Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው

ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትር ተራማጅ አመለካከት ካለው ወጣት ጋር እያወሩ ነው]

 • እንዴት ነህ ወጣቱ?
 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰሞኑን ደግሞ አልተቻልክም፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሚዲያውን በአጠቃላይ ተቆጣጥረኸዋል እኮ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ጊዜው የእኛ እኮ ነው፡፡
 • የእኛ ስትል?
 • አገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ አይደለች እንዴ?
 • ብትሆንስ ታዲያ?
 • ለውጡን እየመራ ያለው ወጣቱ ትውልድ ነዋ፡፡
 • ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም ሲባል አልሰማህም?
 • ምን ማለት ነው?
 • ይኸው የእናንተ ለውጥማ አገሪቱን ሊያፈራርሳት ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አገሪቱን ልታፈራርሷት የነበራችሁትማ እናንተ ናችሁ፡፡
 • ሰሞኑን በመላ አገሪቷ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ነገር እየተከታተልክ ነው ለመሆኑ?
 • ክቡር ሚኒስትር ሁልጊዜ ሊነጋ ሲል ይጨልማል ሲባል አልሰሙም?
 • እኔ የምፈራው በዚያው ጨልሞብን እንዳይቀር ነው፡፡
 • ለምንድነው ሁሌ ጨለምተኛ የምትሆኑት?
 • አሁን የምናየው ነገር ጨለማ ብቻ ስለሆነ ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ እኮ የሚገርም ለውጥ ላይ ናት፡፡
 • የምን ለውጥ ነው?
 • አፋኝ፣ ጨቋኝና አምባገነን የነበረ ሥርዓት እየተለወጠ ነው፡፡
 • ወደ ምንድነው የተለወጠው?
 • ይኸው ሁላችንም በአንፃራዊነት ነፃነት አግኝተን የፈለግነውን እየተናገርን ለአገራችን የበኩላችንን እያበረከትን ነው፡፡
 • ስማ በእኔ ዕይታ አገሪቱ እልም ወዳለ ሥርዓተ አልበኝነት ነው እየተቀየረች ያለችው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ታፍኖ የነበረው ወጣት ድምፁን ማሰማት ሲጀምር አነስተኛ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡
 • ችግሩ አነስተኛ ነው ብለህ ነው?
 • እናንተ አገሩን ሙሉ እስር ቤት አድርጋችሁት ስለነበር በአንዴ ሕዝቡ ሁሉ ሲፈታ የተለያዩ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
 • ምንም ብትለኝ አገሪቱ ውስጥ እየታየ ያለው ሥርዓተ አልበኝነት ተቀባይነት የለውም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በእናንተ ዘመን የነበረውን ሥርዓተ አልበኝነት ዘነጉት እንዴ?
 • የምን ሥርዓተ አልበኝነት?
 • በሥልጣናችሁ ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ራሳችሁን በማገልገል ስንትና ስንት ገንዘብ ስትዘርፉ አልነበር እንዴ?
 • እ. . .
 • ከዚያም በላይ ለእናንተ ሥጋት የሚመስላችሁን ማንኛውንም ግለሰብና ሐሳብ ስታጠቁ ነበር፡፡
 • እዚህ ላይ እንዳትሳሳት፡፡
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እኛ የገነባው ሥርዓት ልማት፣ ዴሞክራሲና ሰላምን በአገሪቱ ላይ ያሰፈነ ነበር፡፡
 • የትኛዋ አገር ላይ?
 • ኢትዮጵያ ላይ ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ለአፍዎ ትንሽ አይከብድዎትም?
 • ምኑ ነው የሚከብደኝ?
 • ሕዝቡ ላለፉት ሦስት ዓመታት አምፆ ለውጥ ያመጣው ልማት፣ ዴሞክራሲና ሰላም አስክሮት ነው?
 • ጥቂቶች አመፁ ብለህ አመፁን የሕዝብ አታድርገው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይህች አገር እኮ እርስዎ በሚሉት መንገድ ቀጥላ ቢሆን ኖሮ መጨረሻዋ መፈራረስ ብቻ ነበር፡፡
 • ስማ እኛ ከሕዝቡ ቀድመን በማሰብ አመራር የምንሰጥ እንጂ በሕዝብ የምንመራ አይደለንም፡፡
 • እናንተማ እንደተባለው ሕዝቡን መንዳት እንጂ መምራት መቼ ታውቁበታላችሁ?
 • ብንነዳውም እኮ ምርጫ አሸንፈን በሕጋዊ መንጃ ፈቃድ ነው የነዳነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የሚያሳዝነው እሱ አይደል እንዴ?
 • ምኑ ነው የሚያሳዝነው?
 • ያለመንጃ ፈቃድ ነበር የምትነዱት፡፡
 • ምን ለማለት ነው?
 • መንጃ ፈቃዳችሁ ምን እንደሆነ ተደርሶበታል፡፡
 • ምንድነው?
