Skip to main content
x
ለሐሳብ የበላይነት እንጂ ለብሽሽቅ ቦታ አይሰጥ!

ለሐሳብ የበላይነት እንጂ ለብሽሽቅ ቦታ አይሰጥ!

የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል በተጠናቀቀ ማግሥት ካለፈው ዓመት በተሻለ ለመሥራት ጠንክሮ መነሳት ያስፈልጋል፡፡ የአገሪቱ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ከውጭ ገብተው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ለማድረግ ተዘጋጅተዋል፡፡ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በጣም ተመራጩ ሥልት ስለሆነ፣ ለሐሳብ የበላይነት መዘጋጀት ይገባል፡፡ የሐሳብ የበላይነት ሊኖር የሚችለው ግን የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ሲስማሙ ነው፡፡ ይህ ስምምነት ሊኖር የሚችለው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለአገሩ በቅን ልቦና ሲያስብ ነው፡፡ አሁን ከፊታችን ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ተስፋዎችና ዕድሎች አሉ፡፡ ይኼንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ፣ ሐሳቦች ያለ ገደብ እንዲንሸራሸሩ፣ መጪው ጊዜ ብሩህ መሆኑን የሚያመላክቱ የተለያዩ የውይይት መድረኮች እንዲኖሩና ከጥላቻና ከቂም በቀል የፀዳ ከባቢ እንዲፈጠር ወገብን ጠበቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ኋላ ቀር የሆነው የብሽሽቅ ፖለቲካ ለሐሳብ የበላይነት መገዛት አለበት፡፡

የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ለግልጽ፣ ለገንቢና ለደፋር የፖለቲካ ንግግሮችና ድርድሮች ዝግጁ መሆናቸው የሚጠቅመው፣ ሁሉም ፓርቲዎች በነፃነት የሚወዳደሩበት የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚያራምዱት ዓላማ፣ ፕሮግራምና ደንብ ልዩነቶቻቸው ተጠብቀው ለጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ግን በአንድነት ሊሠለፉ ይገባል፡፡ የጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች የሚባሉት የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት፣ በነፃነት ሐሳብን መግለጽ፣ በፍትሕና በእኩልነት መኖር፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥና ካሁን በኋላ ኢ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን እንዳይያዝ ማድረግና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአገር ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን አለበት፡፡ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን የሚያስማማ የተቋማት ግንባታ መጀመር ይኖርበታል፡፡ መጪው ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንዲሆን የሚረዱ ተግባራት እንዲከናወኑ፣ ሁሉም ወገኖች በእኩልነት የሚሳተፉበት መደላድል መፈጠር አለበት፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ደግሞ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ንግግር በፍጥነት መጀመር የግድ ይሆናል፡፡

በፖለቲካ ሰጥቶ መቀበል ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው መርህ ነው፡፡ በሁሉም ንግግሮችና ድርድሮች መስማማት አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን ልዩነቶችን አስታርቆ የጋራ አማካይ መፈለግ የሥልጣኔ መገለጫ ነው፡፡ ተቃራኒ ሐሳቦችን የማስተናገድ ጥቅሙ የተለያዩ ምልከታዎችን ለማግኘት የሚረዳ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አጋዥ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ግጭት የሚቀሰቀሰው ግትር በመሆን እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ በማለት በሚፈጠር ጀብደኝነት ምክንያት ነው፡፡ ጀብደኛ መቼም ቢሆን ዴሞክራት መሆን አይቻለውም፡፡ ፈተናዎች ቢበረቱም እንኳ ሐሳቦች በነፃነት ተንሸራሽረው፣ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው ሕዝብ የፈለገውን በነፃነት የሚመርጥበት ዓውድ መፍጠር የዘመናችን ዋነኛ አጀንዳ ነው፡፡ በውይይቶችና በድርድሮች ጊዜ ከበድ ያሉ ውጥረቶች ቢፈጠሩ እንኳ፣ ሁሌም ጎን ለጎን ለመፍትሔዎች ቅርብ መሆን ችግሩን ያቀለዋል፡፡ በብሽሽቅ የሚካሄድ ፖለቲካ ግን እኔ ብቻ ነኝ የማውቀውና የምበጀው የሚል ግብዝነት ስላለበት ለዚህ ዘመን አይመጥንም፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ኋላ የጎተተው እንዲህ ዓይነቱ ከንቱነት ነው፡፡

