Skip to main content
x
‹‹የኢትዮጵያን ችግር ለመቅረፍ ኢትዮጵያዊ ሥርዓተ ትምህርት ያስፈልጋል››

‹‹የኢትዮጵያን ችግር ለመቅረፍ ኢትዮጵያዊ ሥርዓተ ትምህርት ያስፈልጋል››

ዶ/ር ዳምጠው ወልደ ማርያም፣ በጃፓይጎ የጤና ዘርፍ የሰው ሀብት ልማት ፕሮጀክት ዳይሬክተር

ዶ/ር ዳምጠው ወልደ ማርያም የጃፓይጎ ከሚተገብራቸው ፕሮጀክቶች መካከል የሆነው በጤናው ዘርፍ የሰው ሀብት ልማት ላይ አተኩሮ የሚሠራው ፕሮጀክት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ጃፓይጎ መቀመጫውን በባልቲሞር ያደረገ የጆንሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አካል የሆነ ግብረ ሰናይ ተቋም ነው፡፡ ከተቋቋመ ከ45 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፣ 150 አገሮች ላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያም እ.ኤ.አ. ከ2003 ጀምሮ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን እየሠራ ይገኛል፡፡ የፕሮጀክቶቹ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን መንግሥት አቅም ማጎልበትና ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረጉ ከሚገኙ ፕሮጀክቶቹ መካከል ዶ/ር ዳምጠው የሚመሩት አንዱ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱን እንቅስቃሴና በጤና ዘርፉ ያሉ ከሰው ኃይል ጋር የተያያዙ ክፍተቶችን በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ጃፓይጎ ለኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ የሚያደርገው በምን በምን ጉዳዮች ላይ ነው?

ዶ/ር ዳምጠው፡- እኔ በኃላፊነት የምመራውን ፕሮግራምን ምሳሌ አድርጌ ላስረዳሽ፡፡ የሰው ሀብት ልማት ፕሮጀክት አራት ዓላማዎችን ሰንቆ የያዘ ነው፡፡ የመጀመርያ ዓላማ የአመራር አቅም ማጎልበት ነው፡፡ ከፌዴራል ጤና ጥበቃ ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉትን የአመራር አካላት አቅም ለማጎልበት የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ በጤናው ዘርፍ ያሉ የአመራር አካላት ዕውቀት ክህሎት እንዲኖራቸውም እገዛ ያደርጋል፡፡  ከሠራቸው ሥራዎች አንዱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን የ11ዱን የጤና ቢሮዎች፣ የምግብ፣ የመድኃኒት ጤና ክብካቤ ቁጥጥር አስተዳደር ባለሥልጣንና ሁለት የሙያ ማኅበራትን ማለትም የኢትዮጵያ አዋላጅ ነርሶች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማኅበር ምን ዓይነት የአመራር ችግር አለባቸው? የችግሩ ግዝፈትስ ምን ያህል ነው? በሚል የዳሰሳ ጥናት አደረግን፡፡ በጥናቱ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ለየን፡፡ የተገኙት ችግሮች የሚወገዱባቸው የሦስት ዓመት ዕቅድ በጋራ አዘጋጅተን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ችግሮቹ እንዲወገዱ የእኛ ፕሮጀክት እስካሁን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡  

ሪፖርተር፡- በዳሰሳ ጥናታችሁ የተለዩ ችግሮች ምንድናቸው?

