Skip to main content
x
በበጎ ፈቃደኞች የሚታደሱ ቤቶች ቁጥር እየጨመረ ነው

በበጎ ፈቃደኞች የሚታደሱ ቤቶች ቁጥር እየጨመረ ነው

በአዲስ አበባ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የሚገነቡ ቤቶች ቁጥር ከ114 ወደ 133 ከፍ ማለቱ ተገለጸ፡፡ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች ከሚገኙ ወረዳዎች አንዳንድ የችግረኛ ቤቶችን መርጦ የማደሱ ተግባር የተጀመረው ከሳምንታት በፊት ሲሆን፣ እስካሁን የ118ቱ ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ ነዋሪዎች ቤቶቻቸውን ተረክበዋል፡፡ የተቀሩት የ15 ቤቶች ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝና እስከመጪው ሳምንት ድረስ ተጠናቆ ለባለቤቶቹ እንደሚተላለፉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የበጎ ፈቃደኛ ተግባራት አስተባባሪ ኮሚቴ አባል አቶ ዮናስ አረጋዊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ይህ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ ንቅናቄ ከአንድ ሳምንት በኋላ የሚጠናቀቅ ቢሆንም በርካታ የተቸገሩን መርዳት የሚፈልጉ የኅብረተሰቡ አካላት በከተማው ከሚገኙ ሊወድቁ ከደረሱ ቤቶች መካከል የተወሰኑትን ወስደው የማደስ ጥያቄ እያቀረቡ ስለሆነ ቀጣይነት እንደሚኖረው ታውቋል፡፡ በመጀመርያ ለመገንባት ታቅዶ በነበረው የቤቶች ቁጥር ላይ የ15 ቤቶች ጭማሪ የመጣውም መሥራት እንፈልጋለን የሚሉ በጎ ፈቃደኞች በመኖራቸው ነው፡፡

መገንባት እንፈልጋለን የሚለው ጥያቄ አሁንም ድረስ በተከታታይ እየተስተናገዱ ሲሆን፣ ተራ አስከባሪዎች አሥር ቤቶችን ለመገንባት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡ የዲባባ ቤተሰቦችም (እነ ጥሩነሽ ዲባባ) እንዲሁ ቤቶችን የማደስ ፍላጎት እንዳላቸው፣ በከተማው ከሚገኙ ቤቶች መካከል አንገብጋቢ ችግር ያለባቸው ተመርጦ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ አቶ ዮናስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

በበጎ ፈቃደኞች የሚታደሱ ቤቶች ቁጥር እየጨመረ ነው
አርቲስቶች በቤት እድሳቱ ተሳታፊዎች ሆነዋል

 

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ከማኅበረሰቡ ጋር በማስተባበር የተጀመረው ይህ ቤቶችን የማደስ ተግባር የተለየ በጀት ያልተመደበለት፣ ነገር ግን ጥቂት ለማይባሉ ሰዎች እፎይታን የሰጠ ነው፡፡ ካለው ውስን አቅም አንፃር ቤቶቹ እየታደሱ ያሉት የሚያፈስ ጣራ ያላቸው ከኅብረተሰቡ በተገኙ ባገለገሉ ቆርቆሮዎች፣ የዘመሙ ቤቶች ደግሞ ወራጅና ማገራቸው እየተቀየረላቸውና በጭቃ እየተመረጉ ነው፡፡

169 አርቲስቶችን ያካተተው ይህ የበጎ ተግባር ንቅናቄ የዘመቻ ሥራ ብቻ ሳይሆን ወደ ፊትም ቀጣይነት እንዲኖረው ታልሞ የተጀመረ ነው፡፡ ‹‹አርቲስቶቻችን በእግራቸው ጭቃ እያቦኩና እየለጠፉ ነው የቆዩት፤›› ይላሉ አቶ ዮናስ፡፡ በዚህ የአዲስ ዓመትን ድባብ በቀየረውና በጎፈቃደኝነትን የዘመናዊነት መገለጫ ባደረገው በዚህ ንቅናቄ የከተማው አስተዳደር አካላት በስፋት የተንቀሳቀሱበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሳይቀሩ በእድሳት ሒደቱ ላይ የተካፈሉበት ነበር፡፡

