Skip to main content
x
ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ እስራት ፈርቶ የተደበቀ ጓደኛቸው ደወለላቸው

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ እስራት ፈርቶ የተደበቀ ጓደኛቸው ደወለላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ምነው የተጨናነቅክ ትመስላለህ?
 • ምን እባክሽ እኔ መቼ ጭንቅላቴ ያርፋል ብለሽ ነው?
 • ምን ሆንክ ደግሞ?
 • ያው ጊዜው የለውጥ ስለሆነ እኔም በብዙ ነገር ለመለወጥ እያሰብኩ ነው፡፡
 • በምንድነው ደግሞ የምትለወጠው?
 • ከለውጡ ጋር ቢዝነሶቻችንንም መለወጥ አለብን፡፡
 • ያሉን ቢዝነሶቻችን ምን አሉን?
 • ያሉን ቢዝነሶችማ ከዚህ በኋላ ሊቀጥሉ የማይችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ እኮ ነው፡፡
 • ለምንድነው የማይቀጥሉት?
 • አገሪቱ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ አታውቂም?
 • መደመር፣ መቀነስ ምናምን ነዋ እየተካሄደ ያለው፡፡
 • አየሽ የሚቀነሱ ነገሮች አሉ ማለት ነው፡፡
 • ታዲያ እኛ ምን አገባን?
 • ስሚ እኛ የምንሠራቸው ቢዝነሶች በጠቅላላ ሕገወጥ መሆናቸውን አትርሺ፡፡
 • እኔና አንተ መቼ ሕጋዊ ሥራ ሠርተን እናውቃለን?
 • አሁን ብዙ ሕገወጥ ነገሮች እየቆሙ ስለሆነ እኛም ቆም ብለን ማሰብ አለብን፡፡
 • በፍፁም እንዳትሳሳት፡፡
 • ምን እያልሽ ነው?
 • አሁን እንዲያውም ብዙ ሕገወጥ ድርጊቶች እየበዙ ነው የመጡት፡፡
 • ሴትዮ ከተማ ውስጥ የለሽም እንዴ?
 • በሚገባ አለሁ እንጂ፡፡
 • ታዲያ የኮንትሮባንድ ንግዱ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተመታ እኮ ነው፡፡
 • ቢመታስ ታዲያ?
 • እኛም ቢዝነሳችንን ሳንቀይር በዚሁ ከቀጠልን ዜሮ መግባታችን ነው፡፡
 • እኔ ግን ምንም አያሳስበኝም፡፡
 • ስንትና ስንት ሰው መቀመቅ ውስጥ እየገባ ነው፡፡
 • እኛ ምን ቸገረን አማራጭ ቢዝነሶች አሉን እኮ?
 • አማራጭ ቢዝነሳችንም ሕገወጥ እንደሆነ አታውቂም?
 • ምኑ ነው ሕገወጥ?
 • የዶላር ምንዛሪ እኔ ሳላውቅ ሕጋዊ ሆኗል እንዴ?
 • ከእሱ ይልቅ የሚያሳስበኝ በዶላር መውደቅ የከሰርነው ነው፡፡
 • ለዚህ እኮ ነው በሁሉም ዘርፍ ቢዝነስ ይኑረን የምልሽ?
 • አሁን የቢዝነስ ሐሳብ መጥቶልህ ነው?
 • አዎን ግን እንዴት ተግባራዊ እንደምናደርገው ግራ አጋብቶኝ ነው?
 • ቢዝነሱ አሪፍ ከሆነማ ቶሎ ፈቃድ አውጥተን ወደ ሥራ መግባት ነዋ፡፡
 • እኔ እሱ አይደል እንዴ የጨነቀኝ?
 • ምኑ ነው የጨነቀህ?
 • እኛ ሕጋዊ ፈቃድ አውጥተን ቢዝነስ ሠርተን ስለማናውቅ፣ አዲሱ የቢዝነስ ሐሳቤን እንዴት ተግባራዊ እናደርገዋለን ብዬ ነዋ?
 • ስማ እሱ በጣም ቀላል ነው፡፡
 • ለቢዝነሱ እኮ ጠቀም ያለ ገንዘብ ያስፈልገናል፡፡
 • ስለዚህ የቢዝነስ ሐሳቡን ለባለሀብቶች አቅርበን በሽርክና እንሠራለና፡፡
 • እስከ ዛሬ ከእኔ ጋር ቢዝነስ መሥራት የቻለው ያ ደላላ ብቻ እንደሆነ ታውቂያለሽ እሱም ከእርስዎ ጋር ቢዝነስ ከመሥራት ከሰይጣን ጋር መሥራት ቀላል ነው እንዳለኝ መቼም ታስታውሻለሽ፡፡
 • ካልሆነ ደግሞ አክሲዮን መሸጥ ነዋ፡፡
 • ከእኔ ጋር ቢዝነስ መሥራት ማንም አይፈልግም አልኩሽ እኮ?