ዶ/ር ዳምጠው፡- ለምሳሌ በቂ የሆነ የተማረ አመራር ሊሰጥ የሚችል ባለሙያ በቦታው አለመኖር፡፡ ዕቅድ ያለማውጣት ችግሮች ታይተዋል፡፡ እነዚህን ለመቅረፍ ተከታታይነት ያለው ሥልጠና በመስጠት፣ ቁጥጥር በማድረግ፣ የቴክኒካልና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እንዲወገዱ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ ሲቀረፅ የመነሻ ጥናት ሠርተን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በማኔጅመንት የተመረቁ በርካታ ባለሙያዎች ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በጤና ማኔጅመንት ወይም በሒውማን ሪሶርስ ፎር ሔልዝ ማኔጅመንት የተመረቁ ባለሙያዎች አልነበሩም፡፡ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች በብዛት አሉ ግን በሔልዝ ኢኮኖሚክስ የተመረቁ በብዛት አልነበሩም፡፡ እነዚህ የትምህርት ዘርፎች እንዲጀመሩ አድርገናል፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በአዲስ አበባ ኮንቲኔንታል ኢንስቲትዩሽን ኦፍ ፐብሊክ ሔልዝ ሠራተኞች እየሠሩ በርቀት የትምህርት ፕሮግራም በድኅረ ምረቃ እንዲሠለጥኑ አድርገናል፡፡ የመጀመርያው ሁለት ተመራቂዎችም ከሀቻምና ጀምሮ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ጃፓይጎ የዚህ ሐሳብ አመንጪ ሆኖ፣ አስፈላጊነቱ ላይ አሳምኖ ፕሮግራሞቹ እንዲጀመሩ አስቻለ እንጂ ከዚህ በኋላ የእኛ ፕሮጀክት ኖረም አልኖረ ቀጣይነት የሚኖራቸው የመንግሥት ፕሮግራሞች ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተመረቁ ተማሪዎች ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ወደፊትም እንደ አስፈላጊነቱ ይመደባሉ፡፡ በቂ የአመራር ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች እጥረት ለማሻሻል በሰው ኃይል ማኔጅመንት የሥልጠና መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ ከ2,500 በላይ የሚሆኑ አመራሮች አጭር ሥልጠና ወስደዋል፡፡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሥልጠና መመርያ እንዲወጣና ካሪኩለም እንዲቀረፅ አድርጓል፡፡ ጥናቱን በምናደርግበት ወቅት በዞንና በወረዳ በሚገኙ ትልልቅ ሆስፒታሎች ለሥራ ተመጣጣኝነት ያለው የሰው ኃይል መዋቅር አልነበርም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ መዋቅሩ ኖሮ ባለሙያ አልነበረም፡፡ አንዳንዶቹ ላይ ደግሞ በመንግሥት ፈቃድ የተሰጠው መደብ አልነበረም፡፡ ይህንን መቅረፍ የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለውን ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ወደ 1,300 የሚሆኑ አዳዲስ መዋቅሮች እንዲፈጠሩ አድርገናል፡፡ በተዘጋጁት 1,300 መዋቅሮች 96 በመቶ በሚሆኑት ምደባ ተደርጓል፡፡ ፕሮጀክቱ (ጃፓይጎ) ኖረም አልኖረም የተሠሩ ሥራዎች ቀጣይነት ያላቸው ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በጤናው ዘርፍ ካሉ ትልልቅ ችግሮች መካከል የጤና ባለሙያው ከጠቅላላው ሕዝብ አንፃር ሲታይ እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ላይ ጃፓይጎ ምን እያደረገ ነው?

ዶ/ር ዳምጠው፡- እናቶችን በጤና ማዕከላት ማዋለድ፣ ጠንከር ያለ የክትባት መርሐ ግብር መስጠት የመሳሰሉ መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ማድረስ ላይ ያተኮሩ ግቦችን የዓለም ጤና ድርጅት የምዕት ዓመቱ ግቦች ናቸው፡፡ መሰል አገልግሎቶችን ለመስጠትም መኖር ያለባቸውን የባለሙያዎች ቁጥር ከሕዝብ ብዛት አንፃር አስቀምጧል፡፡ ለምሳሌ ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ለ1,000 ሰዎች 2.3 ዶክተሮች፣ ነርሶችና አዋላጅ ነርሶች እንደሚያስፈልጉ ተቀምጧል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2002 የእኛ ፕሮጀክት ሲቀረፅ ይህ ቁጥር ከአንድ በታች ነበር፡፡ ስለዚህ 2.3 ማለት በጣም የተለጠጠ ትልቅ ቁጥር አይደለም፡፡ ከሰሃራ በታች ላሉ አገሮች ተብሎ የተቀመጠ ነው፡፡ እኛ ግን እዚያ አልደረስንም በአሁኑ ወቅትም ወደ 1.6 እየተጠጋን ነው ያለው፡፡ የእኛ ፕሮጀክት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ወደ 37 ሺሕ የሚሆኑ ባለሙያዎች እንዲመረቁ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ይህ ትልቁ ቁጥር ነው፡፡ ነገር ግን ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ባለበት አገር በቂ አይደለም፡፡ ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት ኃይል ሊጎለብት ይገባል፡፡ ተጨማሪ ሕክምና የሚያስተምሩ ሊኖሩ ይገባል፡፡ በአገሪቱ 84 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የሚኖረው በገጠር ነውና ሥርጭቱም ይህንን መሠረት ያደረገ መሆን ይገባዋል፡፡ ሕዝቡ ባለበት ሁሉ የጤና ባለሙያዎች የሚሰማሩበትና ብቃት ያለው አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡-  በርካቶች ሐኪም የመሆን ፍላጎት ባላቸው የኢትዮጵያ ምድር፣ ለዚህ የተዘጋጁ ኮሌጆች ባላነሱበት ሁኔታ ያለው የጤና ባለሙያ ቁጥር ውስንነት ከምን የመነጨ ነው?