 • ፎርጅድ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ አገሩ በቅርቡ ከተመለሰ ዳያስፖራ ጋር እያወሩ ነው]

 • ለበዓል ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣኸው?
 • ከዚህ በኋላማ መኖሪያዬ ኢትዮጵያ ናት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ተገኘና?
 • ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አገራችሁ ግቡ አሉን አይደል እንዴ?
 • የእሳቸውን ጥሪ ተቀብለህ ነው የመጣኸው?
 • ምን ጥያቄ አለው ክቡር ሚኒስትር?
 • እኛ ስንቴ ነበር አገራችሁ ግቡ እያልን ጥሪ ያቀረብንላችሁ?
 • ለእናንተ ጥያቄማ ጥሪ አንቀበልም ነበር መልሳችን፡፡
 • ታዲያ አሁን ምን ተወለጠ?
 • አሁንማ አገራችን የእኛን ድጋፍ የምትፈልግበት ወቅት ነው፡፡
 • በፊትስ ማን ከለከለህ?
 • በፊትማ ሀብታችንን እንጂ መቼ እኛን ትፈልጉ ነበር?
 • ደግሞ ምን ሀብት አላችሁ?
 • አዩ ክቡር ሚኒስትር፣ ሀብት ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ዜጎች በራሳቸው የአገር ሀብት ናቸው፡፡
 • ይኼን ስብከትህን ለተደመሩት ንገራቸው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ካልተደመሩ እየተደናበሩ ነው ማለት ነው?
 • አሁን ወሬውን ተወውና ምን ልትሠራ አሰብክ?
 • እኔማ በሰው አገር ሳህን አጥቤና ታክሲ ነድቼ ያፈራሁትን ሀብት አገሬ ላይ ለማፍሰስ ተዘጋጅቻለሁ፡፡
 • እንደዚያ ከሆነማ  እኔ ላማክርህ እችላለሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ኮንሰልታንት ሆነዋል እንዴ?
 • እዚህ አገር ላይ ስኬታማ የሆነ ቢዝነስ ሁሉ እኔ ያማከርኩት ነው፡፡
 • እርስዎ ግን ኮንሰልታንት ነኝ ሲሉ አያፍሩም?
 • ምን ያሳፍረኛል?
 • በፊት ዓይን አውጥታችሁ ነበር የምትዘርፉት፣ አሁን ደግሞ ሌላ ባርኔጣ አድርጋችሁ ሕዝብ ልትዘርፉ ትፈልጋላችሁ?
 • ምን እያልክ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር እናንተ እኮ ስኳር ሳይሆን የስኳር ፋብሪካ የምትቅሙ፣ እሱ አልበቃ ብሏችሁ ባቡር፣ ኮንዶሚኒየምና መንገድ ሳይቀር የምትቅሙ ናችሁ፡፡
 • አንተ ግን ከቤትህ ቅመህ ነው የወጣኸው መሰለኝ?
 • ከዚያም በላይ ሕዝቡን ቃሚ አድርጋችሁ ይህ ሁሉ ይቅርታና ምሕረት ይገባችኋል ብዬ አላስብም፡፡
 • እና እንድታሰር ነበር የምትፈልገው?
 • ከሠራችሁት አንፃርማ እስር ቤት ለእናንተ ሽልማት ነው፡፡
 • ምን ይላል ይኼ?
 • ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ እኮ በእናንተ ምክንያት ከገደል አፋፍ ላይ ልትፈጠፈጥ ብላ ለጥቂት ነው የተረፈችው፡፡
 • ይኼ ሁሉ ልማትና ዕድገት በእኛ መምጣቱን እንዳትረሳው?
 • ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር አሁን ድምፃችሁን አጥፍታችሁ በሰላም ብትኖሩ ይሻላችኋል፡፡
 • ስማ መርሳት የሌለብህ እኮ ለእኔም አገሬ ናት፡፡
 • ስለዚህ አርፈው ቢቀመጡ ይሻልዎታል፡፡
 • ምን ታስፈራራኛለህ እኔ እኮ በሀብትም ቢሆን አለ የተባልኩ ሚሊየነር ነኝ፡፡
 • መቼም ሚሊየነር እንዴት እንደሆኑ ያውቃሉ፡፡
 • እንዴት ነው የሆንኩት?
 • በአንድ ጀምበር ነዋ፡፡
 • ምን ችግር አለው ታዲያ?
 • አሁን ደግሞ በአንድ ጀምበር መግባትዎ አይቀርም፡፡
 • ወደ ምን?
 • ወደ ዜሮ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ምነው ጠፋህ?
 • ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
 • ማለት?
 • ከግራ መጋባት እኮ ወደ ተስፋ መቁረጥ ተሸጋግሬ ነው፡፡
 • ለምንድነው ተስፋ የቆረጥከው?
 • ክቡር ሚኒስትር የእኛ ጉዳይ ያበቃለት ይመስለኛል፡፡
 • አበቃለት ስትል?