 የቤታቸው እድሳት እስኪጠናቀቅ ነዋሪዎች በጎረቤትና ዘመድ ጋር እየተጠለሉ እንደሚቆዩ፣ የጭቃ ምርጊቱ እስኪጠናቀቅ በትንሹ አንድ ሳምንት እንደሚፈጅ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በኮልፌ፣ በቦሌ፣ በልደታ፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ አንዳንድ ቤቶችም በብሎኬት እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡ ይኼንን የሚያደርጉት የንቅናቄው አካል የሆኑ ወጣቶች የአንዱን ከአንዱ በማበላለጥ ሳይሆን ራሳቸው ባለ ሀብቶች በብሎኬት የመገንባት ጥያቄ ስለሚያነሱ መሆኑ ታውቋል፡፡

የዚሁ ንቅናቄ አካል በሆነው በሸራተን አዲስ በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራምም 31 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ባለሀብቶች ቃል ገብተዋል፡፡ ይህም በከተማዋ የሚገኙ እንደ ምግብና ትምህርት ያሉ ፍላጎቶቻቸውን ማግኘት ህልም ለሆነባቸው 30 ሺሕ ችግረኛ ልጆች የሚውል ነው፡፡ ገንዘቡ ለልጆቹ በምንና እንዴት ባለ መንገድ ይደርሳል የሚለውን ጉዳይ የሚወስነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ይሆናል፡፡

በሚሌኒየም አዳራሽ ተዘጋጅቶ በነበረው የስጦታ ፕሮግራምም እንዲሁ በቼክ የተሰጠውን ሳይጨምር 2.5 ሚሊዮን ብር ወደ ንግድ ባንክ ገቢ ተደርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ 600 ከረጢት አልባሳት፣ 169 ከረጢት መጫሚያዎች፣ 100 ሺሕ ደብተሮች መሰብሰብ ተችሏል፡፡ 500 ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኞች የተሰበሰበ ሲሆን፣ መጠናቸው ያልተገለፀ ዘይት፣ ጤፍ፣ ስንዴና ሌሎችም አስቤዛዎች ተሰብስበዋል፡፡ ከብረት ምጣድ ጀምሮ እስከ ሶፋ የሚደርሱ ልዩ ልዩ የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎችም በዚሁ ፕሮግራም ተገኝተዋል፡፡

 ከዚህም ባሻገር በክረምት ወራት ወጣቱን በማስተባበር 66 ሺሕ ተማሪዎች በ99 ትምህርት ቤቶች ነፃ የክረምት ትምህርት እንዲማሩ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ 4,000 በጎ ፈቃደኛ አስተማሪዎችም በሙያቸው እገዛ አድርገዋል፡፡ 2,800 ተማሪ በጎ ፈቃደኛ ትራፊኮችንም ማሰማራት መቻሉን የሚገልጹት አቶ ዮናስ፣ ‹‹ማኅበራዊ ሕይወታችን በራሱ ከበጎ ፈቃድ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ችግሩ እንዴት መጠቀም እንዳለብን አለማወቃችን ነው፤›› ይላሉ፡፡

ለመታደስ ከተመረጡ መኖሪያ ቤቶች መካከል አንዱ በነበረው ሾላ ገበያ አካባቢ በሚገኘው ብሎኬት ግቢ ሪፖርተር ተገኝቶ በሰፊ ዘገባ መሸፈኑ አይዘነጋም፡፡ መርካቶ አካባቢ የሚገኙ በግላቸው ስለሚንቀሳቀሱ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በአካባቢው ለሚገኙ ችግረኛ ነዋሪዎች ምን ያህል አለኝታ መሆናቸውንም እንዲሁ ሪፖርተር ባለፈው ሳምንት ዕትሙ አስነብቧል፡፡