ዶ/ር ዳምጠው፡- በአሁኑ ወቅት ያሉት ወደ 30 የሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች በሕክምና ትምህርት ያስመርቃሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው ሐኪም እሆናለሁ ስላለ ሐኪም ይሆናል ማለት አይደለም፣ ብቁ ሐኪም ይሆናል ማለትም አይደለም፡፡ ፍላጎት ያላቸው ጠንካሮች፣ በየጊዜው ራሳቸውን ማሻሻል የሚችሉና ብቁ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ በምልመላ ተለይተው ወደ ዩኒቨርሲቲ ይገባል፡፡ የሕክምና ትምህርት ሲባል የክፍል ትምህርት ብቻ አይደለም፡፡ ከፍተኛ ዕውቀት፣ ክህሎትና መልካም አመለካከት ይጠይቃል፡፡ ክህሎትና ጥሩ አመለካከት የሚቀረፀው በክፍል ትምህርት ብቻ ሳይሆን በተግባር ትምህርት ነው፡፡ ወጣት ሐኪሞች የተግባር ትምህርት የሚማሩት ከሆስፒታሎችና ከጤና ማሠልጠኛ ተቋማት ነው፡፡ ስለዚህም ዩኒቨርሲቲ ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ምቹና ዘመናዊ የሆነ፣ በሰው ኃይልና በመሣሪያ የተደራጀ የማስተማሪያ ሆስፒታሎች ያስፈልጓቸዋል፡፡ አንድ የማስተማሪያ ሆስፒታል ብቻ ሳይሆን በአካባቢያቸው የሚገኙ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎችን በማስተማሪያነት ሊጠቀሙ ይገባል፡፡ ይህ በአንድ ጀንበር የሚፈጸም ሳይሆን እየታቀደ በጀት እየተያዘ ዩኒቨርሲቲዎችን ማጎልበት፣ የቅበላ አቅም ከፍ ማድረግ፣ ቁጥር ብቻ ሳይሆን ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚችል ዕውቀት ያለው እንዲሆኑ ብዙ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በምዕት ዓመት ግቡ ያስቀመጠውን 2.3 ባለሙያ አሁን በዘላቂ የልማት ግቦች ወደ 4.5 ለ1,000 አድርጎታል፡፡ እዚህ ላይ ለመድረስ ኢትዮጵያ ብዙ መሥራት አለባት፡፡  

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የማስተማሪያ ሆስፒታሎች ያሏቸው የትኞቹ ናቸው?

ዶ/ር ዳምጠው፡- ሁሉም እንደዚያ ነው የሚያስተምሩት፡፡ ለምሳሌ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል አለ፡፡ እኔ ለረዥም ጊዜ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ነበርኩኝ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው ያሉትን ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ለማስተማሪያነት ይጠቀማል፡፡ አጋሮ ጤና ጣቢያ፣ አሰንዳቦ ጤና ጣቢያ፣ ሸቤ ጤና ጣቢያ፣ ሊሙ ሆስፒታልና የመሳሰሉት ላይ ፕሮግራም አውጥቶ ተማሪዎችን እየላከ ያስተምራል፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲም እንደዚሁ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ነው፡፡ ከዚያ ወጣ ብሎ ወደ ጠዳ ጤና ሳይስን ኮሌጅ፣ እስከ ደብረ ታቦር ወርዶ ተማሪዎችን እየላከ ያስተምራል፡፡ እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ቢቻል በሰው ኃይል፣ በመሣሪያና ሌሎች መሠረተ ልማት የተደራጀ የማስተማሪያ ሆስፒታል ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ተማሪዎች እስከ ጤና ጣቢያው ድረስ ዘልቀው በመግባት ትክክለኛ የማኅበረሰቡን ችግር ማወቅና ለችግሩ መፍትሔ መስጠት የሚችሉ ባለሙያዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸው ማስተማሪያ ሆስፒታሎች አላቸው፡፡ በዙሪያቸው ከሚገኙ ጋር ትስስር ፈጥረው እንዲሠሩ እኛም ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- የጤና አገልግሎት ጥራትን በተመለከተ ጃፓይጎ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ሥራ ካለ?