 • ታዲያ ለምን ከባንክ አንበደርም?
 • ከባንክ ለመበደር ደግሞ ኮላተራል ያስፈልገናል፡፡
 • ከዚህ ሁሉ ቤት በአንዱ እንበደርበታ?
 • ምን ነካሽ ሀብታችንማ መታወቅ የለበትም፡፡
 • ምን ይሻላል ታዲያ?
 • እኔማ አንድ ሐሳብ መጥቶልኛል፡፡
 • ምን ዓይነት ሐሳብ?
 • አንድ ፕሮግራም ማዘጋጀት ፈልጌያለሁ፡፡
 • ምን ዓይነት ፕሮግራም?
 • ገቢ ማሰባሰቢያ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ኢንቨስተር ይደውልላቸዋል]

 • ክቡር ሚኒስትር ምን እየተካሄደ ነው ያለው?
 • ምን ሆንክ?
 • እኔ በዚች አገር ብዙ ተስፋ ነበረኝ፡፡
 • አገሪቱማ ለዓለም ሳይቀር ተስፋ ናት፡፡
 • አሁንማ በጣም ተስፋ እያስቆረጠችኝ ነው፡፡
 • በምን ምክንያት?
 • እየሄድንበት ያለው ጎዳና በጣም እያስፈራኝ ነው፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ እኮ ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደች ነው፡፡
 • ምነው እንደዚህ ጨለምተኛ ሆንክ?
 • በምድሪቷ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ ስመለከት እንዴት ጨለምተኛ አልሆን?
 • አልተደመርክም ማለት ነው?
 • እኔማ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በፊት ነው የተደመርኩት፡፡
 • ምን አልክ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ዕድሜዬን ሙሉ በውጭ አገር ያፈራሁትን ጥሪት አገሬ ካፈሰስኩ በርካታ ዓመታት ሆነውኛል፡፡
 • እሱን ማድረግህማ ጥሩ ነው፡፡
 • ይኸው አገሬን ለማልማት ፋብሪካ ከፍቼ ከአንድ ሺሕ በላይ ሠራተኞችን ቀጥሬ ማሠራት ከጀመርኩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
 • ታዲያ ለምንድን ነው የምትማረረው?
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን ግን ምንም ሥራ መሥራት አልቻልኩም፡፡
 • የዶላር እጥረት ገጥሞህ ነው?
 • ከዶላሩ ይልቅ ያስቸገሩኝ የአካባቢው ወጣቶች ናቸው፡፡
 • እነሱ ደግሞ ምን አደረጉህ?
 • ክቡር ሚኒስትር በየጊዜው እየመጡ ሥራ እንድሰጣቸው ይጠይቁኛል፡፡
 • ታዲያ ለምን አትሰጣቸውም?
 • አንድ ሺሕ ሰው መቅጠር ቀላል ነገር ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እሱማ አይደለም፡፡
 • ከዚህ በላይ ታዲያ እኔ ምን ላድርግ?
 • ቦታ የለኝም ስትላቸው ምን ይሉሃል?
 • ባንሠራም ክፈለን ይሉኛል፡፡
 • እነዚህማ ወጣት ጡረተኞች ናቸው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ችግሩን ለአካባቢው አስተዳደር ባሳውቅም መፍትሔ ላገኝ አልቻልኩም፡፡
 • እንደ አንተ ዓይነት ኢንቨስተርማ ሊደናቀፍ አይገባም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እንደዚህ የምቸገረው እኔ ብቻ ሳልሆን በርካቶች ናቸው፡፡
 • ይኼማ ተቀባይነት የለውም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር መደመርና ፍቅር ወደ ሥራ ካልተቀየረ ዋጋ የለውም፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • እንደመር ሲባል ሁሉም ባለው አቅምና ዕውቀት አገሩን ማገልገል ካልቻለ ወደፊት መሄድ አንችልም፡፡
 • እሱስ ልክ ነህ፡፡
 • ስለዚህ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡
 • ለአንተማ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥህ አደርጋለሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር መፍትሔው ጊዜያዊ ሳይሆን ዘለቄታዊ መሆን ይገባዋል፡፡
 • ምን ዓይነት ዘለቄታዊ መፍትሔ?
 • በአገሪቱ ውስጥ የሰፈነው ሥርዓተ አልበኝነት የሚወገደው አሠራራችን መቀየር ስንችል ነው፡፡
 • ወደ ምን?