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መብቱ ተከብሮለት በነፃነት መኖር የሚችለው፣ የተጀመረው ለውጥ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በንቃትና በብቃት መሳተፍ ሲችል ነው፡፡ መብትና ግዴታውን ጠንቅቆ ሲረዳ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎቻቸው በስሜት ሳይሆን በምክንያት እንዲደግፏቸው የማበቃት ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይ በአገሪቱ ውስጥ የሚስተዋለው ለውጥን በምልዓት ተቀብሎ በብልኃት ለማካሄድ የሚታየው ችግር፣ ብዙኃኑ ውስጥ የመበደልና የመከፋት ስሜት ከመጠን በላይ ንሮ ከቁጥጥር ውጪ ስለሚወጣ ነው፡፡ ከቁጥጥር ውጪ የሚሆን ነገር ደግሞ ለአገር ሰላምና ለሕዝብ ደኅንነት ጠንቅ ነው፡፡ ግልጽ ውይይትና ክርክር ኖሮ የተለያዩ ሐሳቦች ሲደመጡ ግን፣ የታመቁ ነገሮች ስለሚተነፍሱ ችግር አይፈጥሩም፡፡ የታመቀ ሁሉ ሐሳቡን በግልጽ እያቀረበ የውይይትና የድርድር ባህል ያድጋል፡፡ የብሽሽቅ ፖለቲካ ከእነ ግሳንግሱ ይራገፋል፡፡ በሐሳብ የበላይነት የሚመራ አገር ሰላም ይኖረዋል፡፡ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግና ይፈጠራል፡፡ አድሏዊነትና ዘረኝነት ሥፍራ ያጣሉ፡፡

ለሐሳብ የበላይነት ቅድሚያ ሲሰጥ ኢትዮጵያዊያን በነፃነት የፈለጉትን ይመርጣሉ፡፡ የፍርድ ቤቶች ነፃነት ተከብሮ ፍትሕ ይሰፍናል፡፡ የአገር መከላከያና የፀጥታ ኃይሎች በገለልተኝነት አገርንና ሕዝብን ይጠብቃሉ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በነፃነትና በገለልተኝነት የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት ይወጣሉ፡፡ የሲቪክና የሙያ ማኅበራት ያብባሉ፡፡ ሦስቱ የመንግሥት አካላት ማለትም ሕግ አውጪው፣ ተርጓሚውና አስፈጻሚው እየተናበቡና እርስ በርስ እየተቆጣጠሩ ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡ ብልሹ አሠራሮች ተወግደው የመንግሥት ሥራ በግልጽነትና በተጠያቂነት ይከናወናል፡፡ የሕግ የበላይነት በተግባር ተረጋግጦ ሕገወጥነት አደብ ይገዛል፡፡ የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠት ይወገዳል፡፡ ሕዝብ በሰላምና በነፃነት ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት የተጎዳችበት አምባገነናዊ አስተሳሰብ ደግሞ ላይመለስ ታሪክ ሆኖ ይቀራል፡፡ ይህ ሁሉ ምኞት ዕውን የሚሆነው ለሐሳብ የበላይነት ትልቅ ትኩረት ሲሰጥ ነው፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ ተሰሚነት ያላቸው ልሂቃን ከብሽሽቅ ፖለቲካ ወጥተው፣ ለአገር ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በፍጥነት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ የጎራ ፖለቲካን ከአገር በላይ አስቀድሞ ብሽሽቅ ውስጥ ውሎ ማደር ፋይዳ የለውም፡፡ ልሂቃን ለሐሳብ የበላይነት ልዕልና ይሟገቱ፡፡ በደመኛ አስተሳሰብ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሄድ አይቻልም፡፡

ደም የተቃቡ ትውልዶች ያለፉበትን መከራ በዚህ ዘመን ለመድገም መሞከር መዘዙ ለአገር ይተርፋል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ደፍርሶ ጥላቻና ቁርሾ ለዓመታት የተንሰራፉት፣ በጋራ ለሚያስማሙ ጉዳዮች ትኩረት እየተነፈገ መተናነቅ ስለከፋ ነው፡፡ ልዩነትን ከማጥበብ ይልቅ ማስፋት፣ ከመነጋገር ይልቅ መጠላለፍ፣ ከጋራ ጉዳዮች ይልቅ ቡድናዊ ፍላጎቶችን ማግነን፣ ወዘተ ልማድ የሆኑት ለሐሳብ ነፃነት የተዛባ ግምት በመሰጠቱ ነው፡፡ አሁን በተያዘው የለውጥ ጎዳና ላይ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥኑ ድርጊቶች በአስቸኳይ መቀጨት አለባቸው፡፡ ለውጡን ማንም ያምጣው ማን ለስኬቱ በጋራ መቆም ከተቻለ፣ የሐሳብ የበላይነት ያለው የሕዝብን ልብ ማርኮ አገር የማስተዳደር ኃላፊነቱን ይረከባል፡፡ ይህ በሠለጠኑት አገሮች የተለመደ አሠራር ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር ሕዝብን አስተባብሮ ለጋራ ጉዳይ በአንድነት መነሳት ከተቻለ፣ የብሽሽቅ ፖለቲካ ሥፍራ አይኖረውም፡፡ የሕዝብ ፍላጎትና የአገር ህልውና ዘለቄታ እንዲኖረው ከተፈለገ፣ ለሐሳብ የበላይነት እንጂ ለብሽሽቅ ቦታ መስጠት አያስፈልግም!