ዶ/ር ዳምጠው፡- የጃፓይጎ ሦስተኛው የፕሮጀክቱ ዓላማ ጥራት ማምጣት ነው፡፡ ጥራት ላይ በጣም መሠራት ይኖርበታል፡፡ እኛም የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ነው፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት እየሠራን ነው፡፡ ከተቋሙ ጋር በመተባበር የጤና ደረጃዎች እንዲወጡ አድርገናል፡፡ ለምሳሌ ለነርሲንግ ሥልጠና የሚያስፈልጉ ደረጃዎች ምንድናቸው? የሚለውን አውጥተናል፡፡ እነዚያን ደረጃዎች ለማሟላት ነው አንዲት ነርስ መማር ያለባት፡፡ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታና መመርያ ያገናዘበ ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ አንዲት ነርስ ተምራ ስትወጣ ምን ዓይነት ዕውቀትና አመለካከት ይዛ መውጣት አለባት? የሚለውን የሚያጣጥም ነው፡፡ ለአዋላጅ ነርሶችም እንደዚሁ ተመሳሳይ ደረጃ ወጥቷል፡፡ በሕክምናም እንዲሁ፡፡ በአጠቃላይ በሁሉም የጤና ሥልጠናዎች ደረጃ ተዘጋጀቷል፡፡ ለ52 ዩኒቨርሲቲና ኮሌጆችም የጤና ሳይንስ ትምህርት ልማት ማዕከል እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ የዚህ ማዕከል ዋና ሥራ እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ የሚሰጠው ሥልጠና ጥራት ያለው እንዲሆን በባለቤትነት ይሠራል፡፡ በየጊዜው የትምህርት ሥርዓቱን ይገመግማል፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች የሚሠለጥኑበት ካሪኩለም ትክክለኛ ነው ወይስ ጊዜ ያለፈበት? የሚለውን ይመዝናል፡፡ ከአሜሪካ ሙሉ ለሙሉ የተወሰደ ነው ወይስ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያንፀባርቃል? ኢትዮጵያ ድርብርብ የበሽታ ጫና እንዳለበት ነው የሚታወቀው፡፡ ድሮ የነበሩ ከድህነት ጋር የተያያዙ እንደ ቲቢ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች አሁንም ድረስ በብዛት አሉ፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ደግሞ ተላላፊ ያልሆኑ እንደ ስኳር፣ ካንሰር፣ የልብ፣ የኩላሊትና ሌሎችም በሽታዎች በከፍተኛ መጠን ይከሰታሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በትራፊክ አደጋ የሚያጋጥም ሞትና ጉዳት ነው፡፡ እነኝህ ላይ በጥልቀት አውቀውና ተመራምረው ነው መውጣት ያለባቸው፡፡ ከዩኒቨርሲቲ እንደወጡ ብቃት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ይገባል፡፡ ስለዚህ የጤና ሳይንስ ትምህርት ልማት ማዕከሎች የሕክምና ተማሪዎች የሚማሩበት ካሪኩለም ይህንን እውነታ ያገናዘበ ነው ወይ? ዘመናዊ ነው ወይ? አሰጣጡ ተማሪ ተኮር ነው ወይ? የሚለውን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ይገመግማል፡፡ አስፈላጊ ከሆነ አዲስ ካሪኩለም ያዘጋጃል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕክምና ተማሪዎች የሚማሩበት ሥርዓተ ትምህርት ላይ ምን ዓይነት ችግር ይታያል?

ዶ/ር ዳምጠው፡- የነበረው ሥርዓተ ትምህርት አብዛኛውን ከውጭ የተኮረጀ ነው፡፡ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታን ያልዳሰሰ ከሆነ አስፈላጊነት አይኖረውም፡፡ የምናሠለጥናቸው ሠልጣኞች በዋናነት የኢትዮጵያ ችግር ሊቀርፉ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያን ችግር ለመቅረፍ ኢትዮጵያዊ ሥርዓተ ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት ካሪኩለሙ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ሊኖረው አይገባም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያን ጥሶ አይደለም ዓለም አቀፍ ደረጃን ማሟላት ያለበት፡፡ ከዚህ ባሻገር ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ አዳዲስ ነገሮችን የሚያካትቱ ወቅታዊ ካሪኩለሞች መቀረፅ አለባቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ካሪኩለሞች ሳይሻሻሉ ለዘመናት ተማሪዎችን እናስተምራለን፡፡ ይህ መሆን የለበትም፡፡ የነበረው የመማር ማስተማር ሒደት ገለጻን መሠረት ያደረገና አስተማሪ ለተማሪ የሚያወራበት ነው፡፡ ይህንን ሚዛናዊ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ተማሪ ተኮር የሆነ ሥልጠና መሰጠት አለበት፡፡ ይህ ሲባል በአንድ በኩል የእያንዳንዱ ተማሪ ፍላጎት ምንድነው? የሚለው በሚገባ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ተማሪዎች በመማር ማስተማር ሒደቱ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር አለ ብለው ችግሩን ሊፈቱ የሚችሉበትን ሥርዓት ሊሆን ይገባል፡፡ መምህራንን የማብቃት ሥራም ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ አብዛኞቹ መምህራን ወጣቶች ናቸው፡፡ አንድ አስተማሪ ምን እንደሚያስተምር ሊያውቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን እንዴት ማስተማር አለበት? የሚለው ጋር ስንመጣ ችግሮች እናስተውላለን፡፡ ስለዚህ በእኛ ፕሮጀክት የፔዳጎጂ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ አንድ አስተማሪ ሲያስተምር መልዕክቱ በሚገባ ለተማሪ መድረሱን የሚያረጋግጥበት፣ ከካሪኩለም ቀረፃ ጀምሮ የተለያዩ ሥልጠናዎች እንሰጣለን፡፡