 • ወደ ተቋማዊ አሠራር፡፡
 • በሚገባ እስማማለሁ፡፡
 • ያበለዚያ ባለሀብቱ ከመደመር ይልቅ የሚመርጠው ሌላ ነው፡፡
 • ምን?
 • መደንበር!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር ያለንበት ወቅት በጣም አደገኛ ነው፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • በቅርቡ አሰሳ እንደሚጀመር አልሰሙም?
 • የምን አሰሳ ነው?
 • በሕገወጥ ገንዘብ ላይ ፍተሻ ይካሄዳል፡፡
 • ገንዘብህን ለምን ወደ ዶላር አትቀይረውም?
 • ክቡር ሚኒስትር ዶላርም ይዞ መገኘት እኮ ሕገወጥ ነው፣ በዚያ ላይ ዶላር አሁን ስለወረደ እስኪወጣ እየጠበቅኩ ነው፡፡
 • ከዚህ በኋላማ እንደ ድሮው ዶላር ይሰቀላል ብለህ አትጠብቅ፡፡
 • እኔ ተስፋ አልቆርጥም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ላም አለኝ በሰማይ እንዳይሆንብህ?
 • ለማንኛውም በርካታ ሰዎች ይህ ጉዳይ እያሳሰባቸው ነው፡፡
 • ምኑ ነው ያሳሰባቸው?
 • ገንዘባችንን የት እናድርገው የሚለው ጉዳይ ነዋ፡፡
 • ባንክ ቤት ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይህን ሁሉ ሚሊዮን ብር ባንክ ከሚከቱ በቀጥታ እጃቸውን ለፖሊስ ቢሰጡ አይቀልም?
 • ምን እያልክ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ይህን ያህል ገንዘብ ባንክ ዝም ብሎ አይቀበልም፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • ገንዘቡ የቆሸሸ ነዋ፡፡
 • ታዲያ ገንዘቡን ማጠብ ነዋ፡፡
 • ለዚያ አይደል እንዴ እኛን የሚፈልጉን፡፡
 • ገንዘቡን እንድናጥብላቸው?
 • እህሳ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን ያን ሁሉ ሚሊዮን ብር ማን ነው የሚያጥብልን?
 • ካሰብንበትማ ገንዘቡን ማጠብ ቀላል ነው፡፡
 • ምንድነው የምታወራው ሰውዬ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ያን ሁሉ ገንዘብ ለማጠብ ምን ያህል ኦሞ እንደሚፈጅ ታውቃለህ?
 • እ. . .
 • እና ይኼን ሁሉ ገንዘብ ማጠብ ከባድ ሥራ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ስለ Money Laundering ነው የማወራዎት፡፡
 • ገብቶኛል፡፡
 • አሪፍ ጥቅም እናገኝበታለን እኮ፡፡
 • እንዲያ ካልክማ በአፋጣኝ እናቋቁማ፡፡
 • ምን?
 • ላውንድሪ ቤት!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ እስራት ፈርቶ የተደበቀ ጓደኛቸው ደወለላቸው]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ልበል?
 • በድምፄ እንኳን አላስታወሱኝም?
 • ይቅርታ አላወቅኩህም፡፡
 • ወዳጅዎ ነኝ፡፡
 • ስልክህን ቀየርክ እንዴ?
 • የበፊቱን ስልኬንማ ቆረጡብኝ፡፡
 • ለመሆኑ ከአገር ወጥተህ ነው የጠፋኸው?
 • ተሳክቶልኝ ብወጣማ ተገላግለዬ ነበር፡፡
 • ታዲያ የት ጠፍተህ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ይኸው ፈርቼ ከተደበቅኩ እኮ ወራት ተቆጠሩ፡፡
 • ለምንድነው የምትፈራው?
 • ካሁን አሁን ወይ እታሰራለሁ ወይ ጥቃት ይደርስብኛል ብዬ ፈርቼ ነው ያለሁት፡፡
 • በዚህ የምሕረትና የይቅርታ ዘመን እንደዚህ ለምን ታስባለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ከፍተኛ ወንጀል በመሥራቴ ማንም ይቅርታ አያደርግልኝም፡፡
 • ቆይ ተገናኝተን ለምን ሻይ እየጠጣን አናወራም?
 • ኧረ እኔ የትም መንቀሳቀስ አልችልም፡፡
 • ራስህን የቁም እስረኛ አድርገሃል ማለት ነው?
 • ምን አማራጭ አለኝ?
 • አማራጩማ መደመር ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ምን እንደሚጠብቀኝ አውቀዋለሁ፡፡
 • ምንድን ነው የሚጠብቅህ?
 • በቅርቡ ሙዚየም የሆነ ቦታ ነዋ፡፡
 • የት ነው?
 • ማዕከላዊ!