 • እኔማ ተስፋ ያደረግኩት እናንተን ነበር፣ እናንተም ግን ያበቃላችሁ መሰለኝ፡፡
 • ማነው ያለው?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔማ እንደለመዳችሁት አፈር ልሳችሁ ትነሳላችሁ ብዬ ነበር፣ አሁን ግን ያበቃላችሁ ትመስላላችሁ፡፡
 • ስማ እኛማ አንድ ጥይት እስክትቀር ድረስ መታገላችን አይቀርም፡፡
 • እኔማ ያስጀመርኳቸውን ፕሮጀክቶች ኮሚሽኖች እንኳን እስካስጨርስ ዕድሜ አላችሁ ብዬ ነበር፣ ግን አልመሰለኝም፡፡
 • እንደዚህማ ተስፋ አትቁረጥ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ለእኔ አማካሪዬ፣ አስተማሪዬና የሌብነትን መንገድ ጥርት አድርገው ያሳዩኝ ነበሩ፡፡
 • አልገባኝም?
 • ክቡር ሚኒስትር በጣም ያስጨነቀኝ ነገር አለ፡፡
 • ምንድነው የሚያስጨንቅህ?
 • ይህች ምሕረት ምናምን ያሏት ነገር ምንም አላምር ብላኛለች፡፡
 • እ. . .
 • ይኸው ሕዝብ በየቦታው የራሱን ፍርድ እየሰጠ ያለው መንግሥት በሌቦቹ ላይ ፍርድ አልሰጠም ብሎ ስለሆነ፣ በኋላ ላይ እነሱም ሲረጋጉ ሒሳብ የሚያወራርዱብን እየመሰለኝ ነው፡፡
 • ምነው እንደዚህ ተሸብረህ ታሸብረኛለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ነገሩ ምንም አላምር ስላለኝ ለመጥፋት እያሰብኩ ነው፡፡
 • ወዴት ነው የምትጠፋው?
 • ነገሮች ከተረጋጉ እንገናኛለን ብዬ አስባለሁ፡፡
 • ተው እንጂ ወዳጄ?
 • ሁሌም ግን የሚቆጨኝ አንድ ነገር ነበር፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ያንን ነገር ላስፈጽም ደፋ ቀና እያልኩ ይኼ ለውጥ በመምጣቱ በጣም ነው የቆጨኝ፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ለእኔም ሆነ ለአገር ላበረከቱ አስተዋጽኦ አንድ ሽልማት ይገባዎታል ብዬ ደፋ ቀና እያልኩ ነበር፡፡
 • ለእኔ ሽልማት?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፣ ሽልማቱ ከግራሚም፣ ከኦስካርም ሆነ ከኖቤል የተሻለ ሽልማት ይሆናል ብዬ አስቤ ነበር፡፡
 • ምን ተብዬ ነው ደግሞ የምሸለመው?
 • የክፍለ ዘመናችን ባለራዕይ ሌባ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው]

 • ምንድነው እየሰማሁ ያለሁት?
 • ምን ሰሙ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሊታጠፉ ነው የሚባለው?
 • ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ አልሰሙም እንዴ?
 • እኔማ ዝም ብሎ የተወራ ወሬ መስሎኝ ነው፡፡
 • እንዲያውም የእርስዎ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከሚታጠፉት መካከል አንዱ ነው፡፡
 • እ. . .
 • በአዲሱ ካቢኔ አይካተቱም፡፡
 • አንተ እንዴት አወቅክ?
 • የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹን ሽግሽግ የሚያጠናው ኮሚቴ ውስጥ አለሁበት፡፡
 • ትልቅ ስህተት እየሠራችሁ ነዋ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ይህች አገር እኮ ያለችው በእኔ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ነው፡፡
 • ምን አሉኝ?
 • ተደመር አላችሁኝ ተደመርኩ፣ አሁን በምን ሥሌት ነው እኔን የምትቀንሱኝ?
 • ክቡር ሚኒስትር ባለፈው መደመር ውስጥ መቀነስ እንዳለ አልሰሙም ነበር?
 • ታዲያ የእኔን መሥሪያ ቤት ከምትቀንሱት አገሪቱን እናፍርሳት ብትሉኝ አይሻልም?
 • ምን እያሉ ነው?
 • አገሪቱ ያለ እኔ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እንዴት ትቀጥላለች?
 • እንዲያውም ለአገሪቱ ፀር የእርስዎ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መሆኑ ተደርሶበታል፡፡
 • ስለዚህ እኔን አውላላ ሜዳ ላይ ልትጥሉኝ?
 • ክቡር ሚኒስትር ምን ይደረግ እያሉ ነው?
 • እኔ ያለኝ ልምድ ለአገሪቱ ጠቃሚ ነው፡፡
 • ከፍተኛ የሆነ ልምድ እንዳለዎትማ እኛም ደርሰንበታል፡፡
 • ታዲያ እንዴት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቴን ታፈርሱታላችሁ?
 • ሌላ እንዲቋቋምልዎት ነዋ፡፡
 • የምን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት?
 • የሸርና የተንኮል!