውን ሥራ ለመሥራትም የአባላቱ መልካም ባህሪ ወሳኝ ስለሆነ እዚህ ላይም ሥራ ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ ማኅብረሰቡ ራሱ ሙስናን የሚፀየፍ ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ ጉቦ የወሰደው ብቻ ሳይሆን ሰጪውም እኮ ሌባ ነው፡፡ ሰጪ ቢከስ ተቀባይ አይኖርም፡፡ ከዚህ ባሻገርም በፖሊሲ ላይ ብቻ የተመሠረተ የትራፊክ ቁጥጥር መከተልም የለብንም፡፡ ሌሎች አገሮች የሚጠቀሟቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እያስገቡ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሲሲቲቪ ካሜራዎችን በመጠቀም ደንብ የሚጥሱ እግረኞችን ለይቶ የሚያወጣ፣ ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ የሚያሽከረክሩትን ሰሌዳቸውን በፎቶግራፍ በማስቀረት ቅጣት ያሉበት ድረስ ወስዶ መስጠት የሚያስችሉ ቴከኖሎጂዎችን ወደ መጠቀም መሄድ አለብን፡፡  

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ እስከ 40 ዓመታት ድረስ የሠሩና ከጥቅም ውጭ የሆኑ መኪኖች ጎማቸው ስለተሽከረከረ ብቻ ሲነዱ ይታያል፡፡ ይህ በትራፊክ ደኅንነት ላይ ምን ያህል ሥጋት ነው? ምንስ መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ ጅሬኛ፡- ይህ እስካሁን በበቂ ያልተሠራበት ትልቅ ችግር ነው፡፡ ከውጭ የምናስገባው በብዛት አሮጌ መኪኖችን ነው፡፡ መሪያቸው ራሱ ከግራ ወደ ቀኝ የዞረላቸው መኪኖች ሁሉ ይሸጣሉ፡፡ ይህ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ የምናየው ነው፡፡ መኪና በቦታ አይወሰንም የትም ይንቀሳቀሳል፡፡ ስለዚህም ደንብና ስታንዳርድ ወጥቶ በዕድሜ እንኳ ባይሆን ማሟላት ያለባቸው ብቃቶችን በማውጣት ከደረጃ በታች የሚሆኑ ከመንገድ የሚወጡበት አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡ በየጊዜው ቦሎ ሲያሳድሱ የሚታየው ዋና ነገር እኮ ይኼ ነበር፡፡ ይሁንና በትክክል ስለማይሠራ ከደረጃ በታች የሆኑ ተሽከርካሪዎች ሁሉ ፍቃድ ያገኛሉ፡፡ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ባለሥልጣን የተወሰኑ መኪኖችን ከመንገድ እንዲወጡ አድርጓል፡፡ በማስጠንቀቂያ የታለፉም አሉ፡፡ ዋናው ነገር ይህን ችግር በአንዴ ማጥፋት አይቻልም፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን አሮጌ መኪኖች ከመንገድ መውጣት አለባቸው፡፡ ሌላው ቢቀር አሮጌ መኪኖች የሚንቀሳቀሱበት መንገድ መለየት አለበት፡፡ በሰዓት 30 ኪሎ ሜትር መጓዝ የማይችል መኪና የፍጥነት መንገድ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ኤክስፕረስ መንገድ ላይ ሁሉ ይገባል፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሁሉ መታየት አለባቸው፡፡ ያገለገሉ መኪኖች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡም ጉሙሩክ መቆጣጠር አለበት እኮ፡፡ የዋጋቸውን መርከስ ብቻ ሳይሆን ቆይተው ዋጋ እንደሚያስከፍሉና ከባቢ አየር እንደሚበክሉ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ኤጀንሲው በ2011 ዓ.ም. ለመተግበር ያቀዳቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ምንድናቸው?

አቶ ጅሬኛ፡- በ2011 ዓ.ም. 31 መጋጠሚያዎች መብራት ይተከልላቸዋል፡፡ የፍጥነት ቁጥጥርና ጠጥቶ ማሽከርከርን ለማስቀረት የሚደረገው ሥራም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ 130 ኪሎ ሜትር መንገድ ላይም የፍጥነት ምልክት በ2010 ዓ.ም. የተደረገ ሲሆን፣ በመጪው ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የፍጥነት መቀነሻ ግንባታዎችም እንዲሁ የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡ መንገድ ጥገናም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ሌላው ብዙ ሰዎች የሚሞቱት ሌሊት በሚደርስ አደጋ ነው፡፡ ስለዚህም የመንገድ ዳር መብራቶችን ማስጠገን ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል፡፡ የእግረኛ መሻገሪያ መንገዶችም በሰፊው ይሠራሉ፡፡ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ እያስከተሉ ያሉት የንግድ ተሽከርካሪዎች፣ ባሶች፣ ሚኒባሶች፣ ሲኖትራኮችና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ ሰፊ ጥናት አካሂደን ለፖሊሲና ለትግበራ የሚሆኑ ሐሳቦችንም ለመስጠት አቅደናል፡፡